አልማ ፵፩
  Footnotes

  ምዕራፍ ፵፩

  በትንሣኤ ሰዎች መጨረሻ ለሌለው ደስታ ወይንም መጨረሻ ለሌለው ስቃይ ይመጣሉ—ኃጢያት በጭራሽ ደስታ ሆኖ አያውቅም—ስጋ ለባሽ ሰዎች በዓለም ሳሉ ከእግዚአብሔር ጋር አይደሉም—ማንኛውም ሰው በትንሣኤው ወቅት፣ ሟች በነበረበት ጊዜ ያገኘውን ባህሪና ፀባይ እንደገና ይቀበላል። በ፸፬ ም.ዓ. ገደማ።

  እናም እንግዲህ ልጄ፣ ስለተነገሩት ዳግሞ መመለስ በተመለከተ በመጠኑ የምለው አለኝ፤ እነሆም፣ አንዳንድ ሰዎች የቅዱሳን መፃህፍትን ትርጉም ያጣምማሉ፣ እናም በዚህ ነገር ምክንያት እጅግ ተሳስተዋል። እናም አዕምሮህ ይህንን ነገር በተመለከተ ደግሞም እንደተጨነቀ አስተውላለሁ። ነገር ግን እነሆ፣ ላንተ እገልፅልሃለሁ።

  ልጄ እንዲህ እልሃለሁ፣ የዳግሞ መመለስ ዕቅድ በእግዚአብሔር ፍትህ መሰረት አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ሁሉም ነገሮች ወደ ተገቢው ስርዓት እንዲመለሱ አስፈላጊ ነው። እነሆ፣ በክርስቶስ ኃይል እና ትንሣኤ መሰረት የሰው ነፍስ ወደ ሰውነቱ መመለሱ፣ እናም ማንኛውም የሰውነት ክፍል ወደ ቀድሞው መመለሱ አስፈላጊና ፍትህ ነው።

  እናም በእግዚአብሔር ፍርድ ሰዎች እንደስራቸው እንዲፈረድባቸው አስፈላጊ ነው፤ እናም በዚህ ህይወት ስራቸው መልካም ከሆነና፣ የልባቸው ፍላጎት መልካም ከሆነ፣ በመጨረሻው ቀን ደግሞ መልካም ወደሆነው መመለስ አለባቸው።

  እናም ስራቸው መጥፎ ከሆነ፣ በእነርሱ ላይ ለመጥፎ ይመለሱባቸዋል። ስለዚህ፣ ሁሉም ነገር ወደ ተገቢው ስርዓት ይመለሳል፣ ማንኛውም ነገር ወደ ተፈጥሮአዊው አቋም ይመለሳል—ሟች የሆነው የማይሞት በመሆን፣ የሚበሰብሰው ወደ ማይበሰብሰው—የእግዚአብሔርን መንግስት ለመውረስ መጨረሻ ወደሌለው ደስታም ይነሳሉ—አለበለዚያም የዲያብሎስን መንግስት ለመውረስ መጨረሻ ወደሌለው ስቃይ ይነሳሉ፣ አንዱ በዚህኛውም፣ ሌላው በሌላኛው—

  አንደኛው ደስታን በመፈለግ ለደስታ ይነሳል፣ ወይም ለመልካም ፍላጎቱም መልካም ሆኖ ይነሳል፣ እናም ለመጥፎ ፍላጎቱ ሌለኛው መጥፎ ሆኖ ይነሳል፤ ቀኑን በሙሉ ክፉ ማድረግ በመፈለጉ ጨለማው በሚመጣበት ጊዜ ለክፋቱ ብድራቱን ይቀበላል።

  እናም በሌላ መልኩም እንዲሁ ነው። ለኃጢአቱ ንስሃን ከገባ፣ እናም እስከ ዘመኑ ፍፃሜም ድረስ ፅድቅን ከፈለገ እንዲህ በማድረጉ የጽድቅን ዋጋ ይቀበላል።

  በጌታ የሚድኑት እነኚህ ናቸውና፤ አዎን፣ እነዚህ መጨረሻ ከሌለው የጨለማው ምሽት የወጡት፣ የተለቀቁት ናቸው፤ እናም እንደዚህም ይጸናሉ ወይም ይወድቃሉ፤ እነሆም፣ መልካምም ይሁን መጥፎ ለማድረግ በራሳቸው ላይ ፈራጅ ይሆናሉ።

  እንግዲህ፣ የእግዚአብሔር አዋጅ የሚለወጡ አይደሉም፤ ስለዚህ፣ በጌታ መንገድ ለሚራመደው መንገዱ ተዘጋጅቷል፣ በዚህ የሚራመድም ይድናል።

  እናም አሁን እነሆ ልጄ፣ ከዚህ ጊዜ በፊት ኃጢያትን በመፈፀም እንዳደረከው፣ በእነዚህ ትምህርቶች በተመለከተ በአምላክህ ላይ አንድም እንኳን በደልን አታድርግ።

  ስለዳግሞ መመለስ በመነገሩ ከኃጢያት ወደ ደስታ እመለሳለሁ ብለህ አትገምት። እነሆ እንዲህ እልሃለሁ ክፋት በፍፁም ደስታ ሆኖ አያውቅም።

  ፲፩ እናም አሁን ልጄ፣ በተፈጥሮአዊው ሁኔታ ያሉ ሰዎች በሙሉ፣ ወይንም እኔ እንደምለው በስጋ ያሉት ሁሉ፣ በመራራ መርዝና፣ በክፋት ሰንሠለት ናቸው፤ በዓለም ያለ አምላክ ናቸው፣ እናም ከእግዚአብሔር ባህርይ ጋር ተቃርነዋል፤ ስለዚህ፣ ከደስታ ባህርይ ጋርም ተቃራኒ በሚሆን ሁኔታ ውስጥ ናቸው።

  ፲፪ እናም አሁን እነሆ፣ ዳግሞ መመለስ የሚለው ቃል ትርጉሙ ነገር ከተፈጥሮአዊው ሁኔታ ወስዶ እናም ተፈጥሮአዊ ወዳልሆነ ቦታ ማስቀመጥ፣ ወይንም ከተፈጥሮአዊው ተቃራኒ የሆነውን ቦታ ማስቀመጥ ነውን?

  ፲፫ ልጄ ሆይ፣ ሁኔታው ይህ አይደለም፣ ነገር ግን የዳግሞ መመለስ የቃል ትርጉም መጥፎን ለመጥፎ፣ ስጋን ለስጋ ወይንም ዲያብሎስን ለዲያብሎስ መልሶ ማምጣት ነው—መልካም ለሆነው መልካምን፣ ፃድቅ ለሆነው ፅድቅን፤ ፍትሃዊ ለሆነው ፍትህን፤ መሃሪ ለሆነው ምህረትን ማምጣት ነው።

  ፲፬ ስለዚህ ልጄ፣ ለወንድሞችህ መሃሪ ለመሆንህ እርግጠኛ ሁን፣ ለሰዎች ፍትሃዊ ሁን፣ በትክክል ፍረድ፣ እናም ያለማቋረጥ መልካምን ስራ፤ እናም ይህንን ሁሉ የምታደርግ ከሆነ ደመወዝህን ታገኛለህ፤ አዎን፣ ምህረት በድጋሚ ይመለስልሃል፤ በድጋሚም ፍትህ ይመለስልሃል፣ በድጋሚም ጻድቃዊ ፍርድ ይመለስልሃል፣ እናም በድጋሚ መልካም ደመወዝ ታገኛለህ።

  ፲፭ የምትልከው በድጋሚ ወዳንተው ይመጣል፣ እናም ዳግሞ ይመለሳልና፤ ስለዚህ ዳግሞ መመለስ የሚባለው ቃል ኃጢአተኛውን ሙሉ በሙሉ ይፈርድበታልም፣ በምንም ዓይነት አያፀድቀውም።