ክፍል ፴፫
ጥቅምት ፲፰፻፴ (እ.አ.አ.)፣ በፈየት፣ ኒው ዮርክ በነቢዩ በጆሴፍ ስሚዝ አማካይነት ለእዝራ ታይር እና ኖርዝሮፕ ስዊት የተሰጠ ራዕይ። ይህንን ራዕይ በማስተዋወቅ፣ የጆሴፍ ስሚዝ ታሪክ እንደሚያረጋግጠው፣ “በእምነት ተግተው ለሚሹት ጌታ ሊያስተምራቸው ዘወትር ዝግጁ ነው።”
፩–፬፣ ሰራተኞች በአስራ አንደኛው ሰዓት ወንጌልን እንዲያውጁ ተጠርተዋል፤ ፭–፮፣ ቤተክርስቲያኗ ተመስርታለች፤ እና የተመረጡትም ይሰበሰባሉ፤ ፯–፲፣ ንሰሀ ግቡ፣ መንግስተ ሰማያት ቀርባለችና፤ ፲፩–፲፭፣ ቤተክርስቲያኗ በወንጌል አለት ላይ ተመስርታለች፤ ፲፮–፲፰፣ ለሙሽራው ምጽአት ተዘጋጁ።
፩ እነሆ፣ እንዲህ እልሀችኋለሁ፣ አገልጋዮቼ እዝራ እና ኖርዝሮፕ፣ ጆሮቻችሁን ክፈቱ እናም ፈጣን እና ሀያል፣ ቃሉ ሁለት አንደበት ካለው ሰይፍ ይልቅ የተሳለ፣ ነፍስንና መንፈስን፣ መገጣጠሚያን እና መቅኔን እስኪለይ ድረስ የሚሰራውን የጌታን ድምፅ አድምጡ፣ እናም የልብን ሐሳቦችና ምኞቶች የሚያውቅ ነው።
፪ እውነት፣ እውነት፣ እላችኋለሁ፣ ድምጻችሁን እንደ መለከት ድምጽ ከፍ እንድታደርጉ እና ወንጌሌን በጠማማና በክፉ ትውልድ መካከል እንድታውጁ ተጠርታችኋልና።
፫ እነሆም፣ የእርሻው ስፍራ ነጭ ሆኖ አዝመራው ዝግጁ ነው፤ እናም አስራ አደኛው ሰዓት፣ እና ለመጨረሻ ጊዜ ወደ እኔ የወይን ስፍራ አገልጋዮቼን የምጠራበት ጊዜ ነው።
፬ እናም አንዳች ፍሬ እንኳን ሳይቀር የወይን ስፍራዬም ተበላሽቷል፤ እናም ከጥቂቶቹ በስተቀር መልካምን የሚያደርጉ የሉም፤ እናም ሁሉም ብልሹ አእምሮ በካህን ተንኮል ምክንያት በብዙ መንገዶች ጥፋት ላይ ወድቀዋል።
፭ እናም እውነት፣ እውነት፣ እላችኋለሁ፣ ይህችን ቤተክርስቲያን መስርቻታለሁ እናም ከምድረበዳ እንድትወጣ ጠርቻታለሁ።
፮ እናም ምርጦቼን፣ እንዲሁም በእኔ የሚያምኑትን፣ እና ድምጼን የሚያዳምጡትን ሁሉ፣ ከአራቱም የምድር ማዕዘናት ቢሆንም እሰበስባለሁ።
፯ አዎን፣ እውነት፣ እውነት፣ እላችኋለሁ፣ የእርሻው ስፍራ ነጭ ሆኖ አዝመራው ዝግጁ ነው፤ ስለዚህ፣ በማጭዶቻችሁ እጨዱ፣ እናም በሙሉ ኃይላችሁ፣ አዕምሮአችሁ፣ እናም ጉልበታችሁ ሰብስቡ።
፰ አንደበታችሁን ክፈቱ እንዲሁም ይሞላሉ፣ ከኢየሩሳሌም በምድረበዳ እንደተጓዘው፣ እንደጥንቱ ኔፊም ትሆናላችሁ።
፱ አዎን፣ አንደበታችሁን ከፍታችሁ ከመናገር አትቆጠቡ፣ እናም ነዶንም በጀርባችሁ የተጫናችሁ ትሆናላችሁ፣ እኔም ከናንተ ጋር ነኝና።
፲ አዎን፣ አንደበታችሁን ክፈቱ እናም ይሞላሉ፣ እንዲህ በማለትም ተናገሩ፥ ንሰሀ ግቡ፣ ንሰሀ ግቡ፣ እናም የጌታን መንገድ አዘጋጁ፣ ጎዳናውንም አስተካክሉ፤ መንገሥተ ሰማይ ተቃርባለችና፤
፲፩ አዎን፣ ለኃጢአታችሁም ስርየት፣ እያንዳንዳችሁም ንሰሀ ግቡ እና ተጠመቁ፤ አዎን፣ በውሀም ተጠመቁ፣ እናም በመቀጠልም የእሳት እና የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ይመጣል።
፲፪ እነሆ፣ እውነት፣ እውነት፣ እላችኋለሁ፣ ይህ ወንጌሌ ነው፤ እናም በእኔ እምነት ከሌላቸው በስተቀር በምንም መንገድ ሊድኑ አይችሉም፤
፲፫ እናም በዚህ አለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እገነባለሁ፣ አዎን፣ በዚህም አለት ላይ ተገንብታችኋል፣ እናም የምትቀጥሉም ከሆነ፣ የሲዖል ደጆችም አያሸንፏችሁም።
፲፬ እናም የቤተክርስቲያኗን መመሪያዎች እና የተስፋ ቃላትን መጠበቅ ታስታውሳላቸሁ።
፲፭ እናም እምነት ያላቸውን ሁሉ በቤተክርስቲያኔ ውስጥ እጆቻችሁን በመጫን ታጸኗቸዋላችሁ፣ እናም እኔም የመንፈስ ቅዱስን ስጦታን እሰጣቸዋለሁ።
፲፮ እናም መፅሐፈ ሞርሞን እናም ቅዱሳን መጻህፍት ለእናንተ መማሪያነት ከእኔ ለእናንተ ተሰጥተዋል፤ እናም የመንፈሴም ኃይል ነገሮችን ሁሉ ህይወት ይሰጣል።
፲፯ ሰለዚህ፤ ሙሽራው በሚመጣበት ጊዜ ዝግጁ መሆን እንድትችሉ፣ መብራታችሁን አስተካክላችሁ በመለኮስ እና ዘይታችሁን በመያዝ፣ ታማኝ ሁኑ፣ ዘውትርም ጸልዩ—
፲፰ እነሆም፣ እውነት፣ እውነት፣ እላችኋለሁ፣ በቶሎም እመጣለሁ። እንዲህም ይሁን። አሜን።