አልማ ፵፬
  Footnotes

  ምዕራፍ ፵፬

  ሞሮኒ ላማናውያን ከኔፋውያን ጋር ሰላም እንዲፈጥሩ አለበለዚያም እንዲጠፉ ቃል ኪዳን እንዲገቡ አዘዘ—ዛራሄምናህ የቀረበውን ሀሳብ ተቃወመ፣ እናም ጦርነቱም ቀጠለ—የሞሮኒ ወታደሮች ላማናውያንን አሸነፉ። ከ፸፬–፸፫ ም.ዓ. ገደማ።

  እናም እንዲህ ሆነ እነርሱም አቆሙና እርምጃቸውን ፈቀቅ አሉላቸው። እናም ሞሮኒ ለዛራሄምናህ እንዲህ አለው፥ እነሆ ዛራሄምናህ፣ እኛ የደም ሰዎች መሆን አንፈልግም። እናንተ በእኛ እጅ ውስጥ መሆናችሁን ታውቃላችሁ፤ ይሁን እንጂ ልንገድላችሁ አንፈልግም።

  እነሆ፣ ለስልጣን ስንል ደማችሁን እናፈሰው ዘንድ ከእናንተ ጋር ለመዋጋት አልመጣንም፤ ወይም ማናችሁንም በባርነት ቀንበር ስር እንድናመጣችሁ አንፈልግም። ነገር ግን ይህ እናንተ በእኛ ላይ የመጣችሁበት ዋናው ምክንያት ነው፤ አዎን፣ እናም በኃይማኖታችን የተነሳም በእኛ ላይ ተቆጥታችኋል።

  ነገር ግን አሁን፣ ጌታ ከእኛ ጋር መሆኑን ተመልክታችኋል፤ እናም እናንተንም በእኛ እጅ ስር እንድትሆኑ ማድረጉን ተመልክታችኋል። እናም አሁን ይህ በኃይማኖታችንና በክርስቶስ ባለን እምነት መሆኑን እንድትገነዘቡ እፈልጋለሁ። እናም አሁን ይህንን እምነታችንን ማጥፋት እንደማትችሉ ትመለከታላችሁ።

  እንግዲህ ይህ እውነተኛ የሆነው የእግዚአብሔር እምነት መሆኑን ትመለከታላችሁ፣ አዎን በእግዚአብሔር በእርሱ፣ እናም በእምነታችንና፣ በኃይማኖታችን ታማኝ ሆነን እስከቆየን እንደሚረዳንና እንደሚጠብቀን እንዲሁም እንደሚያድነን ታያላችሁ፤ በመተላለፍ ካልወደቅን እናም እምነታችንን ካልካድን በቀር ጌታ እንድንጠፋ አይፈቅድም።

  እናም እንግዲህ፣ ዛራሄምናህ፣ በእምነታችን፣ በኃይማኖታችንና በአምልኮአችን ስርዓት፣ እናም በቤተክርስቲያናችንና ለሚስቶቻችን፣ ለልጆቻችንም በምናደርገው ቅዱስ ድጋፍ፣ ለምድራችንና ለሀገራችን ባለን የህልውና ነፃነት፣ በእናንተ ላይ ኃይል እንድናገኝ ክንዳችንን ባበረታው አዎን፣ እናም ደግሞ የእግዚአብሔርን ቅዱስ ቃል በመጠበቅ ደስታችንን ሁሉ በምናገኝበት፤ እናም ከሁሉም በላይ በእኛ ዘንድ ይበልጥ በተወደደው በኃያሉ አምላክ ስም አዝሃለሁ—

  አዎን እናም ይህ ብቻም አይደለም፤ ለህይወት ባላችሁ ፍላጎቶች ሁሉ እንዲህ ስል አዛችኋለሁ፤ የጦር መሳሪያዎቻችሁን ሁሉ ለእኛ አስረክቡን፣ እናም እኛ የእናንተን ደም አንፈልግም፣ ነገር ግን ተመልሳችሁ ከሄዳችሁና ለጦርነት በእኛ ላይ ዳግም ካልመጣችሁ ህይወታችሁን እናተርፍላችኋለን።

  እናም አሁን፣ ይህንን ካላደረጋችሁ፣ እነሆ በእጃችን ናችሁ፣ እናም ህዝቤን እናንተን እንዲያጠቁና፣ ከምድረ ገፅ እስከምትጠፉ በሰውነታችሁ በሞት ቁስል እንዲያቁስሏችሁ አዛለሁ፤ ከዚያም በዚህ ህዝብ ላይ ማን ኃይል እንደሚኖረው እንመለከታለን፤ አዎን፣ ወደባርነት የሚመጣው ማን እንደሆነም እንመለከታለን።

  እናም አሁን እንዲህ ሆነ ዛራሄምናህ ይህንን አነጋገር በሰማ ጊዜ መጣና፣ ጎራዴውንም፣ ሻምላውንም፣ እና ቀስቱን፣ ለሞሮኒ በእጁ ሰጠውና፣ እንዲህ ሲል ተናገረው፥ የጦር መሳሪያዎቻችን እነሆ፣ መሳሪያዎቹን በሙሉ እንሰጣችኋለን፣ ነገር ግን እኛም ሆንን ልጆቻችን ልናፈርሰው እንደምንችል ስለምናውቅ መሃላ ልንወስድ አንፈቅድም፤ ነገር ግን የጦር መሳሪያዎቻችንን ውሰዱ፣ እናም ወደ ምድረበዳው እንድንሄድ ዘንድ ፍቀዱልን፤ አለበለዚያ ግን ጎራዴዎቻችንን መልሰን እንይዛለንና እንጠፋለን ወይንም እናሸንፋለን።

  እነሆ፣ የእኛ የእናንተ እምነት አባል አይደለንም፤ እግዚአብሔርም በእናንተ እጅ እንድንወድቅ እንዳደረገን አናምንም፤ ነገር ግን ብልጠታችሁ ከጎራዴያችን እንደጠበቃችሁ እናምናለን። እነሆ፣ የደረት ኪሶቻችሁ እና ጋሻዎቻችሁ ጠብቀዋችኋል።

  እናም አሁን ዛራሄምናህ ንግግሩን እንደጨረሰ፣ ሞሮኒ የተቀበለውን ጎራዴና የጦር መሳሪያዎች ወደ ዛራሄምናህ በመመለስ እንዲህ ሲል ተናገረ፥ እነሆ፣ ጦርነቱን እንፈፅማለን።

  ፲፩ እንግዲህ የተናገርኳቸውን ቃላት መልሼ ልወስድ አልችልም፤ ስለዚህ ጌታ ህያው እንደሆነ፣ ለጦርነት በድጋሚ እንዳትመለሱ በመሃላው ካልሄዳችሁ በቀር አትሄዱም። እናም በእጃችን ስለሆናችሁ ደማችሁን በመሬት ላይ እናፈሰዋለን፣ ወይንም ያቀረብኳቸውን ሀሳቦች ትቀበላላችሁ።

  ፲፪ እናም እንግዲህ ሞሮኒ እነዚህን ቃላት በተናገረ ጊዜ፣ ዛራሄምናህ ጎራዴውን መልሶ ያዘና፣ በሞሮኒ ተቆጥቶ ነበር፣ ሞሮኒንም ይገድለው ዘንድ ወደ እርሱ ዘንድ ሮጠ፤ ነገር ግን ጎራዴውን ባነሳ ጊዜ፣ እነሆ፣ ከሞሮኒ ወታደሮች አንዱ መታውና በመሬት ላይ ወደቀና፣ በእጀታው ተሰበረ፤ እናም ደግሞ የዛራሄምናህን አናት መትቶ ገሸለጠውና በመሬት ላይ ወደቀ። እናም ዛራሄምናህ ከእነርሱ ፊት ወደ ወታደሮቹ መካከል ሸሸ።

  ፲፫ እናም እንዲህ ሆነ በአጠገቡ ቆሞ የነበረው፣ የዛራሄምናህን አናት የገሸለጠው፣ ቆቡን ከፀጉሩ ጋር ከመሬት ላይ አነሳውና፣ በጎራዴው ጫፍ ላይ አስቀመጠው፣ እናም ወደእነርሱም ከፍ አድርጎ በማሳየት በኃይል እንዲህ ሲል ጮኸ፥

  ፲፬ ይህ የአለቃችሁ ቆብ የሆነው በመሬት ላይ እንደወደቀ፣ የጦር መሳሪያዎቻችሁን ካልሰጣችሁን እናም በሰላም ለመሄድ ቃል ኪዳን ካልገባችሁ በቀር እንዲሁ በመሬት ላይ ትወድቃላችሁ።

  ፲፭ እንግዲህ ብዙዎች እነኚህን ቃላት በሰሙበት ጊዜ እናም በጎራዴው ላይ የነበረውን ቆብም በተመለከቱ ጊዜ በፍርሃት ተሞሉ፤ እናም ብዙዎች መጡና፣ የጦር መሳሪያዎቻቸውን በሞሮኒ እግር ስር ጣሉት፣ የሰላም ቃል ኪዳንን ገቡም። እናም ቃል ኪዳን የገቡት ሁሉ ወደ ምድረበዳው እንዲሄዱ ፈቀዱላቸው።

  ፲፮ እንግዲህ እንዲህ ሆነ ዛራሄምናህ እጅግ ተናደደ፣ እናም ቀሪዎቹ ወታደሮቹ ከኔፋውያን ጋር በኃይል እንዲጣሉ በቁጣ አነሳሳቸው።

  ፲፯ እናም እንግዲህ ሞሮኒ በላማናውያን ግትርነት የተነሳ ተቆጥቶ ነበር፤ ስለዚህ ህዝቡ እንዲወጉአቸውና እንዲገድላቸው አዘዘ። እናም እንዲህ ሆነ እነርሱን መግደል ጀመሩ፤ አዎን እናም ላማናውያን በጎራዴዎቻቸውና በኃይላቸው ተዋጉ።

  ፲፰ ነገር ግን እነሆ፣ የላማናውያን ባዶ ሰውነትና፣ ባዶ ራሶቻቸው ለኔፋውያን የሰሉ ጎራዴዎች ተጋልጠው ነበር፤ አዎን እነሆ ተበሳስተውና ተመትተው ነበር፣ አዎን፣ እናም በኔፋውያን ጎራዴዎችም ፊት በፍጥነት ይወድቁ ነበር፤ እናም የሞሮኒ ወታደር እንደተነበየም መወገድ ጀምረው ነበር።

  ፲፱ እንግዲህ ዛራሄምናህ፣ እነርሱ በሙሉ ሊጠፉ መቃረባቸውን በተመለከተ ጊዜ፣ ቀሪውን ህይወታቸውን የሚያተርፉት ከሆነ፣ በድጋሚ ለጦርነት ወደ እነርሱ በጭራሽ እንደማይመጡ፣ እርሱ እናም ደግሞ ህዝቡ ቃል ኪዳን እንደሚገቡ ለሞሮኒ በኃይል በመጮህ ቃል ገባ።

  እናም እንዲህ ሆነ ሞሮኒ የሞት ስራ በህዝቡ መካከል በድጋሚ እንዲቆም አደረገ። የጦር መሳሪያዎችንም ከላማናውያን ወሰደ፤ እናም ለሰላም ቃል ኪዳን ከእርሱ ጋር ከገቡ በኋላ ወደ ምድረበዳው እንዲሄዱ ተፈቅዶላቸው ነበር።

  ፳፩ እንግዲህ የሞቱባቸው ቁጥር ብዙ በመሆኑ ሊቆጠር አይችልም ነበር፤ አዎን በኔፋውያንም ሆነ በላማናውያን በኩል የሟቾቹ ቁጥር እጅግ ብዙ ነበር።

  ፳፪ እናም እንዲህ ሆነ የሞቱባቸውን ወደ ሲዶም ወንዝ ጣሉአቸው፤ እናም ተወስደውና በባህሩ ጥልቅ ውስጥ ተቀብረው ነበር።

  ፳፫ እናም የኔፋውያንም ሆኑ የሞሮኒ ሠራዊት ተመለሱ፣ እናም ወደ ቤታቸውና ወደ ምድራቸው መጡ።

  ፳፬ እናም በኔፋውያን ላይ አስራ ስምንተኛው ዓመት የመሣፍንት አገዛዝ በዚሁ ተፈፀመ። እናም በኔፊ ሰሌዳዎች ላይ የተፃፈው የአልማ ምዝገባም ተጠናቀቀ።