ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፲፮


ክፍል ፲፮

ሰኔ ፲፰፻፳፱ (እ.አ.አ.) በፈየት፣ ኒው ዮርክ፣ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ አማካይነት ለፒተር ዊትመር ዳግማዊ፣ የተሰጠ ራዕይ። (የክፍል ፲፬ ርዕስን ተመልከቱ)። በኋላም ፒተር ዊትመር ዳግማዊ ከስምንቶቹ አንዱ የመፅሐፈ ሞርሞን ምስክር ሆነ።

፩–፪፣ የጌታ ክንድ በምድር ላይ ሁሉ ነው፤ ፫–፮፣ ወንጌልን መስበክ እና ነፍሳትን ማዳን ታላቅ ዋጋ ያለው ነገር ነው።

፩ አድምጥ፣ አገልጋዬ ፒተር እናም የጌታህን እና የአዳኝህን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃላት አድምጥ።

፪ ስለሆነም እነሆ፣ ክንዴ በምድር ሁሉ ላይ ስለሆነ፣ በስልጣን እና በሀይል እናገርሀለሁ።

፫ ከእኔ እና ከአንተ ብቻ በቀር ማንም ሰው የማያውቀውን ነገር እነግርሀለሁ—

፬ ስለሆነ ብዙ ጊዜ ለአንተ ትልቅ ዋጋ ያለው ነገር ምን እንደሆነ ከእኔ ለማወቅ ፈልገሀል።

፭ እነሆ፣ ስለ እነዚህ ነገሮች፣ እናም የሰጠሁህን ቃላቴን በትእዛዛቴ መሰረት ስለተናገርክ የተባረክ ነህ።

፮ እናም አሁን፣ እነሆ እንዲህ እልሀለሁ፣ ለአንተ ታላቅ ዋጋ ያለው፣ ነፍሳትን ወደ እኔ ታመጣ ዘንድ፣ ከእነርሱ ጋር በአባቴ መንግስት ታርፍ ዘንድ፣ ለዚህ ህዝብ ንስሀን ማወጅ ይሆናል። አሜን።