ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፺፫


ክፍል ፺፫

በግንቦት ፮፣ ፲፰፻፴፫ (እ.አ.አ.) በከርትላንድ ኦሀዮ ውስጥ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በኩል የተሰጠ ራዕይ።

፩–፭፣ ታማኝ የሆኑ ሁሉ ጌታን ያያሉ፤ ፮–፲፰፣ የእግዚአብሔር ልጅ የአብን ክብር በሙላት እስከሚቀበል ድረስ ከጸጋ ወደ ጸጋ እንደሄደ ዮሐንስ መሰከረ፤ ፲፱–፳፣ ታማኝ ሰዎች፣ ከጸጋ ወደ ጸጋ በመሄድ ሙሉነቱን ደግመው መቀበል ይችላሉ፤ ፳፩–፳፪፣ በክርስቶስ በኩል የተወለዱትም የበኩር ቤተክርስቲያን ናቸው፤ ፳፫–፳፰፣ ክርስቶስ የእውነትን ሁሉ ሙላት ተቀበለ፣ እና ሰውም በታዛዥነት ይህንኑ ሊያደርግ ይችላል፤ ፳፱–፴፪፣ ሰው በመጀመሪያም ከእግዚአብሔር ጋር ነበር፤ ፴፫–፴፭፣ ንጥረ-ነገሮች ዘለአለማዊ ናቸው፣ እና ሰው የደስታን ሙላት በትንሳኤ ሊቀበል ይችላል፤ ፴፮–፴፯፣ የእግዚአብሔር ክብር የመረዳት ችሎታ ነው፤ ፴፰–፵፣ በክርስቶስ ቤዛነት ምክንያት ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ንጹሀን ናቸው፤ ፵፩–፶፫፣ መሪ ወንድሞች ቤተሰቦቻቸውን በስርዓት እንዲያደራጁ ታዘዙ።

፩ በእውነት፣ ጌታ እንዲህ ይላል፥ ኃጢአቶቹን የሚተውና ወደ እኔ የሚመጣ፣ እና ስሜን የሚጠራ፣ እና ድምጼን የሚያከብር፣ እና ትእዛዛቴን የሚያከብር እያንዳንዱ ነፍስ ሁሉ ፊቴን የሚያይበት እና እኔ እንደሆንኩም የሚያውቅበት ጊዜ ይመጣል፤

፪ እና እኔ ወደ አለም ለሚመጣ ለእያንዳንዱ ሰው ሁሉ የማበራ የእውነት ብርሀን ነኝ፤

፫ እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ ነው እናም አብና እኔም አንድ ነን—

፬ ሙላቱን ስለሰጠኝ አብ ነኝ፣ እና በአለም ውስጥ ስለነበርኩና ስጋንም ድንኳኔ ስላደረግሁ፣ እና በሰውም ልጆች መካከል ስለኖርኩ ወልድ ነኝ።

፭ በአለም ውስጥ ነበርኩ እና አባቴንም ተቀበልኩኝ፣ እና ስራዎቹም በግልፅ የታዩ ነበሩ።

፮ እና ዮሐንስ አየና ስለክብሬ ሙላት መሰከረ፣ እና የዮሐንስ ሙሉ ምስክር ከዚህ በኋላ ይገለጣል።

፯ እናም እንዲህ በማለትም መሰከረ፥ ክብሩን፣ አለም ከመሆኗ በፊት ከመጀመሪያ ጀምሮ እንደነበረ አየሁ፤

፰ ስለዚህ፣ በመጀመሪያው ቃል ነበር፣ እርሱም ቃል፣ እንዲሁም የደህንነት መላእክተኛ ነበርና—

፱ የአለም ብርሀን እና አዳኝ፤ አለም በእርሱ ሆኗልና፣ እና በእርሱም ውስጥ የሰዎች ህይወት እና የሰዎች ብርሀን ነበር፣ ወደ አለምም የመጣ የእውነት መንፈስ እርሱ ነውና።

፲ አለማት በእርሱ ሆነዋልና፤ ሰዎችም በእርሱ ተፈጥረዋል፤ ሁሉም ነገሮች በእርሱ፣ በእርሱም አማካይነት፣ እና ከእርሱ ሆነዋል።

፲፩ እና እኔ ዮሐንስ ክብሩን፣ በጸጋ እና በእውነት፣ እንዲሁም በመጣው እና በስጋም በኖረው፣ እና በመካከላችን በኖረው፣ በእውነት መንፈስ ተሞልቶ፣ እንደ አብ አንድያ ልጅ ክብሩን እንዳየሁ እመሰክራለሁ።

፲፪ እና እኔ ዮሐንስ በመጀመሪያ ሙላትን እንዳልተቀበለ፣ ነገር ግን በጸጋ ላይ ጸጋን እንደተቀበለ አየሁ፤

፲፫ እና ሙላትን በመጀመሪያ አልተቀበለም፣ ነገር ግን ሙላትን እስከሚቀበል ድረስ ከጸጋ ወደ ጸጋ ቀጠለ፤

፲፬ እና ሙላትን በመጀመሪያ ስላልተቀበለ፣ በዚህም የእግዚአብሔር ልጅ ተብሎ ተጠርቷል።

፲፭ እና እኔ ዮሐንስ እመሰክራለሁ እና አስተውሉ፣ ሰማያት ተከፈቱ መንፈስ ቅዱስ በእርሱ ላይም በርግብ አምሳል ወረደ፣ እናም አረፈበት፣ እና ድምፅ ከሰማያት መጥቶ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ።

፲፮ እና እኔ ዮሐንስ እርሱ የአብን ክብር በሙላት እንደተቀበለ እመሰክራለሁ፤

፲፯ እና ሀይልን ሁሉ፣ በሰማይ እና በምድር ላይ ተቀበለ፣ እና የአብ ክብርም ከእርሱ ጋር ነበር፣ በእርሱ ውስጥም ይኖራልና።

፲፰ እና እንዲህም ይሆናል፣ እናንት ታማኝ ብትሆኑ የዮሐንስን ምስክር በሙላት ትቀበላላችሁና።

፲፱ እነዚህን አባባል የምሰጣችሁ እንድትረዱ እና እንዴት እንደምታመልኩ እንድታውቁ፣ እና ምን እንደምታመልኩ እንድታውቁ፣ በስሜ ወደ አብ እንድትመጡ፣ እና በጊዜም ሙላትን ትቀበሉ ዘንድ ነው።

፳ ትእዛዛቴን የምታከብሩ ከሆናችሁም ሙላቱን ትቀበላላችሁና፣ እና እኔ በአብ እንደሆንኩ እናንት በእኔ ትከብራላችሁ፤ ስለዚህ፣ እላችኋለሁ፣ በጸጋ ላይ ጸጋን ትቀበላላችሁ።

፳፩ አሁንም፣ እውነት እላችኋለሁ በመጀመሪያም ከአብ ዘንድ ነበርኩኝ፣ እና በኩርም ነኝ፤

፳፪ እና በእኔ የተወለዱትም የዚህ ክብር ተካፋዮች ናቸው፣ እና የበኩር ቤተክርስቲያንም ናቸው።

፳፫ አስቀድማችሁ ከአብ ጋር የነበራችሁ እናንተ መንፈስ፣ እንዲሁም የእውነት መንፈስ ነበራችሁ፤

፳፬ እና ነገሮች እንዳሉ፣ እንደነበሩ፣ እናም ወደፊት እንደሚሆኑ የሚታወቅበት እውነት ነው።

፳፭ እና ማንኛውም ከዚህ በላይ ወይም በታች የሆነው ከክፉው መንፈስ ነው፣ እርሱም ከመጀመሪያ ሀሰተኛ የነበረው ነው።

፳፮ የእውነት መንፈስም እግዚአብሔር ነው። እኔ የእውነት መንፈስ ነኝ፣ እና ዮሐንስ ስለእኔ እንዲህ በማለት መስክሯል፥ የእውነትን ሙላት፣ አዎን፣ እንዲሁም ሁሉንም እውነቶች ተቀበለ።

፳፯ እና ትእዛዛቱን ካላከበረ በስተቀር ማንም ሰው ሙላትን አይቀበልም።

፳፰ ትእዛዛቱን የሚያከብርም፣ በእውነት እና ሁሉንም ነገሮች በማወቅ እስከሚከበር ድረስ፣ እውነት እና ብርሀንን ይቀበላል።

፳፱ ሰው ደግሞ በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር ጋር ነበር። የመረዳት ችሎታ፣ ወይም የእውነት ብርሀን፣ የተፈጠረ ወይም የተሰራ አይደለም፣ በእርግጥም ሊሆን አይችልም።

፴ ሁሉም እውነት እግዚአብሔር ባስቀመጣቸው ተፅዕኖ አካባቢያቸው፣ በራሳቸው የሚሰሩ፣ እንደየራሳቸው የመረዳት ችሎታ፣ ራሳቸውን የቻሉ ናቸው፤ አለበለዚያም ምንም አይኖርም።

፴፩ እነሆ፣ ይህ የሰው ነጻ ምርጫ ነው፣ እና ይህ የሰው ኩነኔ ነው፤ ከመጀመሪያ የነበረው በግልጽ ስለታየላቸው፣ እና ብርሀንንም አልተቀበሉትምና።

፴፪ እና መንፈሱ ብርሀንን የማይቀበል በእርሱ በፍርድ ላይ ነው።

፴፫ ሰው መንፈስ ነውና። ንጥረ-ነገሮች ዘለአለማዊ ናቸው፣ እና መንፈስ እና ንጥረ-ነገር ሳይለያዩ የተያያዙ፣ የደስታን ሙላትን የሚቀበሉ ናቸው።

፴፬ እና ሲለያዩም፣ ሰው የደስታን ሙላት አይቀበልም።

፴፭ ንጥረ-ነገሮች የእግዚአብሔር ድንኳን ናቸው፤ አዎን፣ ሰውም የእግዚአብሔር ድንኳን፣ እንዲሁም ቤተመቅደሳት፣ ነው፤ እና ቤተመቅደሱ የረከሰ ቢሆን፣ እግዚአብሔር ያንን ቤተመቅደስ ያፈርሰዋልና።

፴፮ የእግዚአብሔር ክብር የመረዳት ችሎታ ነው፣ ወይም በሌላ ቃላት፣ ብርሀንና እውነት ነው።

፴፯ ብርሀን እና እውነት ክፉውን ይተዋል።

፴፰ እያንዳንዱ የሰው መንፈስ በመጀመሪያ የዋህ ነበር፤ እና እግዚአብሔር ሰውን ከውድቀቱ ሲያድን፣ ሰዎችም ዳግም በህጻንነት በእግዚአብሔር ፊት የዋህ ሆኑ።

፴፱ ክፉውም መጣ እና፣ ባለመታዘዝና በአባቶቻቸው ባህል ምክንያት፣ ብርሀንን እና እውነትን ከሰዎች ልጆች ነጠቀ።

፵ ነገር ግን ልጆቻችሁን በብርሀን እና በእውነት እንድታሳድጓቸው ዘንድ አዛችኋለሁ።

፵፩ ነገር ግን አገልጋዬ ፍረድሪክ ጂ ዊሊያምስ እውነት እልሀለሁ፣ በዚህ ኩነኔ ቀጥለሀል፤

፵፪ በትእዛዛትም በኩል ልጆችህን ብርሀን እና እውነት አላስተማርክም፤ እና ክፉውም በአንተ ላይ ሀይል አለው፣ እና ይህም የስቃይህ ምክንያት ነው።

፵፫ አሁንም ትእዛዝ እሰጥሀለሁ—የምትድን ቢሆን ቤትህን በስርዓት አደራጅ፣ በቤትህ ውስጥ አያሌ ትክክል ያልሆኑ ነገሮች አሉና።

፵፬ ለአገልጋዬ ስድኒ ሪግደን በእውነት እለዋለሁ፣ በአንዳንድ ነገሮች ልጆቹን በሚመለከት ትእዛዝን አላከበረም፤ ስለዚህ፣ አስቀድሞ ቤቱን በስርዓት ያደራጅ።

፵፭ በእውነት፣ ለአገልጋዬ ጆሴፍ ስሚዝ ዳግማዊ ይህን እላለሁ፣ ወይም በሌላ ቃላት፣ ባልንጀሮቼ ብዬ እጠራችኋለሁ፣ እናንት ባልንጀሮቼ ናችሁና፣ እና ከእኔም ጋር ውርስ ይኖራችኋል—

፵፮ አግልጋዮቼ ብዬ የምጠራችሁ በአለም ምክንያት ነው፣ እና እናንተም ለእነርሱ በእኔ ምክንያት አገልጋዮቻቸው ናችሁ—

፵፯ አሁንም፣ በእውነት ለአገልጋዬ ጆሴፍ ስሚዝ ዳግማዊ እላለሁ—ትእዛዛትን አላከበርክም፣ እና በጌታ ፊትም ተገስጸህ መቆም ያስፈልግሀል፤

፵፰ ቤተሰብህ ንስሀ መግባትና አንዳንድ ነገሮችን መተው አለባቸው፣ እና የምትላቸውንም በቅንነት ማድመጥ ያስፈልጋቸዋል፣ ወይም ከስፍራቸው ይወጣሉ።

፵፱ ለአንዱ የምለው ለሁሉም እላለሁ፤ ዘወትር ጸልዩ አለበለዚያም ክፉው በውስጣችሁ ሀይል ይኖረዋል፣ እና ከስፍራችሁ ያስወጣችኋል።

፶ የቤተክርስቲያኔ ኤጲስ ቆጶስ፣ አገልጋዬ ኒውል ኬ ዊትኒም፣ ሊገሰፅ፣ እና ቤተሰቡን በስርዓት ሊያደራጅ፣ እና በቤትም በተጨማሪ ቅን እና አሳቢ እንዲሆኑ፣ እና ዘወትርም እንዲጸልዩ ሊያደርግ ያስፈልገዋል፣ ወይም ከስፍራቸው ይወጣሉ።

፶፩ ባልንጀሮቼ፣ አሁን እላችኋለሁ፣ አገልጋዬ ስድኒ ሪግደን በጉዞው ይሂድ፣ እና ይፍጠን፣ እና ደግሞም በምሰጠው የንግግር ችሎታ የጌታን የተወደደች አመትን፣ እና የደህንነትን ወንጌልን ያውጅ፤ እና በአንድ አላማ በምታደርጉት የእምነት ጸሎት እደግፈዋለሁ።

፶፪ እና አገልጋዬ ጆሴፍ ስሚዝ ዳግማዊ፣ እና ፍረድሪክ ጂ ዊሊያምስም ይፍጠኑ፣ እና እንድ እምነት ጸሎታቸውም ይሰጣቸዋል፤ እና እኔ የምላችሁን እስከጠበቃችሁ ድረስ በዚህ አለምም፣ ሆነ በሚመጣው አለም አትሸነፉም።

፶፫ እና፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ቅዱስ መጻሕፍቴን ለመተርጎም እንድትፈጥኑ፣ እና የታሪክ፣ እና የሀገሮች፣ እና የመንግስታት፣ የእግዚአብሔር እና የሰው ህግጋት እውቀትን እንድታገኙ ፍቃዴ ነው፣ ይህም ሁሉ ለፅዮን ደህንነት ነው። አሜን።