ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፺፬


ክፍል ፺፬

በነሀሴ ፪፣ ፲፰፻፴፫ (እ.አ.አ.) በከርትላንድ ኦሀዮ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በኩል የተሰጠ ራዕይ። ሀይረም ስሚዝ፣ ሬኖልድስ ከሁን፣ እና ጄርድ ካርተር ለቤተክርስቲያን መገንባት በኮሚቴነት ተመድበዋል።

፩–፱፣ ጌታ ለቀዳሚ አመራር ስራ ስለሚገነባው ቤት የሚመለከት ትእዛዝ ሰጠ፤ ፲–፲፪፣ የማተሚያ ቤት ይገንባ፤ ፲፫–፲፯፣ ልዩ ውርሶች ተመድበዋል።

፩ ደግሞም፣ ባልንጀሮቼ እውነት እላችኋለሁ፣ በዚህ በከርትላንድ ምድር ውስጥ፣ በቤቴ በመጀመር፣ የፅዮን ካስማ ከተማን ጅማሬ መሰረት ለመጣል እና ለማዘጋጀት ትእዛዝን እሰጣችኋለሁ።

፪ እነሆም፣ በሰጠኋችሁ ምሳሌ መሰረት መደረግ አለበት።

፫ እና በደቡብ ያለው የመጀመሪያው ከፊል መሬት ለእኔ፣ ራዕዮችን ለሚቀበሉበት ለአመራር ስራ፣ ለአመራር ቤት መሰሪያ ይቀደስ፤ እናም ይህም ቤተክርስቲያኗን እና መንግስቱን በሚመለከቱ ሁሉም ነገሮች ለአመራር አገልግሎት ስራ ነው።

፬ እውነት እላችኋለሁ፣ ይህም፣ በውስጠኛው አደባባይ፣ አስራ ሰባት ሜትር በሀያ ሜትር ስፋት እና ርዝመቱ ይሁን።

፭ እና፣ ከዚህ በኋላ በሚሰጣችሁ ንድፍ መሰረት፣ የታች አደባባይና የላይ አደባባይ ይኑረው።

፮ እና፣ በክህነት ስልጣን ስርዓት መሰረት፣ ከዚህ በኋላ በሚሰጣችሁ ንድፍ መሰረት፣ ይህ ከመሰረቱ ጀምሮ ለጌታ ይቀደስ።

፯ እና ይህም ለአመራር ስራ ለጌታ ሁሉ ይቀደስ።

፰ እና ማንኛውም እርኩስ ነገር ወደውስጥ እንዲገባ አትፍቀዱ፤ እና ክብሬም በዚያ ይሆናል፣ እና በዚያም እገኛለሁ።

፱ ማንኛውም እርኩስ ነገር ቢገባበት ግን፣ ክብሬ በዚያ አይሆንም፤ እና ወደዚህም አልገባም።

፲ ደግሞም፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ሁለተኛው ከፊሉ መሬት ለእኔ ቤት መሰሪያ፣ ለቅዱስ መጻሕፍቴ መታተምና መተርጎም ስራ፣ እና ለማዛችሁ ማንኛቸውም ነገሮች ሁሉ፣ ለእኔ ይቀደስ።

፲፩ እና ይህም፣ በውስጥ አደባባዩ፣ አስራ ሰባት ሜትር በሀያ ሜትር ስፋት እና ርዝመት ይሁን፤ እና የበታች እና የላይ አደባባይ ይኑረው።

፲፪ እና ይህም ቤት ከመሰረቱ ጀምሮ፣ ለህትመት ስራ፣ በሚሰጣችሁ ንድፍ መሰረት በሁሉም ነገሮች ቅዱስ እና ያልረከሰ እንዲሆን ማንኛቸውም በማዛችሁ ሁሉም ነገሮች ሁሉ ለጌታ ይቀደስ።

፲፫ እና በሶስተኛው ከፊል መሬት ላይ አገልጋዬ ሀይረም ስሚዝ ውርሱን ይቀበል።

፲፬ እና በሰሜን ላይ ባለው በመጀመሪያው እና በሁለተኛው ከፊል ስፍራ ላይ አገልጋዬ ሬኖልድስ ከሁን እና ጀርድ ካርተር ውርሶቻቸውን ይቀበሉ—

፲፭ የመደብኩላቸውን ስራ ያከናውኑ ዘንድ፣ እኔ ጌታ በሰጠኋችሁ ትእዛዝ መሰረት የቤቶቼ የግንባታ ኮሚቴ ይሁኑ።

፲፮ እነዚህ ሁለት ቤቶች እነርሱን በሚመለከት ትእዛዝ እስክሰጣችሁ ድረስ እንዳይገነቡ።

፲፯ አሁንም በዚህ ጊዜ ምንም ተጨማሪ ነገርን አልሰጣችሁም። አሜን።