ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፻፴፯


ክፍል ፻፴፯

በጥር ፳፩፣ ፲፰፻፴፮ (እ.አ.አ.) በከርትላንድ በቤተመቅደስ ውስጥ ለነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ የተሰጠ ራዕይ። ጊዜውም በዚያ ጊዜ ቤተመቅደስን ለመምረቅ በመዘጋጀት ስርዓቶችን በሚያስተዳድርበት ጊዜ ነበር።

፩–፮፣ ነቢዩ ወንድሙን አልቭንን በሰለስቲያል መንግስት ውስጥ አየ፤ ፯–፱፣ የሙታን ደህንነት ትምህርት ተገለጠ፤ ፲፣ ሁሉም ልጆች በሰለስቲያል መንግስት ውስጥ ይድናሉ።

፩ ሰማያት ተከፈቱልን፣ እና የእግዚአብሔርን ሰለስቲያል መንግስትን እና የእዚያን ክብር አየሁ፣ በሰውነት ይሁን ከዚያ ውጪ አላወቅሁም።

፪ በእሳት ነበልባል የተከበበው፣ የዚያ መንግስት ወራሾች የሚገቡበት በር በጣም ታላቅ ውበት እንዳለውም አየሁ።

፫ ደግሞም አብና ወልድ የሚቀመጡበትን በጣም ብሩህ የሆነውን የእግዚአብሔር የክብር ዙፋንንም ተመለከትኩ።

፬ በወርቅ ምንጣፍ አምሳል የሆኑትን የመንግስቱን ውብ መንገዶችንም አየሁ።

፭ አባት አዳምን እና አብርሐምንም፤ እና አባቴና እናቴንም፤ ለብዙ ጊዜ ሞቶ የነበረው ወንድሜ አልቭንንም አየሁ።

፮ እና ጌታ እስራኤልን ዳግም ለመሰብሰብ እጁን ከመዘርጋቱ በፊት ከዚህ ህይወት ሄዶ ስለነበረ፣ እና ለኃጢአት ስርየት ስላልተጠመቀ፣ በዚያ መንግስት ውስጥ እንዴት ውርስ እንዳገኘም ተደነቅሁኝ።

፯ እንዲህም ሲል የጌታ ድምፅ ወደ እኔ መጣ፥ ለመቆየት ቢፈቀድላቸው ይቀበሉት የነበሩት፣ ይህን ወንጌል ባለማወቅ የሞቱት ሁሉ የእግዚአብሔር ሰለስቲያል መንግስት ወራሾች ይሆናሉ።

፰ ደግሞም በሙሉ ልባቸው ይህን ይቀበሉ የነበሩ፣ ካለዚህ እውቀት ከዚህ በኋላ የሞቱት ሁሉ የዚያ መንግስቱ ወራሾች ይሆናሉ፤

፱ እኔ ጌታ ሁሉንም ሰዎች በስራዎቻቸው መሰረት፣ እንደልባቸውም ምኞት እፈርድባቸዋለሁና።

፲ እና በተጠያቂነት እድሜም ከመድረሳቸው በፊት የሞቱትን ልጆች ሁሉ በሰማይ ሰለስቲያል መንግስት ውስጥ እንደዳኑም ተመለከትኩኝ።