ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፻፳፭


ክፍል ፻፳፭

በመጋቢት ፲፰፻፵፩ (እ.አ.አ.)፣ በናቩ ኢለኖይ ውስጥ በአየዋ ክልል ውስጥ ያሉትን ቅዱሳን በሚመለከት ለነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ የተሰጠ ራዕይ።

፩–፬፣ ቅዱሳን ከተማዎችን ይስሩ እና የፅዮን ካስማዎችንም ይሰብስቡ።

በአየዋ ክልል ያሉትን ቅዱሳን በሚመለከት የጌታ ፈቃድ ምንድን ነው?

ጌታ እንዲህ ይላል፣ እውነት እላችኋለሁ በስሜ ራሳቸውን የሚጠሩና ቅዱሳኔ ለመሆን የሚጥሩ፣ የምፈልገውን ቢያደርጉ እና እነርሱን የሚመለከቱ ትእዛዛቴን ቢያከብሩ፣ በአገልጋዬ ጆሴፍ በምመድብላቸው ስፍራዎች ራሳቸውን አብረው ይሰብስቡ፣ እና ለሚመጣው ዘመንም ይዘጋጁ ዘንድ በስሜም ከተማዎችን ይስሩ።

ከናቩ ከተማ የተለየ ከተማ በስሜ ይስሩ፣ እና ስሙም ዛራሔምላ ይሁን።

እና በዚህ ውስጥ ለመኖር ፈቃድ ኖሮአቸው ከምስራቅ፣ እና ከምዕራብ፣ እና ከሰሜን፣ እና ከደቡብ የመጡት ሁሉ፣ ከዚህ፣ እና ከናሽቪል ከተማ፣ ወይም ከናቩ ከተማ፣ ከመደብኳቸው ካስማዎች ሁሉ ውርሶቻቸውን ያግኙ፣ ይላል ጌታ።