ቅዱሳት መጻህፍት
፪ ኔፊ ፳፩


ምዕራፍ ፳፩

የእሴይ ግንድ (ክርስቶስ) በጻድቅነት ይፈርዳል—ስለእግዚአብሔር የሚኖረው እውቀት በአንድ ሺህ ዘመን ምድርን ይሞላል—ጌታም አርማውን ያነሳል እናም እስራኤልን ይሰበስባል—ኢሳይያስ ፲፩ን አነጻፅሩ። ከ፭፻፶፱–፭፻፵፭ ም.ዓ. ገደማ።

፩ እናም ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፣ ከስሩም ቅርንጫፍ ይበቅላል።

፪ እናም የጌታ መንፈስ፣ የጥበብና የመረዳት መንፈስ፣ የምክርና የኃይል መንፈስ፣ የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ በላዩ ላይ ያርፋል፤

፫ እናም በእግዚአብሔር ፍርሃት በፍጥነት የሚረዳ ያደርገዋል፤ እናም እርሱ በዐይኖቹ ባየው አይፈርድም፣ ወይም በጆሮዎቹ በሰማውም አይገስጽም።

፬ ነገር ግን ድሆችን በፅድቅ ይፈርዳል፣ ለምድር ትሁቶችም በእኩልነት ይገስጻል፤ እናም ምድርን በአፉ በትር ይመታል፣ እናም ክፉዎችን በከንፈሮቹ እስትንፋስ ይገድላል።

፭ እናም ፅድቅ የወገቡ መታጠቅያ፣ ታማኝነትም የጎኑ መታጠቅያ ይሆናሉ።

፮ ተኩላውም ደግሞ ከበጉ ጋር ይኖራል፣ አቦሸማኔው ደግሞ ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፣ ጥጃውም የአንበሳ ደቦልም፣ ፍሪዳውም በአንድነት ይሆናሉ፤ ታናሽ ልጅም ይመራቸዋል።

፯ እናም ላምና ድብ አብረው ይመገባሉ፤ ግልገሎቻቸውም በአንድነት ይተኛሉ፤ አንበሳውም እንደበሬ ገለባን ይበላል።

፰ እናም የሚጠባው ህፃን በመርዛማው እባብ ጉድጓድ ላይ ይጫወታል፣ ጡት የጣለውም ህፃን በእፉኝት ቤት ላይ ይጭናል።

፱ በተቀደሰው ተራራዬ ላይ ሁሉ አይጎዱም፣ ወይም አያጠፉም፣ ውኃዎች ባህርን እንደሚሸፍን ሁሉ ምድር በጌታ እውቀትም ትሞላለችና።

፲ እናም በዚያ ቀን ለህዝቡ ምልክት ሆኖ የሚቆም የእሴይ ስር ይኖራል፤ አህዛብም እርሱን ይፈልጋሉ፤ እናም የሚያርፍበትም የተከበረ ይሆናል።

፲፩ እናም በዚያ ቀን እንዲህ ይሆናል ጌታ የቀረውን የህዝቡን ቅሪት ከአሶርና፣ ከግብፅ፣ ከጳትሮስና፣ ከኩሽ፣ ከኢላምና፣ ከሰናዖር፣ ከሐማት፣ ከባህር ደሴቶች መልስ ዳግም ይሰበስብ ዘንድ ለሁለተኛ ጊዜ እጁን ይዘረጋል።

፲፪ እናም እርሱ ለሀገሮች ምልክትን ያቆማል፣ ከእስራኤልም የተሰደዱትን ይሰበስባል፣ እናም በአራቱም የምድር ማዕዘናት የተበተነውን ይሁዳን በአንድነት ይሰበስባል።

፲፫ የኤፍሬም ምቀኝነት ደግሞም ይቆማል፣ የይሁዳም ጠላቶች ይጠፋሉ፤ ኤፍሬም በይሁዳ አይቀናምና፣ እናም ይሁዳ ኤፍሬምን አያበሳጭም።

፲፬ ነገር ግን በምዕራብ በኩል በፍልስጤማውያን ትከሻ ላይ እየበረሩ ይወርዳሉ፤ የምስራቆቹንም ጭምር በአንድነት ያጠፋሉ፤ እጃቸውንም በኤዶምና በሞአብ ላይ ያሳርፋሉ፤ እናም የአሞንም ልጆች ይታዘዙአቸዋል።

፲፭ እናም ጌታ የግብፃውያንን የባህር ሠርጥ ፈፅሞ ያጠፋል፤ በኃያል አውሎ ነፋሱም እጆቹን በወንዞች ላይ ያንቀጠቅጣል፣ ሰባትም ወራጆች አድርጎ ይከፋፍለዋል፣ ሰዎችንም በደረቁ ያሻግራል።

፲፮ እናም እርሱ ከግብፅ ምድር በወጣ ጊዜ ለህዝቡ ቅሪት ሆኖ ለሚቀሩት ከአሶር እስከ እስራኤል የሚደርስን ያህል ጎዳና ያኖርላቸዋል።