ቅዱሳት መጻህፍት
፪ ኔፊ ፲፰


ምዕራፍ ፲፰

ክርስቶስ እንደማሰናከያ ዓለት እና እንቅፋት ይሆናል—ጠንቋይን ሳይሆን ጌታን እሹ—ለመመሪያችሁ በህጉና በምስክርነቱ ላይ ተስፋ አድርጉ—ኢሳይያስ ፰ን አነጻፅሩ። ከ፭፻፶፱–፭፻፵፭ ም.ዓ. ገደማ።

፩ ከዚህም በላይ፣ የጌታ ቃል እንዲህ አለኝ—ትልቁን ጥቅል ውሰድ፣ እናም ማሔር-ሻላል-ኸሽ-ባዝ ብለህ በሰው ብዕር ፃፍበት።

፪ እናም እኔ የታመኑ ምስክሮችን፣ ካህን ኦርዮን እና የበራክዩን ልጅ ዘካርያስን ለምዝገባው ወደ እኔ ወሰድሁ።

፫ እናም እኔ ወደ ነቢይቱ ቀረብሁ፤ እርሷም ፀነሰች እናም ወንድ ልጅ ወለደች። ከዚያም ጌታ እንዲህ አለኝ፥ ማኻር-ሻላል-ሐሽ-ባዝ ብለህ ስሙን ጥራው።

፬ እነሆም፣ ህፃኑ አባቱንና እናቱን መጥራት ሳያውቅ፣ የደማስቆን ሀብትና የሰማርያን ምርኮ በአሶር ንጉስ ፊት ይወስዳል።

፭ ጌታ እንደገና ደግሞ እንዲህ ሲል ተናገረኝ፥

፮ ይህ ህዝብ በቀስታ የሚሄደውን የሰሊሆምን ውሃ እስከጠሉ፣ እናም በረአሶንንና በሮሜልዩም ልጅ በመደሰታቸው የተነሳ፤

፯ ስለዚህ አሁን፣ እነሆ፣ ጌታ ብርቱና ብዙ የሆነውን የወንዝ ውሃ፣ የአሶርን ንጉስና ክብሩን ሁሉ ያመጣባቸዋል፤ እናም እርሱ መስኖዎችን ሁሉ ይሞላል፣ እናም በዳርቻውም ሁሉ ላይ ይፈስሳል።

፰ እናም በይሁዳ ያልፋል፤ እያጥለቀለቀም ያልፋል፣ እስከ አንገትም ይደርሳል፤ እናም አማኑኤል ሆይ፣ የክንፉ መዘርጋት የአገርህን ስፋት ትሞላለች።

፱ ህዝብ ሆይ ተባበሩ፣ እናም በትንንሹ ትከፋፈላላችሁ፤ እናንተም ሩቅ ሀገር ያላችሁ ሁሉ አድምጡ፤ ራሳችሁን አስታጥቁ፣ እናም በትንንሹ ትከፋፈላላችሁ፤ ራሳችሁን አስታጥቁ፣ እናም በትንንሹ ትከፋፈላላችሁ።

፲ በአንድነት ተመካከሩ፣ እናም እርሱ ከንቱ ይሆናል፤ ቃሉን ተናገሩ፣ እናም አትፀናም፣ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነውና።

፲፩ ጌታ በፅኑ እጁ እንዲሁ ተናግሮኛልና፣ እናም በዚህ ህዝብ መንገድ እንዳልራመድ እንዲህ ሲል አዘዘኝ፥

፲፪ ይህ ህዝብ ግብረ-አበራዊ ነው በሚለው ሁሉ ግብረ-አበራዊ ነው አትበሉ፣ መፈራታቸውንም ቢሆን አትፍሩ፣ አትደንግጡ።

፲፫ የሰራዊት ጌታ እራሱን ቀድሱት፣ እናም የእናንተ ፍርሃት እርሱ ይሁን፣ ስጋታችሁም እርሱ ይሁን።

፲፬ እናም እርሱ መሸሸጊያ፤ ነገር ግን ለሁለቱ ለእስራኤል ቤቶች፣ ለእንቅፋት ድንጋይና፣ ለማሰናከያ አለት፣ በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩ ለወጥመድና ለአሽክላ ይሆናል።

፲፭ እናም ብዙዎች ከእነርሱ ጋር ይሰናከላሉ እንዲሁም ይወድቃሉ፣ ይሰበራሉም፣ ይጠመዳሉም፣ እናም ይማረካሉ።

፲፮ በደቀ መዛሙርቶቼም መካከል ምስክርነትን እሰር፣ ህጉንም አትም።

፲፯ እናም ከያዕቆብ ቤት ፊቱን የደበቀውን ጌታ እጠብቃለሁ፣ እናም እርሱን እፈልገዋለሁ።

፲፰ እነሆ፣ እኔና ጌታ የሰጠኝ ልጆቼ በእስራኤል በፅዮን ተራራ ከሚኖረው ከሰራዊት ጌታ ዘንድ ምልክትና ተአምራት ነን።

፲፱ እናም የሚጮሁትንና፣ ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው የሚናገሩትን መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ጠይቁ ባሉአችሁ ጊዜ—ለህያዋን ከሙታን ለመስማት ህዝቡ ከአምላኩ መጠየቅ አይገባውምን?

፳ ወደህግና ወደምስክርነት ተመልከቱ፣ እናም በዚህ ቃል መሰረት ካልተናገሩ፣ ምክንያቱ ብርሃን በውስጣቸው የለም።

፳፩ እነርሱም ይህን በጣም ተጨንቀውና ተርበው ያልፋሉ፤ እናም እንዲህ ይሆናል በተራቡ ጊዜ፣ በጣም ይቆጣሉ፣ እናም አምላካቸውንና ንጉሳቸውን ይረግማሉ፣ ወደ ላይም ይመለከታሉ።

፳፪ እናም ወደ ምድር ይመለከታሉ፣ እናም ችግርን፣ ጨለማን፣ የሚያስጨንቅ ጭጋግን ያያሉ፣ እናም ወደ ጨለማም ይሰደዳሉ።

      • ዕብ. ወደ ብዝበዛው በፍጥነት ለመድረስ፣ የሚታደነውን አጣደፈ።

      • ይህም ባለቤቱ ማለት ነው።

      • ይህም በመጀመሪያ በሰሜን እስራኤል ላይ ማለት ነው።

      • ይህም ህብረትን መፍጠር ማለት ነው።

      • ይህም ይሁዳ (የአማኑኤል ምድር) ይተርፋል ማለት ነው። መዝ. ፵፮፥፯።

      • ይህም ይሁዳ ለደህንነት ከሌሎች ጋር በሚሰራው የሚስጥር ሴራ ላይ መመካት አይገባውም ማለት ነው።

      • ይህም በእግዚአብሔር ፊት አምልኮን የሚያሳይ እና ትሁት ሁን ማለት ነው።

      • ማቴ. ፳፩፥፵፪–፵፬።

      • ኢሳ. ፶፬፥፰።

      • ይህም የኢሳይያስ እና የወንድ ልጆቹ ስም በመከታተል፥ “ያህዌ ያድናል”፤ “የሚቀረው ይመለሳል”፤ እና “ወደ ብዝበዛው በፍጥነት ለመድረስ፣ የሚታደነውን አጣደፈ” ማለት ነው። ፪ ኔፊ ፲፯፥፫፤ ፲፰፥፫።

      • ዘሌዋ. ፳፥፮።

      • ይህም ጠንቋዮች፣ ምዋርተኞች ማለት ነው።

      • ወይም ለ…ጥቅም ማለት ነው።

      • ፩ ሳሙ. ፳፰፥፮–፳።

      • ይህም እስራኤል ስለማያዳምጡ እንደ ምርኮ ይወሰዳሉ ማለት ነው።