ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፺፫


ክፍል ፺፫

በግንቦት ፮፣ ፲፰፻፴፫ (እ.አ.አ.) በከርትላንድ ኦሀዮ ውስጥ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በኩል የተሰጠ ራዕይ።

፩–፭፣ ታማኝ የሆኑ ሁሉ ጌታን ያያሉ፤ ፮–፲፰፣ የእግዚአብሔር ልጅ የአብን ክብር በሙላት እስከሚቀበል ድረስ ከጸጋ ወደ ጸጋ እንደሄደ ዮሐንስ መሰከረ፤ ፲፱–፳፣ ታማኝ ሰዎች፣ ከጸጋ ወደ ጸጋ በመሄድ ሙሉነቱን ደግመው መቀበል ይችላሉ፤ ፳፩–፳፪፣ በክርስቶስ በኩል የተወለዱትም የበኩር ቤተክርስቲያን ናቸው፤ ፳፫–፳፰፣ ክርስቶስ የእውነትን ሁሉ ሙላት ተቀበለ፣ እና ሰውም በታዛዥነት ይህንኑ ሊያደርግ ይችላል፤ ፳፱–፴፪፣ ሰው በመጀመሪያም ከእግዚአብሔር ጋር ነበር፤ ፴፫–፴፭፣ ንጥረ-ነገሮች ዘለአለማዊ ናቸው፣ እና ሰው የደስታን ሙላት በትንሳኤ ሊቀበል ይችላል፤ ፴፮–፴፯፣ የእግዚአብሔር ክብር የመረዳት ችሎታ ነው፤ ፴፰–፵፣ በክርስቶስ ቤዛነት ምክንያት ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ንጹሀን ናቸው፤ ፵፩–፶፫፣ መሪ ወንድሞች ቤተሰቦቻቸውን በስርዓት እንዲያደራጁ ታዘዙ።

በእውነት፣ ጌታ እንዲህ ይላል፥ ኃጢአቶቹን የሚተውና ወደ እኔ የሚመጣ፣ እና ስሜን የሚጠራ፣ እና ድምጼን የሚያከብር፣ እና ትእዛዛቴን የሚያከብር እያንዳንዱ ነፍስ ሁሉ ፊቴን የሚያይበት እና እኔ እንደሆንኩም የሚያውቅበት ጊዜ ይመጣል፤

እና እኔ ወደ አለም ለሚመጣ ለእያንዳንዱ ሰው ሁሉ የማበራ የእውነት ብርሀን ነኝ፤

እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ ነው እናም አብና እኔም አንድ ነን—

ሙላቱን ስለሰጠኝ አብ ነኝ፣ እና በአለም ውስጥ ስለነበርኩና ስጋንም ድንኳኔ ስላደረግሁ፣ እና በሰውም ልጆች መካከል ስለኖርኩ ወልድ ነኝ።

በአለም ውስጥ ነበርኩ እና አባቴንም ተቀበልኩኝ፣ እና ስራዎቹም በግልፅ የታዩ ነበሩ።

እና ዮሐንስ አየና ስለክብሬ ሙላት መሰከረ፣ እና የዮሐንስ ሙሉ ምስክር ከዚህ በኋላ ይገለጣል።

እናም እንዲህ በማለትም መሰከረ፥ ክብሩን፣ አለም ከመሆኗ በፊት ከመጀመሪያ ጀምሮ እንደነበረ አየሁ፤

ስለዚህ፣ በመጀመሪያው ቃል ነበር፣ እርሱም ቃል፣ እንዲሁም የደህንነት መላእክተኛ ነበርና—

የአለም ብርሀን እና አዳኝ፤ አለም በእርሱ ሆኗልና፣ እና በእርሱም ውስጥ የሰዎች ህይወት እና የሰዎች ብርሀን ነበር፣ ወደ አለምም የመጣ የእውነት መንፈስ እርሱ ነውና።

አለማት በእርሱ ሆነዋልና፤ ሰዎችም በእርሱ ተፈጥረዋል፤ ሁሉም ነገሮች በእርሱ፣ በእርሱም አማካይነት፣ እና ከእርሱ ሆነዋል።

፲፩ እና እኔ ዮሐንስ ክብሩን፣ በጸጋ እና በእውነት፣ እንዲሁም በመጣው እና በስጋም በኖረው፣ እና በመካከላችን በኖረው፣ በእውነት መንፈስ ተሞልቶ፣ እንደ አብ አንድያ ልጅ ክብሩን እንዳየሁ እመሰክራለሁ።

፲፪ እና እኔ ዮሐንስ በመጀመሪያ ሙላትን እንዳልተቀበለ፣ ነገር ግን በጸጋ ላይ ጸጋን እንደተቀበለ አየሁ፤

፲፫ እና ሙላትን በመጀመሪያ አልተቀበለም፣ ነገር ግን ሙላትን እስከሚቀበል ድረስ ከጸጋ ወደ ጸጋ ቀጠለ፤

፲፬ እና ሙላትን በመጀመሪያ ስላልተቀበለ፣ በዚህም የእግዚአብሔር ልጅ ተብሎ ተጠርቷል።

፲፭ እና እኔ ዮሐንስ እመሰክራለሁ እና አስተውሉ፣ ሰማያት ተከፈቱ መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ላይም በርግብ አምሳል ወረደ፣ እናም አረፈበት፣ እና ድምፅ ከሰማያት መጥቶ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ።

፲፮ እና እኔ ዮሐንስ እርሱ የአብን ክብር በሙላት እንደተቀበለ እመሰክራለሁ፤

፲፯ እና ሀይልን ሁሉ፣ በሰማይ እና በምድር ላይ ተቀበለ፣ እና የአብ ክብርም ከእርሱ ጋር ነበር፣ በእርሱ ውስጥም ይኖራልና።

፲፰ እና እንዲህም ይሆናል፣ እናንት ታማኝ ብትሆኑ የዮሐንስን ምስክር በሙላት ትቀበላላችሁና።

፲፱ እነዚህን አባባል የምሰጣችሁ እንድትረዱ እና እንዴት እንደምታመልኩ እንድታውቁ፣ እና ምን እንደምታመልኩ እንድታውቁ፣ በስሜ ወደ አብ እንድትመጡ፣ እና በጊዜም ሙላትን ትቀበሉ ዘንድ ነው።

ትእዛዛቴን የምታከብሩ ከሆናችሁም ሙላቱን ትቀበላላችሁና፣ እና እኔ በአብ እንደሆንኩ እናንት በእኔ ትከብራላችሁ፤ ስለዚህ፣ እላችኋለሁ፣ በጸጋ ላይ ጸጋን ትቀበላላችሁ።

፳፩ አሁንም፣ እውነት እላችኋለሁ በመጀመሪያም ከአብ ዘንድ ነበርኩኝ፣ እና በኩርም ነኝ፤

፳፪ እና በእኔ የተወለዱትም የዚህ ክብር ተካፋዮች ናቸው፣ እና የበኩር ቤተክርስቲያንም ናቸው።

፳፫ አስቀድማችሁ ከአብ ጋር የነበራችሁ እናንተ መንፈስ፣ እንዲሁም የእውነት መንፈስ ነበራችሁ፤

፳፬ እና ነገሮች እንዳሉ፣ እንደነበሩ፣ እናም ወደፊት እንደሚሆኑ የሚታወቅበት እውነት ነው።

፳፭ እና ማንኛውም ከዚህ በላይ ወይም በታች የሆነው ከክፉው መንፈስ ነው፣ እርሱም ከመጀመሪያ ሀሰተኛ የነበረው ነው።

፳፮ የእውነት መንፈስም እግዚአብሔር ነው። እኔ የእውነት መንፈስ ነኝ፣ እና ዮሐንስ ስለእኔ እንዲህ በማለት መስክሯል፥ የእውነትን ሙላት፣ አዎን፣ እንዲሁም ሁሉንም እውነቶች ተቀበለ።

፳፯ እና ትእዛዛቱን ካላከበረ በስተቀር ማንም ሰው ሙላትን አይቀበልም።

፳፰ ትእዛዛቱን የሚያከብርም፣ በእውነት እና ሁሉንም ነገሮች በማወቅ እስከሚከበር ድረስ፣ እውነት እና ብርሀንን ይቀበላል።

፳፱ ሰው ደግሞ በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር ጋር ነበር። የመረዳት ችሎታ፣ ወይም የእውነት ብርሀን፣ የተፈጠረ ወይም የተሰራ አይደለም፣ በእርግጥም ሊሆን አይችልም።

ሁሉም እውነት እግዚአብሔር ባስቀመጣቸው ተፅዕኖ አካባቢያቸው፣ በራሳቸው የሚሰሩ፣ እንደየራሳቸው የመረዳት ችሎታ፣ ራሳቸውን የቻሉ ናቸው፤ አለበለዚያም ምንም አይኖርም።

፴፩ እነሆ፣ ይህ የሰው ነጻ ምርጫ ነው፣ እና ይህ የሰው ኩነኔ ነው፤ ከመጀመሪያ የነበረው በግልጽ ስለታየላቸው፣ እና ብርሀንንም አልተቀበሉትምና።

፴፪ እና መንፈሱ ብርሀንን የማይቀበል በእርሱ በፍርድ ላይ ነው።

፴፫ ሰው መንፈስ ነውና። ንጥረ-ነገሮች ዘለአለማዊ ናቸው፣ እና መንፈስ እና ንጥረ-ነገር ሳይለያዩ የተያያዙ፣ የደስታን ሙላትን የሚቀበሉ ናቸው።

፴፬ እና ሲለያዩም፣ ሰው የደስታን ሙላት አይቀበልም።

፴፭ ንጥረ-ነገሮች የእግዚአብሔር ድንኳን ናቸው፤ አዎን፣ ሰውም የእግዚአብሔር ድንኳን፣ እንዲሁም ቤተመቅደሳት፣ ነው፤ እና ቤተመቅደሱ የረከሰ ቢሆን፣ እግዚአብሔር ያንን ቤተመቅደስ ያፈርሰዋልና።

፴፮ የእግዚአብሔር ክብር የመረዳት ችሎታ ነው፣ ወይም በሌላ ቃላት፣ ብርሀንና እውነት ነው።

፴፯ ብርሀን እና እውነት ክፉውን ይተዋል።

፴፰ እያንዳንዱ የሰው መንፈስ በመጀመሪያ የዋህ ነበር፤ እና እግዚአብሔር ሰውን ከውድቀቱ ሲያድን፣ ሰዎችም ዳግም በህጻንነት በእግዚአብሔር ፊት የዋህ ሆኑ።

፴፱ ክፉውም መጣ እና፣ ባለመታዘዝና በአባቶቻቸው ባህል ምክንያት፣ ብርሀንን እና እውነትን ከሰዎች ልጆች ነጠቀ

ነገር ግን ልጆቻችሁን በብርሀን እና በእውነት እንድታሳድጓቸው ዘንድ አዛችኋለሁ።

፵፩ ነገር ግን አገልጋዬ ፍረድሪክ ጂ ዊሊያምስ እውነት እልሀለሁ፣ በዚህ ኩነኔ ቀጥለሀል፤

፵፪ በትእዛዛትም በኩል ልጆችህን ብርሀን እና እውነት አላስተማርክም፤ እና ክፉውም በአንተ ላይ ሀይል አለው፣ እና ይህም የስቃይህ ምክንያት ነው።

፵፫ አሁንም ትእዛዝ እሰጥሀለሁ—የምትድን ቢሆን ቤትህን በስርዓት አደራጅ፣ በቤትህ ውስጥ አያሌ ትክክል ያልሆኑ ነገሮች አሉና።

፵፬ ለአገልጋዬ ስድኒ ሪግደን በእውነት እለዋለሁ፣ በአንዳንድ ነገሮች ልጆቹን በሚመለከት ትእዛዝን አላከበረም፤ ስለዚህ፣ አስቀድሞ ቤቱን በስርዓት ያደራጅ።

፵፭ በእውነት፣ ለአገልጋዬ ጆሴፍ ስሚዝ ዳግማዊ ይህን እላለሁ፣ ወይም በሌላ ቃላት፣ ባልንጀሮቼ ብዬ እጠራችኋለሁ፣ እናንት ባልንጀሮቼ ናችሁና፣ እና ከእኔም ጋር ውርስ ይኖራችኋል—

፵፮ አግልጋዮቼ ብዬ የምጠራችሁ በአለም ምክንያት ነው፣ እና እናንተም ለእነርሱ በእኔ ምክንያት አገልጋዮቻቸው ናችሁ—

፵፯ አሁንም፣ በእውነት ለአገልጋዬ ጆሴፍ ስሚዝ ዳግማዊ እላለሁ—ትእዛዛትን አላከበርክም፣ እና በጌታ ፊትም ተገስጸህ መቆም ያስፈልግሀል፤

፵፰ ቤተሰብህ ንስሀ መግባትና አንዳንድ ነገሮችን መተው አለባቸው፣ እና የምትላቸውንም በቅንነት ማድመጥ ያስፈልጋቸዋል፣ ወይም ከስፍራቸው ይወጣሉ።

፵፱ ለአንዱ የምለው ለሁሉም እላለሁ፤ ዘወትር ጸልዩ አለበለዚያም ክፉው በውስጣችሁ ሀይል ይኖረዋል፣ እና ከስፍራችሁ ያስወጣችኋል።

የቤተክርስቲያኔ ኤጲስ ቆጶስ፣ አገልጋዬ ኒውል ኬ ዊትኒም፣ ሊገሰፅ፣ እና ቤተሰቡን በስርዓት ሊያደራጅ፣ እና በቤትም በተጨማሪ ቅን እና አሳቢ እንዲሆኑ፣ እና ዘወትርም እንዲጸልዩ ሊያደርግ ያስፈልገዋል፣ ወይም ከስፍራቸው ይወጣሉ።

፶፩ ባልንጀሮቼ፣ አሁን እላችኋለሁ፣ አገልጋዬ ስድኒ ሪግደን በጉዞው ይሂድ፣ እና ይፍጠን፣ እና ደግሞም በምሰጠው የንግግር ችሎታ የጌታን የተወደደች አመትን፣ እና የደህንነትን ወንጌልን ያውጅ፤ እና በአንድ አላማ በምታደርጉት የእምነት ጸሎት እደግፈዋለሁ።

፶፪ እና አገልጋዬ ጆሴፍ ስሚዝ ዳግማዊ፣ እና ፍረድሪክ ጂ ዊሊያምስም ይፍጠኑ፣ እና እንድ እምነት ጸሎታቸውም ይሰጣቸዋል፤ እና እኔ የምላችሁን እስከጠበቃችሁ ድረስ በዚህ አለምም፣ ሆነ በሚመጣው አለም አትሸነፉም።

፶፫ እና፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ቅዱስ መጻሕፍቴን ለመተርጎም እንድትፈጥኑ፣ እና የታሪክ፣ እና የሀገሮች፣ እና የመንግስታት፣ የእግዚአብሔር እና የሰው ህግጋት እውቀትን እንድታገኙ ፍቃዴ ነው፣ ይህም ሁሉ ለፅዮን ደህንነት ነው። አሜን።