ምዕራፍ ፲፭
የጌታ የወይን አትክልት ስፍራ (እስራኤል) ባዶ ይሆናል፣ እናም የእርሱ ሕዝቦች ይበተናሉ—በአመፃና በመበተናቸው ጊዜ መከራ በእነርሱ ላይ ይመጣል—ጌታም ምልክቱን ያነሳል እናም እስራኤልን ይሰበስባል—ኢሳይያስ ፭ን አነጻፅሩ። ከ፭፻፶፱–፭፻፵፭ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም ከዚያ ለውድ ወዳጄ የወይን አትክልት ስፍራውን በተመለከተ የወዳጄን ዘፈን እዘፍንለታለሁ። የእኔ ውድ ወዳጄ በጣም ፍሬያማ ኮረብታ ውስጥ የአትክልት ስፍራ አለው።
፪ እናም አጠረው፣ በውስጡ ያሉ ድንጋዮችንም ሰብስቦ አወጣና፣ የተመረጠውን ወይን ተከለ፣ በመካከሉም ግንብን ገነባ፣ ደግሞም በውስጡ የወይን መጭመቂያ ሰራ፤ እናም ወይኑ ያፈራ ዘንድ ጠበቀው፣ የበረሃ ወይንንም አወጣ።
፫ እናም አሁን፣ በኢየሩሳሌም የምትኖሩና የይሁዳ ሰዎች ሆይ፣ በእኔና በወይን የአትክልት ስፍራዬ መካከል እንድትፈርዱ እጠይቃችኋለሁ።
፬ እኔ ያላደረግኩት በወይን የአትክልት ስፍራዬ ውስጥ ሊደረግ የሚገባ ነገር ምን ነበር? ስለዚህ፣ ወይን ያፈራል ብዬ በጠበቅሁት ጊዜ የበረሃ ወይንን አፈራ።
፭ እናም አሁን ሂዱ፤ የወይን አትክልት ስፍራዬን ምን እንደማደርገው እነግራችኋለሁ—አጥሩን እነቅላለሁ፣ ይህም ይበላል፤ እናም በዚያ ያለውን ግድግዳ አፈርሳለሁ፣ ለመራገጫም ይሆናል፤
፮ እናም እኔ አጠፋዋለሁ፤ አይከረከምም ወይም አይቆፈርም፤ ነገር ግን አረምና እሾህ ይበቅልበታል፤ እናም ደግሞ ደመናን በእርሱ ላይ ዝናብ ደግመው እንዳያዘንቡ አዛለሁ።
፯ የሰራዊት ጌታ የወይን አትክልት ስፍራ የእስራኤል ቤት ነውና፣ የደስታውም አትክልት የይሁዳ ሰዎች ናቸው፤ እናም ፍትህን ፈለገ፣ ነገር ግን እነሆ፣ ግፍ አየ፤ ፅድቅን ፈለገ፣ ነገር ግን ልቅሶ ሰማ።
፰ ቦታ እስኪጠፋና እራሳቸው በምድር መካከል ብቻቸውን እስኪቀሩ ድረስ ቤትን ከቤት ለሚያገናኙ ወዮላቸው!
፱ የሰራዊት ጌታ እንዲህ ብሎ ሲምል በጆሮዬ ሰማሁት፣ በእውነት ብዙ ቤቶች ባዶ ይሆናሉ፣ እናም ታላቅና የሚያምሩ ከተሞችም ያለነዋሪዎች ይሆናሉ።
፲ አዎን፣ ከወይኑ ቦታ አስር ጥማድ በሬ ካረሰው አንድ የባዶስ መስፈሪያ ብቻ ይወጣል፣ እናም አንድ የቆሮስ መስፈሪያ ዘር አንድ የኢፍ መስፈሪያ ይሰጣል።
፲፩ በማለዳ ተነስተው ሃይለኛ መጠጥ ለሚፈልጉ፣ እስከማታም ቀጥለው፣ እናም በወይን ለሚሰክሩ ወዮላቸው!
፲፪ እናም መሰንቆና፣ በገና፣ ከበሮና፣ እምቢልታም፣ የወይን ጠጅም በግብዣቸው አለ፤ የጌታን ስራ ግን አልተመለከቱም፣ እጁም ያደረገውን አላስተዋሉም።
፲፫ ስለዚህ፣ ሕዝቦቼ ምንም እውቀት ስለሌላቸው በግዞት ተይዘዋል፤ እናም የተከበሩት ሰዎቻቸው ተርበዋል፣ ሕዝቡም ደግሞ በጥማት ደርቋል።
፲፬ ስለዚህ፣ ሲዖል ራሷን አስፍታለች፣ እናም አፍዋን ያለገደብ ከፍታለች፤ እናም የእነርሱ ክብርና፣ ሕዝባቸው፣ ውበታቸውም፣ እናም ያ የሚደሰተውም፣ ወደ እርሷ ይወርዳል።
፲፭ እናም ተራው ሰው ዝቅ ይላል፣ ታላቁም ሰው ትሁት ይሆናል፣ የኩራተኞች ዐይን ትሁት ትሆናለች።
፲፮ ነገር ግን የሠራዊት ጌታ በፍርዱ ይከብራል፣ እናም ቅዱስ የሆነው እግዚአብሔር በፅድቁ ይቀደሳል።
፲፯ ከዚያም በጎቹ እንደተለመደው ይመገባሉ፣ እንግዶችም የሰቡትን ባድማ ይበላሉ።
፲፰ በግብዝነት ገመድ በደልን፣ እና ኃጢያትንም በሰረገላ ማሰሪያ ይመስል ወደ ራሳቸው ለሚስቡ ወዮላቸው፤
፲፱ እናም ያፍጥን፣ ስራውን ያስቸኩል፣ እኛ እንድናየው፤ እናም የእስራኤሉን ቅዱስ ምክርም እኛ እናውቀው ዘንድ ይቅረብ ለሚሉትም ወዮላቸው።
፳ መጥፎውን መልካም የሚሉ፣ እናም ጥሩውን መጥፎ የሚሉ፣ ጨለማን ብርሃን፣ ብርሃንን ጨለማ፣ መራራውን ጣፋጭ፣ ጣፋጩን መራራ ለሚሉትም ወዮላቸው!
፳፩ በራሳቸው ዐይን ብልህና አስተዋይ ለሆኑት ወዮላቸው!
፳፪ የወይን ጠጅ ለመጠጣት ኃያላንና፣ ጠንካራ መጠጦችን በመደባለቅ ለበረቱት ሰዎች ወዮላቸው፤
፳፫ በደለኛውን ስለ ጉቦ ጻድቅ ለሚያደርጉ፥ የጻድቁንም ጽድቅ ለሚያስወግዱበት ወዮላቸው!
፳፬ ስለዚህ፣ የእሳት ወላፈን ቃርሚያን እንደሚበላ፣ እና እብቅም በነበልባል እንደሚጠፋ፣ ስራቸው የበሰበሰ ይሆናል፣ ቡቃያቸውም እንደትቢያ ይበናል፤ የእግዚአብሔርን የሰራዊት ጌታን ህግ ጥለዋልና፣ የእስራኤሉንም ቅዱስ ቃል ንቀዋልና።
፳፭ ስለዚህ፣ የጌታ ቁጣ በሕዝቡ ላይ ነድዶአል፣ እጁንም በእነርሱ ላይ ዘርግቷል፣ እናም መትቶአቸዋል፤ ተራሮች ተንቀጥቅጠዋል፣ ሬሳዎቻቸውም በመንገዶቻቸው መካከል ተከፍተዋል። በዚህ ሁሉ ግን ቁጣው አልበረደችም፣ ነገር ግን አሁንም እጁን እንደዘረጋ ነው።
፳፮ እናም ለሃገሮች ሁሉ ከሩቅ ምልክትን ያነሳል፣ ከምድር ዳርቻ ይመጡም ዘንድ በፉጨት ይጠራቸዋል፤ እናም እነሆ፣ እነርሱ እየተጣደፉ በፍጥነት ይመጣሉ፤ በመካከላቸውም ደካማና ስንኩል አይኖርም።
፳፯ የሚያንቀላፋም ሆነ የሚተኛ የለም፤ የወገባቸውም መቀነት አይፈታም፣ የጫማቸውም ማሰሪያ አይበጠስም፤
፳፰ ፍላፃዎቻቸው ስለታም ይሆናሉ፣ ቀስቶቻቸውም ሁሉ ተወጥረዋል፣ የፈረሶቻቸው ኮቴ እንደ ባልጩት እና ተሽከርካሪዎቻቸውም እንደአውሎ ነፋስ ይቆጠራሉ፣ ጩኸታቸውም እንደአንበሳ ነው።
፳፱ እንደ አንበሳ ደቦሎች ይጮሃሉ፤ አዎን፣ ይገሳሉም፣ ያዳኑአቸውንም አጥብቀው ይይዛሉ፣ እና በጥንቃቄም ይዘዋቸው ይሄዳሉ፣ ማንም አያድናቸውም።
፴ እናም በዚያ ቀን እንደ ባሕር ጩኸት ይጮሁባቸዋል፤ ወደ ምድር ቢመለከቱ፣ እነሆ ጨለማና መከራን ይመለከታሉ፣ እናም ብርሃንም በዚያም ሰማያት ውስጥ ጨልሟል።