ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፸፭


ክፍል ፸፭

በጥር ፳፭፣ ፲፰፻፴፪ (እ.አ.አ.)፣ በአምኸርስት ኦሀዮ ውስጥ፣ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በኩል የተሰጠ ራዕይ። ይህ ክፍል በአንድ ቀን የተሰጡ ሁለት የተለያዩ ራዕዮችን (የመጀመሪያው ከቁጥር ፩ እስከ ፳፪ ውስጥ እና ሁለተኛው ከቁጥር ፳፫ እስከ ፴፮ ውስጥ ያሉትን) የያዘ ነው። ጊዜውም ጆሴፍ ስሚዝ እንደ ታላቅ ክህነት ፕሬዘደንት ተደግፎ የተሾመበት ጉባኤ ነበር። መልእክታቸውን ሰዎች እንዲገባቸው በሚያደርጉበት ጊዜ ችግር ያጋጠማቸው አንዳንድ ሽማግሌዎች ወዲያውኑ ስለ ሀላፊነታቸው በዝርዝር ለመማር ፍላጎት አደረባቸው። እነዚህ ራዕዮች ተከትለው መጡ።

፩–፭፣ ወንጌልን የሚሰብኩ ታማኝ ሽማግሌዎች ዘለአለማዊ ህይወትን ያገኛሉ፤ ፮–፲፪፣ ሁሉንም ነገሮች የሚያስተምረውን አፅናኙን ለመቀበል ጸልዩ፣ ፲፫–፳፪፣ መልእክታቸውን በማይቀበሉት ላይ ሽማግሌዎች በፍርድ ይቀመጣሉ፤ ፳፫–፴፮፣ የሚስዮኖች ቤተሰቦች ከቤተክርስቲያኗ እርዳታን ይቀበሉ።

እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ እኔ፣ እንዲሁም አልፋና ኦሜጋ፣ ጌታችሁ እና አምላካችሁ፣ በመንፈስ ድምፅም እናገራለሁ—

እናንት ወንጌሌን ለመስበክ፣ እና የወይን ስፍራዬን ለመግረዝ ስማችሁን የሰጣችሁ ሆይ፣ አድምጡ።

እነሆ፣ እንዲህ እላችኋለሁ ሳትዘገዩ፣ ወይም ስራ ሳትፈቱ፣ በአቅማችሁ ሁሉ እየሰራችሁ ትሄዱ ዘንድ ፍቃዴ ነው—

በሰጠኋችሁ ራዕዮች እና ትእዛዛት መሰረት እውነትን በማወጅ ድምጻችሁን እንደ መለከት ድምጽ ከፍ አድርጉ።

እናም ታማኝ ብትሆኑ ብዙ ነዶም በጀርባችሁ ትሸክማላችሁ፣ እናም በክብር፣ እናም በግርማአለሟችነት፣ እናም በዘለአለም ሕይወት አክሊልም ይጫንላችኋል።

ስለዚህ፣ ለአገልጋዬ ዊልያም መክለለን በእውነትም እለዋለሁ፣ ወደ ምስራቅ አገሮች እንዲሄድ የሰጠሁትን ትእዛዝ ሽሬዋለሁ

እናም አዲስ ተልዕኮ እና አዲስ ትእዛዝንም እሰጠዋለሁ፣ በዚህም እኔ ጌታ ለልቡ ስለማጉረምረሙም እገስጸዋለሁ

እናም ኃጢአትን ሰርቷል፤ ይሁን እንጂ፣ ይቅርታ ሰጥቼዋለሁ እና ዳግም እንዲህም እለዋለሁ፣ ወደ ደቡብ አገሮች ሂድ።

እናም አገልጋዬ ሉክ ጆንሰን ከእርሱም ጋር ይሂድ፣ እናም ያዘዝኳቸውን ነገሮችንም ያውጁ—

የሚያስፈልጋቸውን ሁሉንም ነገሮች የሚያስተምራቸውን አፅናኙን በጌታ ስም በመጥራትም—

፲፩ እንዳይታክቱም ዘወትር ይጸልዩ፤ እና ይህን እስካደረጉ ድረስ፣ እስከመጨረሻም አብሬአቸው እሆናለሁ።

፲፪ እነሆ፣ ይህም እናንተን በተመልከተ የጌታ አምላካችሁ ፈቃድ ነው። እንዲሁም ይሁን። አሜን።

፲፫ እናም ዳግም፣ በእውነት ጌታ እንዲህ ይላል፣ አገልጋዬ ኦርሰን ሀይድ እና አገልጋዬ ሳሙኤል ኤች ስሚዝ ወደ ምስራቅ አገሮች ጎዞአቸውን ይጀምሩ፣ እናም ያዘዝኳቸውን ነገሮች ያውጁ፤ እናም ታማኝም ቢሆኑ፣ እስከ መጨረሻም አብሬአቸው እሆናለሁ።

፲፬ እና ደግሞም፣ በእውነት ለአገልጋዬ ላይመን ጆንሰን፣ እናም ለአገልጋዬ ኦርሰን ፕራት ይህን እላቸዋለሁ፣ እነርሱም ወደ ምስራቅ አገሮች ጎዞአቸውን ያቅኑ፣ እናም እነሆ፣ እስከ መጨረሻውም እኔ ከእነርሱ ጋር ነኝና።

፲፭ እና ደግሞም፣ ለአገልጋዬ አሳ ዶድስ፣ እና ለአገልጋዬ ካልቭስ ውልሰን እናገራለሁ፣ እነርሱም ወደ ምእራብ አገሮች ጎዞአቸውን ያቅኑ፣ እናም እንዳዘዝኳቸው ወንጌሌን ያውጁ።

፲፮ እናም ታማኝ የሆነውም ሁሉንም ነገሮች ያሸንፋል፣ እናም በመጨረሻም ቀን ከፍ ይደረጋል።

፲፯ እና ደግሞም፣ ለአገልጋዬ ሜጀር ኤን አሽሊ እና ለአገልጋዬ በር ሪግስ እላቸዋልለሁ፣ ወደ ደቡብ አገሮችም ጉዞአቸውን ያቅኑ።

፲፰ አዎን፣ ሁሉም እንዳዘዝኳቸው፣ በየቤቱ፣ እና በየመንደሩ፣ እና በየከተማው ይጓዙ።

፲፱ እናም በሚገቡበትም ቤት ውስጥ፣ እና ከተቀበሏችሁም፣ በቤቱ ላይ በረከታችሁን ተዉ።

እናም በምትገቡበትም ቤት ውስጥ፣ ባይቀበሏችሁም፣ በቶሎ ከቤቱ ውጡ፣ እናም ምስክር እንዲሆንባቸው ከእግራችሁ ትቢያን አራግፉ

፳፩ እናም በደስታ እና በስኬታማነት ይሞላሉ፤ እናም ይህን እወቁ፣ በፍርድም ቀን የእዚያ ቤት ፈራጆች ትሆናላችሁ እናም ትኮንናቸዋላችሁም፤

፳፪ እናም ከዚያ ቤት ይልቅ ለአረመኔው በፍርድ ቀን ይቀልለታል፤ ስለዚህ፣ ወገባችሁን ታጠቁ እናም ታማኝ ሁኑ፣ እናም ሁሉንም ነገሮች ታሸንፋላችሁ፣ እናም በመጨረሻም ቀን ከፍ ትደረጋላችሁ። እንዲህም ይሁን። አሜን።

፳፫ ደግሞም፣ ጌታ ለእናንተ እንዲህ ይላል፣ ስለእናንተ ያለውን ፈቃዱን ለማወቅ ስማችሁን የሰጣችሁ የቤተክርስቲያኔ ሽማግሌዎች ሆይ—

፳፬ እነሆ፣ እላችኋለሁ፣ እነዚያን ቤተሰቦች መርዳት፣ እናም የተጠሩት እና ወደ አለም ወንጌልን ለመስበክ መሄድ ያለባቸውን ቤተሰቦች መርዳት፣ የቤተክርስቲያኗ ሀላፊነት ነው።

፳፭ ስለዚህ፣ እኔ ጌታ ይህን ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፣ ወንድሞቻችሁ ልቦቻቸውን ለመክፈት ፈቃደኛ እስከሆኑ ድረስ፣ ለቤተሰቦቻችሁ ስፍራዎችን ተቀበሉ።

፳፮ እናም ስፍራዎችን፣ እና የቤተክርስቲያኗን እርዳታ ለቤተሰባቸው ለመቀበል የሚችሉት እንደነዚህ አይነቶች፣ ወደ አለም፣ ወደ ምስራቅም ወይም ምዕራብ፣ ወይም ሰሜን፣ ወይም ወደ ደቡብ፣ ከመሄድ እንዳይቀሩ።

፳፯ ይጠይቁ እናም ይቀበላሉ፣ ያንኳኩ እናም ይከፈትላቸዋል፣ እናም ከላይም፣ እንዲሁም ከአፅናኙ ዘንድ፣ የት መሄድ እንዳለባቸው ያውቃሉ።

፳፰ እና ደግሞም፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ቤተሰቡን የማስተዳደር ሀላፊነት ያለበት እያንዳንዱም ሰው፣ ያስተዳድር፣ እናም ዘውዱን በምንም አያጣውም፣ እናም በቤተክርስቲያኗም ውስጥ ያገልግል።

፳፱ እያንዳንዱም ሰው በሁሉም ነገሮች ይትጋ። እናም ስራ ፈት የሆነ፣ ንስሀ ካልገባ እና መንገዱን ካላሻሻለ፣ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ስፍራ አይኖረውም።

ስለዚህ፣ አገልጋዬ ስሚኦን ካርተር እና አገልጋዬ ኢመር ሀሪስ በአገልግሎት ይተባበሩ፤

፴፩ እና ደግሞም አገልጋዬ ኤዝራ ታየር እና አገልጋዬ ቶማስ ቢ ማርሽም

፴፪ እና ደግሞም አገልጋዬ ሀይረም ስሚዝ እና አገልጋዬ ሬይኖልድ ካሁንም፤

፴፫ እና ደግሞም አገልጋዬ ዳንኤል ስታተን እና አገልጋዬ ሲሞር ብረንሰንም፤

፴፬ እና ደግሞም አገልጋዬ ሲልቨስተር ስሚዝ እና አገልጋዬ ጊድየን ካርተር

፴፭ እና ደግሞም አገልጋዬ ራግልስ ኤምስ እና አገልጋዬ ስቲቨን ባርነትም፤

፴፮ እና ደግሞም አገልጋዬ ማይካ ቢ ዌልተን እና አገልጋዬ ኢድን ስሚዝም። እንዲህም ይሁን። አሜን።