ክፍል ፵፪
የካቲት ፱፣ ፲፰፻፴፩ (እ.አ.አ.) በከርትላንድ፣ ኦሀዮ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ አማካይነት በሁለት ክፍል የተሰጠ ራዕይ። ቁጥር ፩ እስከ ፸፪ የያዘው የመጀመሪያው ክፍልም የተሰጠው በአስራ ሁለት ሽማግሌዎች ፊት እና “ህጉ” በኦሀዮ እንደሚሰጥ ጌታ የገባው የተስፋ ቃል እንዲፈጸም ነበር (ክፍል ፴፰፥፴፪ን ተመልከቱ)። ሁለተኛው ክፍልም ከቁጥር ፸፫ እስከ ፺፫ የሚያጠቃልል ነበር። ነቢዩ ይህ ራዕይ “የቤተክርስቲያኗን ህግ እንደሚያቅፍ” አመለከተ።
፩–፲፣ ሽማግሌዎች ወንጌልን ለመስበክ፣ የሚለወጡትን ለማጥመቅ፣ እና ቤተክርስቲያኗን ለመገንባት ተጠርተዋል፤ ፲፩–፲፪፣ ሊጠሩ እና ሊሾሙ እንዲሁም በቅዱሳን መጻህፍት ውስጥ የሚገኙትን መሰረታዊ መርሆች ያስተምሩ ዘንድ ይገባል፤ ፲፫–፲፯፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ይተንብዩ እናም ያስተምሩ፤ ፲፰–፳፱፣ ቅዱሳን እንዳይድገሉ፣ እንዳይሰርቁ፣ ሀሰትን እንዳይናገሩ፣ እንዳይመኙ፣ እንዳያመነዝሩ፣ ወይም በሌሎች ላይ ርኩሰትን እንዳይናገሩ ታዘዋል፤ ፴–፴፱፣ የንብረቶች ቅደሳን የሚመሩ ህግጋቶች ተሰጥተዋል፤ ፵–፵፪፣ ትዕቢት እና ስራ ፈትነት የተረገሙ ናቸው፤ ፵፫–፶፪፣ ህሙማን በአገልግሎት እና በእምነት ይፈወሳሉ፤ ፶፫–፷፣ ቅዱሳን መጻህፍት ቤተክርስቲያኗን ይገዛሉ እናም ለአለምም ይሰበካሉ፤ ፷፩–፷፱፣ የአዲሲቷ ኢየሩሳሌም ስፍራ እና የመንግስተ ሰማይ ሚስጥራት ይገለጣሉ፤ ፸–፸፫፣ የተቀደሱ ንብረቶች የቤተክርስቲያን አገልጋዮችን ለመርዳት ጥቅም ላይ ይውላሉ፤ ፸፬–፺፫፣ ዝሙትን መፈጸም፣ አመንዝራነትን፣ ግድያን፣ ስርቆትን፣ ኃጢአትን መናዘዝን የሚገዙ ህግጋት ተሰጥተዋል።
፩ በስሜ ባመናችሁና ትእዛዛቴን በጠበቃችሁ መጠን፤ የአለም አዳኝ፣ የህያው እግዚአብሔር ልጅ በሆንኩት በኢየሱስ ክርስቶስ፣ በስሜ ራሳችሁን ያሰባሰባችሁ አቤቱ እናንት የቤተክርስቲያኔ ሽማግሌዎች ሆይ አድምጡ።
፪ ደግሞም እንዲህ እላችኋለሁ፣ አድምጡ ስሙ እንዲሁም በምሰጣችሁም ህግ ታዘዙ።
፫ እውነት እላለሁ፣ ባዘዝኳችሁ ትእዛዝ መሰረት ራሳችሁን አንድ ላይ እንዳሰባሰባችሁ፣ እናም ይህን አንድ ነገር በተመለከተ ስለተስማማችሁ፣ እናም በስሜ አብን ስለጠየቃችሁ እንዲሁ ትቀበላላችሁ።
፬ እነሆ፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ከአገልጋዮቼ ከጆሴፍ ስሚዝ፣ ዳግማዊ እና ከስድኒ ሪግደን በቀር ሁላችሁም በስሜ ወደፊት ትሄዱ ዘንድ ይህን የመጀመሪያ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ።
፭ እናም ለእነርሱም ለተወሰነ ወቅት ይሄዱ ዘንድ ትእዛዝን እሰጣቸዋለሁ፣ እናም መቼ እንደሚመለሱም በመንፈስ ኃይል አማካይነት ይሰጣቸዋል።
፮ እናም እንደ መለከት ድምጽ ድምጻችሁን ከፍ በማድረግ፣ ልክ እንደ እግዚአብሔር መላእክት ቃሌን በማወጅ፣ በመንፈሴ ኃይል ወንጌሌን በመስበክ ሁለት በሁለት በመሆን ወደፊት ትሄዳላችሁ።
፯ እናም ንሰሀ ግቡ፣ ንሰሀ ግቡ መንግስተ ሰማይ ተቃርባለችና በማለት በውሀ እያጠመቃችሁ ትሄዳላችሁ።
፰ እናም ከዚህም ስፍራ በምራዕብ አቅጣጫ ወዳሉ ክልሎች ትሄዳላችሁ፤ እናም የሚቀበሏችሁን ባገኛችኋቸው መጠን በሁሉም ክልሎች ቤተክርስቲያኔን ትገነባላችሁ—
፱ በአንድ ተሰብስባችሁ እናንት ህዝቤ እኔም አምላካችሁ እሆን ዘንድ አዲሲቷም የኢየሩሳሌም ከተማ የምትዘጋጅበት ጊዜው ከላይ የሚገለጥበት ጊዜ እስከሚመጣ ድረስ ቤተክርስቲያኔን ትገነባላችሁ።
፲ እናም ዳግም፣ እላችኋለሁ፣ አገልጋዬ ኤድዋርድ ፓርትሪጅ እንደሾምኩት ስራውን ያከናውን። እና እንዲህም ይሆናል፣ የሚተላለፈ ከሆነ በእርሱ ስፍራ ሌላ ይሾማል። እንዲህም ይሁን። አሜን።
፲፩ ዳግም እላችኋለሁ፣ ስልጣን ባለው ካልተሾመ፣ እና ስልጣንም እንዳለው በቤተክርስቲያኗ የሚታወቅ እና በቤተክርስቲያኗ መሪዎችም ዘንድ በትክክለኛው መንገድ የተሾመ ካልሆነ በስተቀር፣ ለማንም ወንጌሌን እንዲሰብክ ወይም ቤተክርስቲያኔን እንዲገነባ አይሰጠውም።
፲፪ እናም ዳግም፣ የዚህች ቤተክርስቲያን ሽማግሌዎች፣ ካህናት እና መምህራን በመፅሐፍ ቅዱስ እና የወንገሌ ሙላት በሚገኝበት በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ የሚገኙትን የወንጌሌን መሰረታዊ መርሆች ያስተምራሉ።
፲፫ እናም ቃል ኪዳኖቹን እና የቤተክርስቲያን መመሪያዎችን አክብረው ያድርጉ፣ በመንፈስ ሲመሩም፣ እነዚህ የእነርሱ ትምህርት ይሆናሉ።
፲፬ እናም በእምነት ጸሎትም መንፈስ ይሰጣችኋል፤ እናም መንፈስን ካልተቀበላችሁ አታስተምሩምና።
፲፭ እናም የቅዱስ መጽሐፍቴ ሙላት እስኪሰጥ ድረስ ትምህርታችሁን በተመለከተ እንዳዘዝኳችሁ በማክበር ይህን ሁሉ አድርጉ።
፲፮ እናም በአጽናኙም አማካይነት ድምጻችሁን ከፍ ስታደርጉ፣ እኔን መልካም እንደመሰለኝ ትናገራላችሁ እናም ትተነብያላችሁ፤
፲፯ ስለሆነም፣ አጽናኙ ሁሉንም ነገሮች ያውቃል፣ እናም ስለአብ እና ስለወልድ ይመሰክራል።
፲፰ እናም አሁን፣ እነሆ፣ ለቤተክርስቲያኗ እናገራለሁ። አትግደሉ፤ እናም የሚገድል በዚህም አለም ሆነ በሚመጣው አለም ይቅርታን አያገኝም።
፲፱ እናም ዳግም፣ አትግደል እላለሁ፤ ነገር ግን የሚገድል እርሱ ይሞታል።
፳ አትስረቅ፤ የሚሰርቅ እና ንስሀ የማይገባ ወደውጭ ይጣላል።
፳፩ ሀሰትን አትናገር፤ ሀሰት የሚናገር እናም ንሰሀ የሚይገባ ወደውጭ ይጣላል።
፳፪ ሚስትህን በፍጹም ልብህ ውደዳት፣ እናም ከሚስትህም በስተቀር ከማንም ጋር አትጣመር።
፳፫ እናም ሴትን በምኞት የሚመለከት እምነትን ይክዳል፣ እናም መንፈስም አይኖረውም፤ እናም ንሰሀ ካልገባ ወደውጭ ይጣላል።
፳፬ አታመንዝር፤ እናም የሚያመነዝር፣ እናም ንሰሀ የማይገባ፣ እርሱ ወደ ውጭ ይጣላል።
፳፭ ነገር ግን የሚያመነዝር እና በፍጹም ልቡ ንሰሀ የሚገባ፣ እናም የሚትውና ዳግም የማያደርገውን፣ እርሱን ይቅር ትሉታላችሁ፤
፳፮ ነገር ግን ዳግም የሚያደርገው ቢሆን፣ ይቅርታ አይደረግለትም፣ ነገር ግን ወደውጭ ይጣላል።
፳፯ በባልንጀራህ ላይ ክፋትን አትናገር፣ እንዲሁ ጉዳትንም አታድርግ።
፳፰ እነዚህን ነገሮች በተመለከተ በቅዱሳት መጻህፍቴ ውስጥ የተሰጡትን ህግጋቴን ታውቃላችሁ፤ ኃጢአትን የሚሰራና ንስሀ የማይገባ እርሱ ወደ ውጭ ይጣላል።
፳፱ ብትወዱኝ ታገለግሉኛላችሁ እናም ትዛዛቴን ሁሉ ትጠብቃላችሁ።
፴ እናም እነሆ፣ ድሆችን ታስታውሳላችሁ፣ እናም ለእነርሱ እርዳታ የምታካፍሏቸውን ንብረታችሁን ሊሰበር በማይችል ቃል ኪዳን እና ተግባር ትቀድሳላችሁ።
፴፩ ነገሮቻችሁንም ለድሆች እስካካፈላችሁ ድረስ፣ ለእኔ ታደርጉታላችሁ፤ እና እነዚህም በቤተክርስቲያኔ ኤጲስ ቆጶስ እናም ለዚህ አላማ በሚሾማቸው ወይም በሾማቸው እና ለአገልግሎት በለያቸው በሁለቱ ሽማግሌዎች ወይም ሊቀ ካህናት አማካሪዎቹ ፊት ይቅረቡ።
፴፪ እናም እንዲህም ይሆናል፣ እነዚህም በቤተክርስቲያኔ ኤጲስ ቆጶስ ፊት ከቀረቡ በኋላ፣ እናም ስለቤተክርስቲያኔ ንብረቶች መቀደስ፣ ከትእዛዛቴ ጋር በመስማማት ከቤተክርስቲያኗ ለመወሰድ እንደማይቻሉም ምስክሮችን ከተቀበለ በኋላ፣ ሁሉም ሰው ለእኔ ተጠያቂ ይሆናል፣ በንብረቱ ወይም በቅድስና ለእርሱና ለቤተስቡ በበቂ ሁኔታ በተሰጠውም ላይ ጠባቂ ይሆናል።
፴፫ እናም ዳግም፣ ይህ ከመጀመሪያው በቅድስና ከተሰጠ በኋላ በቤተክርስቲያኗ እጆች ውስጥ ወይም በማንም ግለሰብ እጅ ውስጥ ለእርዳታቸው ከሚያስፈልጋቸው በላይ የሆነ ለኤጲስ ቆጶስ የሚቀደስ የቀረ ንብረት ካለ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለሌላቸው እንዲሰጥ፣ ለሚያስፈልገው እያንዳንዱ ሰው በበቂ ሁኔታ እንዲሰጠው እና እንደሚያስፈልገውም መጠን ይቀበል ዘንድ ይቀመጣል።
፴፬ ስለዚህ፣ በቤተክርስቲያኗ ከፍተኛ አማካሪዎች ጉባኤ እና በኤጲስ ቆጶስ እና በአማካሪዎቹ አመራር፣ የቀረው ለድሆች እና በችግር ላይ ላሉት ይሆን ዘንድ በጎተራዬ ይጠበቃል፤
፴፭ እናም ለቤተክርስቲያኗ የህዝብ ጥቅም፣ እናም የአምልኮ ቤት ለመገንባት፣ እናም ከዚህ በኋላ የምትገለጠውን አዲሲቷ ኢየሩሳሌምን ለመገንባት—
፴፮ ወደ ቤተ መቅደሴ በምመጣበት በዚያን ቀን የቃል ኪዳን ህዝቤ በአንድ ላይ እንዲሰበሰቡ በግምጃ ቤቴ ይቀመጣል። እናም ይህን የማደርገው ለህዝቤ መዳን ነው።
፴፯ እናም እንዲህም ይሆናል፣ ኃጢአትን የሚያደርግ እና ንሰሀ የማይገባ እርሱ ከቤተክርስቲያኗ ውጭ ይጣላል፣ እናም በቅድስና ለቤተክርስቲያኔ ድሆች እና ችግረኞች የሰጠውን፣ ወይም በሌላ አባባል ለእኔ የሰጠውን፣ ዳግሞ አይቀበልም—
፴፰ ከሁሉ ለሚያስኑ ለእነዚህ ካደረጋችሁት፣ ለእኔ አድርጋችኋል።
፴፱ እንዲህም ይሆናል፣ በነቢያቴ አንደበት የተናገርኩት ይፈጸማል፤ የእስራኤል ቤት ለሆኑት ድሀ ህዝቤ ይሆን ዘንድ ከአህዛብ መካከል ወንጌሌን የሚቀበሉትን ሀብታቸውን እቀድሰዋለሁና።
፵ እና ደግሞም፣ በልብህም አይታበይ ልብሶችሁም በጣም ያላጌጡ ይሁኑ፣ እናም ውበታቸውም የእጆችህ ስራ ውበት ይሁን፤
፵፩ እናም ሁሉም ነገሮች በፊቴ በንጽህና ይሰሩ።
፵፪ ስራ ፈትም አትሁን፤ ስራ ፈት የሆነ እርሱ የሰራተኞችን እንጀራ አይበላም እንዲሁም ልብስንም አይለብስምና።
፵፫ እናም በመካከላችሁ የታመመ ሰው ቢኖር፣ እናም ለመፈወስ እምነት ባይኖረው፣ ነገር ግን ካመነ፣ በጠላት እጅ ሳይሆን በመልካም ርህራሄ፣ ቅጠላቅጠል እና ለስላሳ ምግብንም በመመገብ እንክብካቤ ይደረግለታል።
፵፬ እናም ሁለት ወይም ከዚያም በላይ የቤተክርስቲያኗ ሽማግሌዎች ይጠሩ፣ ለእነርሱም ይጸልዩ እናም እጆቻቸውን በስሜ በላያቸው ላይ ይጫኑ፣ ቢሞቱም ለእኔ ይሞታሉ፣ ከኖሩም ለእኔ ይኖራሉና።
፵፭ በሞት ላጣችኋቸው፣ በተለይም የክብር ትንሳዔ ተስፋ ለሌላቸው፣ ባለቀሳችሁ መጠን፣ በአንድ ላይ በፍቅር ትኖራላችሁ።
፵፮ እናም እንዲህም ይሆናል በእኔ የሚሞቱ ሞትን አይቀምሱም፣ ለእነርሱም ጣፋጭ ትሆናለችና፤
፵፯ እና በእኔ የማይሞቱም፣ ወዮላቸው፣ ሞታቸውም መራራ ትሆናለችና።
፵፰ እናም ዳግም እንዲህም ይሆናል ለመፈወስ በእኔ እምነት ያለው፣ እና ለሞትም ያልተሰጠ፣ እርሱ ይፈወሳል።
፵፱ ለማየት እምነት ያለው ያያል።
፶ ለመስማትም እምነት ያለው ይሰማል።
፶፩ ለመዘለል እምነት ያለው ሽባም ይዘላል።
፶፪ እናም እነዚህንም ነገሮች ለማድረግ እምነት የሌላቸው፣ ነገር ግን በእኔ የሚያምኑ፣ ልጆቼ ይሆኑ ዘንድ ኃይል አላቸው፤ እናም ህግጋቴን አስካላፈረሱ ድረስ ድካማቸውን ትሸከማላችሁ።
፶፫ በመጋቢነት ስፍራችሁ ትቆማላችሁ።
፶፬ የወንድማችሁንም ልብስ አትውሰዱ፤ ከወንድማችሁ የተቀበላችሁትንም ክፈሉ።
፶፭ እናም ከምትጠቀሙበት በላይ ቢኖራችሁ፣ ሁሉም ነገሮች እንደተናገርኩት ይከናወኑ ዘንድ፣ በጎተራዬ ስጡ፣
፶፮ ጠይቁ፣ እናም እንደመረጥኩትም ቅዱሳን መጽሐፍቴ ይሰጣሉ፣ እናም በመልካም ሁኔታ ይጠበቃሉ፤
፶፯ እናም እነዚህን በተመለከተ ዝምታችሁ፣ እናም ሙሉ ሁሉ እስከምትቀበሏቸውም ድረስ ያለማስተማራችሁ ተገቢ ነው።
፶፰ ከዚያም ሁሉንም ሰዎች እነዚህን ታስተምሩ ዘንድ ለእናንተ ትእዛዝን እሰጣችኋለሁ፤ ሁሉም ህዝብ፣ ነገድ፣ ቋንቋ፣ እና ወገን እንዲማሯቸው ይደረጋልና።
፶፱ በቅዱሳትት መጻህፍቴ ህግ ሆነው የተሰቷችሁን ነገሮች ቤተክርስቲያኔን የሚያስተዳድሩ ህግ ይሆንላችሁ ዘንድ ትቀበሏቸዋላችሁ።
፷ እናም በእነዚህ ነገሮች መሰረት የሚያከናውን እርሱ ይድናል፣ የማያደርጋቸውና በእዚህም የሚቀጥል ከሆነም ይጠፋል።
፷፩ ብትጠየቁ፣ ደስታንና የሚያመጡትን፣ ዘለአለማዊ ህይወትን የሚያመጡትን—ሰላማዊ የሆኑ ነገሮችንና ሚስጥራትንም ታውቁ ዘንድ በራዕይ ላይ ራዕይን፣ በእውቀት ላይ እውቀትን ትቀበላላችሁ።
፷፪ ጠይቁ፣ እናም በራሴ ጊዜ አዲስቷ ኢየሩሳሌም የምትገነባበትምን ስፍራ ይገለጥላችኋል።
፷፫ እናም እነሆ፣ እንዲህም ይሆናል አገልጋዮቼ ወደ ምስራቅ እና ወደ ምዕራብ፣ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ ይላካሉ።
፷፬ እናም አሁንም ቢሆን፣ ወደምስራቅ የሚሄደው የሚለወጡትን ወደ ምዕራብ እንዲሸሹ ያስተምር፣ እናም ይህም የሚሆነው ወደ ምድር በሚመጣው የተነሳ፣ እናም በሚስጥር ሴራዎች ምክንያት ነው።
፷፭ እነሆ፣ እነዚህን ሁሉ ትጠብቃላችሁ፣ እናም ደመወዛችሁም ታላቅ ይሆናል፤ የመንግስቱን ሚስጥራት ታውቁ ዘንድ ለእናንተ ተስጥቷችኋል፣ ነገር ግን አለም እንዲያውቃቸው አልተሰጠም።
፷፮ የተቀበላችሁትን ህግጋት ትጠብቃላችሁ እናም ታማኞችም ትሆናላችሁ።
፷፯ እናም በዚህና በአዲስቷ ኢየሩሳሌም ራሳችሁን ታደራጁ ዘንድ በቂ የሆነ የቤተክርስቲያን ቃል ኪዳንን ከዚህ በኋላ ትቀበላላችሁ።
፷፰ ስለዚህ፣ ጥበብ የሚጎድለው፣ እኔን ይጠይቅ ሳልነቅፍ በነጻ እሰጠዋለሁ።
፷፱ ልባችሁን አንስታችሁ ተደሰቱ፣ መንግስት፣ ወይም በሌላ አባባል፣ የቤተክርስቲያኗ ቁልፎች ለእናንተ ተሰጥተዋልና። እንዲህም ይሁን። አሜን።
፸ እንደ አባላትም፣ ካህናት እና መምህራን መጋቢነታቸውን ያገኛሉ።
፸፩ ኤጲስ ቆጶሱን በአማካሪነት በሁሉም ነገሮች እንዲረዱት የተሾሙት ሽማግሌዎች ወይም ሊቀ ካህናት፣ አስቀድሞ እንደተገለጸው ለድሆች ደህንነት፣ እና በሌላ ጉዳዮች፣ በቅድስና ለኤጲስ ቆጶሱ በተሰጡት ንብረቶች ቤተሰቦቻቸውን ይርዱ።
፸፪ ወይም ለመጋቢነት ወይም በሌላ ጉዳይ አገልግሎታቸው ሁሉ መልካም ይሆናል ተብሎ በታሰበው መንገድ ወይም በአማካሪዎቹና በኤጲስ ቆጶሱ ውሳኔ መሰረት ተገቢውን ክፍያ ያግኙ።
፸፫ ኤጲስ ቆጶሱም፣ እንዲሁ፣ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ለሚሰጠው አገልግሎት እርዳታውን ወይም ትክክለኛ ክፍያን ያግኝ።
፸፬ እነሆ፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ማንኛቸውም ሰዎች ከመካከላችሁ በአመንዝራነት ምክንያት ከባለቤታቸውን በፍቺ ቢለዩ፣ ወይም በሌላ አባባል፣ በፊታችሁ በዚህም ምክንያት በተዋረደ ልብ ቢመሰከሩ፣ ከመካከላችሁ አውጥታችሁ አትጣሏቸው፤
፸፭ ነገር ግን ባለቤታቸውን በአመንዝራነት ምክንያት እንደተዉ፣ እናም እራሳቸው ስህተቱን የፈጸሙ እንደሆኑ፣ እናም ባለቤታቸው በህይወት መኖራቸውን ካወቃችሁ፣ ከመካከላችሁ ይጣላሉ።
፸፮ ደግሞም፣ እንዲህ እላችኋለሁ፣ የተጋቡ ከሆኑ እንደዚህ አይነቶቹን ምንም እንዳትቀበሏቸው በብርቱ ጥያቄ የነቃችሁ እና የተጠነቀቃችሁ ሁኑ፤
፸፯ እና ካላገቡም፣ ለሁሉም ኃጢአታቸው ንስሀ ይግቡ አለበለዚያም አትቀበሏቸውም።
፸፰ እናም ዳግም፣ የዚህች የክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባል የሆነ ሁሉም ሰው የቤተክርስቲያኗን ትእዛዛት እና ቃል ኪዳን ይጠብቅ።
፸፱ እናም እንዲህም ይሆናል፣ ከመካከላችሁ ማንም ሰው የሰውን ነፍስ ቢያጠፋ አሳልፋችሁ ስጧቸው እናም በምድሪቷ ህግ መሰረት ይቀጡ፤ ምክንያቱም እርሱ ይቅርታ እንደሌለው አስታውሱ፤ እና ይህም በምድሪቷ ህግጋት መሰረት ይረጋገጥ።
፹ እናም ማንም ወንድ ወይም ሴት ቢያመነዝር፣ በሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ የቤተክርስቲያን ሽማግሌዎች ፊት ይዳኙ ዘንድ ትቀርባለች ወይም ይቀርባል፣ እናም በጠላቶቹ ወይም ጠላቶቿ ሳይሆን፣ በሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ የቤተክርስቲያን ምስክሮች ፊት እያንዳንዱ በእርሱ ወይም በእርሷ ላይ የሚሰጠው ቃል ይጸናል፣ ነገር ግን ከሁለት በላይ ምስክሮች መኖራቸው ይመረጣል።
፹፩ ነገር ግን በሁለት ምስክሮች አንደበት ይኮነናል ወይም ትኮነናለች፤ እናም ሽማግሌዎች ጉዳዩን በቤተርስቲያኗ ፊት ያቀርባሉ፣ እናም በእግዚአብሔር ህግ ይዳኙ ዘንድ ቤተክርስቲያኗም እጆቿን በእርሱ ወይም በእርሷ ላይ ታነሳለች።
፹፪ እናም፣ ቢቻል፣ ኤጲስ ቆጶሱ መገኘቱም አስፈላጊ ነው።
፹፫ እናም በፊታችሁ ለሚመጡ ጉዳዮች ሁሉ እንዲሁ ታደርጋላችሁ።
፹፬ እናም ወንድ ወይም ሴት ቢዘርፍ ወይም ብትዘርፍ፣ ለምድሪቷ ህግ ይሰጣል ወይም ትሰጣለች።
፹፭ እናም ከሰረቀ ወይም ከሰረቀች፣ ለምድሪቷ ህግ ይሰጣል ወይም ትሰጣለች።
፹፮ እናም ቢዋሽ ወይም ብትዋሽ፣ ለምድሪቷ ህግ ይሰጣል ወይም ትሰጣለች።
፹፯ እናም ማንኛውንም አይነት ኃጢአት ቢያደርግ ወይም ብታደርግ፣ የእግዚአብሔር ህግ ለሆነው ይሰጣል ወይም ትሰጣለች።
፹፰ እናም ወንድሞቻችሁ ወይም እህቶቻችሁ ቢበድሏችሁ፣ ከእርሷ ወይም ከእርሱ ጋር በግል ተገናኙ፤ ከተናዘዘ ወይም ከተናዘዘችም እርቅን ታደርጋላችሁ።
፹፱ እናም ካልተናዘዘ ወይም ካልተናዘዘች፣ ለአባሎቹ ሳይሆን ለሽማግሌዎቹ፣ ለቤተክርስቲያን አልፎ ይሰጣል ወይም ትሰጣለች። እና ይህም በአለም ፊት ሳይሆን፣ በስብሰባ ይደረጋል።
፺ እናም ወንድምህ ወይም እህትህ ብዙዎችን ቢበድል ወይም ብትበድል፣ በብዙዎች ፊት ይገሰጻል ወይም ትገሰጻለች።
፺፩ እናም በግልጽ ማንም ሰው በግልጽ ቢበድል፣ ያፍርበት ወይም ታፍርበት ዘንድ በግልጽ ይገሰጻል ወይም ትገሰጻለች። እናም ባናዘዝባት ወይም ባትናዘዝባት፣ ለእግዚአብሔር ህግ አልፎ ይሰጣል ወይም ትሰጣለች።
፺፪ ማንም ሰው በስውር ቢበድል፣ ለበደለው ወይም ለበደለችው፣ እናም ለእግዚአብሔር በስውር ለመናዘዝ እድል ይኖረው ወይም ይኖራት ዘንድ፣ ቤተክርስቲያኗ በማስጠንቀቅ እንዳትናገረው ወይም እንዳትናገራት ዘንድ፣ በስውር ይገሰጻል ወይም ትገሰጻለች።
፺፫ እናም ሁሉንም ነገሮች በዚህ መልክ ታከናውናላችሁ።