አልማ ፲፮
  Footnotes

  ምዕራፍ ፲፮

  ላማናውያን የአሞኒሀን ህዝብ አጠፉ—ዞራም ኔፋውያን ላማናውያንን ድል እንዲያደርጉ መራቸው—አልማና አሙሌቅ እናም ሌሎች ብዙዎች ቃልን ሰበኩ—ከትንሣኤው በኋላም ክርስቶስ ለኔፋውያን እንደሚገለፅ አስተማሩአቸው። ከ፹፩–፸፯ ም.ዓ. ገደማ።

  እናም እንዲህ ሆነ በኔፋውያን ላይ በመሣፍንቱ አስራ አንደኛ ዓመት የንግስ ዘመን፣ በሁለተኛው ወር አስራ አምስተኛ ቀን፣ በዛራሔምላ ታላቅ ሰላም ሆነ፣ ጦርነትም ይሁን ፀብ ለተወሰኑ ዓመታት፣ እንዲሁም እስከ አስራ አንደኛው ዓመት በሁለተኛው ወር እስከ አምስተኛው ቀን ድረስ እንኳን አልነበረም፣ በምድሪቱ ላይ ሁሉ የጦርነት ጩኸትተሰማ።

  እነሆም፣ የላማናውያን ወታደሮች በምድረበዳው በኩል በምድሪቱ ዳርቻ ወደ አሞኒሀ ከተማ ሄዱ፣ እናም ህዝቡን መግደል ከተማዋንም ማጥፋት ጀመሩ።

  እናም አሁን እንዲህ ሆነ፣ ኔፋውያን እነርሱን ከምድሪቱ ለማስወጣት በቂ ወታደሮችን ከመመልመላቸው በፊት፣ በአሞኒሀ ከተማ ያሉትንና ደግሞ ጥቂት በኖህ ዳርቻ ዙሪያ ያሉትን ሰዎች አጠፉአቸው፣ እናም ሌሎችን በምርኮኛነት ወደ ምድረበዳው ወሰዱአቸው።

  አሁን እንዲህ ሆነ ኔፋውያን ወደ ምድረበዳው በምርኮ የተወሰዱትን ለማግኘት ፈለጉ።

  ስለዚህ፣ በኔፋውያን ወታደሮች ላይ ዋና ሻምበል ሆኖ የተሾመው (ዞራም ተብሎ የሚጠራው፣ እናም ሌሂና አሃ የተባሉ ሁለት ወንድ ልጆች ያሉት)—አሁን ዞራምና ሁለቱ ወንድ ልጆቹ አልማ በቤተክርስቲያኗ ላይ ሊቀ ካህን መሆኑን በማወቃቸው፣ እናም የትንቢት መንፈስ እንዳለው በመስማታቸው፤ ስለዚህ ጌታ በላማናውያን በምርኮ የተወሰዱባቸውን ወንድሞቻቸውን ለመፈለግ ወደ ምድረበዳው የት መሄድ እንዳለባቸው ለማወቅ ወደ እርሱ ሄዱ።

  እናም እንዲህ ሆነ አልማ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ጌታን ጠየቀ። እናም አልማ ተመለሰና እንዲህ አላቸው፥ እነሆ፣ ላማናውያን በምድረበዳው በስተደቡብ በማንቲ ምድር ዳርቻ ራቅ ብሎ የሲዶምን ወንዝ ያቋርጣሉ። እናም እነሆ በሲዶም ወንዝ በስተምስራቅ ከእነርሱ ጋር ትገናኛላችሁ፣ እናም በላማናውያን በምርኮ የተወሰዱትን ወንድሞቻችሁን ጌታ ለእናንተ ይሰጣችኋል።

  እናም እንዲህ ሆነ ዞራምና ወንድ ልጆቹ ከወታደሮቻቸው ጋር የሲዶምን ወንዝ አቋረጡ፣ እናም በማንቲ ዳርቻ በምድረበዳው በስተደቡብ በኩል፣ በሲዶም ወንዝ በስተምስራቅ ዘመቱ።

  እናም በላማናውያን ወታደሮች ላይ መጡባቸው፣ እናም ላማናውያን ተበታተኑና ወደ ምድረበዳው ሸሹ፤ እናም በላማናውያን የተማረኩ ወንድሞቻቸውን ወሰዱና፣ በምርኮ ከተወሰዱት ውስጥ አንድም ነፍስ አልሞተባቸውም ነበር። እናም በወንድሞቻቸው ምድራቸውን ሊወርሱ ዘንድ ተወሰዱ።

  እናም የመሣፍንቱ አስራ አንደኛ ዓመት እንደዚህ ተፈፀመ፤ ላማናውያን ከምድሪቱ ወጡና፣ የአሞኒሀውያን ህዝቦችም ጠፉ፤ አዎን፣ በህይወት የነበሩ አሞናውያን ሁሉ፣ እናም ደግሞ በታላቅነቷ የተነሳ እግዚአብሔር ሊያጠፋት አይቻለውም የተባለላት ታላቋ ከተማቸውም ጠፋች

  ነገር ግን እነሆ፣ በአንድ ቀን ባዶ ሆነች፤ እናም ሬሳዎች በምድረበዳው ውሾችና በዱር አውሬዎች ተቆራረጡ።

  ፲፩ ይሁን እንጂ፣ ከብዙ ቀናት በኋላ ሬሳዎቻቸው በምድሪቱ ላይ ተቆለሉና፣ ጥልቅ ባልሆነ ሽፋን ተሸፈኑ። እናም እንዲሁም ሽታው በማየሉ ህዝቡ ለብዙ ዘመናት የአሞኒያህን ምድር ለመያዝ አልገቡም ነበር። ይህም የኔሆራውያን መውደም ተብሎ ይጠራ ነበር፤ የተገደሉት የኔሆርን ኃይማኖት ተከታዮች ነበሩና፣ እናም ምድራቸው ባዶ ሆና ቀረች።

  ፲፪ እናም መሣፍንቱ በኔፊ ህዝቦች ላይ እስከሚነግሱበት አስራ አራተኛ ዓመት ድረስ ላማናውያን በኔፊ ህዝቦች ላይ ለጦርነት አልመጡም። እናም ለሶስት ዓመታት የኔፊ ህዝብ በምድሪቱ ላይ የማያቋርጥ ሰላምን አገኙ።

  ፲፫ እናም አልማና አሙሌቅ ለህዝቡ ስለንስሃ ለመስበክ በቤተመቅደሶቻቸው፣ እናም ደግሞ በቅዱስ ሥፍራዎቻቸው፣ እናም ደግሞ በአይሁድ ስርዓት በተገነቡት ምኩራቦቻቸው ሄዱ።

  ፲፬ እናም ቃላቸውን ላዳመጡአቸው ሁሉ፣ ያለማዳላት ሳያቋርጡ የእግዚአብሔርን ቃል አካፈሉአቸው።

  ፲፭ እናም አልማና አሙሌቅ፣ ደግሞም ከዚህ የበለጡ ለስራው የተመረጡ ብዙዎች በምድሪቱ ላይ ቃሉን ለመስበክ ሄዱ። እናም ቤተክርስቲያኗ በምድሪቱ ላይ በዙሪያው በኔፋውያን ሁሉ መካከል ተቋቋመች።

  ፲፮ እናም በእነርሱ መካከል ምንም ዓይነት እኩል ያልሆነ አልነበረም፤ ጌታ የሰው ልጆችን አዕምሮ ለማዘጋጀት እንዲሁም በመምጫው ጊዜ በእነርሱ መካከል የሚሰበከውን ቃል ለመቀበል ልባቸውን እንዲያዘጋጁ በምድሪቱ ላይ ሁሉ መንፈሱን አፈሰሰ—

  ፲፯ በቃሉ ላይ ልባቸውን እንዳያጠጥሩ፣ የማያምኑ እንዳይሆኑ፣ እናም ወደ ጥፋት እንዳይሄዱ፣ ነገር ግን ቃሉን በደስታ ይቀበሉት ዘንድ እናም ቅርንጫፉ ወደ እውነተኛው ወይን እንዲዳቀሉ ዘንድ፣ እነርሱም ወደ ጌታ አምላካቸው እረፍት ይገቡ ዘንድ ነው።

  ፲፰ አሁን ውሸቶችንም፣ ማታለልንምቅናትንም፣ ጠብንም፣ ተንኮልንም፣ ስድብንም፣ ስርቆትንም፣ ዝርፊያንም፣ መቀናትንም፣ ግድያንም፣ ዝሙት መፈፀምንም፣ እናም ሁሉም አይነት ምንዝርናን እንዲያስወግዱ ከህዝቡ መካከል የሰበኩት እነዚያ ካህናት፣ እነዚህ ነገሮች እንዳይሆኑ ጮሁ—

  ፲፱ በቅርብ የሚመጡትን ነገሮች ካህናቱ በማወጅ፤ አዎን፣ የእግዚአብሔርን ልጅ መምጣት፣ ስቃዩንና ሞቱን፣ እናም ደግሞ ከሙታን መነሳቱን በማወጅ ጮሁ።

  እናም ብዙዎች የእግዚአብሔር ልጅ የሚመጣበትን ስፍራ በተመለከተ ጠየቁ፤ እርሱም ከትንሣኤው በኋላ እንደሚገለጥላቸው ተምረው ነበር፤ እናም ህዝቡ ይህንን ያዳመጠው በታላቅ ሀሴትና ደስታ ነበር።

  ፳፩ እናም አሁን ቤተክርስቲያኗ በምድሪቱ ላይ ከተመሰረተች በኋላ—በዲያብሎስ ላይ ድል ካገኘች፣ እናም በንፅህና በምድሪቱ ላይ የጌታ ቃል አንድ ላይ ከተሰበከ በኋላ፣ እናም ጌታ በህዝቡ ላይ በረከትን አፈሰሰ—በኔፊ ህዝብ ላይ አስራ አራተኛው የመሣፍንት የንግስ ዘመን በዚሁ ተፈፀመ።