ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፻፲፭


ክፍል ፻፲፭

በሚያዝያ ፳፮፣ ፲፰፻፴፰ (እ.አ.አ.) በፋር ዌስት ሚዙሪ ውስጥ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በኩል የተሰጠውን የእዚያን ስፍራና የጌታን ቤት መገንባት በሚመለከት የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያሳውቅ ራዕይ። ይህ ራዕይ ለቤተክርስቲያኗ አመራር ሀላፊዎች እና አባላት የተሰጠ ንግግር ነው።

፩–፬፣ ጌታ ቤተክርስቲያኑን የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ብሎ ጠራ፤ ፭–፮፣ ፅዮን እና ስቴኳ የቅዱሳን መጠበቂያ እና መሸሸጊያ ናቸው፤ ፯–፲፮፣ ቅዱሳን በፋር ዌስት ላይ የጌታን ቤት እንዲገነቡ ታዝዘዋል፤ ፲፯–፲፱፣ ጆሴፍ ስሚዝ የእግዚአብሔርን መንግስትን ቁልፍ በምድር ይዟል።

ለአገልጋዬ ጆሴፍ ስሚዝ ዳግማዊ እና ደግሞም ለአገልጋዬ ስድኒ ሪግደን፣ እና ደግሞም ለአገልጋዬ ሀይረም ስሚዝ፣ እና ለተመደቡት ከዚህም በኋላ ለሚመደቡት አማካሪዎቻችሁ በእውነት ጌታ እንዲህ ይላል፤

ደግሞም ለአንተ፣ ለአገልጋዬ ኤድዋርድ ፓርትሪጅ እና ለአማካሪዎቹ፤

ደግሞም በፅዮን ውስጥ በቤተክርስቲያኔ ከፍተኛ ሸንጎ አባል ለሆናችሁ ታማኝ አገልጋዮቼ፣ እንዲህም ተብሎ ይጠራልና፣ እና በአለም ሁሉ በውጪ ለተበተኑት ለኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያኔ ሽማግሌዎች እና ህዝብ ሁሉ።

በመጨረሻዎቹ ቀናትም ቤተክርስቲያኔ የምትጠራው በዚህ፣ እንዲሁም በየኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ስም ነው።

ለሁላችሁም እውነት እላችኋለሁ፥ ለህዝቦች መመሪያ ትሆኑ ዘንድ ተነሱ እና አብሩ፤

እና በፅዮን ምድርና በካስማዎቿ ላይ አብሮ መሰብሰቡ ከአውሎ ነፋስ፣ እና ቁጣም ሳይቀላቀል በምድር ሁሉ ላይ ከሚፈሰው መጠበቂያ እና መሸሸጊያ ይሆን ዘንድ ተነሱ እናም አብሩ።

ከተማው፣ ፋር ዌስት፣ ቅዱስና ለእኔ የተቀደሰ ምድር ይሁን፤ እና ከሁሉም በላይ ቅዱስ ይባላል፣ እናንት የቆማችሁበት ምድር ቅዱስ ነውና።

ስለዚህ፣ ያመልኩኝ ዘንድ ለቅዱሳኔ መሰብሰቢያ እንዲሆን፣ ቤትን ትገነቡልኝ ዘንድ አዝዛችኋለሁ።

እና ለዚህም ስራ መጀመሪያ፣ እና መሰረት፣ እና የማዘጋጃውም ስራ በሚቀጥለው በጋ ይሁን፤

እና መጀመሪያውም በሚቀጥለው ሀምሌ ፬ ቀን ላይ ይሁን፤ እና ከዚያም ጊዜ በኋላ ህዝቤ በስሜ ቤት ይገነቡልኝ ዘንድ በቅንነት ይስሩ፤

፲፩ እና ከዚህ ቀን አንድ አመት በኋላ ለቤቴ መሰረትን መገንባት ዳግም ይጀምሩ።

፲፪ በዚህም ከዚያ ቀን ጀምሮ፣ ከማዕዘን ድንጋዩ እስከ ላይኛው ያለው እስከሚፈጸም፣ ምንም ነገር ሳይቅር ሁሉም እስከሚፈጸም ድረስ በቅንነት ይስሩ።

፲፫ እውነት እላችኋለሁ፣ አገልጋዬ ጆሴፍ፣ ወይም አገልጋዬ ስድኒ፣ ወይም አገልጋዬ ሀይረም በስሜ ቤት ለመገንባት ተጨማሪ እዳ አይግቡ፤

፲፬ ነገር ግን ለእነርሱ በማሳያቸው ምሳሌ መሰረት ለስሜ ቤት ይሰራ።

፲፭ እና ህዝቤ ለአመራሮቻቸው በማሳየው ምሳሌ መሰረት ባይገነቡት፣ ከእጆቻቸው ይህን አልቀበልም።

፲፮ ነገር ግን ህዝቤ ለአመራሮቻቸው፣ እንዲሁም ለአገልጋዬ ጆሴፍ እና አማካሪዎቹ፣ በማሳያቸው ምሳሌ መሰረት ቢገነቡ፣ ከዚያም ከህዝቤ እጆች ይህን እቀበላለሁ።

፲፯ ደግሞም፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ቅዱሳኔ በተሰበሰቡበት የፋር ዌስት ከተማ በፍጥነት መገንባቱ ፍቃዴ ነው።

፲፰ ደግሞም በአካባቢው በሚገኙት ስፍራዎችም፣ ከጊዜ ወደጊዜ በአገልጋዬ ጆሴፍ ስሚዝ በሚገለጹበት፣ ለካስማዎች ሌሎች ስፍራዎችም ይመደባሉ።

፲፱ እነሆ፣ እኔ ከእርሱ ጋር እሆናለሁ፣ እናም ከህዝቡም ፊት እቀድሰዋለሁና፤ የዚህን መንግስትና አገልግሎት ቁልፎች ሰጥቼዋለሁና። እንዲህም ይሁን። አሜን።