ምዕራፍ ፳፭
ኔፊ በግልፅነት ይደሰታል—የኢሳይያስ ትንቢቶች በመጨረሻው ዘመናት ግልፅ ይሆናሉ—አይሁድ ከባቢሎን ይመለሳሉ፣ መሲሁንም ይሰቅላሉ፣ እናም ይበተናሉ፣ ይቀሰፋሉም—በመሲሁ ሲያምኑ ደግመው ይመለሳሉ—በመጀመሪያ ሌሂ ኢየሩሳሌምን ከለቀቀ ከስድስት መቶ አመት በኋላ ይመጣል—ኔፋውያን የሙሴን ህግ ይጠብቃሉ፣ የእስራኤሉ ቅዱስ በሆነው ክርስቶስም ያምናሉ። ከ፭፻፶፱–፭፻፵፭ ም.ዓ. ገደማ።
፩ አሁን እኔ ኔፊ፣ በኢሳይያስ አፍ ስለተነገሩት፣ እኔ ስለፃፍኳቸው ቃላት በመጠኑ እናገራለሁ። እነሆም ኢሳይያስ ለብዙ ህዝቦቼ ለመረዳት አስቸጋሪ የሆኑ ብዙ ነገሮችን ተናግሯል፤ እነርሱም በአይሁድ መካከል ስላለው በትንቢት አነጋገር አያውቁምና።
፪ እኔ ኔፊ ስለአይሁዶች አኳኋን ብዙም አላስተማርኳቸውምና፤ ስራዎቻቸው የጨለማ ስራ፣ አድራጎታቸውም የእርኩሰት አድራጎት ነበሩና።
፫ ስለዚህ፣ ለህዝቦቼም ሆነ ከዚህ በኋላ እነዚህን የምፅፋቸውን ለሚቀበሉ ሁሉ፣ የእግዚአብሔርን ፍርድ፣ በሁሉም ሀገሮች ላይ እርሱ በተናገረው ቃል መሰረት እንደሚመጡ ያውቁ ዘንድ ይህንን እፅፋለሁ።
፬ ስለዚህ፣ የእስራኤል ቤት የሆናችሁ ህዝቤ ሆይ፣ አዳምጡኝ፣ ቃላቶቼንም ለመስማት ጆሮአችሁን ስጡ፣ የኢሳይያስ ቃላት ለእናንተ ግልፅ አይደሉም፣ ይሁን እንጂ በትንቢት መንፈስ ለተሞሉት ሁሉ ግልፅ ናቸው። ነገር ግን እኔ በውስጤ ባለው መንፈስ መሰረት ይህንን ትንቢት እሰጣችኋለሁ፤ ስለዚህ ከአባቴ ጋር ኢየሩሳሌምን ለቅቄ ከወጣሁ ጊዜ ጀምሮ ባለኝ ግልፅነት እተነብይላችኋለሁ፤ እነሆም ህዝቦቼ ይማሩ ዘንድ ነፍሴ በግልፅነት ትደሰታለች።
፭ አዎን፣ ነፍሴ በኢሳይያስ ቃላት ትደሰታለች፣ እኔ ከኢየሩሳሌም ወጥቻለሁና፣ አይኖቼም የአይሁዶችን ነገር አይታለች፣ እናም አይሁድ የነቢዩን ነገሮች እንደተረዱት አውቃለሁ፣ እናም በአይሁዶች ጉዳይ የተማሩ ካልሆኑ በስተቀር ለአይሁዶች የተነገሩትን ነገሮች ከራሳቸው በቀር የሚረዳው ማንም የለም።
፮ ነገር ግን፣ እነሆ፣ እኔ ኔፊ፣ ልጆቼን የአይሁድ ጉዳዮችን አላስተማርኳቸውም፤ ነገር ግን እነሆ፣ እኔ ራሴ፣ በኢየሩሳሌም ኖሬአለሁ፣ ስለዚህ በዙሪያዬ ስለነበሩት ክልሎች በተመለከተ አውቃለሁ፤ ለልጆቼም ኢሳይያስ በተናገረው ሁሉ መሰረት በአይሁድ መካከል ሊመጣ ስላለውም የእግዚአብሔር ፍርድ ለልጆቼ ገልጬላቸዋለሁ፣ እናም እኔ አልፅፋቸውም።
፯ ነገር ግን እነሆ፣ እኔ በግልፅነቴ መሰረት የራሴን ትንቢት እቀጥላለሁ፤ በዚህም ማንም ሰው እንደማይሳሳት አውቃለሁ፣ ይሁን እንጂ፣ የኢሳይያስ ትንቢት በሚፈፀምበት ጊዜ፣ ሆነውም ሲያልፉ፣ ሰዎች እርግጠኛነቱን ያውቃሉ።
፰ ስለዚህ፣ ለሰው ልጆች ጥቅም አላቸው፣ እናም አይኖራቸውም ብሎ የሚያስብ፣ እኔ እነርሱን በተለይ እናገራቸዋለሁ፣ እናም ለህዝቤ ብቻ ቃሉን እናገራለሁ፤ ምክንያቱም በመጨረሻ ቀናት ለእነርሱ ታላቅ ዋጋ እንደሚኖራቸው አውቃለሁ፤ በዚያ ቀንም ይረዱአቸዋልና፤ ስለሆነም፣ ለጥቅማቸው ፅፌአቸዋለሁና።
፱ እናም በክፋታቸው የተነሳ ከአይሁዶች መካከል እንደጠፋው አንድ ትውልድ፣ እንደ ክፋታቸው እነርሱም ከትውልድ እስከ ትውልድም ሊጠፉ ችለዋል፤ እናም በጌታ ነቢያት አማካኝነት አስቀድሞ ካልተነገረላቸው በስተቀር ማናቸውም አልጠፉም።
፲ ስለሆነም፣ አባቴ ኢየሩሳሌምን ከለቀቀ ወዲያው በእነርሱ ላይ የሚመጣባቸውን ጥፋት በተመለከተ ተነግሯቸዋል፤ ይሁን እንጂ፣ እነርሱ ልባቸውን አጠጠሩ፤ እናም በትንቢቴ መሰረት ወደ ባቢሎን በምርኮ ከተወሰዱት በስተቀር ሌሎች ጠፍተዋል።
፲፩ እናም አሁን ይህን የምናገረው በውስጤ ባለው መንፈስ የተነሳ ነው። እናም እነርሱ ቢወሰዱም እንኳን እንደገና ይመለሳሉ፣ የኢየሩሳሌምን ምድርንም ይወርሳሉ፤ ስለሆነም፣ ወደ ርስት ምድራቸው እንደገና ይመለሳሉ።
፲፪ ነገር ግን፣ እነሆ፣ ጦርነትና የጦርነት ወሬዎች በመካከላቸው ይኖራቸዋል፤ እናም የአብ አንድያ ልጅ፣ አዎን፣ የሰማይና የምድር አባት የሆነውም እንኳን፣ በስጋ እራሱን የሚገልፅበት ቀን በሚመጣበት ጊዜ፣ እነሆ፣ በክፋታቸውና በልባቸው ጠጣርነት እንዲሁም በአንገተ ደንዳናነታቸው ምክንያት አይቀበሉትም።
፲፫ እነሆ፣ ይሰቅሉታል፤ እናም ከድንጋይ ከተወቀረው መቃብር ውስጥ ለሶስት ቀን ከቆየ በኋላ፣ ፈውስን በክንፎቹ ይዞ ከሙታን ይነሳል፤ እናም በስሙ የሚያምኑ ሁሉ በእግዚአብሔር መንግስት ይድናሉ። ስለሆነም፣ ነፍሴ እርሱን በተመለከተ ለመተንበይ ትደሰታለች፣ ቀኖቹን አይቻለሁና፣ ልቤም ቅዱስ ስሙን ታመሰግናለች።
፲፬ እናም እነሆ እንዲህ ይሆናል መሲሁ ከሞት ከተነሳ እናም፣ በስሙ ለሚያምኑ ለብዙዎች ሕዝቦቹ ራሱን ከገለጸ በኋላ፣ እነሆ፣ ኢየሩሳሌም በድጋሚ ትጠፋለች፤ ከእግዚአብሔርና ከቤተክርስቲያኑ ሰዎች ጋር ለሚጣሉ ወዮላቸው።
፲፭ ስለሆነም፣ አይሁዶች በሀገር ሁሉ መካከል ይበተናሉ፤ አዎን፣ እናም ደግሞ ባቢሎን ትጠፋለች፤ ስለሆነም፣ አይሁዶች በሌሎች ሀገሮች ይበተናሉ።
፲፮ እናም እነርሱ ከተበተኑና፣ ለብዙ ዘመን ጌታ እግዚአብሔር በሌሎች ሀገሮች ከቀጣቸው በኋላ፣ አዎን፣ ከትውልድ እስከ ትውልድ በእግዚአብሔር ልጅ በክርስቶስ፣ እና ለሁሉም የሰው ዘር ያልተገደበውን የኃጢያት ክፍያ ለማመን እስኪገደዱም ድረስ—እናም በክርስቶስ የሚያምኑበትና፣ በፍፁም ልብና በንፁህ እጃቸው አብን በስሙ የሚያመልኩበት፣ እናም ሌላ መሲህ ይመጣል ብለውም የማይጠብቁበት ያ ቀን ሲመጣ፣ በኋላም፣ በዚያን ጊዜ እነዚህን ነገሮች ማመን ለእነርሱ አስፈላጊ የሚሆንበት ቀን ይመጣል።
፲፯ እናም ጌታ ለሁለተኛ ጊዜ ህዝቡን ከጥፋትና ከውድቀት ለመመለስ እጁን ይዘረጋል። ስለዚህ፣ በሰው ልጆች መካከል አስደናቂውንና ድንቅ ስራውን መስራት ይቀጥላል።
፲፰ ስለዚህ፣ ቃሉን ይገልፅላቸዋል፣ እነዚህም ቃላት በመጨረሻውም ቀን ይፈርድባቸዋል፣ ምክንያቱም በእነርሱ ስለተነቀፈው ስለ እውነተኛው መሲህ ዓላማ ለማሳመን ተሰጥቶአቸዋልና፤ እናም ከእንግዲህ መሲሁ ይመጣል ብለው እንዳይጠብቁ ለማሳመን፣ ህዝቡን የሚያታልለው ሀሰተኛው መሲህ ካልሆነ ሌላ ማንም ሊመጣ አይገባውምና፤ በነቢያት የተነገረበት አንድ መሲህ ብቻ ነው ያለውና፣ እናም ያ መሲህ በአይሁዶች የተነቀፈው ነው።
፲፱ በነቢያቶቹ ቃል መሰረት፣ አባቴ ኢየሩሳሌምን ለቆ ከወጣ ከስድስት መቶ ዓመት በኋላ መሲሁ ይመጣል፤ እናም እንደ ነቢያቱ ቃል፣ ደግሞም በእግዚአብሔር መልአክ ቃል መሰረት፣ ስሙም ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የእግዚአብሔር ልጅ ይሆናል።
፳ እናም አሁን ወንድሞቼ እንዳትሳሳቱ ዘንድ በግልፅ ነግሬአችኋለሁ። እናም ከግብፅ ምድር እስራኤልን ያወጣና፣ ለሙሴ ህዝቡ በመርዘኛ እባብ ከተነደፉ በኋላ በፊታቸው ከፍ ያደረገውን እባብ ላይ አይናቸውን ከጣሉ ለመፈወስ ይችል ዘንድ ኃይልን የሰጠው፣ እናም ደግሞ ድንጋዩን መትቶ ውኃ እንዲፈልቅለት ኃይልን የሰጠው ጌታ እግዚአብሔር ህያው እንደሆነ፤ አዎን፣ እነሆ እንዲህ እላችኋለሁ፥ እነዚህ ነገሮች እውነት ናቸው፣ እናም ጌታ እግዚአብሔር ህያው እንደሆነ እኔ እንደተናገርኩበት ከዚህ ከኢየሱስ ክርስቶስ በስተቀር ሰው ሊድንበት የሚችል ምንም አይነት ስም ከሰማይ በታች የተሰጠ የለም።
፳፩ ስለዚህ፣ በዚህ ምክንያት ነው ጌታ እግዚአብሔር እነዚህን የፃፍኳቸው ነገሮች እንደሚጠበቁና እንደሚቀመጡ፣ እናም ዘሮቹ ምድር እስካለችም ድረስ እንደማይጠፉ ለዮሴፍ የተገባለት ቃል ኪዳን እንዲሟላ ዘንድ ከትውልድ እስከ ትውልድ ለዘሮቼ እንደሚተላለፉ ቃል የገባልኝ።
፳፪ ስለሆነም፣ እነዚህ ነገሮች ምድር እስካለች ድረስ ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋሉ፤ እናም እነሱም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድና ደስታ ይተላለፋሉ፤ እናም እነርሱ ያሏቸውም ሀገሮች በተፃፉት ቃል መሰረት ይፈረድባቸዋል።
፳፫ ለመጻፍ፣ ልጆቻችንን እናም ደግሞ ወንድሞቻችንን በክርስቶስ እንዲያምኑና ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቁ ለማሳመን በትጋት እንሰራለንና፤ ምክንያቱም በጸጋ የምንድነው የምንችለውን ካደረግን በኋላ እንደሆነ እናውቃለንና።
፳፬ እናም በክርስቶስ ብናምንም እንኳን የሙሴን ህግ እንጠብቃለን፣ እናም ህጉ እስከሚፈፀም ድረስ በፅኑነት ወደፊት ወደክርስቶስን እንመለከታለን።
፳፭ ይህ ህግ የተሰጠው ለዚህ አላማ ነበርና፤ ስለሆነም ህጉ ለእኛ ሙት ሆኗል፣ እናም እኛ በእምነታችን ምክንያት በክርስቶስ ህያው ሆነናል፤ ቢሆንም ግን ህጉን በትዕዛዝ ምክንያት እንጠብቃለን።
፳፮ እናም ልጆቻችን ለኃጢአታቸው ስርየት የትኛውን ምንጭ መመልከት እንዳለባቸው ያውቁ ዘንድ፣ ስለክርስቶስ እንናገራለን፣ በክርስቶስ እንደሰታለን፣ ስለክርስቶስ እንሰብካለን፣ ስለክርስቶስ ትንቢት እንናገራለን፣ እናም በትንቢታችን መሰረት እንፅፋለን።
፳፯ ስለዚህ፣ ህጉን በተመለከተ ልጆቻችን የህጉን መሞት ያውቁት ዘንድ እንናገራለን፤ እናም እነርሱ የህጉን ሞት በማወቅ፣ በክርስቶስ የሚመጣውን ህይወት ይጠብቃሉ እናም ህጉ ለምን ዓላማ እንደተሰጠ ያውቃሉ። እናም ህጉ በክርስቶስ ከተፈፀመ በኋላ፣ ህጉ በሚፈፀምበት ጊዜ በእርሱ ልባቸውን ማጠጠር እንደማያስፈልጋቸው እንዲያውቁም ነው።
፳፰ እናም አሁን እነሆ ህዝቦቼ፣ አዎን እናንተ አንገተ ደንዳና ህዝብ ናችሁ፤ እኔ በግልፅ የተናገርኳችሁ አንዳትደናገሩም ነው። የምናገረው ቃል እንደምስክር በእናንተ ላይ ይቆማሉ፤ ምክንያቱም እነርሱ ማንኛውንም ሰው ትክክለኛውን መንገድ ለማስተማር በቂ ናቸውና፤ ትክክለኛው መንገድ በክርስቶስ ማመንና እርሱን አለመካድ ነውና፤ ምክንያቱም እርሱን በመካድ እናንተ ደግሞ ነቢያትንና ህጉን ትክዳላችሁና።
፳፱ እናም እነሆ አሁን፣ ትክክለኛው መንገድ በክርስቶስ ማመን ነው እላችኋለሁ፣ እርሱንም አትካዱ፤ እናም ክርስቶስ የእስራኤል ቅዱስ ነው፤ ስለዚህ በፊቱ መስገድና፣ በሙሉ ኃይላችሁ፣ አእምሮአችሁና ጉልበታችሁ እንዲሁም በፍፁም ነፍሳችሁ እርሱን ማምለክ አለባችሁ፤ እናም ይህን ካደረጋችሁ በምንም ሁኔታ አትጣሉም።
፴ እናም አስፈላጊ እስከሆነ፣ ለሙሴም የተሰጠው ህግ እስከሚፈፀም ድረስ የእግዚአብሔርን ስራና ስርዓቱን መጠበቅ አለባችሁ።