“ነቢዩ ዮናስ፣” የብሉይ ኪዳን ታሪኮች [2021 (እ.አ.አ)]
“ነቢዩ ዮናስ፣” የብሉይ ኪዳን ታሪኮች
ዮናስ 1–4
ነቢዩ ዮናስ
በጌታ ምህረት መታመንን መማር
ዮናስ ነቢይ ነበር። ንስሐ ካልገቡ ከተማቸው እንደምትጠፋ በነነዌ ያሉ ሰዎችን እንዲያስጠነቅቅ ጌታ ነገረው።
ዮናስ 1፥1–2
ነገር ግን የነነዌ ሰዎች ለእስራኤላውያን ጠላቶች ነበሩ። ዮናስ ለእነርሱ ለመስበክ አልፈለገም። ስለዚህ ከነነዌ በጣም ርቆ ለመጓዝ በመርከብ ተሳፈረ።
ዮናስ 1፥3
ዮናስ በመርከቡ ላይ እያለ ሃይለኛ አውሎ ነፋስ መጣ። በመርከቡ ላይ የነበሩት ሰዎችም ለህይወታቸው ፈርተው ነበር። እንዲያድናቸው ወደጌታ እንዲጸልይ ዮናስን ጠየቁት።
ዮናስ 1፥4–6
ዮናስ ጌታ እንዲያደርግ ከጠየቀው እየሸሸ ስለሆነ ጌታ ማዕበሉን እንደላከው አወቀ። ዮናስም በመርከቡ ላይ ያሉትን ሰዎች ለማዳን ፈለገ። ወደ ባህር ውስጥ ቢጥሉት አውሎ ንፋሱ እንደሚቆም ተናገረ።
ዮናስ 1፥12
ሰዎቹም ዮናስን ከመርከቡ ውጪ ለመጣል አልፈለጉም ነበር። መርከቡን ወደ ደረቅ ምድር ለመውሰድ ሞከሩ፣ ነገር ግን አውሎ ንፋሱ ሃይለኛ ነበር። በመጨረሻም፣ ዮናስን ወደ ባህር ጣሉት።
ዮናስ 1፥13–15
አውሎ ንፋሱ ቆመ። ነገር ግን በዚያን ጊዜ ዮናስ በትልቅ አሳ ተውጦ ነበር።
ዮናስ 1፥15፣ 17
ዮናስም በአሳው ሆድ ውስጥ ለሶስት ቀን እና ለሶስት ምሽት ቆየ። በዚያም ጊዜ ዮናስ ጸለየ እንዲሁም ንስሀ ገባ። ትክክል የሆነውን ለማድረግና ጌታን ለማድመጥ ፈለገ። ጌታ የዮናስን ጸሎቶች ሰማና አሳው ዮናስን በደረቅ ምድር ላይ እንዲተፋው አደረገ።
ዮናስ 1፥17፤ 2፥1–10
እንደገናም ዮናስ ለነነዌ ሰዎች እንዲሰብክ ጌታ ነገረው። በዚህ ጊዜ ግን ዮናስ ታዘዘ። ወደ ነነዌ ሄደ፤ ከዚያም ሕዝቡ ንስሐ እንዲገቡ አለበለዚያ ጌታ ከተማቸውን እንደሚያጠፋ ነገራቸው። ንጉሱ እና ህዝቡ ንስሀ ገቡ። ጌታ ይቅር አላቸው፤ ነነዌንም አላጠፋም።
ዮናስ 3
ነገር ግን ዮናስ ሰዎቹ ባለመጥፋታቸው ቅር ተሰኘ። ይቅርታ ማግኘት የሚገባቸው አልመሰለውም።
ዮናስ 4፥1–2
ዮናስን ለማስተማርም ጌታ ዮናስን ከጸሀይ ለማስጠለል የሚችል አንድ ዛፍ አሳደገ። ከዚያም ተክሉ ደረቀ፤ እናም ዮናስ ስለተክሉ አዘነ።
ዮናስ 4፥5–9
ጌታ ዮናስን ስለልጆቹ እያስተማረው ነበር። ዮናስም ሰዎች ንስሐ በማይገቡበት ጊዜ ማዘን እንዳለበት እና ሲገቡም ደስተኛ መሆን እንዳለበት ተማረ።
ዮናስ 4፥10–11