ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፲፩


ክፍል ፲፩

ግንቦት ፲፰፻፳፱ (እ.አ.አ.) በሀርመኒ፣ ፔንስልቬንያ፣ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ አማካይነት ለወንድሙ ለሀይረም ስሚዝ የተሰጠ ራዕይ። ይህም ራዕይ የተሰጠው በኡሪም እና ቱሚም አማካይነት ለጆሴፍ ልመናና ጥያቄ መልስ ለመስጠት ነበር። ይህ ራዕይ የአሮናዊ ክህነት ዳግመኛ ከተመለሰ በኋላ መሰጠቱን የጆሴፍ ስሚዝ ታሪክ ያሳስባል።

፩–፮፣ በወይኑ ስፍራ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ደህንነትን ያገኛሉ፤ ፯–፲፬፣ ጥበብን እሹ፣ ንስሐን አውጁ፣ በመንፈስ ታመኑ፤ ፲፭–፳፪፣ ትዕዛዛቱን ጠብቁ፣ እናም የጌታን ቃል አጥኑ፤ ፳፫–፳፯፣ የራዕይን እናም የትንቢትን መንፈስን አትካዱ፤ ፳፰–፴፣ ክርስቶስን የሚቀበሉ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆናሉ።

በሰዎች ልጆች መካከል ታላቅ እና ድንቅ ስራ ሊመጣ ነው።

እነሆ፣ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ፈጣን እና ሀያል፣ ሁለት አንደበት ካለው ሰይፍ ይልቅ የተሳለ፣ መገጣጠሚያን እና መቅኔን የሚለየውን ቃሌን አድምጥ፤ ስለዚህ ቃሌን እድምጥ።

እነሆ፣ የእርሻው ስፍራ ነጭ ሆኖ አዝመራው ዝግጁ ነው፤ ስለዚህ፣ መሰብሰብ የሚሻ ሁሉ ኃይሉ ይጨድ፣ እናም ለነፍሱም ዘለአለማዊ ደህንነት በእግዚአብሔር መንግስት ያከማች ዘንድ ቀን ሳለ ይሰብስብ።

አዎን፣ ማንኛውም የሚያጭድ እናም የሚሰበስብ ሁሉ እንዲሁ በእግዚአብሔር የተጠራ ነው።

ስለዚህ፣ እኔን ከጠየቅህ ትቀበላለህ፤ ካንኳኳህ ይከፈትልሀል።

አሁን፣ እንደጠየቅኸው፣ እነሆ፣ እንዲህ እልሀለሁ፣ ትእዛዛቴን ጠብቅ እናም የፅዮንን አስተሳሰብ ለማምጣት እና ለመመስረት ፈልግ፤

ጥበብን እንጂ ባለጠግነትን አትሻ፤ እናም፣ እነሆ፣ የእግዚአብሔር ሚስጥራት ይገለጡልሀል፣ እናም ባለጠጋም ትሆናለህ። እነሆ፣ ዘለዓለማዊ ሕይወት ያለው ሰው ባለጠጋ ነው።

እውነት፣ እውነት፣ እልሀለሁ፣ ላደርግልህ እንደምትሻው እንዲሁ ይደረግልሀል፤ እናም፣ ፈቃድህም ከሆነ፣ በዚህ ትውልድ ውስጥ የብዙ መልካም ስራ መከናወን መንስኤ ትሆናለህ።

ለዚህ ትውልድ ከንስሀ በቀር ሌላ ምንም አትናገር፤ ትእዛዛቴን ጠብቅ፣ እናም ስራዬን በትእዛዜ መሰረት እንዲከናወን እርዳ፣ እናም ትባረካለህ።

እነሆ፣ ስጦታ አለህ፣ ወይም በእምነት፣ በታመነ ልብ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ሀይል፣ ወይም አንተን በሚናገርህ ሀይሌ በማመን ከእኔ ከፈለግህ ስጦታ ይኖርሀል፤

፲፩ ስለሆነም፣ እነሆ፣ የምናገረው እኔ ነኝ፣ በጭለማ የማበራው ብርሀን እኔ ነኝ፣ እናም ለአንተ እነዚህን ቃላት በሀይሌ እሰጥሀለሁ።

፲፪ እናም አሁን፣ እውነት፣ እውነት፣ እልሀለሁ፣ ወደ መልካም፣ አዎን፣ በትክክል ለመስራት፣ በትህትና ለመራመድ፣ በጽድቅ ለመፍረድ፣ በሚመራው መንፈስ ላይ እምነትህን አድርግ፤ እና መንፈሴም ይህ ነው።

፲፫ እውነት፣ እልሀለሁ፣ ከመንፈሴ አእምሮህን እንዲያበራ፣ ነፍስህን በደስታ እንዲሞላ እሰጥሀለሁ፤

፲፬ እናም ከዚያም ታውቃለህ፣ ወይም የጽድቅን ነገሮች በተመለከተ ከእኔ የምትሻቸውን ማናቸውንም ነገሮች ሁሉ በእምነት በእኔ በማመን እንደምትቀበል በዚህ ታውቃለህ።

፲፭ እነሆ፣ እስከምትጠራ ድረስ ለመስበክ እንደተጠራህ አድርገህ ማሰብ እንደሌለብህ አዝሀለሁ።

፲፮ የትምህርቴን እርግጠኝነት ታውቅ ዘንድ ቃሌን፣ አለቴን፣ ቤተክርስቲያኔን እናም ወንጌሌን እስክትቀበል ድረስ፣ ለጥቂት ጊዜ ጠብቅ።

፲፯ እናም ከዚያም፣ እነሆ እንደመሻትህ፣ አዎን፣ እንደ እምነትህም እንዲሁ ይደረግልሀል።

፲፰ ትእዛዛቴን ጠብቅ፤ ዝም በል፤ ለመንፈሴ መቃቀትን አድርግ፤

፲፱ አዎን፣ የተነገሩትን ነገሮች ወደብርሀን በማምጣት ትረዳ ዘንድ፣ በሙሉ ልብህ ወደ እኔ ጽና—አዎን፣ የስራዬን ትርጉም፤ እስከምታጠናቅቅም ድረስ ትዕግስተኛ ሁን።

እነሆ፣ አዎን፣ በሙሉ ሀይልህ፣ አዕምሮህ እናም ጉልበትህ፣ ትእዛዛቴን መጠበቅ ይህ የአንተ ስራ ነው።

፳፩ ቃሌን ለማወጅ አትፈልግ፣ ነገር ግን አስቀድመህ ቃሌን ለማግኘት ፈልግ፣ እናም ከእዚያ አንደበትህ ይፈታል፤ ከዚያም፣ ፈቃድህ ከሆነ፣ አዎን፣ ሰዎችን ለማሳመን የእግዚአብሔር ሀይል የሆነውን ቃሌን እና መንፈሴን ትቀበላለህ።

፳፪ ነገር ግን አሁን ዝም በል፤ አዎን፣ በዚህ ትውልድ ለሰው ልጆች የምሰጠውን እስክትቀበል ድረስ፣ በሰዎች መካከል የሄደውን ቃሌን አጥና እናም ደግሞም በሰዎች መካከል የሚመጣውን ቃሌን፣ ወይም አሁን እየተተረጎመ ያለውን አጥና፣ እናም ሁሉም ነገሮች በዚያ ላይ ይጨመራሉ።

፳፫ እነሆ አንተ ልጄ ሀይረም ነህ፣ የእግዚአብሔርን መንግስት ፈልግ፣ እናም እንደ ፅድቅ መሰረት ሁሉም ነገሮች ይጨመራሉ።

፳፬ አለቴ በሆነው በወንጌሌ ላይ ታነፅ፤

፳፭ የራዕይ መንፈስንም ሆነ፣ የትንቢትን መንፈስ አትካድ፣ ይህንን ለሚክድ ለእርሱ ወዮለት፤

፳፮ ስለዚህ፣ በእኔ ጥበብ እስክትወጣ ድረስ በልብህ ቃሌን አከማች

፳፯ እነሆ፣ መልካም ፈቃድ ላላቸው፣ እናም በማጭዳቸው ለመሰብሰብ ለሚያጭዱ ሁሉ እናገራለሁ።

፳፰ እነሆ፣ እኔ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነኝ። እኔ የአለም ህይወት እና ብርሀን ነኝ።

፳፱ የእኔም ወደሆኑት መጥቼ የእኔም ያልተቀበሉኝ እኔው ራሴው ነኝ፤

ነገር ግን እውነት፣ እውነት፣ እልሀለሁ፣ ለተቀበሉኝ ሁሉ፣ በስሜ ለሚያምኑት እንኳን፣ ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ስልጣንን እሰጣቸዋለሁ። አሜን።