አልማ ፲፬
  Footnotes

  ምዕራፍ ፲፬

  አልማና አሙሌቅ ታሰሩ እናም ተመቱ—የሚያምኑትና ቅዱሳን መፃሕፍቶቻቸው በእሳት ተቃጠሉ—እነዚህ ሰማዕታት በጌታ በክብር ተወሰዱ—የወህኒ ቤቱ ግድግዳ ተሰነጣጠቀ እናም ወደቀ—አልማና አሙሌቅ ተለቀቁ እናም ያሰቃዩአቸው ተገደሉ። ከ፹፪–፹፩ ም.ዓ. ገደማ።

  እናም እንዲህ ሆነ አልማ ለህዝቡ መናገሩን ከጨረሰ በኋላ ብዙዎች በቃሉ አመኑ፣ እናም ንስሃ መግባትና ቅዱሳት መጻሕፍትን መመርመር ጀመሩ።

  ነገር ግን ብዙዎች አልማንና አሙሌቅን ለማጥፋት ፈልገው ነበር፣ አልማ ለዚኤዝሮም በተናገራቸው ቃላት ግልፅነት ተቆጥተው ነበርና፣ እናም ደግሞ አሙሌቅ ዋሽቶናል፣ እናም ህጋቸውንና ደግሞ የህግ አዋቂዎቻቸውንና ዳኞቻቸውን ተሳድቧል ብለዋልና።

  እናም ደግሞ በአልማና በአሙሌቅ ተቆጥተው ነበር፤ እናም በክፋታቸው ላይ በግልፅ በመመስከራቸው፣ በድብቅ ሊያጠፏቸው ፈለጉ።

  ነገር ግን እንዲህ ሆነ አላጠፏቸውም፤ ነገር ግን ወሰዱዋቸውና በጠንካራ ገመድ አሰሩአቸው፣ እናም በምድሪቱ ዋና ዳኛ ፊት አቀረቡአቸው።

  እናም ህዝቡ ወደፊት መጣና በእነርሱ ላይ መሰከረ—በህጉ ላይና በህግ አዋቂዎቻቸውና በምድሪቱ ዳኞች፣ ደግሞም በምድሪቷ ላይ ያሉትን ህዝቦች ሁሉ ላይ ክፉ እንደተናገሩ፤ እናምደግሞ ከአንድ አምላክ በላይ እንደሌለና እርሱ በህዝቡ መካከል ልጁን ይልካል፣ ነገር ግን አያድናቸውም ብለዋል በማለት መሰከሩባቸው፣ እናም እንደዚህ ዓይነት ብዙ ነገሮችን ህዝቡ በአልማና በአሙሌቅ ላይ መሰከረ። አሁን ይህ የተደረገው በምድሪቱ ዋና ዳኛ ፊት ነበር።

  እናም እንዲህ ሆነ በተነገሩበት ቃላት ዚኤዝሮም ተገርሞ ነበር፣ እናም ደግሞ በህዝቡም መካከል በውሸታም ቃላቱ ስለአዕምሮአቸው መታወር ያደረገውን ያውቃል፤ እናም ነፍሱ በጥፋቱ እውቀት የተነሳ መሰቃየት ጀመረች፤ አዎን በሲኦል ህመም መከበብ ጀመረ።

  እናም እንዲህ ሆነ ለህዝቡም እንዲህ በማለት መጮህ ጀመረ፥ እነሆ እኔ ጥፋተኛ ነኝ፣ እነዚህ ሰዎችም በእግዚአብሔር ፊት እንከን የለሽ ናቸው። እናም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለእነርሱ መለመን ጀመረ፤ ነገር ግን እንዲህ በማለት ሰደቡት፤ አንተ ደግሞ በዲያብሎስ የተያዝህ ነህን? እናም ተፉበት፣ ከእነርሱም መካከል እርሱን፣ እናም ደግሞ በአልማና በአሙሌቅ በተነገሩት ቃላት ያመኑትን ሁሉ አውጥተው ጣሉ፤ እናም አውጥተው ጣሉአቸው፣ በድንጋይ የሚወረውሩባቸው ሰዎችንም ላኩባቸው።

  እናም ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን በአንድ ላይ አመጡ፣ እናም ማንኛውም በእግዚአብሔር ያመነም ሆነ እንዲያምን የተማረን ወደ እሳት እንዲጣል አደረጉ፤ ደግሞም ቅዱሳት መጻሕፍትን የያዙትን መዛግብቶቻቸውን አመጡና፣ ደግሞ በእሳት ይቃጠሉና ይጠፉ ዘንድ ወደእሳቱ ጣሉአቸው።

  እናም እንዲህ ሆነ አልማና አሙሌቅን ወሰዱና በእሳት የተበሉትን ጥፋት ይመለከቱ ዘንድ ወደ ሰማዕት ቦታ ወሰዱዋቸው።

  እናም አሙሌቅ በእሳት የተበሉትን ሴቶችና ልጆች ስቃይ በተመለከተ ጊዜ፣ እርሱም ደግሞ ህመሙ ተሰምቶት ነበር፣ እናም ለአልማ እንዲህ አለ፥ ይህንን አሰቃቂ ትዕይንት እንዴት ልንመለከት እንችላለን? ስለዚህ እጃችንን እንዘርጋ፣ በውስጣችን ያለውንም የእግዚአብሔርን ኃይል እንለማመድ፣ እናም እነርሱን ከነበልባሉ እሳት እናድናቸው።

  ፲፩ ነገር ግን አልማ እንዲህ አለው፥ መንፈስ እጆቼን መዘርጋት እንደሌለብኝ ገታኝ፤ እነሆ ጌታ ወደእራሱ በክብር ተቀብሏቸዋልና፤ እናም ይህንን ነገር እንዲያደርጉ ወይም እንደልባቸው መጠጠር ህዝቡ ይህን ነገር ያደርጉ ዘንድ የፈቀደላቸው፣ በእነርሱ ላይ በቁጣው የሚመጣው ፍርድ ጻድቅ ይሆን ዘንድ ነው፤ እናም የንፁሃን ደም በእነርሱ ላይ ለምስክርነት ይቆማል፤ አዎን፣ እናም በመጨረሻው ቀን በእነርሱ ላይ በኃይል ይጮሃል።

  ፲፪ አሁን አሙሌቅ ለአልማ እንዲህ አለው፥ እነሆ እኛንም ደግሞ ምናልባት ያቃጥሉን ይሆናል።

  ፲፫ እናም አልማ እንዲህ አለ፥ እንደጌታ ፈቃድ ይሁን። ነገር ግን እነሆ ስራችን አላለቀም፤ ስለዚህ አያቃጥሉንም።

  ፲፬ አሁን እንዲህ ሆነ ወደ እሳቱ የተጣሉት ሰውነቶቻቸው እናም ደግሞ ከእነርሱ ጋር አብረው የተጣሉት መዝገቦቻቸው ሲቃጠሉ፣ የምድሪቱ ዋና ዳኛ፣ በታሰሩት በአልማና በአሙሌቅ ፊት ቆመ፤ እናም በእጁ ፊታቸው ላይ መታቸውና እንዲህ አላቸው፣ እናንተ ይህንን ካያችሁ በኋላ በድጋሚ ለዚህ ህዝብ ወደ እሳቱ ባህርና ዲን እንደሚጣሉ ትሰብካላችሁን?

  ፲፭ እነሆ፣ በእሳት የተጣሉትን ለማዳን ሀይል እንደሌላችሁ ትመለከታላችሁ፤ ወይም እግዚአብሔርም እነርሱ ከእናንተ እምነት በመሆናቸው አላዳናቸውም። እናም ዳኛው በድጋሚ ፊታቸው ላይ መታቸው፣ እናም እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፥ ስለራሳችሁስ ምን ትላላችሁ?

  ፲፮ አሁን ይህ ዳኛ ጌዴዎንን ከገደለው ኔሆር ስርዓትና እምነት ጋር ነበር።

  ፲፯ እናም እንዲህ ሆነ አልማና አሙሌቅ ምንም አልመለሱለትም፤ እናም በድጋሚ መታቸውና ወደ ወህኒ ቤት እንዲጣሉ ለባለስልጣኖች አሳልፎ ሰጣቸው።

  ፲፰ እናም ለሶስት ቀናት በወህኒ በተጣሉ ጊዜ፣ የኔሆር ኃይማኖተኞች የሆኑ ብዙ ጠበቃዎችና ዳኞች፣ እንዲሁም ካህናት፣ እንዲሁም መምህራን መጡ፤ እናም እነርሱን ለማየት ወደ ወህኒ ቤት መጡና፣ ስለ ብዙ ቃላት ጠየቁአቸው፣ ነገር ግን ምንም አልመለሱላቸውም ነበር።

  ፲፱ እናም እንዲህ ሆነ ዳኛው ከፊታቸው ቆመና እንዲህ አላቸው፥ የዚህን ህዝብ ጥያቄ ለምን አትመልሱም? ወደነበልባሉ እናንተን ለመጣል ስልጣን እንዳለኝ አታውቁምን? እናም እንዲናገሩ አዘዛቸው፣ ነገር ግን ምንም አልመለሱም።

  እናም እንዲህ ሆነ ወደ ጉዳያቸውም ተመልሰው ሄዱ፣ ነገር ግን በሚቀጥለው ቀን በድጋሚ መጡ፤ እናም ዳኛው ደግሞ በድጋሚ በፊታቸው ላይ መታቸው። ብዙዎችም ደግሞ መጡና፣ መቷቸው፣ እንዲህም አሉአቸው፥ ይህንን ህዝብ ለመፍረድና ህጋችንን ለመኮነን በድጋሚ ትቆማላችሁን? እንደዚህ ዓይነት ታላቅ ሀይል ካላችሁ ራሳችሁን ለምን አታድኑም?

  ፳፩ እናም እንደነዚህ ያሉ ብዙ ነገሮችን ተናገሩአቸው፣ ጥርሶቻቸውንም አፏጩባቸውና፣ ተፉባቸው፣ እንዲህም አሉአቸው፥ ስንኮነንስ ምን እንመስላለን?

  ፳፪ እናም እንደነዚህ ያሉ ብዙ ነገሮችን አሉዋቸው፣ አዎን፣ እንደነዚህ ያሉ ነገሮችን ሁሉ እንዲህ ሲሉ ተናገሩዋቸው። ለብዙ ቀናትም ተሳለቁባቸው። እናም እንዲራቡ ምግብ፣ እንዲጠሙ ውሃን ለብዙ ቀናት ከለከሉአቸው፤ ደግሞም እንዲራቆቱ ልብሶቻቸውን ነጠቁአቸው፤ እናም በጠንካራ ገመድ ታስረው በወህኒ ቤት የቆዩት እንዲህ ነበር።

  ፳፫ እናም እንዲህ ሆነ ለብዙ ቀናት ከተሰቃዩ በኋላ (እና ይህም በአስረኛው ወር በአስራ ሁለተኛው ቀን በኔፊ ህዝብ ላይ በመሣፍንቱ አስረኛ ዓመት የንግስ ዘመን ነበር) ዋናው የአሞኒሀ ዋና ዳኛና፣ ብዙ መምህራኖቻቸውና፣ የህግ አዋቂዎቻቸው፣ አልማና አሙሌቅ በሲባጎ ወደ ታሰሩበት ወህኒ ቤት ሄዱ።

  ፳፬ እናም ዋናው ዳኛ በፊታቸው ቆመና፣ በድጋሚ መታቸው፣ እንዲህም አለ፥ የእግዚአብሔር ኃይል ካላችሁ ራሳችሁን አስለቅቁ፣ ከእዚያም እኛም በቃላችሁ መሰረት ጌታ ይህንን ህዝብ እንደሚያጠፋ እናምናለን።

  ፳፭ እናም እንዲህ ሆነ ሁሉም፣ እስከመጨረሻውም እነዚህን ቃላት ደግመው እየተናገሩ፣ ወደ እነርሱ ተጠጉና መቱአቸው፤ እናም የመጨረሻው በተናገራቸው ወቅት የእግዚአብሔር ኃይል በአልማና በአሙሌቅ ላይ ነበር፣ እናም ተነስተው በእግራቸው ቆሙ።

  ፳፮ እናም አልማ እንዲህ በማለት ጮኸ፥ አቤቱ ጌታ፣ ለምን ያህል ጊዜ ነው ይህንን ታላቅ ስቃይ የምንሰቃየው? አቤቱ ጌታ፣ እስከመዳን ድረስ በክርስቶስ ባለን እምነታችን መሰረት ጥንካሬን ስጠን። እናም የታሰሩበትን ገመድ በጠሱት፤ ህዝቡም ይህንን በተመለከተ ጊዜ፣ መሸሽ ጀመሩ፣ የጥፋት ፍርሃት በእነርሱ ላይ መጥቷልና።

  ፳፯ እናም እንዲህ ሆነ ፍርሃታቸው ታላቅ ስለነበር በመሬት ላይ ወደቁና፣ የወህኒ ቤቱን የመውጫ በር አላገኙትም ነበር፤ እናም መሬት በኃይል ተንቀጠቀጠች፣ የወህኒ ቤቱ ግድግዳም ለሁለት ተከፈለ ወደ ምድርም ወደቁ፣ እናም አልማንና አሙሌቅን የመቱት ዋናው ዳኛና፣ የህግ አዋቂዎቹና፣ ካህናት፣ እንዲሁም መምህራን በፍርስራሹ ተገደሉ።

  ፳፰ እናም አልማና አሙሌቅ ከወህኒ ቤቱ ወጡ፣ እናም አልተጎዱም ነበር፤ በክርስቶስ ላይ በነበራቸው እምነት ጌታ ኃይልን ሰጥቷቸዋልና። ወዲያውም ከእስር ቤቱ ወጡና፣ ከታሰሩበትም ገመድ ተፈትተው ነበር፤ እናም ወህኒ ቤቱ ፈራርሶ ወደቀና፣ ከአልማና ከአሙሌቅ በስተቀር በወህኒ ቤቱ የነበሩት ነፍሳት ሁሉ ተገድለው ነበር፤ እናም በፍጥነት ወደ ከተማው ሄዱ።

  ፳፱ አሁን ጩኸቱን የሰሙ ሰዎች የሆነውን ለማወቅ ህዝቡ በሩጫ ተሰብስበው መጡ፤ አልማና አሙሌቅ ከእስር ቤት ወጥተው የወህኒ ቤቱ ግድግዳ ፈራርሶ በመሬት መውደቁን ሲመለከቱ በታላቅ ፍርሀት ተመቱና፣ ፍየል ከነልጆችዋ ከአንበሶች ፊት እንደምትሸሸው ከአልማና ከአሙሌቅ ፊት ሸሹ፤ እና እንደዚህም ከአልማና ከአሙሌቅ ፊት ሸሹ።