ቅዱሳት መጻህፍት
፪ ኔፊ ፳፩


ምዕራፍ ፳፩

የእሴይ ግንድ (ክርስቶስ) በጻድቅነት ይፈርዳል—ስለእግዚአብሔር የሚኖረው እውቀት በአንድ ሺህ ዘመን ምድርን ይሞላል—ጌታም አርማውን ያነሳል እናም እስራኤልን ይሰበስባል—ኢሳይያስ ፲፩ን አነጻፅሩ። ከ፭፻፶፱–፭፻፵፭ ም.ዓ. ገደማ።

እናም ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፣ ከስሩም ቅርንጫፍ ይበቅላል።

እናም የጌታ መንፈስ፣ የጥበብና የመረዳት መንፈስ፣ የምክርና የኃይል መንፈስ፣ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ በላዩ ላይ ያርፋል፤

እናም በእግዚአብሔር ፍርሃት በፍጥነት የሚረዳ ያደርገዋል፤ እናም እርሱ በዐይኖቹ ባየው አይፈርድም፣ ወይም በጆሮዎቹ በሰማውም አይገስጽም።

ነገር ግን ድሆችን በፅድቅ ይፈርዳል፣ ለምድር ትሁቶችም በእኩልነት ይገስጻል፤ እናም ምድርን በአፉ በትር ይመታል፣ እናም ክፉዎችን በከንፈሮቹ እስትንፋስ ይገድላል።

እናም ፅድቅ የወገቡ መታጠቅያ፣ ታማኝነትም የጎኑ መታጠቅያ ይሆናሉ።

ተኩላውም ደግሞ ከበጉ ጋር ይኖራል፣ አቦሸማኔው ደግሞ ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፣ ጥጃውም የአንበሳ ደቦልም፣ ፍሪዳውም በአንድነት ይሆናሉ፤ ታናሽ ልጅም ይመራቸዋል።

እናም ላምና ድብ አብረው ይመገባሉ፤ ግልገሎቻቸውም በአንድነት ይተኛሉ፤ አንበሳውም እንደበሬ ገለባን ይበላል።

እናም የሚጠባው ህፃን በመርዛማው እባብ ጉድጓድ ላይ ይጫወታል፣ ጡት የጣለውም ህፃን በእፉኝት ቤት ላይ ይጭናል።

በተቀደሰው ተራራዬ ላይ ሁሉ አይጎዱም፣ ወይም አያጠፉም፣ ውኃዎች ባህርን እንደሚሸፍን ሁሉ ምድር በጌታ እውቀትም ትሞላለችና።

እናም በዚያ ቀን ለህዝቡ ምልክት ሆኖ የሚቆም የእሴይ ስር ይኖራል፤ አህዛብም እርሱን ይፈልጋሉ፤ እናም የሚያርፍበትም የተከበረ ይሆናል።

፲፩ እናም በዚያ ቀን እንዲህ ይሆናል ጌታ የቀረውን የህዝቡን ቅሪት ከአሶርና፣ ከግብፅ፣ ከጳትሮስና፣ ከኩሽ፣ ከኢላምና፣ ከሰናዖር፣ ከሐማት፣ ከባህር ደሴቶች መልስ ዳግም ይሰበስብ ዘንድ ለሁለተኛ ጊዜ እጁን ይዘረጋል።

፲፪ እናም እርሱ ለሀገሮች ምልክትን ያቆማል፣ ከእስራኤልም የተሰደዱትን ይሰበስባል፣ እናም በአራቱም የምድር ማዕዘናት የተበተነውን ይሁዳን በአንድነት ይሰበስባል

፲፫ የኤፍሬም ምቀኝነት ደግሞም ይቆማል፣ የይሁዳም ጠላቶች ይጠፋሉ፤ ኤፍሬም በይሁዳ አይቀናምና፣ እናም ይሁዳ ኤፍሬምን አያበሳጭም።

፲፬ ነገር ግን በምዕራብ በኩል በፍልስጤማውያን ትከሻ ላይ እየበረሩ ይወርዳሉ፤ የምስራቆቹንም ጭምር በአንድነት ያጠፋሉ፤ እጃቸውንም በኤዶምና በሞአብ ላይ ያሳርፋሉ፤ እናም የአሞንም ልጆች ይታዘዙአቸዋል።

፲፭ እናም ጌታ የግብፃውያንን የባህር ሠርጥ ፈፅሞ ያጠፋል፤ በኃያል አውሎ ነፋሱም እጆቹን በወንዞች ላይ ያንቀጠቅጣል፣ ሰባትም ወራጆች አድርጎ ይከፋፍለዋል፣ ሰዎችንም በደረቁ ያሻግራል።

፲፮ እናም እርሱ ከግብፅ ምድር በወጣ ጊዜ ለህዝቡ ቅሪት ሆኖ ለሚቀሩት ከአሶር እስከ እስራኤል የሚደርስን ያህል ጎዳና ያኖርላቸዋል።