ቅዱሳት መጻህፍት
አልማ ፴፱


አልማ ለልጁ ቆሪያንቶን የሰጠው ትዕዛዛት።

ከምዕራፍ ፴፱ እስከ ፵፪ አጠቃሎ የያዘ።

ምዕራፍ ፴፱

የፍትህወት ኃጢያት እርኩሰት ነው—የቆሪያንቶን ኃጢያት ዞራማውያንን ቃሉን ከመቀበል አገዳቸው—የክርስቶስ ቤዛነት በፊት የነበሩትን ታማኞች ለማዳን ወደኋላ ተመልሶ የሚሠራ ነው። በ፸፬ ም.ዓ. ገደማ።

እናም እንግዲህ ልጄ፣ ለወንድምህ ከተናገርኩት የበለጠ ለአንተ በመጠኑ የምናገረው አለኝ፤ እነሆ፣ የወንድምህን ፅኑነት፣ ታማኝነት እናም የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት በመጠበቅ ትጋቱን አልተመለከትህምን? እነሆ፣ ለአንተስ ጥሩ ምሳሌ አልሆነምን?

አንተ ግን በዞራማውያን ሰዎች መካከል ወንድምህ እንዳደረገው ለቃላቴ ጆሮህን አልሰጠኸኝም። እንግዲህ ይህ እኔ ከአንተ የምቃረንበት ነው፤ አንተም በጉልበትህ እና በጥበብህ እየኮራህ ሄደህ ነበር።

እንግዲህ ልጄ ይህ ብቻም አይደለም። ለእኔ የሚያሳዝነኝን አድርገሃል፤ ምክንያቱም አገልግሎቱን ጥለህ ሄደሃል፣ እናም በላማናውያን ምድር ዳርቻም ጋለሞታዋን ኢሳቤልን ተከትለህ ወደ ሲሮን ምድር ሄደሃል።

አዎን፣ እርሷም የብዙዎቹን ልብ ሰርቃለች፤ ነገር ግን ልጄ ይህ ለአንተ የምታመካኝበት አይሆንም። በአደራ ለተሰጠህም ለአገልግሎቱ ታማኝ መሆን ነበረብህ።

ልጄ እነዚህ ነገሮች በጌታ አመለካከት የረከሱ እንደሆኑ፤ አዎን፣ የንፁሃንን ደም ከማፍሰስ ወይንም መንፈስ ቅዱስን ከመካድ በቀር ከሌሎች ኃጢአቶች ሁሉ ይበልጥ አስከፊ መሆናቸውን አታውቅምን?

እነሆም፣ በአንተ ውስጥ ስፍራ የነበረውን መንፈስ ቅዱስን የምትክድ ከሆነ፤ እናም እንደካድከው ካወቅህ፤ እነሆ፣ ይህ ይቅር የማይባል ኃጢያት ነው፤ አዎን፣ እናም ማንም ከእግዚአብሔር ብርሃንና እውቀት ተቃራኒ በመሆን የገደለ፤ ለእርሱም ይቅርታን ማግኘት ቀላል አይደለም፤ አዎን ልጄ እንዲህ እልሃለሁ፣ ለእንደዚህ ዓይነቱ ሰው ይህን ይቅርታን ማግኘት ቀላል አይደለም።

እናም አሁን ልጄ፣ እንደዚህ አይነት በሆኑ ወንጀሎች ጥፋተኛ እንዳልሆንክ ምኞቴ ነበር። ለአንተ መልካም ባይሆን ኖሮ ነፍስህን ለማሰቃየት ስለወንጀልህ በመናገር አልቀጥልም።

ነገር ግን እነሆ፣ ወንጀልህን ከእግዚአብሔር ለመደበቅ አትችልም፤ እናም ንስሃ ካልገባህ በመጨረሻው ቀን በአንተ ላይ ለምስክርነት ይቆማሉ።

እንግዲህ ልጄ፣ ለኃጢያትህ ንስሃ መግባትና መተው፣ እናም በዓይንህ ምኞት ከእንግዲህ እንዳትጓዝ እፈልጋለሁ፤ ነገር ግን እነዚህን ነገሮች ሁሉ አስወግድ፤ ይህንን ካላደረግህ በምንም ዓይነት የእግዚአብሔርን መንግስት ልትወርስ አትችልምና። አቤቱ፣ አስታውስ፣ እናም በእራስህ ውሰደው፣ ከእነዚህም ነገሮች ራስህን አስወግድ።

እናም በድርጊቶችህ ከታላላቅ ወንድሞችህ ጋር እንድትመካከር አዝሃለሁ፤ እነሆም አንተ ወጣት ነህና፣ በወንድሞችህ እንክብካቤን ያስፈልግሀል። እናም ምክራቸውን አድምጥ።

፲፩ በከንቱ ወይንም በማይረባ ነገር እንድትመራ አታድርግ፤ በኃጢአተኞች ጋለሞታዎች በድጋሚ ዲያብሎስ ልብህን እንዲያስተው አትፍቀድለት። እነሆ ልጄ ሆይ፣ በዞራማውያን ላይ እንዴት ያለ ታላቅ ክፋትን አምጥተሃል፤ የአንተን ፀባይ በተመለከቱ ጊዜም ቃሌን አላመኑትምና።

፲፪ እናም አሁን የጌታ መንፈስ እንዲህ ሲል ተናገረኝ፥ የብዙ ሰዎችን ልብ ወደጥፋት እንዳይመሩ ልጆችህን መልካም እንዲያደርጉ እዘዛቸው፤ ስለዚህ ልጄ፣ እግዚአብሔርን በመፍራት ከጥፋቶችህ እንድትቆጠብ አዝሃለሁ፤

፲፫ በሙሉ አዕምሮህ፣ ኃይልህ፣ እናም ጉልበትህ ወደ ጌታ እንድትመለስ፤ ከእንግዲህ የማንንም ልብ ወደ ክፋት እንዳትመራም፤ ነገር ግን ወደ እነርሱ እንድትመልሳቸው፣ እናም ጥፋትህንና የሰራኸውን ስህተት እንድትቀበል አዝሀለሁ።

፲፬ ሀብትን እንዲሁም የዚህን ዓለም ከንቱ ነገሮች አትፈልግ፤ እነሆም፣ ከአንተም ጋር ይዘሀቸው ለመሄድ አትችልም።

፲፭ እናም አሁን ልጄ፣ ስለክርስቶስ መምጣት በመጠኑ እነግርሃለሁ። እነሆ፣ እርሱ ነው በእርግጥ የዓለምን ኃጢያት ሊወስድ የሚመጣው፤ አዎን፣ ለዚህ ህዝብ የደህንነትን የምስራች ዜና ለማወጅ ይመጣል።

፲፮ እናም እንግዲህ ልጄ፣ ለዚህ አገልግሎት የተጠራኸው አዕምሮአቸውን ለማዘጋጀት፣ ወይም ደህንነት ይመጣለት ዘንድ፣ በሚመጣበት ጊዜም ቃሉን እንዲሰሙ የልጆቻቸውን አዕምሮ እንዲያዘጋጁ ለህዝቡ የምስራቹን ዜና እንድትናገር ነበር።

፲፯ እናም እንግዲህ በዚህ ጉዳይ ጭንቀትህን አቀልልሃለሁ። እነሆ፣ እነዚህ ነገሮች አስቀድመው ለምን እንዲታወቁ ተደረጉ ብለህ ትገረማለህ። እነሆ እንዲህ እልሃለሁ፤ በዚህን ጊዜ ያለው ነፍስ በክርስቶስ መምጫ ጊዜ እንደሚኖረው ነፍስ ለእግዚአብሔር ውድ የሆነ አይደለምን?

፲፰ የቤዛነት ዕቅድ ለዚህ ህዝብ እናም ለልጆቻቸው እንዲያውቁት መደረጉ አስፈላጊ አይደለምን?

፲፱ ጌታ መላዕክቱን ለልጆቻችን፣ ወይም እርሱ ከመጣበት ጊዜ በኋላ፣ እነዚህን የምስራቹን ዜና ያውጅ ዘንድ ለመናገር መላኩ፣ ወደ እኛም ለመላክ የሚቀለው አይደለምን?