ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፻፳፱


ክፍል ፻፳፱

በየካቲት ፱፣ ፲፰፻፵፫ (እ.አ.አ.) የአገልጋይ መላዕክት እና የመናፍስትን ትክክለኛ ተፈጥሮን ለመለየት የሚቻልበትን ሶስት ታላላቅ ቁልፎች ለማሳወቅ ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ የሰጣቸው መመሪያዎች።

፩–፫፣ ከሞት የተነሱ እና የመንፈስ አካላት በሰማያት ውስጥ አሉ፤ ፬–፱፣ ከመጋረጃው አልፈው የሚመጡ መልእክተኞችን ለይቶ የማወቂያ ቁልፎች ተሰጥተዋል።

፩ ሁለት አይነት የሰማይ ፍጥረታት አሉ፣ እነርሱም፥ ከሞት የተነሱ ሰዎች፣ የስጋ እና የአጥንት አካል ያሏቸው መላዕክት—

፪ ለምሳሌ፣ ኢየሱስ፥ በእኔ እንደምታዩት፥ መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና እኔን ዳስሳችሁ እዩ አላቸው።

፫ ሁለተኛ፥ ከሞት ያልተነሱ፣ ነገር ግን ያንን አይነት ክብር የሚወረሱ፣ ፍጹም የሆኑ የጻድቅ ሰዎች መናፍስት።

፬ ከእግዚአብሔር መልእክት አለኝ ብሎ መልእክተኛ ሲመጣ፣ እጆቻችሁን ስጡት እና ከእናንተም እጆች ጋር እንዲጨባበጥ ጠይቁት።

፭ መልአክ ከሆነ ይህን ያደርጋል፣ እና እጁንም በመዳደስ ይሰማችኋል።

፮ ፍጹም የሆነ የጻድቅ ሰው መንፈስ ከሆነ በክብሩ ይመጣል፤ ሊመጣም የሚችልበት መንገድ ይህ ብቻ ነውና—

፯ ከእጆቻችሁም ጋር እንዲጨባበጥ ጠይቁት፣ ነገር ግን አይንቀሳቀስም፣ ምክንያቱም ይህ ፍጹም የሆነው ሰው ይታለል ዘንድ ከሰማይ ስርዓት ጋር የሚቃረን ነውና፤ ነገር ግን መልዕክቱን ያበስራል።

፰ ዲያብሎስ በብርሀን መልአክ አምሳል ቢሆን፣ እጆቻችሁንም እንዲጨብጥ ብትጠይቁት እጁንም ይሰጣችኋል፣ እና ምንም ነገር አይሰማችሁም፤ በዚህም ልታውቁት ትችላላችሁ።

፱ እነዚህም ከእግዚአብሔር የመጡ አገልግሎቶች እንደሆኑ ለማወቅ የምትችሉባቸው ሶስት ታላቅ ቁልፎች ናቸው።