ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፻


ክፍል ፻

በጥቅምት ፲፪፣ ፲፰፻፴፫ (እ.አ.አ.) በፔሪስበርግ ኒው ዮርክ ለነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ እና ለስድኒ ሪግደን የተሰጠ ራዕይ። ሁለቱ ወንድሞች፣ ለብዙ ቀናት ከቤተሰቦቻቸው ተለያይተው ስለነበር፣ ስለእነርሱ አስበው ነበር።

፩–፬፣ ጆሴፍ እና ስድኒ ለነፍሳት ደህንነት ወንጌሉን ይስበኩ፤ ፭–፰፣ የሚናገሩትም በዚያች ሰዓት ይሰጣቸዋል፤ ፱–፲፪፣ ስድኒ ቃል ተቀባይ ይሁን እና ጆሴፍ ገላጭ እና በምስክርም ሀያል ይሁን፤ ፲፫–፲፯፣ ጌታ ንጹህ ህዝብ ያነሳል፣ እና የሚታዘዙም ይድናሉ።

፩ በእውነት ባልንጀሮቼ ስድኒ እና ጆሴፍ፣ ጌታ ለእናንተ እንዲህ ይላል፣ ቤተሰቦቻችሁ ደህና ናቸው፤ በእጆቼም ውስጥ ናቸው፣ እና መልካም እንደሚመስለኝም አደርግባቸዋለሁ በእኔ ሁሉም ሀይል አለና።

፪ ስለዚህ፣ ተከተሉኝ፣ እና የምሰጣችሁንም ምክር አድምጡ።

፫ እነሆ፣ እናም አስተውሉ፣ በዚህ ስፍራ፣ በዚህ ክፍለ ሀገር አካባቢ ብዙ ህዝብ አሉኝ፤ እና ውጤታማ በር በዚህ አካባቢ፣ በዚህ በምስራቅ ምድር ውስጥ ይከፈታል።

፬ ስለዚህ፣ እኔ ጌታ ወደዚህ ስፍራ ትመጡ ዘንድ ፈቀድኩኝ፤ ለነፍሳትም ደህንነት ይህም በእኔ ዘንድ አስፈላጊ ነበርና።

፭ ስለዚህ፣ እውነት እላችኋለሁ፣ ወደ እነዚህ ህዝብ ድምጾቻችሁን ከፍ አድርጉ፤ በልባችሁ የምጨምረውን ሀሳብ ተናገሩ፣ እና በሰዎችም ፊት አታፍሩም፤

፮ የምትናገሩት በዚያች ሰዓት፣ አዎን፣ በዚያች ጊዜም፣ ምን እንደምትናገሩ ይሰጣችኋልና።

፯ ነገር ግን የምታውጁትን ማንኛውንም ነገር በስሜ፣ በሁሉም ነገሮች በተረጋጋ ልብ፣ በትሁት መንፈስ ታውጁ ዘንድ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ።

፰ እና ይህን የተስፋ ቃል እሰጣችኋለሁ፣ ይህን ስታደርጉ ለምትሉት ማንኛቸውም ነገሮች ሁሉ ምስክር ይሰጣችሁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ይላካል።

፱ እና አንተ አገልጋዬ ስድኒ ለዚህ ህዝብ ቃል ተቀባይ እንድትሆን ፍቃዴ ነው፤ አዎን፣ በእውነትም በዚህ ሀላፊነት፣ እንዲሁም እንደ አገልጋዬ ጆሴፍ ቃል ተቀባይ እንድትሆኑ፣ እሾምሀለሁ።

፲ እና ለእርሱም በምስክር ሀያል እንዲሆን ሀይል እሰጠዋለሁ።

፲፩ እና ቅዱሳን መጻህፍትን ሁሉ ለመዘርዘር ሀያል እንድትሆንም ዘንድ፣ ለእርሱም ቃል ተቀባይ እንድትሆን ዘንድ ሀይልን እሰጥሀለሁ፣ እና በምድር ላይ ስላለችው መንግስቴ ነገሮች በሚመለከት የሁሉም ነገሮች እርግጠኛነትን ታውቅ ዘንድ እርሱም ለአንተ ገላጭ ይሆናል።

፲፪ ስለዚህ፣ በጉዞአችሁ ቀጥሉ እና ልባችሁ ይደሰቱ፤ እነሆ፣ እና አስተውሉ፣ እኔ እስከመጨረሻም ከእናንተ ጋር ነኝና።

፲፫ አሁንም ፅዮንን በተመለከት ቃልን እሰጣችኋለሁ። ምንም እንኳን ለጥቂት ዘመን ብትገሰፅም፣ ፅዮን ትድናለች።

፲፬ ወንድሞቻችሁ፣ አገልጋዮቼ ኦርሰን ሀይድ እና ጆን ጉልድ፣ በእጆቼ ውስጥ ናቸው፤ እና ትእዛዛቴን እስከጠበቁ ድረስ ይድናሉ።

፲፭ ስለዚህ፣ ልባችሁ ይፅናኑ፤ በቅንነት ለሚራመዱት፣ እና ለቤተክርስቲያኗ ቅድስ እና ጥቅም ሁሉም ነገሮች አብረው ይሰራሉና።

፲፮ ለራሴም በፅድቅ የሚያገለግሉኝ ንጹህ ህዝብ አስነሳለሁና፤

፲፯ እና የጌታን ስም የሚጠሩት፣ እና ትእዛዛቱን የሚጠብቁ ሁሉ ይድናሉ። እንዲህም ይሁን። አሜን።