ምዕራፍ ፲፰
ክርስቶስ እንደማሰናከያ ዓለት እና እንቅፋት ይሆናል—ጠንቋይን ሳይሆን ጌታን እሹ—ለመመሪያችሁ በህጉና በምስክርነቱ ላይ ተስፋ አድርጉ—ኢሳይያስ ፰ን አነጻፅሩ። ከ፭፻፶፱–፭፻፵፭ ም.ዓ. ገደማ።
፩ ከዚህም በላይ፣ የጌታ ቃል እንዲህ አለኝ—ትልቁን ጥቅል ውሰድ፣ እናም ማሔር-ሻላል-ኸሽ-ባዝ ብለህ በሰው ብዕር ፃፍበት።
፪ እናም እኔ የታመኑ ምስክሮችን፣ ካህን ኦርዮን እና የበራክዩን ልጅ ዘካርያስን ለምዝገባው ወደ እኔ ወሰድሁ።
፫ እናም እኔ ወደ ነቢይቱ ቀረብሁ፤ እርሷም ፀነሰች እናም ወንድ ልጅ ወለደች። ከዚያም ጌታ እንዲህ አለኝ፥ ማኻር-ሻላል-ሐሽ-ባዝ ብለህ ስሙን ጥራው።
፬ እነሆም፣ ህፃኑ አባቱንና እናቱን መጥራት ሳያውቅ፣ የደማስቆን ሀብትና የሰማርያን ምርኮ በአሶር ንጉስ ፊት ይወስዳል።
፭ ጌታ እንደገና ደግሞ እንዲህ ሲል ተናገረኝ፥
፮ ይህ ህዝብ በቀስታ የሚሄደውን የሰሊሆምን ውሃ እስከጠሉ፣ እናም በረአሶንንና በሮሜልዩም ልጅ በመደሰታቸው የተነሳ፤
፯ ስለዚህ አሁን፣ እነሆ፣ ጌታ ብርቱና ብዙ የሆነውን የወንዝ ውሃ፣ የአሶርን ንጉስና ክብሩን ሁሉ ያመጣባቸዋል፤ እናም እርሱ መስኖዎችን ሁሉ ይሞላል፣ እናም በዳርቻውም ሁሉ ላይ ይፈስሳል።
፰ እናም በይሁዳ ያልፋል፤ እያጥለቀለቀም ያልፋል፣ እስከ አንገትም ይደርሳል፤ እናም አማኑኤል ሆይ፣ የክንፉ መዘርጋት የአገርህን ስፋት ትሞላለች።
፱ ህዝብ ሆይ ተባበሩ፣ እናም በትንንሹ ትከፋፈላላችሁ፤ እናንተም ሩቅ ሀገር ያላችሁ ሁሉ አድምጡ፤ ራሳችሁን አስታጥቁ፣ እናም በትንንሹ ትከፋፈላላችሁ፤ ራሳችሁን አስታጥቁ፣ እናም በትንንሹ ትከፋፈላላችሁ።
፲ በአንድነት ተመካከሩ፣ እናም እርሱ ከንቱ ይሆናል፤ ቃሉን ተናገሩ፣ እናም አትፀናም፣ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነውና።
፲፩ ጌታ በፅኑ እጁ እንዲሁ ተናግሮኛልና፣ እናም በዚህ ህዝብ መንገድ እንዳልራመድ እንዲህ ሲል አዘዘኝ፥
፲፪ ይህ ህዝብ ግብረ-አበራዊ ነው በሚለው ሁሉ ግብረ-አበራዊ ነው አትበሉ፣ መፈራታቸውንም ቢሆን አትፍሩ፣ አትደንግጡ።
፲፫ የሰራዊት ጌታ እራሱን ቀድሱት፣ እናም የእናንተ ፍርሃት እርሱ ይሁን፣ ስጋታችሁም እርሱ ይሁን።
፲፬ እናም እርሱ መሸሸጊያ፤ ነገር ግን ለሁለቱ ለእስራኤል ቤቶች፣ ለእንቅፋት ድንጋይና፣ ለማሰናከያ አለት፣ በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩ ለወጥመድና ለአሽክላ ይሆናል።
፲፭ እናም ብዙዎች ከእነርሱ ጋር ይሰናከላሉ እንዲሁም ይወድቃሉ፣ ይሰበራሉም፣ ይጠመዳሉም፣ እናም ይማረካሉ።
፲፮ በደቀ መዛሙርቶቼም መካከል ምስክርነትን እሰር፣ ህጉንም አትም።
፲፯ እናም ከያዕቆብ ቤት ፊቱን የደበቀውን ጌታ እጠብቃለሁ፣ እናም እርሱን እፈልገዋለሁ።
፲፰ እነሆ፣ እኔና ጌታ የሰጠኝ ልጆቼ በእስራኤል በፅዮን ተራራ ከሚኖረው ከሰራዊት ጌታ ዘንድ ምልክትና ተአምራት ነን።
፲፱ እናም የሚጮሁትንና፣ ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው የሚናገሩትን መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ጠይቁ ባሉአችሁ ጊዜ—ለህያዋን ከሙታን ለመስማት ህዝቡ ከአምላኩ መጠየቅ አይገባውምን?
፳ ወደህግና ወደምስክርነት ተመልከቱ፣ እናም በዚህ ቃል መሰረት ካልተናገሩ፣ ምክንያቱ ብርሃን በውስጣቸው የለም።
፳፩ እነርሱም ይህን በጣም ተጨንቀውና ተርበው ያልፋሉ፤ እናም እንዲህ ይሆናል በተራቡ ጊዜ፣ በጣም ይቆጣሉ፣ እናም አምላካቸውንና ንጉሳቸውን ይረግማሉ፣ ወደ ላይም ይመለከታሉ።
፳፪ እናም ወደ ምድር ይመለከታሉ፣ እናም ችግርን፣ ጨለማን፣ የሚያስጨንቅ ጭጋግን ያያሉ፣ እናም ወደ ጨለማም ይሰደዳሉ።