ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፷፫


ክፍል ፷፫

በነሀሴ ፴፣ ፲፰፻፴፩ (እ.አ.አ.)፣ በከርትላንድ ኦሀዮ ውስጥ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በኩል የተሰጠ ራዕይ። ነቢዩ፣ ስድኒ ሪግደን፣ እና ኦሊቨር ካውድሪ በነሀሴ ፳፯ ከሚዙሪ ጉዞአቸው ወደ ከርትላንድ ደርሰው ነበር። የጆሴፍ ስሚዝ ታሪክ ይህን ራዕይ እንዲህ በማለት ገልጿል፥ “ቤተክርስቲያኗ አዲስ በሆነችበት በእነዚህ ቀናት፣ ደህንነታችንን በሚመለከት ከጌታ ቃልን ለማግኘት ታላቅ ጉጉት ነበር፤ እናም አሁን የፅዮን ምድርን በሚመለከት የጊዜው አሳሳቢጉዳይ ስለነበር፣ ስለ ቅዱሳን መሰባሰብ እና መሬቶችን ስለመገዛት እና ስለ ሌሎች ጉዳዮች ከጌታ ተጨማሪ መረጃዎችን ጠየቅሁ።”

፩–፮፣ በኃጢአተኞች ላይ የቁጣ ቀን ይመጣል፤ ፯–፲፪፣ ምልክቶች በእምነት አማካይነት ይመጣሉ፤ ፲፫–፲፱፣ በልባቸው የሚያመነዝሩ እምነትን ይክዳሉ እናም ወደ እሳቱ ባሕር ይጣላሉ፤ ፣ የታመኑ በክብር በተለወጠችው ምድር ውርሳቸውን ይቀበላሉ፤ ፳፩፣ በክብር የመለወጥ ተራራ ላይ የነበረው ሙሉ ታሪክ ገና አልተገለጡም፤ ፳፪–፳፫፣ ታዛዡ የመንግስትን ሚስጥራት ይቀበላል፤ ፳፬–፴፩፣ የፅዮን ውርሶች ይገዙ፤ ፴፪–፴፭፣ ጌታ ጦርነቶችን አውጇል፣ እናም ኃጢአተኛ ኃጢአተኛውን ይገድላል፤ ፴፮–፵፰፣ ቅዱሳን ወደ ፅዮን ይሰባሰባሉ እናም ይህን ለመገንባትም ገንዘብ ይስጡ፤ ፵፱–፶፬፣ ለታማኞቹ በትንሳኤ፣ እና በአንድ ሺህ ዘመን ዳግም ምፅአት በረከቶች ተረጋግጠውላቸዋል፤ ፶፭–፶፰፣ ይህም የማስጠንቀቂያ ቀን ነው፤ ፶፱–፷፮፣ ያለስልጣን በሚጠቀሙት ዘንድ የጌታ ስም በከንቱ ይጠራል።

አድምጡ፣ እናንት ህዝብ ሆይ፣ እናም ልባችሁን ክፈቱ እናም ከሩቅም ስሙ፤ እናም፣ ራሳችሁን የጌታ ህዝብ ብላችሁ የምትጠሩትም ስሙ፣ እናም እናንተን በሚመለከት የጌታን ቃል እና ፍላጎት አድምጡ።

አዎን፣ እውነትም እላለሁ፣ በኃጢአተኛው እና በአመጸኛው ላይ የተቀጣጠለውንም የቁጣውን ቃል አድምጡ፤

ለመውሰድ የሚፈልገውን ይወስዳል፣ እና ለማዳን የሚፈልገውንም በህይወት ያድናል፤

እንደራሱ ፈቃድ እና ደስታም ይገነባል፤ እናም የፈለገውንም ያጠፋል፣ እናም ነፍስንም ወደ ገሀነም ይጥል ዘንድ ይቻለዋል።

እነሆ፣ እኔ ጌታ ድምጼን አሰማለሁ፣ እና ይህም ይከበራል።

ስለዚህ፣ በእውነት እላለሁ፣ ኃጢአተኛው ያድምጥ፣ እናም አመጸኛውም ይፍራ እናም ይንቀጥቀጥ፤ እናም የማያምኑትም ከንፈሮቻቸውን ይያዙ፣ እንደ አውሎ ነፋስ የቁጣው ቀን ይመጣባቸዋልና፣ እናም ስጋ ለባሽ ሁሉ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንኩኝም ያውቃሉ

እናም ምልክቶችን የሚሻ ምልክቶችን ያገኛል፣ ነገር ግን ለደህንነት አይሆንለትም።

እውነት እላችኋለሁ፣ በመካከላችሁ ምልክቶችን የሚሹ አሉ፣ እናም እንደነዚህ አይነቶችም ከመጀመሪያ ጀምሮም ነበሩ።

ነገር ግን፣ እነሆ፣ እምነት በምልክቶች አይመጣምና፣ ነገር ግን ምልክቶች የሚያምኑትን ይከተሏቸዋል።

አዎን፣ ምልክቶች የሚመጡት በእምነት ነው፣ በሰዎች ፈቃድ ወይም ፍላጎት ሳይሆን፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው።

፲፩ አዎን፣ ምልክቶች ታላቅ ስራዎች ይሆኑ ዘንድ በእምነት ይመጣሉ፣ ምክንያቱም ያለ እምነት ማንም ሰው እግዚአብሔርን ሊያስደስት አይችልምና፤ እናም እግዚአብሔር የተቆጣበት በእርሱም አይደሰትም፤ ስለዚህ፣ ለእንደእነዚህ አይነቶች፣ በቁጣ ከእርግማን በቀር፣ ምንም ምልክቶችን አያሳይም።

፲፪ ስለዚህ፣ እኔ ጌታ፣ በመካከላችሁ ለእምነት ምልክቶችን እና ድንቆችን ለሰዎች ጥቅም እና ለክብሬ ሳይሆን ለፈቃዳቸው በሚሹ ላይ አልተደሰትኩም።

፲፫ ይሁን እንጂ፣ ትእዛዛትን ሰጥቻለሁ፣ እናም ብዙዎችም ከትእዛዛቴ ፈቀቅ ብለዋል እናም አልጠበቋቸውም።

፲፬ በመካከላችሁም ዘማዊ እና ዘማዊት ነበሩ፤ አንዳንዶቹም ከእናንተ ተለይተዋል፣ እናም ከዚህ በኋላ የሚገለጡት ሌሎቹም ከእናንተ ጋር ቀርተዋል።

፲፭ እንደዚህ አይነቶቹ ይጠንቀቁ እናም ፈጥነውም ንስሀ ይግቡ፣ አለበለዚያም ፍርድ እንደ አጥማጅ ይመጣባቸዋል፣ እናም ሞኝነታቸውም በግልፅ ይታያል፣ እናም በህዝብ አይኖች ውስጥ ስራዎቻቸውም ይከተሏቸዋል።

፲፮ እናም፣ አስቀድሜ እንደተናገርሁ፣ በእውነት እንዲህ እላችኋላሁ፣ ሴትን የተመለከተ እናም የተመኛትም፣ ወይም ማናቸውም በልባቸው ቢያመነዝሩ፣ መንፈስም አይኖራቸውም፣ ነገር ግን እምነትን ይክዳሉ እናም ይፈራሉ።

፲፯ ስለዚህ፣ እኔ ጌታ እንዳልኩት፣ የሚፈሩና የማያምኑ፣ እናም የሐሰተኞችም ሁሉ፣ እናም ሀሰትን የሚወዱ እና የሚዋሹ፣ እና የሴሰኞችም፣ እና የአስማተኞችም፣ እና ጣዖትንም የሚያመልኩ፣ ዕድላቸው በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባሕር ነው፤ ይኸውም ሁለተኛው ሞት ነው።

፲፰ በእውነት አላለሁ፣ እነርሱ በመጀመሪያው ትንሳኤ ስፍራ አይኖራቸውም።

፲፱ እናም አሁን እነሆ፣ እኔ ጌታ እንዲህ እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች በመካከላችሁ ስላሉ፣ ትጸድቁ ዘንድ አይቻላችሁም።

ይሁን እንጂ፣ በእምነት የጸናው እና ፈቃዴንም የሚያደርገው፣ እርሱ ያሸንፋል፣ እናም በክብር የመለወጥ ቀን ሲመጣም ውርሱን ይቀበላል

፳፩ እንዲሁም፣ ሙሉ ታሪኩን ገና ያልተቀበላችሁትን፣ ለሐዋሪያቴ በተራራው ላይ ባሳየሁት ስርዓት ምድር በክብር ስትለወጥም፣ ውርሱን ይቀበላል።

፳፪ እናም አሁን፣ በእውነት እላችኋላሁ፣ እንደተናገርኳችሁ ፈቃዴን አሳውቃችኋለሁ፣ እነሆ እንድታውቁትም አደርጋለሁ፣ ይህም በትእዛዝ አይደለም ምክንያቱም ትእዛዛቴን የማያከብሩ ብዙዎች አሉና።

፳፫ ነገር ግን ትእዛዛቴን ለሚጠብቀው ለእርሱ የመንግስቴን ሚስጥራት እሰጠዋለሁ፣ እና በእርሱም ውስጥ ለዘለአለም ሕይወት የሚፈልቅ የህያው ውኃ ምንጭ ይሆናል።

፳፬ እናም አሁን፣ እነሆ ይህም ጌታ አምላካችሁ ለቅዱሳኑ ያለው ፍላጎት ይህ ነው፣ ቸነፈር የሚያመጣው ግራ መጋባት እንዳይኖር፣ በፍጥነት ሳይሆን፣ በፅዮን ምድር ራሳቸውን ይሰብስቡ።

፳፭ እነሆ፣ የፅዮንን ምድር—እኔ ጌታ በእጆቼ ይዣታለሁ፤

፳፮ ይሁን እንጂ፣ እኔ ጌታም የቄሣርን ለቄሣር አስረክቤአለሁ።

፳፯ ስለዚህ፣ እኔ ጌታ በአለም ትጠቀሙ ዘንድ፣ በአለምም የእኛ ነው የምትሉት እንዲኖራችሁ፣ እነርሱም በቁጣም እንዳይነሳሱባቸው፣ መሬቶች እንድትገዙ ፍቃዴ ነው።

፳፰ ሰይጣንም፣ ደምን እስከማፍሰስ ድረስም፣ እንዲያስቆጣቸው በልቦቻቸው ውስጥ ቁጣን ያነሳሳል።

፳፱ ስለዚህ፣ የፅዮን ምድርም በመግዛት ወይም በደም በስተቀር አይገኝም፣ አለበለዚያም ለእናንተ ምንም ውርስ የላችሁም።

እና በመግዛትም ቢሆን፣ እነሆ የተባረካችሁ ናችሁ፤

፴፩ እናም በደምም ቢሆን፣ ደምን ለማፍሰስ ስለተከለከላችሁ፣ እነሆ፣ ጠላቶቻችሁ ያጠቋችኋል፣ እናም ከከተማ ወደ ከተማም፣ ከምኩራብ ወደ ምኩራብ ትቀጣላችሁ፣ እናም ውርስን ለመቀበል ጥቂቶች ብቻ ይቀራሉ።

፴፪ እኔ ጌታም በኃጢአተኞቹ ተቆጣሁ፤ መንፈሴንም ከምድር ኗሪዎች እከለክላለሁ።

፴፫ በቁጣዬም ማልሁ፣ እናም በምድርም ፊት ላይ ጦርነቶችን አወጅኩኝ፣ እናም ኃጢአተኛውም ኃጢአተኛውን ይገድላል፣ እናም ፍርሀትም በእያንዳንዱ ሰው ላይ ይመጣል፤

፴፬ እናም ቅዱሳንም ደግመው አያመልጡም፤ ይሁን እንጂ፣ እኔ ጌታ ከእነርሱ ጋር ነኝ፣ እና ከአባቴ ፊትም ከሰማይ እወርዳለሁ እናም ኃጢአተኞቹንም በማይጠፋ እሳት አነዳቸዋለሁ።

፴፭ እናም እነሆ፣ ይህም ገና አይደለም፣ ነገር ግን በቅርቡ የሚሆን ነው።

፴፮ ስለዚህ፣ በምድር ላይ እነዚህን ነገሮች ሁሉ እኔ ጌታ በማወጄ ምክንያት፣ የእኔ ቅዱሳን ራሳቸውን በፅዮን ምድር መሰብሰባቸው ፍቃዴ ነው፤

፴፯ እናም እያንዳንዱ ሰው ፅድቅን በእጆቹ እና ታማኝነትን በወገቡ ይውሰድ፣ እናም የማስጠንቀቂያ ድምፅም ወደ ምድር ኗሪዎች ይሰማ፤ እናም በቃል እና ፈጥኖ በመሄድ በስደት በኃጢአተኞች ላይ ክፉ ነገሮች እንደሚመጡ ይገለጹ።

፴፰ ስለዚህ፣ በከርትላንድ ውስጥ በዚህ እርሻ የሚኖሩት ደቀ መዛሙርቴ የስጋዊ ጉዳያቸውን ያዘጋጁ።

፴፱ አገልጋዬ ታይተስ ቢሊንግስ፣ በሚመጣው ጸደይ፣ ትእዛዝ እስከምሰጣቸው ድረስ ከማይሄዱት ለራሴ ከምጠብቃቸው በስተቀር በዚህ ስፍራ ከሚኖሩት ጋር፣ ወደ ፅዮን ምድር ለመጓዝ መዘጋጀት እንዲችል፣ ሀላፊነት ያለበትን መሬትን ይሽጥ።

እናም የሚቀረውም ገንዝብ ሁሉ፣ ብዙም ይሁን ጥቂት ግድ የለኝም፣ ወደ ፅዮን ምድር እንዲቀበሉ ለሾምኳቸው ይላክ።

፵፩ እነሆም እኔ ጌታ፣ ለአገልጋዬ ጆሴፍ ስሚዝ ዳግማዊ ወደ ፅዮን ምድር የሚሄዱትን፣ እና በዚህም የሚቀሩትን ደቀ መዛሙርቴን ለመለየት የሚያስችለውን ሀይል እሰጠዋለሁ።

፵፪ እናም አገልጋዬ ኒውል ኬ ውትኒ የግምጃ ቤቱን፣ ወይም በሌላ ቃላት፣ የግምጃ ቤቱን በትንሽ ወቅት እንደያዘ ይቀጥል።

፵፫ ይሁን እንጂ፣ ለመስጠት የሚችለውን ገንዘብ ሁሉ ወደ ፅዮን ምድር እንዲላክ ይስጥ።

፵፬ እነሆ፣ እነዚህ ነገሮች በእጆቹ ውስጥ ናቸው፣ በጥበብም ያድርጋቸው።

፵፭ በእውነትም እላለሁ፣ ለሚቀሩትም ደቀ መዛሙርት ወኪል እንዲሆንም ይሾም፣ እናም ለዚህ ሀይልም ይሾም፤

፵፮ እናም አሁን፣ ከአገልጋዬ ኦሊቨር ካውድሪ ጋር፣ እነዚህን ነገሮች በማብራራት፣ ፈጥኖም ቤተክርስቲያኖችን ይጎብኝ። እነሆ፣ ገንዘብን እንደመራሁት ማግኘቱ ፍቃዴ ነው።

፵፯ ታማኝ የሆነው እና የሚጸናውም አለምን ያሸንፋል።

፵፰ ወደ ፅዮን ምድር ሀብትን የላከው በዚህ አለም ውርስን ይቀበላል፣ እናም ስራዎቹ ይከተሉታል፣ እናም በሚመጣው አለምም ዋጋው ይሰጠዋል።

፵፱ አዎን፣ እናም፣ ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው፣ ጌታ ሲመጣም፣ እና አሮጌው ነገሮች አልፈው፣ እናም ሁሉም ነገሮች አዲስ ሲሆኑም፣ ከሞት ይነሳሉ እናም ከዚህም በኋላ አይሞቱምና፣ እናም በቅዱስ ከተማውም ከጌታም ውርስን ይቀበላሉ።

እናም ጌታ ሲመጣ የሚኖረው፣ እና ሀይማኖትን የጠበቀውም፣ እርሱ የተባረከ ነው፤ ይሁን እንጂ በሰው እድሜ እንዲሞትም ተወሰኖለታል።

፶፩ ስለዚህ፣ ልጆች እድሜአቸው እስኪገፋ ድረስም ያድጋሉ፤ ሽማግሌዎችም ይሞታሉ፤ ነገር ግን በምድርም ትቢያ ውስጥ አያንቀላፉም፣ ነገር ግን በቅጽበት ዓይንም ይለወጣሉ

፶፪ ስለዚህ፣ ለዚህም ምክንያት ነው ሀዋሪያት ለአለም ስለሙታን ትንሳኤ የሰበኩት።

፶፫ እነዚህ ነገሮች ወደፊት መመልከት ያለባችሁ ነገሮች ናቸው፤ እናም፣ እንደ ጌታ አነጋገር፣ እናም በሚመጣው ጊዜም፣ እንዲሁም በሰው ልጅ ምፅዓት ቀን፣ አሁንም ቀርቧልና

፶፬ እናም እስከዚያም ሰአት ድረስ በብልህ መካከል ሰነፎች ደናግል ይኖራሉ፤ እናም በዚያም ሰዓት ጻድቃን ከኃጢአተኞቹ ሁሉ የሚለዩበት ይመጣል፤ እናም በዚያም ቀን ኃጢአተኞቹን ነቅለው እንዲያወጡ እና በማይጠፋው እሳት ውስጥ እንዲወረውሯቸው መላእክቴን እልካለሁ።

፶፭ እናም አሁን እነሆ፣ እውነት እላችኋለሁ፣ እኔ ጌታ በአገልጋዬ ስድኒ ሪግደን አልተደሰትኩም፤ በልቡም ራሱን ከፍ ከፍ ያደርጋል፣ እናም ምክርንም አልተቀበለምና፣ ነገር ግን መንፈስንም አሳዝኗል፤

፶፮ ስለዚህ የእርሱ ፅሑፍ በጌታ ዘንድ ተቀባይነት የለውም፣ እናም ሌላም ይጻፍ፤ እናም ጌታ ይህን ካልተቀበለውም፣ እነሆ በሾምኩበት ሹመትም አይቆምም።

፶፯ እና ደግሞም፣ እውነት እላችኋለሁ፣ በየዋህነት ኃጢአተኞችን ንስሀ እንዲገቡ ለማስጠንቀቅ በልቦቻቸው ፍላጎት ያላቸው፣ በዚህ ሀይልም ይሾሙ።

፶፰ ይህም፣ የብዙ ቃላት ቀን ሳይሆን፣ የማስጠንቀቂያ ቀን ነውና። እኔ ጌታም በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ አይዘበትብኝምና።

፶፱ እነሆ፣ እኔም ከበላይ ነኝ፣ እናም በበታችም ሀይሌ ይኖራል። ከሁሉም በላይ፣ እና በሁሉም የምሰራ፣ እናም በሁሉም የምኖር ነኝ፣ እናም ሁሉንም እመረምራለሁ፣ እናም ሁሉም ነገሮች ለእኔ ተገዢ የሚሆኑበትም ቀን ይመጣል።

እነሆ፣ እኔ አልፋና ኦሜጋ፣ እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ነኝ።

፷፩ ስለዚህ፣ ሁሉም ሰዎች እንዴት ስሜን በከንፈሮቻቸው እንደሚይዙ ይጠንቀቁ—

፷፪ ምክንያቱም እነሆ፣ እውነት እላለሁ፣ የጌታን ስም በከንቱ የሚጠቀሙ፣ እናም ያለስልጣን የሚጠሩ፣ በዚህ እርግማን ውስጥ ያሉ ብዙዎች አሉ።

፷፫ ስለዚህ፣ ቤተክርስቲያን ለኃጢአታቸው ንስሀ ይግቡ፣ እናም እኔ ጌታ የእኔ አደርጋቸዋለሁ፤ አለበለዚያም ይቆረጣሉ።

፷፬ ከላይ የሚመጣውእርሱ ቅዱስ እንደሆነ፣ እናም በጥንቃቄ እና በመንፈስም ቁጥጥር መነገር እንዳለበትም አስታውሱ፤ እና በዚህም ውስጥ እርግማን የለም፣ እናም መንፈሱን የምትቀበሉት በጸሎት በኩል ነው፤ ስለዚህ፣ ይህ ባይሆን በእርግማን ይቀራሉ።

፷፭ በጸሎት በመንፈስ እንደተማሩት፣ አገልጋዮቼ ጆሴፍ ስሚዝ ዳግማዊ እና ስድኒ ሪግደን ቤትን ይፈልጉባቸው።

፷፮ እነዚህ ከሁሉም ይልቅ የዘለአለም ክብርን፣ አለበለዚያም ታላቅን እርግማን፣ ይቀበሉ ዘንድ፣ እነዚህንም ነገሮች በትዕግስት ማሸነፍ ይቻል ዘንድ ነውና። አሜን።