ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፶፭


ክፍል ፶፭

በሰኔ ፲፬፣ ፲፰፻፴፩ (እ.አ.አ.)፣ በከርትላንድ ኦሀዮ ውስጥ፣ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በኩል ለውልያም ደብሊው ፈልፕስ የተሰጠ ራዕይ። አታሚው ውልያም ደብሊው ፈልፕስ እና ቤተሰቡ ከርትላንድ ውስጥ ገና ደርሰው ነበር፣ እና ነቢዩም ስለ እርሱ ጉዳይ ጌታ መረጃ እንዲሰጠው ፈልጎ ነበር።

፩–፫፣ ውልያም ደብሊው ፈልፕስ እንዲጠመቅ፣ እንደ ሽማግሌ እንዲሾም፣ እና ወንጌሉን እንዲሰብክ ተጠርቷል እናም ተመርጧል፤ ፣ በቤተክርስቲያኗ ትምህርት ቤት ውስጥ ላሉትም ልጆች መጻህፍትንም እንዲጽፍ ነው፤ ፭–፮፣ የስራው አካባቢ ወደ ሆነው፣ ወደ ሚዙሪም ይጓዝ።

እነሆ፣ ጌታ፣ አዎን፣ እንዲሁም የአለም ሁሉ ጌታ፣ ለአንተ ለአገልጋዬ ውልያም እንዲህ ይላልህ፣ ተጠርተሀል እናም ተመርጠሀል፤ እና በውሀ ከተጠመቅህ በኋላ፣ ሙሉ አይንህን ወደ እግዚአብሔር ክብር በማድረግ ይህንንም ካላደረግህ፣ ለኃጢአቶችህ ስርየትን ታገኛለህ እና እጅንም በመጫን መንፈስ ቅዱስን ትቀበላለህ፤

እና ከዚያም በአገልጋዬ ጆሴፍ ስሚዝ፣ ዳግማዊ እጅ፣ በህያው እግዚአብሔር ልጅ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በመጠመቅ ንስሀን እና የኃጢአት ስርየትን ለመስበክ በዚህ ቤተክርስቲያን ሽማግሌ እንድትሆን ትሾማለህ።

እና በማንም ላይ እጆችህን ስትጭን፣ በፊቴ የተዋረዱ ከሆኑ፣ መንፈስ ቅዱስን የመስጠት ሀይል ይኖርሀል።

እና ዳግም፣ ለቤተክርስቲያኗ ትምህርት ቤቶች መጻህፍትን በማተም በመምረጥ እና በመጻፍ አገልጋዬን ኦሊቨር ካውድሪን በስራው እንድትረዳው፣ በዚህም እንደሚያስደስተኝ ህጻናት ልጆች በፊት ለፊቴ መመሪያን እንዲቀበሉ ታደርግ ዘንድ ትሾማለህ።

እና ዳግም፣ በእውነት እልሀለሁ፣ ለዚህም ምክንያት፣ ይህን ስራ ለማከናወን በምትወርስበት ምድር በዚያ ጸንተህ ትቆይ ዘንድ ከአገልጋዮቼ ጆሴፍ ስሚዝ፣ ዳግማዊ እና ስድኒ ሪግደን ጋር ትጓዛለህ።

እና ዳግም፣ አገልጋዬ ጆሴፍ ኮ ከእነርሱ ጋር ይጓዝ። እንዲሁም፣ እንደ ፈቃዴም፣ የሚቀረው ከዚህ በኋላ ይገለጻል። አሜን።