ክፍል ፵፩
የካቲት ፬፣ ፲፰፻፴፩ (እ.አ.አ.)፣ በከርትላንድ፣ ኦሀዮ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ አማካይነት ለቤተክርስቲያኗ የተሰጠ ራዕይ። ይህ ራዕይ ነቢዩን እና የቤተክርስቲያኗን ሽማግሌዎች የእግዚአብሔርን “ህግጋት” ለመቀበል እንዲጸልዩ ያስተምራል (ክፍል ፵፪ን ተመልከቱ)። ጆሴፍ ስሚዝ ከከርትላንድ ወደ ኒው ዮርክ ገና መድረሱ ነበር፣ እናም በቶምሰን ኦሀዮ የሚኖረው የቤተክርስቲያኗ አባል ሊመን ኮፕሊ “ወንድሞች ጆሴፍ እና ስድኒ (ሪግደን)…ከእርሱ ጋር እንዲኖሩ እና እርሱም ቤቶች እና ድጋፎች እንደሚሰጣቸው ጠየቀ።” የሚቀጥለው ራዕይ ጆሴፍ እና ስድኒ የት መኖር እንደሚገባቸው ይገልጻል እና ደግሞም ኤድዋርድ ፓርትሪጅን እንደ ቤተክርስቲያኗ የመጀመሪያ ኤጲስ ቆጶስ ጥሪን ይሰጣል።
፩–፫፣ ሽማግሌዎቹ ቤተክርስቲያኗን በራዕይ መንፈስ ያስተዳድራሉ፤ ፬–፮፣ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት የጌታን ህግ ይቀበላሉ እናም ይጠብቃሉ፤ ፯–፲፪፣ ኤድዋርድ ፓርትሪጅ ለቤተክርስቲያኗ ኤጲስ ቆጶስነት ተሹሟል።
፩ የምትሰሙኝ፣ ከበረከቶች ሁሉ ታላቅ በሆነው በረከት ልባርካችሁ ደስተኛ የሆንኩት እናንት ህዝቤ ሆይ፣ አድምጡ እናም ስሙ ይላል ጌታ እና አምላካችሁ፤ እናም የማያደምጡኝን እና በከንቱ ስሜን የጠሩትን ከእርግማኖች ሁሉ ከባድ በሆነው እርግማን እረግማቸዋለሁ።
፪ እኔ የጠራኋችሁ የቤተክርስቲያኔ ሽማግሌዎች ሆይ አድምጡ፣ እነሆ በቃላቴ ላይ እንድትስማሙና ራሳችሁን እድታሰባስቡ ትእዛዝን እሰጣችኋለሁ።
፫ እናም ቤተክርስቲያኔን እንዴት ማስተዳደር እንዳለባችሁ እንድታውቁ እና ነገሮችን ሁሉ በፊቴ መልካም ታደርጉ ዘንድ በእምነታችሁ ጸሎት ህጌን ትቀበላላችሁ።
፬ እናም እኔ በምመጣበት ጊዜ የእናንተ ገዢ እሆናለሁ፤ እናም እነሆ፣ በቶሎም እመጣለሁ፣ ህጌም እንዲጠበቅ አድርጉ።
፭ ህጌን ተቀብሎ የሚያደርገው፣ እርሱ ደቀ መዛሙሬ ነው፤ እናም ተቀብየዋለሁ የሚል እና የማያደርገው፣ እርሱ ደቀ መዛሙሬ አይደለም፣ እናም ከመካከላችሁ ወጥቶ ይጣላል፤
፮ የመንግስተ ስማይ ልጆች የሆኑ ነገሮችን ወስዶ፣ ብቁ ላልሆኑ ወይም ለውሾች ሊሰጥ አይገባም፣ ወይም ዕንቁዎችም በእሪያዎች ፊት እንዳይጣሉ ዘንድ አይገባምና።
፯ እናም ዳግም፣ ለአገልጋዬ ለጆሴፍ ስሚዝ፣ ዳግማዊ፣ የሚኖርበትና የሚተረጉምበት ቤት ሊገነባለት ይገባል።
፰ እናም ዳግም፣ ትእዛዛቴን እስከጠበቀ ድረስ አገልጋዬ ሲድኒ ሪግደን መልካም እንደመሰለው ይኖር ዘንድ ይገባል።
፱ ደግሞም፣ አገልጋዬን ኤድዋርድ ፓርትሪጅን ጠርቼዋለሁ፤ በቤተክርስቲያኗ ድምጽ እንዲመረጥ እና ለቤተክርስቲያኗ ኤጲስ ቆጶስነት እንዲሾም እናም ንግዱን ትቶ ሙሉ ጊዜውን ለቤተክርስቲያኗ አገልግሎት እንዲያውል ትእዛዝን እሰጣለሁ፤
፲ ህግጋቴን በምሰጥ ጊዜ የሚሰጡትን ነገሮች ሁሉ በዚያው መሰረት እንዲያከናውንም ትእዛዝን እሰጣለሁ።
፲፩ እናም ይህም የሆነበት ምክንያት ልቡ በፊቴ ንጹህ ስለሆነ ነው፣ እሱ ለእኔ ተንኮል እንደሌለው እንደ ጥንቱ ናትናኤል ነውና።
፲፪ እነዚህ ቃላት ለእናንተ ተሰጥተዋችኋል፣ እናም በፊቴም ንጹህ ናቸው፤ ስለዚህም፣ በፍርድ ቀን በነፍስህ ስለሚመለሱ፣ እንዴት እንደምትይዛቸውም ተጠንቀቅም። እንዲህም ይሁን። አሜን።