ቅዱሳት መጻህፍት
፪ ኔፊ ፲፯


ምዕራፍ ፲፯

ኤፍሬምና ሶርያ በይሁዳ ላይ ጦርነትን አወጁ—ክርስቶስ ከድንግል ይወለዳል—ኢሳይያስ ፯ን አነጻፅሩ። ፭፻፶፱–፭፻፵፭ ም.ዓ. ገደማ።

እናም እንዲህ ሆነ በአካዝ በኢዮአታም ልጅ ዘመን፣ በይሁዳ ንጉስ በኡዝያን ልጅ፣ የሶርያው ንጉስ ረአሶን፣ እና የሮሜልዩ ልጅ፣ የእስራኤልም ንጉስ ፋቁሔ ኢየሩሳሌምን ሊወጉ ወጡ፣ ነገር ግን ሊያሸንፉአትም አልቻሉም።

እናም ለዳዊት ቤት ሶርያ ከኤፍሬም ጋር ተባብራለች የሚል ወሬ ተነገረ። እናም የጫካ ዛፍ በንፋስ እንደሚናወጥ የእርሱ ልብና የህዝቡም ልብ ተናወጠ።

ከዚያም ጌታ ኢሳይያስን አለው—አሁን አንተና ልጅህ ያሱብ ከአካዝ ጋር ትገናኙት ዘንድ በልብስ አጣቢው እርሻ መንገድ ወዳለው ወደ ላይኛው የኩሬ መስኖ ጫፍ ውጡ፤

እናም እንዲህ በለው—ተጠንቀቅ፣ ዝምም በል፣ ስለእነዚህ ስለሚጨሱ ስለሁለት ጥላሸቶች፣ ስለረአሶን በሶርያና፣ ሮሜልዩም ልጅ ቁጣ አትፍራ

ምክንያቱም ሶርያ፣ ኤፍሬምና የሮሜልዩም ልጅ በአንተ ላይ እንዲህ ሲሉ ክፋትን መክረዋልና፤

ወደ ይሁዳ እንውጣና እናስጨንቀው፣ እናም ለራሳችን በእዚያም እንስበረው፣ በመካከሉም ንጉስ፣ አዎን፣ የጠብኤልንም ልጅ፣ እናስቀምጥ።

እንዲሁም ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል—ይህ ምክር አይፀናም፣ አይሆንምም።

የሶርያ ራስ ደማስቆ ነውና፣ እናም የደማስቆም ራስ ረአሶን ነውና፤ እናም በስድሳ አምስት ዓመት ውስጥ ኤፍሬም ይሰባበራል፣ ህዝብም አይሆንም።

እናም የኤፍሬም ራስ ሰማርያ ነው፣ እናም የሰማርያ ራስ የሮሜልዩ ልጅ ነው። የማታምኑ ከሆነ በእርግጥ አትፀኑም።

ከዚያም በላይ ጌታ አካዝን በድጋሚ እንዲህ ብሎ ተናገረው—

፲፩ ከጥልቁ ወይም ከከፍታውም ቢሆን ከጌታ ከአምላክህ ምልክትን ለምን።

፲፪ ነገር ግን አካዝም፣ አልለምንም፣ ጌታንም አልፈተንም አለ።

፲፫ እናም እርሱ አለ፥ የዳዊት ቤት ሆይ፣ አሁን ስሙኝ፤ በእውነት ሰውን ማድከም ቀላል ሆነባችሁ፣ ግን አምላኬን ደግሞ ልታደክሙ ነውን?

፲፬ ስለዚህ፣ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል—እነሆ፣ ድንግል ትፀንሳለች፣ እናም ወንድ ልጅም ትወልዳለች፣ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።

፲፭ እርሱም ክፉን ለመጥላትና መልካሙን ለመምረጥ ማወቅ ይችል ዘንድ ቅቤና ማር ይበላል።

፲፮ ህፃን መጥፎውን ከመጥላቱና ጥሩውን ከመምረጡ በፊት፣ የጠላኸው መሬት በሁሉም ነገሥታቶች ይተዋል።

፲፯ ጌታ ኤፍሬም ከይሁዳ ከተለየበት ቀን ጀምሮ ያልመጣውን ዘመን በአንተና በሕዝብህ በአባትህም ቤት ላይ ያመጣል፤ እርሱም የአሦር ንጉሥ መምጣት ነው።

፲፰ እናም በዚያ ቀን እንዲህ ይሆናል ጌታ በግብፅ ዳርቻ ያለውን ዝንብ እና በአሶር ምድር ያለውን ንብ በፉጨት ይጠራል።

፲፱ እናም ይመጣሉ፣ እነርሱም ሁሉ በበረሃ ሸለቆ፣ እና በድንጋይም ዋሻና በእሾህ ላይ ሁሉ፣ በቁጥቋጦውም ሁሉ ላይ ያርፋሉ።

በዚያም ቀን ጌታ ከወንዙ ባሻገር፣ በቀጠራቸው በአሶር ንጉስ፣ የራስና የእግሩን ጠጉር ይላጫል፣ እናም ምላጩ ደግሞ ጢሙን ይበላል።

፳፩ እናም በዚያ ቀን እንዲህ ይሆናል፣ አንድ ሰው ጊደርና ሁለት በጎችን ይመግባል

፳፪ እናም እንዲህ ይሆናል፣ ከሚሰጡት ወተት ብዛት የተነሳ እርሱ ቅቤን ይበላል፣ በሀገሪቱም መካከል የቀረ ማንም ሰው ቅቤና ማር ይበላል።

፳፫ እናም በዚያ ቀን እንዲህ ይሆናል፣ ሺህ ብር የሚያወጣው ሺህ የወይን ግንድ በነበረበት ቦታ ሁሉ ኩርንችትና እሾህ ብቻ ይሆናሉ።

፳፬ በምድሪቱ ሁሉ ኩርንችትና እሾህ በመሆኑ ሰዎች በፍላፃና በቀስት ወደዚያ ይመጣሉ።

፳፭ እናም በመቆፈሪያ ወደ ተቆፈሩ ኮረብቶች ሁሉ፣ ከኩርንችትና እሾህ ፍርሀት ወደዚያ ማንም አይሄድም፤ ነገር ግን የበሬ ማሰማሪያና የታናሽ ከብት መረገጫ ይሆናል።