አልማ ፶፩
  Footnotes

  ምዕራፍ ፶፩

  የንጉሱ የሆኑትን ሰዎች ህጉን ለመለወጥ እናም ንጉሥን ለመምረጥ ፈለጉ—ፓሆራን እናም የነበረውን መንግስት የሚደግፉት በህዝቡ ድምፅ ተደግፈው ነበር—ሞሮኒ የንጉሱ የሆኑትን ሰዎች ሀገራቸውን እንዲከላከሉ አለበለዚያም እንዲገደሉ አስገደዳቸው—አማሊቅያ እናም ላማናውያን ብዙ የተመሸጉ ከተማዎችን ያዙ—ቴአንኩም የላማናውያንን ወረራ መለሰ እናም አማሊቅያን በድንኳኑ ውስጥ ገደለው። ከ፷፯–፷፮ ም.ዓ. ገደማ።

  እናም እንግዲህ እንዲህ ሆነ በኔፊ ህዝብ ላይ በመሣፍንቱ ሀያ አምስተኛ ዓመት የንግስና ዘመን መሬታቸውን በተመለከተ በሌሂና በሞሪያንተን ህዝብ መካከል ሰላምን መሰረቱ፣ እናም ሀያ አምስተኛውን ዓመት በሰላም ጀመሩ፤

  ይሁን እንጂ፣ የኔፊ ህዝብ በምድሪቱ በሙሉ ለረጅም ጊዜ ሰላምን ማቆየት አልቻሉም፣ ምክንያቱም ዋናውን ዳኛ ፓሆራንን በተመለከተ በህዝቡ መካከል ፀብ ተጀመረ፤ እነሆ፣ ከህዝቡ የተወሰነው ክፍል በህጉ ጥቂት ነጥቦች እንዲለወጡ ፈልገው ነበርና።

  ነገር ግን እነሆ፣ ፓሆራን ህጉን አልለወጠም፣ እንዲለወጥም አልፈቀደም ነበር፤ ስለዚህ፣ የህጉን መለወጥ በተመለከተ ከአቤቱታቸው ጋር ድምፃቸውን የላኩትንም አላዳመጣቸውም ነበር።

  ስለዚህ፣ ህጉ እንዲለወጥ የፈለጉት በእርሱ ተቆጥተው ነበር፤ እናም በምድሪቱ ላይ ከእንግዲህ ዋና ዳኛ እንዲሆን አልፈለጉም፤ ስለዚህ ይህንን በተመለከተ የጋለ ፀብ ተነሳ፣ ነገር ግን እስከ ደም መፋሰስ አልነበረም።

  እናም እንዲህ ሆነ ፓሆራን ከፍርድ ወንበር ዙፋን እንዲወርድ ፈልገው የነበሩት የንጉሱ ሰዎች ተብለው ይጠሩ ነበር፤ ምክንያቱም ህጉ ነፃ መንግስቱን በመጣል እናም ምድሪቱም በንጉስ እንዲገዛ ፈልገው ነበር።

  እናም ፓሆራን በምድሪቱ ላይ ዋና ዳኛ ሆኖ እንዲቀር የሚፈልጉ ለራሳቸው ነፃ ሰዎች የሚለውን ስም ወስደው ነበር፤ እናም እንደዚህ በመካከላቸው ክፍፍል ነበር፣ ምክንያቱም ነፃ ሰዎቹ መብታቸውንና፣ በነፃው መንግስት የኃይማኖታቸውን ነፃነት ለመጠበቅ መሀላ እንዲሁም ቃል ኪዳን ገብተው ነበርና።

  እናም እንዲህ ሆነ እንዲህ ዓይነቱ ፀብ በህዝቡ ድጋፍ መልስ አግኝቶ ነበር። እናም እንዲህ ሆነ የህዝቡ ድምፅ የነፃ ሰዎችን ደገፈና፣ ፓሆራን የፍርድ ወንበር ያዘ፣ ይህም በፓሆራን ወንድሞች እናም በነፃነት ሰዎች መካከል ታላቅ ደስታን ፈጠረ፤ ደግሞም ብዙዎቹ የነፃነት ሰዎች ንጉሳዊ የሆነውን ስርዓት እንዳይቃወሙ፣ ነገር ግን የነፃነቱን መንስኤ እንዲከላከሉ ተገደው ነበር።

  እንግዲህ ንጉሶቹን ይደግፉ የነበሩት፣ በትውልድ ታላቅ ስፍራ የነበራቸው፤ እናም ንጉስ ለመሆንም የፈለጉ ነበሩ፤ እናም ኃይልንና ስልጣንን በህዝቡ ላይ በሚፈልጉትም ይደገፉ ነበር።

  ነገር ግን እነሆ፣ ይህ በኔፊ ህዝብ መካከል እንደዚህ ዓይነቱ ፀብ ወሳኝ የሆነበት ጊዜ ነበር፤ ምክንያቱም እነሆ፣ አማሊቅያ የላማናውያን ሰዎችን ልብ በኔፊ ህዝብ ላይ በድጋሚ አነሳስቶ ነበር፤ እናም ከምድሪቱ ከሁሉም ክፍል ወታደሮችን በአንድ ላይ ሰበሰበና፣ አስታጠቃቸው፣ እናም በሙሉ ትጋቱ ለጦርነት አዘጋጃቸው፤ ምክንያቱም የሞሮኒን ደም ለመጠጣት ምሎ ነበርና።

  ነገር ግን እነሆ፣ እርሱ የገባው ቃል ኪዳን የተጣደፈ መሆኑን እንመለከታለን፤ ይሁን እንጂ እራሱን እና ወታደሮቹን ከኔፋውያን ጋር ለመዋጋት አዘጋጀ።

  ፲፩ አሁን የእርሱ ወታደሮች ከዚህ ቀደም እንደነበሩት ታላቅ አልነበሩም፣ ምክንያቱም ብዙ ሺዎች በኔፋውያን ተገድለው ነበርና፤ ነገር ግን ታላቅ ውድቀት ቢደርስባቸውም፣ አማሊቅያ ወደ ዛራሔምላ ምድር ለመምጣት የማይፈራ እስከሚሆን ድረስ፣ በሚያስገርም ሁኔታ ብዙ ወታደሮችን በአንድነት ሰብስቦ ነበር።

  ፲፪ አዎን፣ አማሊቅያም ቢሆን ራሱ ላማናውያንን በመምራት መጥቶ ነበር። እናም ይህም የነበረው በመሣፍንቱ የሀያ አምስተኛ ዓመት የንግስና ዘመን ነበር፤ እናም በዚሁ ጊዜ ነበር ኔፋውያን ዋና ዳኛ የነበረውን ፓሆራንን በተመለከተ ለፀባቸው መፍትሔ መፈለግ የጀመሩት።

  ፲፫ እናም እንዲህ ሆነ የንጉሱ ሰዎች ተብለው የሚጠሩት ሰዎች ላማናውያን ከእነርሱ ጋር ለመዋጋት መምጣታቸውን በሰሙ ጊዜ በልባቸው ተደስተው ነበር፤ እናም በዋናው ዳኛና፣ ደግሞ በነፃነቱ ሰዎች፣ እጅግ በመቆጣታቸው የጦር መሳሪያቸውን ለማንሳት አልፈቀዱም፣ ሀገራቸውንም ለመከላከል የጦር መሳሪያዎችን አላነሱም ነበር።

  ፲፬ እናም እንዲህ ሆነ ሞሮኒ ይህንን፣ እናም ደግሞ በምድሪቱ ዳርቻ ላማናውያን መምጣታቸውን በተመለከተ ጊዜ፣ እነርሱን ለመጠበቅ በታላቅ ትጋት ከእርሱ ጋር አብረው የሰሩት ሰዎች ግትር በመሆናቸው እጅግ ተቆጥቶ ነበር፤ አዎን፣ በእጅግ ተቆጥቶ ነበር፤ ነፍሱም በእነርሱ ላይ በቁጣ ተሞልታ ነበር።

  ፲፭ እናም እንዲህ ሆነ ሞሮኒ ወደ ምድሪቱ ገዢ እንዲያነበው የፈለገውን፣ እናም ሀገራቸውን ለመከላከል የሚቃወሙትን እንዲያስገድድ፣ አለበለዚያም እንዲገድላቸው ለእርሱ (ለሞሮኒ) ስልጣንን እንዲሰጠው ከህዝቡ ድጋፍ ጋር አቤቱታውን ላከ።

  ፲፮ በህዝቡ መካከል እንደዚህ ዓይነቱን ፀብና ተቃውሞ ማቆም የእርሱ የመጀመሪያው ጥንቃቄ ነበር፤ እነሆ ይህ ከዚህ ቀደም የጥፋታቸው ሁሉ መንስኤ ስለነበር ነው። እናም እንዲህ ሆነ በህዝቡም ድምፅ የተነሳ ይህ ተፈቅዶ ነበር።

  ፲፯ እናም እንዲህ ሆነ ሞሮኒ የንጉሱን ሰዎች፣ ትምክህታቸውንና፣ ክብራቸውን እንዲያጠፉ፣ እናም እንዲገድሉአቸው፣ አለበለዚያም የጦር መሳሪያዎቻቸውን እንዲወስዱና፣ ነፃነታቸውን እንዲደግፉ እንዲያደርጉ ወታደሮቹን አዘዛቸው።

  ፲፰ እናም እንዲህ ሆነ ሠራዊቱ በሰዎቹ ላይ ዘመቱ፤ እናም እነርሱ ትምክህታቸውንና ክብራቸውን እንደዚህ ያህል ገፈፉባቸው፣ ከሞሮኒ ሰዎች ጋር ለመዋጋት የጦር መሳሪያዎቻቸውን ሲያነሱ በጎራዴዎቻቸው ድባቅ ተመቱና ተገደሉ።

  ፲፱ እናም እንዲህ ሆነ ከተቃዋሚዎቹ አራት ሺህ የሚሆኑት በጎራዴው ተመትተው ነበር፤ እናም በጦርነቱ ያልተገደሉት መሪዎቻቸውን በዚህን ጊዜ እነርሱን ለፍርድ ለማቅረብ ጊዜ ባለመኖሩ ተወስደውና ወደ ወህኒ ቤቱ ተጣሉ።

  እናም ከተቃዋሚዎቹ የተቀሩት፣ በጎራዴ ተመትተው ከተገደሉት ይልቅ፣ የነፃነት አርማን ደገፉ፣ እናም በምሶሶዎቻቸው ላይና፣ በከተሞቻቸው ላይ የነፃነት አርማቸውን እንዲሰቅሉና፣ ሀገራቸውን ለመከላከል የጦር መሳሪያዎቻቸውን እንዲያነሱ ተገደዱ።

  ፳፩ እናም የንጉሱ ሰዎች ተብለው በመጠራት ዳግም እንዳይታወቁ ሞሮኒ የንጉሱ ሰዎች የሆኑትን ፍፃሜ አደረገ፤ እናም የልዑልነት ደም አለን በሚሉት ትምክህተኛና ግትር ሰዎች ላይ እንደዚህ መጨረሻቸውን አደረገ፤ ነገር ግን እንደ ወንድሞቻቸው እራሳቸውን ትሁት ማድረግና፣ ከባርነት ለመላቀቅ በጀግንነት እንዲዋጉ አደረጋቸው።

  ፳፪ እነሆ፣ እንዲህ ሆነ ሞሮኒ በህዝቡ መካከል ጦርነቱ፣ እናም ፀቡ እንዲቆምና፣ ህዝቡ ለሰላምና ለስልጣኔ ባስገደደ፣ እናም ከላማናውያን ጋር ለመዋጋት እንዲዘጋጁ ህጎችን ባዘጋጀ ጊዜ፣ እነሆ፣ ላማናውያን በባህሩ ዳርቻ ወደሞሮኒ ምድር መጥተው ነበር።

  ፳፫ እናም እንዲህ ሆነ ኔፋውያን በሞሮኒ ከተማ በበቂ ሁኔታ ጠንካሮች አልነበሩም፤ ስለዚህ አማሊቅያ ብዙዎችን ኔፋውያን በመግደል፣ እንዲሸሹ አደረገ። እናም እንዲህ ሆነ አማሊቅያ ከተማዋን፣ አዎን፣ ምሽጋቸውን በሙሉ ያዘ።

  ፳፬ እናም ከሞሮኒ ከተማ የሸሹት ወደ ኒፋአያህ ከተማ መጡ፤ እናም ደግሞ የሌሂ ከተማ ሰዎች እራሳቸውን በአንድ ላይ ሰበሰቡና፣ ዝግጅት አደረጉና፣ ላማናውያንን በጦርነት ለመቀበል እራሳቸውን አዘጋጅተው ነበር።

  ፳፭ ነገር ግን እንዲህ ሆነ አማሊቅያ ላማናውያን በኒፋአያህ ከተማ ለመዋጋት እንዲሄዱ አልፈቀደላቸውም፣ ነገር ግን በባህሩ ዳርቻ እንዲቆዩ አደረገ፣ ሰዎችንም በሁሉም ከተማ በማድረግ ከተሞቹን እንዲከላከሉ እናም እንዲጠብቁ ተዋቸው።

  ፳፮ እናም የኒፋአያህን ከተማና፣ የሌሂን ከተማ፣ የሞሪያንተንንም ከተማ፣ የኦምነርን ከተማ፣ እናም የጊድን ከተማ፣ እንዲሁም የሙሌቅን ከተማ፣ ሁሉንም በባህሩ ዳርቻ በስተምስራቅ የሚገኙትን ከተሞች መያዙን ቀጠለ።

  ፳፯ እናም በአማሊቅያ ጮሌነት ላማናውያን ቁጥር ስፍር በሌላቸው ሠራዊቶቻቸው፣ በሞሮኒ ምሽግ የተመሸጉትን ብዙ ከተሞችን አገኙ፤ እነዚህም በሙሉ ለላማናውያን ጠንካራ ስፍራዎችን ሰጣቸው።

  ፳፰ እናም እንዲህ ሆነ ላማናውያን፣ ኔፋውያንን ከፊታቸው በማባረርና ብዙዎችን በመግደል ወደለጋስ ምድር ወሰን ዘመቱ።

  ፳፱ ነገር ግን እንዲህ ሆነ ሞሪያንተንን የገደለውን፣ እናም ህዝቡንም ከመሸሽ ካቆማቸው ከቴአንኩም ጋር ተገናኙ።

  እናም እንዲህ ሆነ፣ ከበርካታ ወታደሮቹ ጋር፣ የለጋስን ምድር፣ እናም ደግሞ በስተሰሜን በኩል ያለውን መሬት ለመውሰድ ወደፊት የተጓዘውን አማሊቅያንም ደግሞ አቆመው።

  ፴፩ ነገር ግን እነሆ በቴአንኩም እናም በእርሱ ሰዎች በመመለሱ፣ እነርሱም ታላቅ ጦረኞች በመሆናቸው ቁጣን አገኘ፤ ማንኛውም የቴአንኩም ሰው የሆነ ላማናውያንን በብርታት እንዲሁም በጦር ስልት ስለሚበልጠው፣ ስለዚህም በላማናውያን ላይ የበላይነትን አገኙ።

  ፴፪ እናም እንዲህ ሆነ እነርሱም ጨለማ እስከሚሆን ድረስ አስፈራሩአቸውና ገደሉአቸው። እናም እንዲህ ሆነ ቴአንኩምና፣ ሰዎቻቸው በለጋስ ምድር ዳርቻ ድንኳናቸውን ተከሉ፤ አማሊቅያም በባህሩ ዳር በኩል ባለው የባህር ዳርቻ በኩል ድንኳኑን ተከለና፣ በዚህም ሁኔታ ነበር የተባረሩት።

  ፴፫ እናም እንዲህ ሆነ ምሽት በሆነም ጊዜ፣ ቴአንኩምና አገልጋዩ በቀስታ በምሽት ወጡ፣ ወደ አማሊቅያ የጦር ሰፈርም ሄዱ፤ እናም እነሆ፣ በስራቸውና በቀኑ ሙቀት የተነሳ እጅግ በመድከማቸው እንቅልፍ ጥሏቸው ነበር።

  ፴፬ እናም እንዲህ ሆነ ቴአንኩም በቀስታ በድብቅ በመሆን ወደ ንጉሱ ድንኳን ገባና፣ በጦር ልቡን ወጋው፣ እናም እርሱም የንጉሱ አገልጋዮች እንዳይነቁ ሞቱን በፍጥነት አደረገው።

  ፴፭ እናም ቴአንኩም በድጋሚ በሚስጥር ወደራሱ የጦር ሰፈር ተመለሰ፣ እናም እነሆ፣ ሰዎቹም ተኝተው ነበር፣ እርሱም ቀሰቀሳቸውና፣ ያደረጋቸውን ነገሮች በሙሉ ነገራቸው።

  ፴፮ እናም ላማናውያን ነቅተው በእነርሱ ላይ ይመጣሉ ብሎ በመፍራቱ ወታደሮቹ እንዲዘጋጁ አደረገ።

  ፴፯ እናም በኔፊ ህዝብ ላይ የመሣፍንቱ የሀያ አምስተኛ የንግስ ዘመን እንደዚህ ተፈፀመ፤ እናም የአማሊቅያ ዘመንም እንዲህ ተፈፀመ።