አልማ ፵
  Footnotes

  ምዕራፍ ፵

  ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ ትንሣኤ እንዲሆን አደረገ—ፃድቃን ሆነው የሞቱት ወደገነት ይሄዳሉ፣ እናም ኃጢአተኛ ሆነው የሞቱት እስከትንሳኤው ቀን ለመጠበቅ ወደ ድቅድቅ ጨለማ ይሄዳሉ—በትንሣኤ ሁሉም ነገር ወደ ተገቢው እናም ፍፁም ወደሆነው ቅርፅ ይመለሳል። በ፸፬ ም.ዓ. ገደማ።

  እንግዲህ ልጄ፣ ለአንተ በተጨማሪ የምለው ነገር ይህ ነው፤ ምክንያቱም አዕምሮህ ስለሙታን ትንሣኤ ተጨንቋልና።

  እነሆ፣ እንዲህ እልሃለሁ፣ ትንሣኤ የለም፣ ወይም በሌላ አነጋገር እንዲህ እላለሁ፣ ክርስቶስ ከመምጣቱ በኋላ ድረስ ይህ የሚሞተው ወደማይሞተው፣ ይህ የሚበሰብሰው ወደማይበሰብሰው አይለወጥም

  እነሆ፣ እርሱ የሙታን ትንሣኤ እንዲሆን ያደርጋል። ነገር ግን እነሆ፣ ልጄ፣ ትንሳኤው ገና ነው። እንግዲህ፣ ሚስጥሩን እገልፅልሃለሁ፤ ይሁን እንጂ፣ እግዚአብሔር እራሱ ካልሆነ በቀር ማንም የማያውቃቸው ብዙ በአምላክ የተደበቁ ሚስጥሮች አሉ። ነገር ግን እግዚአብሔርን አውቀው ዘንድ በትጋት የጠየቅሁትን አንድ ነገር ለአንተ አሳይሃለሁ፤ እርሱም ትንሣኤን በተመለከተ ነው።

  እነሆ፣ ሁሉም ከሙታን እንዲነሱበት የተወሰነ ጊዜ አለ። እንግዲህ ይህ የምመጣበትን ጊዜ ማንም አያውቅም፤ ነገር ግን የተወሰነውን ጊዜ እግዚአብሔር ያውቃል።

  እንግዲህ የመጀመሪያዎቹም ሆኑ ሁለተኛዎቹ፣ እንዲሁም ሦስተኞቹ ከሞት የሚነሱበት ጊዜ መኖሩ ልዩነት የለውም፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር እነዚህን ነገሮች ሁሉ ያውቃልና፤ እናም ይህ እንደሚሆን—ሁሉም ከሞት የሚነሱበት የተወሰነ ጊዜ እንዳለ ማወቅ ለእኔ ይበቃኛል።

  እንግዲህ በሞት እናም በትንሳኤ መካከል ጊዜ መኖሩ አስፈላጊ ነው።

  እናም እንግዲህ እንዲህ ብዬ እጠይቃለሁ፥ የሰው ነፍስ ከሞተበት ጊዜ ጀምሮ ለትንሣኤው እስከተወሰነበት ጊዜ ድረስ ምን ይሆናል?

  እንግዲህ ሰዎች እንዲነሱ የተወሰነላቸው ጊዜ ከአንዴ የበለጠ ቢሆን ምንም ልዩነት አያመጣም፤ ምክንያቱም ሁሉም በአንዴ አይሞቱምና፣ እናም ይህም ምንም አይደለም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉም እንደ አንድ ቀን ነው፤ እናም ጊዜ በሰዎች ብቻ ይለካል።

  ስለዚህ፣ ሰዎች ከሞት የሚነሱበት ቀን ተወስኗል፤ እናም በሞትና በትንሣኤ መካከል ጊዜ አለ። እናም እንግዲህ፣ ይህን ጊዜ በተመለከተም፣ የሰዎች ነፍስ ምን ይሆናል ብዬ ጌታን በትጋት የጠየቅሁት ይህን ነገር ነው፤ እናም የማውቀው ነገር ይህን ነው።

  እናም ሁሉም ከሞት የሚነሱበት ጊዜው ሲደርስ፤ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የተወሰነውን ጊዜ በሙሉ ማወቁንም ያውቃሉ።

  ፲፩ እንግዲህ፣ በሞትና በትንሣኤ መካከል የነፍስ ሁኔታን በተመለከተ—እነሆ፣ የሰዎች መንፈስ ሁሉ ከዚህ ሟች ከሆነው ሰውነታቸው እንደተለየ፣ አዎን፣ የሰዎች መንፈስ ሁሉ፣ መልካምም ይሁኑ መጥፎ፣ ህይወትን ወደ ሰጣቸው ወደ እግዚአብሔር እንደሚወሰድ በመልአኩ አማካኝነት እንዳውቀው ተደረገ።

  ፲፪ እናም እንዲህ ሆነ የፃድቃኖች መንፈስ፣ ከሁሉም ችግር፣ ውጣ ውረድና ሀዘን ወደሚያርፉበት፣ ገነት ተብላ ወደምትጠራው፣ የእረፍት ቦታ፣ የሰላም ቦታ ውስጥ ወደ ደስታ ሁኔታ ይገባሉ።

  ፲፫ እናም እንዲህ ሆነ የኃጢአተኞች መንፈስ፣ አዎን፣ ክፉዎች የሆኑትም—እነሆም፣ የጌታ መንፈስ ፈንታም ሆነ ድርሻ የላቸውም፤ እነሆም፣ ከመልካሙ ስራ ይልቅ መጥፎውን መርጠዋልና፤ ስለዚህ የዲያብሎስ መንፈስ በውስጣቸው ገብቷል፣ ቤታቸውንም የእርሱ አድርጎታል—እናም እነኚህ ወደ ድቅድቅ ጨለማ ይጣላሉ፤ በዚያም ልቅሶና ዋይታ እናም የጥርስ ማፏጨት ይኖራል፣ ይህም በክፋታቸው የተነሳ፣ በዲያብሎስ ፈቃድም በምርኮ ስለተመሩ ይሆናል።

  ፲፬ እንግዲህ ይህ የክፉዎች የነፍሳቸው ሁኔታ ነው፤ አዎን፣ በጨለማ ውስጥ እናም በእራሳቸው ላይ የእግዚአብሔር ሀይለኛ ንዴት ቁጣ በመጠበቅ አሰቃቂውና በአስፈሪውም በሆነ በእንደዚህም አይነት ሁኔታ ሲቆዩ፣ ፃድቃኖችም እስከትንሳኤው ድረስ በገነት ይቆያሉ።

  ፲፭ እንግዲህ፣ ከትንሳኤው በፊት እንደዚህ ዓይነቱን የነፍስ ደስታን እና መከራን የመጀመሪያው ትንሳኤ ነው በማለት የሚረዱት ጥቂት ሰዎች አሉ። አዎን፣ በተነገሩት ቃላት መሠረት የነፍስ ወይንም የመንፈስ መነሳትንና በደስታ ወይንም በችግር መሰየም ምናልባት ትንሳኤ ተብሎ ሊጠራ እንደሚችል እቀበለዋለሁ።

  ፲፮ እናም እነሆ፣ በድጋሚ በክርስቶስ ከሙታን መነሳት ድረስ የነበሩት፣ ወይንም ያሉት ወይንም የሚኖሩት ሁሉ ትንሣኤ፣ የፊተኛው ትንሳኤ እንዳለም ተነግሯል።

  ፲፯ አሁን፣ በዚህ ሁኔታ የተነገረው ይህ የመጀመሪያው ትንሳኤ፣ የነፍስ ትንሳኤ እንዲሁም የደስታቸው ወይም የሥቃያቸው ስያሜ ሊሆን እንደሚችል አልገመትንም። ይህ ትርጉሙ ይሆናል ብለህ መገመትም አትችልም።

  ፲፰ እነሆ፣ እንዲህ እልሃለሁ፣ አይደለም፤ ነገር ግን ይህ ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ትንሣኤ ድረስ ለነበሩት የነፍስ እና የስጋ ውህደት ማለት ነው።

  ፲፱ እንግዲህ ቀድሞ የተነናግርኩባቸው ኃጥአንም ሆነ ፃድቃን ነፍሳቸው ከስጋቸው ጋር በአንድ ጊዜ ይዋሃዳል ብዬ አልናገርም፤ ሁሉም ይነሳሉ ማለቴ ብቻ በቂ ነው፤ ወይም በሌላ አነጋገር፣ ትንሣኤአቸው ከክርስቶስ ትንሳኤ በኋላ ከሞቱት በፊት ይሆናል።

  እንግዲህ፣ ልጄ፣ ትንሣኤያቸው በክርስቶስ ትንሣኤ ይመጣል አላልኩሁም፤ ነገር ግን እነሆ፣ በክርስቶስ ትንሣኤ እንዲሁም ወደ ሰማይ ባረገበት ጊዜ የፃድቃኖች ነፍስ ከስጋቸው ጋር መዋሃዱን አስተያየቴን እሰጣለሁ።

  ፳፩ ነገር ግን በትንሣኤውም ሆነ ከትንሣኤውም በኋላ እንደዚህ አልልም፤ ነገር ግን ይህንን ያህል እናገራለሁ፣ ሙታን እንደሚነሱ፣ ነፍስም ከስጋ ዳግም እስከሚገናኝ እንዲሁም በእግዚአብሔር በተወሰነላቸው ቀን እንደስራቸው በእግዚአብሔር ፊት በመቆም እስከሚፈረድባቸው ድረስ በሞትና በአካል ትንሳኤ መካከል ጊዜ፣ እናም ነፍስ በደስታ ወይም በስቃይ የሚገኝበት ጊዜ አለ።

  ፳፪ አዎን፣ ይህም በነቢያት አንደበት የተነገሩትን ነገሮች በሙሉ ዳግሞ መመለስን ይመጣል።

  ፳፫ ነፍስ ወደ ስጋ፣ ስጋም ወደ ነፍስ በዳግም ይመለሳል፤ አዎን፣ እናም ማንኛውም እጅና እግር እንዲሁም መገጣጠሚያ ወደ ቀድሞ ቦታው ይመለሳል፤ አዎን፣ የራስ ፀጉርም ቢሆን አይጠፋም፤ ነገር ግን ሁሉም ነገር ወደ ተገቢው እናም ትክክለኛ አቋሙ ይመለሳል።

  ፳፬ እናም እንግዲህ፣ ልጄ፣ ይህ በነቢያት አንደበት የተነገረው ዳግሞ መመለስ ነው—

  ፳፭ እና ከእዚያም ፃድቃኖች በእግዚአብሔር መንግስት ያበራሉ።

  ፳፮ ነገር ግን እነሆ፣ አሰቃቂው ሞት በኃጢአተኞች ላይ ይሆናል፤ ፅድቅ ለሆኑት ነገሮች ሞተዋልና፤ ምክንያቱም እነርሱ ንፁህ አይደሉምና፣ እናም ምንም እርኩስ ነገር የእግዚአብሔርን መንግስት ሊወርስ አይችልም፤ ነገር ግን መጥፎ የሆኑትን የስራቸውን ውጤት እንዲካፈሉ ይጣላሉ፣ እናም መራራውን አተላ ይጎነጫሉ።