ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፶፪


ክፍል ፶፪

በሰኔ ፮፣ ፲፰፻፴፩ (እ.አ.አ.)፣ በከርትላንድ ኦሀዮ ውስጥ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በኩል ለቤተክርስቲያኗ ሽማግሌዎች የተሰጠ ራዕይ። በሰኔ ፫ ተጀምሮ በሰኔ ፮ የተዘጋ ጉባኤ ከርትላንድ ውስጥ ተካሂዶ ነበር። በዚህ ጉባኤ ውስጥም የመጀመሪያው ልዩ የሊቀ ካህን ሀላፊነት ሹመቶች ተደርገው ነበር፣ እናም የሀሰት እና የሚያታልሉ መናፍስትም ተገልጠው እና ተገስጸውም ነበር።

፩–፪፣ የሚቀጥለው ጉባኤ በሚዙሪ ውስጥ እንዲሆን ተወስኗል፤ ፫–፰፣ አንዳንድ ሽማግሌዎች አብረው እንዲጓዙም ተመድበዋል፤ ፱–፲፩፣ ሽማግሌዎችም ሐዋርያት እና ነቢያት የጻፉትን ያስተምሩ፤ ፲፪–፳፩፣ በመንፈስ የሚታነጹት የምስጋና እና የጥበብ ፍሬ ያመጣሉ፤ ፳፪–፵፬፣ ወደ ሚዙሪ ለጉባኤው እየተጓዙ እያሉ፣ ወንጌልን እየሰበኩ እንዲሄዱ የተለያዩ ሽማግሌዎች ተመድበዋል።

፩ እነሆ፣ ጌታ በእነዚህ በመጨረሻው ቀናት ለጠራቸው እና ለመረጣቸው ሽማግሌዎች በመንፈሱም ድምፅ፣ እንዲህ ይላል—

፪ እንዲህም አለ፤ እኔ ጌታ በቃል ኪዳን ወራሾች ለሆኑት፣ እና ለያዕቆብ ቅሪት ለሆኑት ህዝቤ፣ በቀደስኩላቸው ምድር ላይ፣ በሚዙሪ ውስጥ የሚቀጥለው ጉባኤ እስከሚጠራ ድረስ ምን እንደምታደርጉ አስታውቃችኋለሁ።

፫ ስለዚህ፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ቤታቸውን ትተው ለመሄድ ለመዘጋጀት በሚችሉበት፣ አገልጋዮቼ ጆሴፍ ስሚዝ ዳግማዊ፣ እና ስድኒ ሪግደን ወዲያው ይጓዙ፣ እና ወደ ሚዙሪ ምድርም ይጓዙ።

፬ እናም ለእኔ ታማኝ እስከሆኑም ድረስ፣ ምን እንደሚያደርጉ እንዲያውቁም ይደረግላቸዋል፤

፭ እናም ደግሞ፣ ታማኝ እስከሆኑም ድረስ፣ የውርሳችሁን ምድር እንዲያውቁት ይደረጋል።

፮ እና ታማኝ እስካልሆኑም ድረስ፣ በእኔ ፈቃድ፣ እና መልካም እንደሚመስለኝምይገለላሉ።

፯ እና ደግሞም፣ እውነት እላችኋለሁ፣ አገልጋዬ ላይመን ዋይት እና አገልጋዬ ጆን ኮርል ፈጥነው ይጓዙ፤

፰ እና አገልጋዬ ጆን መርዶክ፣ እና አገልጋዬ ሀይረም ስሚዝ በድትሮይት በኩል ወደዚያ ይጓዙ።

፱ ከዚያም ስፍራ፣ ነቢያት እና ሐዋርያት ከጻፉት፣ እና በእምነት ጸሎት አማካይነት አፅናኙ ካስተማራቸው ሌላ ምንም ሳይሉ፣ ቃሉን በሚያልፉበት ስፍራዎች እየሰበኩ ይጓዙ።

፲ ሁለት በሁለት ሆነውም ይጓዙ፣ እና በዚህም በሚያልፉበትም ስፍራዎች፣ በውሀ በማጥመቅ እና በውሀውም አጠገብ እጃቸውን በመጫን፣ በእያንዳንዱ ስብሰባዎች ውስጥ ይስበኩ።

፲፩ ጌታም እንዲህ ይላል፣ በፅድቅም ስራዬን በአጭር እቆርጣለሁ፣ ድል ለመንሣት ፍርድን የማመጣበት ቀን ይመጣልና።

፲፪ አገልጋዬ ላይመን ዋይትም ይጠንቀቅ፣ ሰይጣን እንደ ገለባ ሊያበጥረው ይፈልጋልና።

፲፫ እናም እነሆ፣ ታማኝ የሆነው እርሱ በብዙ ነገሮች ላይ ገዢ ይሆናልና።

፲፬ እና ደግሞም፣ እንዳትታለሉም ለሁሉም ነገሮች ንድፍን እሰጣችኋለሁ፤ ሰይጣን በምድር ላይ አለና፣ እና አገሮችን እያሳታቸውም ይሄዳል—

፲፭ ስለዚህ የሚጸልየው፣ መንፈሱ የተዋረደውም፣ ስርዓቴን ካከበረ፣ እርሱም በእኔ ዘንድ ተቀባይነትን ያገኛል።

፲፮ መንፈሱ ትሁት፣ ቋንቋውም ቅንና የሚያንፅ የሆነው፣ የሚናገረውም፣ ስርዓቶቼን ቢያከብር፣ እርሱ ከእግዚአብሔር ነው።

፲፯ እና ደግሞም፣ በሀይሌ የሚንቀጠቀጠውም እርሱ ጠንካራ እንዲሆን ይደረጋል፣ እና በምሰጣችሁ ራዕዮች እና እውነቶች በኩልም የምስጋና እና የጥበብ ፍሬዎችን ያመጣል።

፲፰ እና ደግሞም የተሸነፈውም እና በዚህም ንድፍ አማካይነት፣ ፍሬ የማያመጣውም ከእኔ አይደለም።

፲፱ ስለዚህ፣ ከሰማይ በታች ሁሉ በዚህ ንድፍ አማካይነት መናፍስትን በሁሉም ጉዳዮች ታውቃላችሁ።

፳ ቀኖቹም ቀርበዋል፤ ሰዎችም እንደ እምነታቸው ይከናወንላቸዋል።

፳፩ እነሆ፣ ይህ ትእዛዝ ለመረጥኳቸው ሽማግሌዎች ሁሉ የተሰጠው ነው።

፳፪ እና ደግሞም፣ እውነት እላችኋለሁ፣ አገልጋዬ ቶማስ ቢ ማርሽ እና አገልጋዬ እዝራ ቴይርም ቃሉን በየመንገዳቸው እየሰበኩ ወደ እዚያ ምድር ደግመውም ይጓዙ።

፳፫ እና ደግሞም፣ አገልጋዬ አይዛክ ሞርሊ እና አገልጋዬ እዝራ ቡዝ፣ ቃሉን በዚያም ምድር እግረ መንገዳቸውን እየሰበኩ፣ ደግመው ይጓዙ።

፳፬ እና ደግሞም፣ አገልጋዮቼ ኤድዋርድ ፓርትሪጅ እና ማርቲን ሀሪስ ከአገልጋዮቼ ስድኒ ሪግደን እና ጆሴፍ ስሚዝ፣ ዳግማዊ ጋር ይጓዙ።

፳፭ አገልጋዮቼ ዴቪድ ዊትመር እና ሀርቪ ውትሎክም፣ ደግመውም እግረ መንገዳቸውን እየሰበኩ ወደ እዚያው ምድር ይጓዙ።

፳፮ እናም አገልጋዮቼ ፓርሊ ፒ ፕራት እና ኦርሰን ፕራትም፣ እግረ መንገዳቸውን፣ እንዲሁም ወደ እዚያው ምድር እየሰበኩ ይጓዙ።

፳፯ እናም አገልጋዮቼ ሰለሞን ሀንኮክ እና ሰሚየን ካርተርም ወደ እዚያ ምድርም ደግመውም ይጓዙ፣ እናም እግረ መንገዳቸውን ይስበኩ።

፳፰ አገልጋዮቼ ኤድሰን ፉለር እና ጄከብ ስኮትም እንዲሁ ይጓዙ።

፳፱ አገልጋዮቼ ሊቫይ ደብሊው ሀንኮክ እና ዘበዲ ኮልትርንም እንዲሁ ይጓዙ።

፴ አገልጋዮቼ ሬኖልድዝ ካሁን እና ሳሙኤል ኤች ስሚዝም እንዲሁ ይጓዙ።

፴፩ አገልጋዮቼ ዊለር ቦልድውን እና ውልያም ካርተርም እንዲሁ ይጓዙ።

፴፪ እናም አገልጋዮቼ ኑወል ናይት እና ሴላ ጄ ግርፍንም ይሾሙ፣ እናም እንዲሁ ይጓዙ።

፴፫ አዎን፣ እውነት እላለሁ፣ እነዚህ ሁሉ ወደ አንድ ስፍራ በተለያዩ መንገዶቻቸው ይጓዙ እናም አንድ በሌላው ሰው መሰረት ላይ አያንጽም፣ ወይም በሌላ ሰውም መንገድ አይጓዝም።

፴፬ ታማኝ የሆነው፣ እርሱ ይጠበቃል እና ብዙ ፍሬ በማፍራትም ይባረካል።

፴፭ እና ደግሞም፣ እንዲህ እላችኋለሁ፣ አገልጋዮቼ ጆሴፍ ዌክፊልድና ሰለሞን ሀምፍሪ ወደ ምስራቅ አገሮች ይጓዙ፤

፴፮ ትንቢቶቹ እንዲሟሉ፣ ካዩት እና ከሰሙት እናም በእርግጥ ከሚያምኑት፣ ከነቢያትና ከሐዋርያት በቀር ምንም ነገሮችን ሳያውጁ፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋርም ያገልግሉ።

፴፯ በኃጢአት ምክንያትም፣ ለሂምን በሰት የተሰጠውም ይወሰድበት፣ እናም ለሳይመንድስ ራይደር ይሰጥ።

፴፰ እና ደግሞም፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ጀርድ ካርተር እንደ ካህን ይሾም፣ ጆርጅ ጄምስም እንዲሁ እንደ ካህን ይሾም።

፴፱ የሚቀሩት ሽማግሌዎችም ቤተክርስቲያኖችን ይጠብቁ፣ እና በአካባቢያቸውም ቃሉን ያውጁ፤ እናም የጣኦት አምላኮም እንዳይኖር እና ጥፋት እንዳይሰራም በገዛ እጆቻቸው ይስሩ።

፵ እናም በሁሉም ነገሮችም ድሀውን እና ችግረኛውን፣ የታመመውን እና የተሰቃየውን አስታውሱ፣ ይህን የማያደርግም፣ እርሱ ደቀ መዝሙሬ አይደለምና።

፵፩ እና ደግሞም፣ አገልጋዮቼ ጆሴፍ ስሚዝ፣ ዳግማዊ፣ እና ስድኒ ሪግደን እና ኤድዋርድ ፓርትሪጅ ከቤተክርስቲያኗ ማስተዋወቂያ ይውሰዱ። እና አንድ ደግሞ ለአገልጋዬ ኦሊቨር ካውድሪ ይሰጠው።

፵፪ እና በዚህም፣ እንዲሁም እንዳልኩት፣ ታማኝ ከሆናችሁ፣ የውርሳችሁ ምድር በሆነው፣ እና አሁንም የጠላቶቻችሁ ምድር በሆነው፣ በሚዙሪ ምድር ለመደሰት ራሳችሁን ትሰበሰባላችሁ።

፵፫ ነገር ግን፣ እነሆ፣ እኔ ጌታ ከተማውን በጊዜው አፈጥነዋለሁ፣ እና ታማኝ የሆነውንም በደስታ እና በሀሴት አነግሰዋለሁ።

፵፬ እነሆ፣ እኔ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ፣ እናም በኋለኛው ቀን አነሳቸዋለሁ። እንዲሁም ይሁን። አሜን።