ቅዱሳት መጻህፍት
፪ ኔፊ ፳፫


ምዕራፍ ፳፫

የባቢሎን ጥፋት በዳግም ምፅአት የሚኖረው ጥፋት ምልክት ነው—የቁጣና የበቀል ቀን ይሆናል—ባቢሎን (አለም) ለዘለዓለም ትወድቃለች—ኢሳይያስ ፲፫ን አነጻፅሩ። ከ፭፻፶፱–፭፻፵፭ ም.ዓ. ገደማ።

፩ የአሞፅ ልጅ ኢሳይያስ የተመለከተው የባቢሎን ሸክም።

፪ ከፍ ባሉ ተራራ ላይ አርማን አቁሙ፣ ድምፃችሁንም ወደ እነርሱ ከፍ አድርጉ፣ ወደ ልዑላት ደጃፍ ይሄዱ ዘንድ ጠቁሙአቸው።

፫ ቅዱሳኖቼን አዝዤአለሁ፣ ኃያላኖችንም ጠርቻቸዋለሁ፣ ቁጣዬ በእኔ ታላቅነት በሚደሰቱት ላይ አይደለችምና።

፬ በተራሮቹ ያሉት ህዝቦች ጩኸት እንደ በርካታ ሰዎች ነው፣ ከመጠን በላይ የሚንጫጩ ሀገሮች መንግስታት ተከማችተዋል፣ የሰራዊት ጌታ የጦር ሰራዊቱን ይሰበስባል።

፭ እነርሱ፣ አዎን፣ ጌታ እና የእርሱ የቁጣው መሳሪያ ምድርን ሊያጠፋት ከሩቅ ሀገር፣ ከሰማይ ዳርቻም መጥተዋል።

፮ የጌታ ቀን ቀርባለችና አልቅሱ፤ ሁሉን ከሚገዛ እንደጥፋት ትመጣለች።

፯ ስለዚህ ሁሉም እጆች ይዝላሉ፣ የሁሉም ሰዎች ልብ ትቀልጣለች።

፰ እናም እነርሱ ይፈራሉ፣ ኃይለኛ ህመምና ሀዘንም ይይዛቸዋል፤ አንዱም በሌላው ይደነቃል፤ ፊቶቻቸው በእፍረት እንደነበልባል ይሆናሉ።

፱ እነሆ፣ ጨካኝ በሆነ ቁጣና ከኃይለኛ ንዴት ጋር ምድርን ባድማ ሊያደርጋት የጌታ ቀን ይመጣል፤ ኃጢአተኞችንም ከውስጧ ያጠፋል።

፲ የሰማይ ከዋክብትና ህብር ከዋክብቶች ብርሃናቸውን አይሰጡም፤ ፀሐይም በወጣች ጊዜ ትጨልማለች፣ ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም።

፲፩ እናም ዓለምን በመጥፎ ስራዋ፣ ክፉዎችንም ለግፍ ስራቸው እቀጣለሁ፤ የትዕቢተኞችንም ኩራት አስቆማለሁ፣ የጨካኞችንም ኩራት አዋርዳለሁ።

፲፪ ሰውንም ከነጠረ ወርቅ የበለጠ የከበረ አደርገዋለሁ፤ ሰውም ከኦፊር ወርቅ ይልቅ የከበረ ይሆናል።

፲፫ ስለዚህ፣ በሰራዊት ጌታ መዐት እናም በታላቁ ቁጣው ቀን እኔ ሰማያትን አናውጣለሁ ምድርንም ከቦታዋ ፈቀቅ አደርጋታለሁ።

፲፬ እናም እንደሚሳደድ ድብ፣ ማንም ሰው እንደማይሰበስባቸው በጎች ይሆናሉ፤ እናም ሁሉም ሰው ወደ ራሱ ህዝብ ይዞራል፣ እናም ሁሉም ወደ ራሱ ምድር ይሸሻል።

፲፭ የሚኮራ ሰው ሁሉ ይወጋል፣ አዎን፣ ከኃጢአተኞች የተቀላቀለ ሰው ሁሉ በሰይፍ ይወድቃል።

፲፮ ልጆቻቸውም በዐይኖቻቸው ፊት ይከሰከሳሉ፤ ቤቶቻቸው ይበዘበዛል፣ ሚስቶቻቸውም ይደፈራሉ።

፲፯ እነሆ፣ ብር እና ወርቅ የማይሹትንና በዚህም የማይደሰቱትን ሜዶናውያንን በላያቸው አስነሳለሁ።

፲፰ ፍላፃዎቻቸውም ወጣቶቻቸውን ይጨፈጭፏቸዋል፤ ለማህፀኑም ፍሬ ምህረት አይኖራቸውም፤ ዐይኖቻቸውም ህፃናትን በህይወት አይተዉም።

፲፱ እናም የመንግስታት ክብር፣ የከለዳውያን ቆንጆ ክቡር የሆነችው ባቢሎን እግዚአብሔር ሰዶምንና ገሞራን ባፈረሰ ጊዜ እንደነበረ ትሆናለች።

፳ ለዘለዓለም የሚቀመጥባት አይገኝም፣ ከትውልድ እስከትውልድም የሚኖርባት አይኖርም—አረባውያንም ቢሆኑ ድንኳኑን በዚያ አይተክልም፤ እረኞችም ቢሆኑ እንኳ መንጋቸውን በዚያ አያሰማሩም።

፳፩ ነገር ግን የበረሃ የዱር አራዊት በዚያ ያርፋሉ፤ ሰጎኖችም ቤቶቻቸውን ይሞሉታል፣ ጉጉቶችም በዚያ ይኖራሉ፤ አጋንንትም በዚያ ይጨፍራሉ።

፳፪ እናም የደሴቶቹ አውሬዎች በባዶ ቤቶቻቸው፣ ቀበሮዎችም በአስደሳች ስፍራዎቻቸው ይጮሃሉ፤ እናም ጊዜዋ ቀርቧል፣ ቀኗም አይራዘምም። እኔ በፍጥነት አጠፋታለሁና፤ አዎን፣ እኔ ለህዝቦቼ መሃሪ እሆናለሁና፣ ነገር ግን ኃጢአተኞች ይጠፋሉ።