ቅዱሳት መጻህፍት
፪ ኔፊ ፲፯


ምዕራፍ ፲፯

ኤፍሬምና ሶርያ በይሁዳ ላይ ጦርነትን አወጁ—ክርስቶስ ከድንግል ይወለዳል—ኢሳይያስ ፯ን አነጻፅሩ። ፭፻፶፱–፭፻፵፭ ም.ዓ. ገደማ።

፩ እናም እንዲህ ሆነ በአካዝ በኢዮአታም ልጅ ዘመን፣ በይሁዳ ንጉስ በኡዝያን ልጅ፣ የሶርያው ንጉስ ረአሶን፣ እና የሮሜልዩ ልጅ፣ የእስራኤልም ንጉስ ፋቁሔ ኢየሩሳሌምን ሊወጉ ወጡ፣ ነገር ግን ሊያሸንፉአትም አልቻሉም።

፪ እናም ለዳዊት ቤት ሶርያ ከኤፍሬም ጋር ተባብራለች የሚል ወሬ ተነገረ። እናም የጫካ ዛፍ በንፋስ እንደሚናወጥ የእርሱ ልብና የህዝቡም ልብ ተናወጠ።

፫ ከዚያም ጌታ ኢሳይያስን አለው—አሁን አንተና ልጅህ ያሱብ ከአካዝ ጋር ትገናኙት ዘንድ በልብስ አጣቢው እርሻ መንገድ ወዳለው ወደ ላይኛው የኩሬ መስኖ ጫፍ ውጡ፤

፬ እናም እንዲህ በለው—ተጠንቀቅ፣ ዝምም በል፣ ስለእነዚህ ስለሚጨሱ ስለሁለት ጥላሸቶች፣ ስለረአሶን በሶርያና፣ ሮሜልዩም ልጅ ቁጣ አትፍራ።

፭ ምክንያቱም ሶርያ፣ ኤፍሬምና የሮሜልዩም ልጅ በአንተ ላይ እንዲህ ሲሉ ክፋትን መክረዋልና፤

፮ ወደ ይሁዳ እንውጣና እናስጨንቀው፣ እናም ለራሳችን በእዚያም እንስበረው፣ በመካከሉም ንጉስ፣ አዎን፣ የጠብኤልንም ልጅ፣ እናስቀምጥ።

፯ እንዲሁም ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል—ይህ ምክር አይፀናም፣ አይሆንምም።

፰ የሶርያ ራስ ደማስቆ ነውና፣ እናም የደማስቆም ራስ ረአሶን ነውና፤ እናም በስድሳ አምስት ዓመት ውስጥ ኤፍሬም ይሰባበራል፣ ህዝብም አይሆንም።

፱ እናም የኤፍሬም ራስ ሰማርያ ነው፣ እናም የሰማርያ ራስ የሮሜልዩ ልጅ ነው። የማታምኑ ከሆነ በእርግጥ አትፀኑም።

፲ ከዚያም በላይ ጌታ አካዝን በድጋሚ እንዲህ ብሎ ተናገረው—

፲፩ ከጥልቁ ወይም ከከፍታውም ቢሆን ከጌታ ከአምላክህ ምልክትን ለምን።

፲፪ ነገር ግን አካዝም፣ አልለምንም፣ ጌታንም አልፈተንም አለ።

፲፫ እናም እርሱ አለ፥ የዳዊት ቤት ሆይ፣ አሁን ስሙኝ፤ በእውነት ሰውን ማድከም ቀላል ሆነባችሁ፣ ግን አምላኬን ደግሞ ልታደክሙ ነውን?

፲፬ ስለዚህ፣ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል—እነሆ፣ ድንግል ትፀንሳለች፣ እናም ወንድ ልጅም ትወልዳለች፣ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።

፲፭ እርሱም ክፉን ለመጥላትና መልካሙን ለመምረጥ ማወቅ ይችል ዘንድ ቅቤና ማር ይበላል።

፲፮ ህፃን መጥፎውን ከመጥላቱና ጥሩውን ከመምረጡ በፊት፣ የጠላኸው መሬት በሁሉም ነገሥታቶች ይተዋል።

፲፯ ጌታ ኤፍሬም ከይሁዳ ከተለየበት ቀን ጀምሮ ያልመጣውን ዘመን በአንተና በሕዝብህ በአባትህም ቤት ላይ ያመጣል፤ እርሱም የአሦር ንጉሥ መምጣት ነው።

፲፰ እናም በዚያ ቀን እንዲህ ይሆናል ጌታ በግብፅ ዳርቻ ያለውን ዝንብ እና በአሶር ምድር ያለውን ንብ በፉጨት ይጠራል።

፲፱ እናም ይመጣሉ፣ እነርሱም ሁሉ በበረሃ ሸለቆ፣ እና በድንጋይም ዋሻና በእሾህ ላይ ሁሉ፣ በቁጥቋጦውም ሁሉ ላይ ያርፋሉ።

፳ በዚያም ቀን ጌታ ከወንዙ ባሻገር፣ በቀጠራቸው በአሶር ንጉስ፣ የራስና የእግሩን ጠጉር ይላጫል፣ እናም ምላጩ ደግሞ ጢሙን ይበላል።

፳፩ እናም በዚያ ቀን እንዲህ ይሆናል፣ አንድ ሰው ጊደርና ሁለት በጎችን ይመግባል፤

፳፪ እናም እንዲህ ይሆናል፣ ከሚሰጡት ወተት ብዛት የተነሳ እርሱ ቅቤን ይበላል፣ በሀገሪቱም መካከል የቀረ ማንም ሰው ቅቤና ማር ይበላል።

፳፫ እናም በዚያ ቀን እንዲህ ይሆናል፣ ሺህ ብር የሚያወጣው ሺህ የወይን ግንድ በነበረበት ቦታ ሁሉ ኩርንችትና እሾህ ብቻ ይሆናሉ።

፳፬ በምድሪቱ ሁሉ ኩርንችትና እሾህ በመሆኑ ሰዎች በፍላፃና በቀስት ወደዚያ ይመጣሉ።

፳፭ እናም በመቆፈሪያ ወደ ተቆፈሩ ኮረብቶች ሁሉ፣ ከኩርንችትና እሾህ ፍርሀት ወደዚያ ማንም አይሄድም፤ ነገር ግን የበሬ ማሰማሪያና የታናሽ ከብት መረገጫ ይሆናል።

      • ይህም ሰሜን እስራኤል በሙሉ በሰሜን ጎሳዎች መሪ በሆነው በኤፍሬም ስም ተጠርተዋል ማለት ነው።

      • ዕብ. የሚቀሩት ይመለሳሉ።

      • ይህም በጥቃቱ አትደንግጥ፤ እነዚያ ሁለት ንጉሶች የቀራቸው ትንሽ እሳት ነው ማለት ነው።

      • ዕብ. ተከፋፈሉት።

      • ፪ ዜና ፳፥፳።

      • ይህም ፈትን፣ ሞክር፣ ወይም እርግጠኛ አድርግ ማለት ነው።

      • ፩ ነገሥ. ፲፪፥፲፮–፲፱።

      • ፪ ዜና ፳፰፥፲፱–፳፩።

      • ወይም ማፏጨት፤ ይህም ምልክት መስጠት፣ መጥራት ማለት ነው። ኢሳ. ፭፥፳፮።

      • ፪ ነገሥ. ፲፮፥፭–፱።

      • ይህም ምድሯ ከውጪ በሚመጡ ወራሪዎች ህዝቧ በሙሉ ይጠፋሉ ማለት ነው።

      • ይህም ለሚተርፉት እራሳቸውን ለመደገፍ የሚችሉ ብቻ ይቀራሉ ማለት ነው።

      • ወይም የብር ቁራጭ።

      • ዕብ. በጎች ወይም ፊየሎች።