ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፴፮


ክፍል ፴፮

ታህሳሥ ፱፣ ፲፰፻፴ (እ.አ.አ.) በፈየት፣ ኒው ዮርክ አቅራቢያ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ አማካይነት ለኤድዋርድ ፓርትሪጅ የተሰጠ ራዕይ (የክፍል ፴፭ ርዕስን ተመልከቱ)። የጆሴፍ ስሚዝ ታሪክ ስለኤድዋርድ ፓርትሪጅ እንደገለጸው “የቅድስና ምሳሌ፣ እና ከጌታ ታላላቅ ሰዎች አንዱ ነው።”

፩–፫፣ በስድኒ ሪግደን አማካይነት ጌታ እጁን በኤድዋርድ ፓርትሪጅ ላይ ጭኗል፤ ፬–፰፣ ወንጌልንና ክህነትን የሚቀበል ወንድ ሁሉ እንዲሄድ እና እንዲሰብክ ይጠራል።

፩ የእስራኤል ኃያል የሆነው፣ ጌታ አምላክ እንዲህ ይላል፥ እነሆ፣ አገልጋዬ ኤድዋርድ እንዲህ እልሀለሁ፣ አንተ የተባረክህ ነህ፣ እናም ኃጢአትህም ተሰርዮልሀል፣ እንዲሁም እንደመለከት ድምጽ ወንጌሌን እንድትሰብክ ተጠርተሀል፤

፪ እናም በአገልጋዬ በስድኒ ሪግደን እጄን በአንተ ላይ እጭናለሁ፣ እናም የመንግስትን የሰላም ነገሮች የሚያስተምርህን አጽናኝ የሆነውን መንፈሴን፣ መንፈስ ቅዱስን ትቀበላለህ።

፫ እናም ሆሳዕና፣ ልዑል እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን በማለት፣ ከፍ ባለ ድምጽም ታውጀዋለህ።

፬ እናም አሁን ሰዎችን ሁሉ በተመለከተ፣ ይህን ጥሪና ትእዛዝ እሰጥሀለሁ—

፭ በአገልጋዮቼ በስድኒ ሪግደን እና በጆሴፍ ስሚዝ፣ ዳግማዊ ፊት ይህንን ጥሪና ትእዛዝ ተቀብለው የሚመጡት ሁሉ፣ ይሾማሉ እናም በአህዛብ መካከል ዘለአለማዊ ወንጌሌን እንዲሰብኩ ይላካሉ—

፮ ንስሀንም በመጮህ፣ እንዲህ ይበሉ፥ ከዚህ ጠማማ ትውልድ ራሳችሁን አድኑ፣ እናም ከእሳት ውስጥም ተነጥቃችሁ ውጡ፣ በረከሰ ስጋ የተበከለውንም ልብስ ተጸየፉ።

፯ እኔ እንደተናገርኩት በአንድ ልብ ይህን የሚቀበል ሁሉ እንዲሾምና እንዲላክ ይህ ትእዛዝ ለቤተክርስቲያኔ ሽማግሌዎች ይሰጣል።

፰ እኔ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነኝ፤ ስለዚህ ወገባችሁን እሰሩ እናም በድንገትም ወደ ቤተመቅደሴ እመጣለሁ። እንዲህም ይሁን። አሜን።