ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፹፪


ክፍል ፹፪

በሚያዝያ ፳፮፣ ፲፰፻፴፪ (እ.አ.አ.)፣ በኢንድፐንደንስ፣ በጃክሰን የግዛት ክፍል ሚዙሪ ለነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ የተሰጠ ራዕይ። ጊዜው በቤተክርስቲያኗ ሊቀ ካህናት እና ሽማግሌዎች የምክር ስብሰባ ላይ ነበር። በምክር ስብሰባው ላይ፣ ከዚህ በፊት በጥር ፳፭፣ ፲፰፻፴፪ (እ.አ.አ.) በአምኸርስት ኦሀዮ ውስጥ በሊቀ ካህናት፣ በሽማግሌዎች፣ እና በአባላት ጉባኤ ላይ ለዚህ ሀላፊነት የተሾመው ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ እንደ ታላቅ ክህነት ፕሬዘደንት ተደግፎ ነበር (የክፍል ፸፭ ርዕስን ተመልከቱ)። ይህ ራዕይ ከዚህ በፊት (ክፍል ፸፰) የቤተክርስቲያኗን ንግድ እና የማተም ጥረቶችን የሚቆጣጠር የትብብር ድርጅት ተብሎ ይታወቅ የነበረውን ድርጅት (በኋላም፣ በጆሴፍ ስሚዝ አመራር፣ “ስርዓት” የሚለው ቃል “ድርጅት” የሚለውን ተካ) እንዲመሰረት ተደጋጋሚ መመሪያ ሰጠ።

፩–፬፣ ብዙ ለተሰጠው፣ ከእርሱ ብዙ ይጠበቃል፤ ፭–፯፣ ጭለማ በአለም ላይ ነግሷል፤ ፰–፲፫፣ እሱ ያለውን ስናደርግ ጌታ በቃሊ ይታሰራል፤ ፲፬–፲፰፣ ፅዮን በውበት እና በቅድስና መጨመር አለባት፤ ፲፱–፳፬፣ እያንዳንዱ ሰው ለባልንጀራው መልካም ሊሻ ይገባዋል።

አገልጋዮቼ እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ፣ እርስ በርስ መተላለፋችሁን ይቅር ብትባባሉ፣ እኔ ጌታ እንዲሁ ይቅር እላችኋለሁ።

ይህም ቢሆን፣ በመካከላችሁ ታላቅ ኃጢአት የሰሩ አሉ፤ አዎን፣ ሁላችሁም ኃጢአት ሰርታችኋል፤ ነገር ግን፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ተጠንቀቁ፣ እናም ከኃጢአት ተቆጠቡ፣ አለበለዚያ የበለጠ ፍርድ በራሳችሁ ላይ ይወድቅባችኋል።

ብዙ ለተሰጠው ከእርሱ ብዙ ይጠበቅበታልና፤ እናም በታላቅ ብርሀን ላይ ኃጢአት የሚሰራ የባሰውን ፍርድ ይቀበላል።

ለራዕዮች ስሜን ትጠራላችሁ፣ እናም እኔ እሰጣችኋለሁ፤ እናም የምሰጣችሁን፣ የምለውን ባትጠብቁ፣ ህግ ተላላፊዎች ትሆናላችሁ፤ እናም ፍትህና ፍርድ በህጌ ላይ የተመደቡ ቅጣት ናቸው።

ስለዚህ፣ ለአንዱ የምናገረው ለሁሉም የተናገርሁት ነው፥ ነቅታችሁ ጠብቁጠላትም ተፅዕኖውን እያስፋፋ ነው፣ እናም ጭለማም ነግሷል፤

እናም የእግዚአብሔር ቁጣ በምድር ኗሪዎች ላይ ተቀጣጥሏል፣ እናም ማንም መልካምን አያደርግም፣ ሁሉም መንገዳቸውን ስተዋል

እናም አሁን፣ እውነት እላችኋለሁ፣ እኔ ጌታ እናንተን በምንም ኃጢአት ሀላፊ አላደርጋችሁም፤ መንገዳችሁን ሂዱ ዳግመኛም ኃጢአትን አትስሩ፤ ነገር ግን ኃጢአት ለሚሰራው ነፍስ የቀድሞው ኃጢአት ይመለስበታል፣ ይላል ጌታ አምላካችሁ።

እና ደግሜም፣ እላችኋለሁ፣ ለእናንተ ያለኝ ፈቃዴን ትረዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤

ወይም፣ በሌላ አባባል፣ ለደህንነታችሁ ይሆንላችሁ ዘንድ፣ በፊቴ ምን ማድረግ እንዳለባችሁ መመሪያ እሰጣችኋለሁ።

እኔ ጌታ የምለውን ስታደርጉ በቃሌ እታሰራለሁ፤ ነገር ግን የምለውን ባታደርጉ፣ የተስፋ ቃል የላችሁም።

፲፩ ስለዚህ፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ፍርድ ወዲያውኑ ሊመጣ ካልሆነ በቀር፣ በተለያዩ ሀላፊነታችሁ አገልጋዮቼ ኤድዋርድ ፓርትሪጅ እና ኒወል ኬ ውትኒ፣ ኤ ስድኒ ጊልበርት እና ስድኒ ሪግደን፣ እና አገልጋዬ ጆሴፍ ስሚዝ፣ እና ጆን ዊትመር እና ኦሊቨር ካውድሪ፣ እና ደብሊው ደብሊው ፌልፕስ እና ማርቲን ሀሪስ በመተላለፍ ሊሰበር በማይቻል ስምምነት እና ቃል ኪዳን ይስማሙ—

፲፪ የድሆችን ጉዳዮች፣ በፅዮን ምድር እና በከርትላንድ ምድር ውስጥ ከኤጲስ ቆጶስ አመራር ጋር ግንኙነት ያላቸውን ነገሮች ሁሉ ለማስተዳደር በቃል ኪዳን ይስማሙ፤

፲፫ የከርትላንድን ምድር በራሴ ጊዜ ለልዑል እግዚአብሔር ቅዱሳን ጥቅም፣ እና ለፅዮን ካስማ፣ ቀድሼዋለሁና።

፲፬ ፅዮን በውበት፣ እና በቅድስና፣ ልትልቅ ይገባል፤ ድንበሮችዋም ሊሰፉ፣ ካስማዎቿም ሊጠናከሩ፣ አዎን፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ፅዮን ልትነሳ እና የውበት ልብሷን ልትለብስ ይገባል።

፲፭ ስለዚህ፣ በዚህ ቃል ኪዳን ራሳችሁን እንድታስተሳስሩ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፣ እናም ይህም በጌታ ህግጋት መሰረት መደረግ አለበት።

፲፮ እነሆ፣ ይህም በእኔ ዘንድ መልካም የሚሆንላችሁ ጥበብም ነው።

፲፯ እናም እናንተም እኩል ትሆኑ ዘንድ ይገባል፣ ወይም በሌላ አባባል፣ የሀላፊነታችሁን ጉዳዮች የማስተዳደር ጥቅም፣ እያንዳንዱ ሰው፣ ፍላጎቱ ትክክለኛ እስከሆነ ድረስ፣ በፍላጎቱ እና በሚያስፈልገው፣ በንብረቶች ላይ እኩል መብት ይኖረዋል—

፲፰ እናም ይህ ሁሉ ለህያው እግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ጥቅም፣ እያንዳንዱ ሰው ችሎታውን ያሻሽል ዘንድ፣ እያንዳንዱም ሰው ሌሎች ችሎታዎችን ያገኝ ዘንድ፣ አዎን፣ ከአንድ መቶ እጥፍ፣ የቤተክርስቲያኗ ሁሉ የጋራ ንብረት እንዲሆን ወደ ጌታ ጎተራ ያገባ ዘንድ—

፲፱ እያንዳንዱ ሰው የባልንጀራውን ፍላጎት እንዲሻ፣ እናም ለሁሉም ነገሮች ሙሉ አይኑን ወደ እግዚአብሔር ክብር ያደርግ ዘንድ ነው።

ይህ ስርዓት፣ ኃጢአት ካልሰራችሁ በስተቀር፣ እንደ ዘለአለም ስርዓት ለእናንተ፣ እና ለእናንተ ተተኪዎቻችሁ መድቤአለሁ።

፳፩ እናም በዚህ ቃል ኪዳን ላይ ኃጢአት የሚፈፅም ነፍስ፣ እና ልቡን በዚህ ላይ የሚያደነድን፣ በቤተክርስቲያኔ ህግጋት መሰረት ይደረግባቸዋል፣ እናም እስከቤዛ ቀን በሰይጣን እንዲጎሰሙ ይሰጣሉ።

፳፪ እና አሁን፣ እውነት እላችኋለሁ፣ እና ይህ ጥበብ ነው፣ በዓመፃ ገንዘብ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ፣ እናም እነዚህም አያጠፏችሁም።

፳፫ ፍርድን ለእኔ ብቻ ተዉት፣ የእኔ ነውና እናም እከፍለዋለሁ። ሰላም ከእናንተ ጋር ይሁን፣ በረከቶቼ ከእናንተ ዘንድ ይኑሩ።

፳፬ ከፅናታችሁ ካልወደቃችሁ፣ መንግስትም የእናንተ ናትና፣ እናም ለዘለአለምም ትሆናለች። እንዲሁም ይሁን። አሜን።