ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፲፭


ክፍል ፲፭

ሰኔ ፲፰፻፳፱ (እ.አ.አ.) በፈየት፣ ኒው ዮርክ፣ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ አማካይነት ለጆን ዊትመር የተሰጠ ራዕይ (የክፍል ፲፬ ርዕስን ተመልከቱ)። ይህ በቅርበት እና በሚገርም ሁኔታ የግል መልዕክት ነው፣ ጌታ በጆን ዊትመር እና በራሱ ብቻ የሚታወቀውን ይናገራል። ጆን ዊትመር በኋላም ከስምንቶቹ አንዱ የመፅሐፈ ሞርሞን ምስክር ሆነ።

፩–፪፣ የጌታ ክንድ በምድር ላይ ሁሉ ነው፤ ፫–፮፣ ወንጌልን መስበክ እና ነፍሳትን ማዳን ታላቅ ዋጋ ያለው ነገር ነው።

፩ አድምጥ፣ አገልጋዬ ጆን እናም የጌታህን እና የአዳኝህን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃላት አድምጥ።

፪ ስለሆነም እነሆ፣ ክንዴ በምድር ሁሉ ላይ ስለሆነ፣ በስልጣን እና በሀይል እናገርሀለሁ።

፫ እናም ከእኔ እና ከአንተ ብቻ በቀር ማንም ሰው የማያውቀውን ነገር እነግርሀለሁ—

፬ ስለሆነ ብዙ ጊዜ ላንተ ትልቅ ዋጋ ያለው ነገር ምን እንደሆነ ከእኔ ለማወቅ ፈልገሀል።

፭ እነሆ፣ ስለ እነዚህ ነገሮች፣ እናም የሰጠሁህን ቃላቴን በትእዛዛቴ መሰረት ስለተናገርህ የተባረክ ነህ።

፮ እናም አሁን፣ እነሆ፣ እንዲህ እልሀለሁ፣ ለአንተ ታላቅ ዋጋ ያለው ነገር፣ ነፍሳትን ወደ እኔ ታመጣ ዘንድ ከእነርሱም ጋር በአባቴ መንግስት ታርፍ ዘንድ ለዚህ ህዝብ ንስሀን ማወጅ ይሆናል። አሜን።