ቅዱሳት መጻህፍት
፪ ኔፊ ፲፭


ምዕራፍ ፲፭

የጌታ የወይን አትክልት ስፍራ (እስራኤል) ባዶ ይሆናል፣ እናም የእርሱ ሕዝቦች ይበተናሉ—በአመፃና በመበተናቸው ጊዜ መከራ በእነርሱ ላይ ይመጣል—ጌታም ምልክቱን ያነሳል እናም እስራኤልን ይሰበስባል—ኢሳይያስ ፭ን አነጻፅሩ። ከ፭፻፶፱–፭፻፵፭ ም.ዓ. ገደማ።

እናም ከዚያ ለውድ ወዳጄ የወይን አትክልት ስፍራውን በተመለከተ የወዳጄን ዘፈን እዘፍንለታለሁ። የእኔ ውድ ወዳጄ በጣም ፍሬያማ ኮረብታ ውስጥ የአትክልት ስፍራ አለው።

እናም አጠረው፣ በውስጡ ያሉ ድንጋዮችንም ሰብስቦ አወጣና፣ የተመረጠውን ወይን ተከለ፣ በመካከሉም ግንብን ገነባ፣ ደግሞም በውስጡ የወይን መጭመቂያ ሰራ፤ እናም ወይኑ ያፈራ ዘንድ ጠበቀው፣ የበረሃ ወይንንም አወጣ።

እናም አሁን፣ በኢየሩሳሌም የምትኖሩና የይሁዳ ሰዎች ሆይ፣ በእኔና በወይን የአትክልት ስፍራዬ መካከል እንድትፈርዱ እጠይቃችኋለሁ።

እኔ ያላደረግኩት በወይን የአትክልት ስፍራዬ ውስጥ ሊደረግ የሚገባ ነገር ምን ነበር? ስለዚህ፣ ወይን ያፈራል ብዬ በጠበቅሁት ጊዜ የበረሃ ወይንን አፈራ።

እናም አሁን ሂዱ፤ የወይን አትክልት ስፍራዬን ምን እንደማደርገው እነግራችኋለሁ—አጥሩን እነቅላለሁ፣ ይህም ይበላል፤ እናም በዚያ ያለውን ግድግዳ አፈርሳለሁ፣ ለመራገጫም ይሆናል፤

እናም እኔ አጠፋዋለሁ፤ አይከረከምም ወይም አይቆፈርም፤ ነገር ግን አረምና እሾህ ይበቅልበታል፤ እናም ደግሞ ደመናን በእርሱ ላይ ዝናብ ደግመው እንዳያዘንቡ አዛለሁ።

የሰራዊት ጌታ የወይን አትክልት ስፍራ የእስራኤል ቤት ነውና፣ የደስታውም አትክልት የይሁዳ ሰዎች ናቸው፤ እናም ፍትህን ፈለገ፣ ነገር ግን እነሆ፣ ግፍ አየ፤ ፅድቅን ፈለገ፣ ነገር ግን ልቅሶ ሰማ።

ቦታ እስኪጠፋና እራሳቸው በምድር መካከል ብቻቸውን እስኪቀሩ ድረስ ቤትን ከቤት ለሚያገናኙ ወዮላቸው!

የሰራዊት ጌታ እንዲህ ብሎ ሲምል በጆሮዬ ሰማሁት፣ በእውነት ብዙ ቤቶች ባዶ ይሆናሉ፣ እናም ታላቅና የሚያምሩ ከተሞችም ያለነዋሪዎች ይሆናሉ።

አዎን፣ ከወይኑ ቦታ አስር ጥማድ በሬ ካረሰው አንድ የባዶስ መስፈሪያ ብቻ ይወጣል፣ እናም አንድ የቆሮስ መስፈሪያ ዘር አንድ የኢፍ መስፈሪያ ይሰጣል።

፲፩ በማለዳ ተነስተው ሃይለኛ መጠጥ ለሚፈልጉ፣ እስከማታም ቀጥለው፣ እናም በወይን ለሚሰክሩ ወዮላቸው!

፲፪ እናም መሰንቆና፣ በገና፣ ከበሮና፣ እምቢልታም፣ የወይን ጠጅም በግብዣቸው አለ፤ የጌታን ስራ ግን አልተመለከቱም፣ እጁም ያደረገውን አላስተዋሉም።

፲፫ ስለዚህ፣ ሕዝቦቼ ምንም እውቀት ስለሌላቸው በግዞት ተይዘዋል፤ እናም የተከበሩት ሰዎቻቸው ተርበዋል፣ ሕዝቡም ደግሞ በጥማት ደርቋል።

፲፬ ስለዚህ፣ ሲዖል ራሷን አስፍታለች፣ እናም አፍዋን ያለገደብ ከፍታለች፤ እናም የእነርሱ ክብርና፣ ሕዝባቸው፣ ውበታቸውም፣ እናም ያ የሚደሰተውም፣ ወደ እርሷ ይወርዳል።

፲፭ እናም ተራው ሰው ዝቅ ይላል፣ ታላቁም ሰው ትሁት ይሆናል፣ የኩራተኞች ዐይን ትሁት ትሆናለች።

፲፮ ነገር ግን የሠራዊት ጌታ በፍርዱ ይከብራል፣ እናም ቅዱስ የሆነው እግዚአብሔር በፅድቁ ይቀደሳል።

፲፯ ከዚያም በጎቹ እንደተለመደው ይመገባሉ፣ እንግዶችም የሰቡትን ባድማ ይበላሉ።

፲፰ በግብዝነት ገመድ በደልን፣ እና ኃጢያትንም በሰረገላ ማሰሪያ ይመስል ወደ ራሳቸው ለሚስቡ ወዮላቸው፤

፲፱ እናም ያፍጥን፣ ስራውን ያስቸኩል፣ እኛ እንድናየው፤ እናም የእስራኤሉን ቅዱስ ምክርም እኛ እናውቀው ዘንድ ይቅረብ ለሚሉትም ወዮላቸው።

መጥፎውን መልካም የሚሉ፣ እናም ጥሩውን መጥፎ የሚሉ፣ ጨለማን ብርሃን፣ ብርሃንን ጨለማ፣ መራራውን ጣፋጭ፣ ጣፋጩን መራራ ለሚሉትም ወዮላቸው!

፳፩ በራሳቸው ዐይን ብልህና አስተዋይ ለሆኑት ወዮላቸው!

፳፪ የወይን ጠጅ ለመጠጣት ኃያላንና፣ ጠንካራ መጠጦችን በመደባለቅ ለበረቱት ሰዎች ወዮላቸው፤

፳፫ በደለኛውን ስለ ጉቦ ጻድቅ ለሚያደርጉ፥ የጻድቁንም ጽድቅ ለሚያስወግዱበት ወዮላቸው!

፳፬ ስለዚህ፣ የእሳት ወላፈን ቃርሚያን እንደሚበላ፣ እና እብቅም በነበልባል እንደሚጠፋ፣ ስራቸው የበሰበሰ ይሆናል፣ ቡቃያቸውም እንደትቢያ ይበናል፤ የእግዚአብሔርን የሰራዊት ጌታን ህግ ጥለዋልና፣ የእስራኤሉንም ቅዱስ ቃል ንቀዋልና

፳፭ ስለዚህ፣ የጌታ ቁጣ በሕዝቡ ላይ ነድዶአል፣ እጁንም በእነርሱ ላይ ዘርግቷል፣ እናም መትቶአቸዋል፤ ተራሮች ተንቀጥቅጠዋል፣ ሬሳዎቻቸውም በመንገዶቻቸው መካከል ተከፍተዋል። በዚህ ሁሉ ግን ቁጣው አልበረደችም፣ ነገር ግን አሁንም እጁን እንደዘረጋ ነው።

፳፮ እናም ለሃገሮች ሁሉ ከሩቅ ምልክትን ያነሳል፣ ከምድር ዳርቻ ይመጡም ዘንድ በፉጨት ይጠራቸዋል፤ እናም እነሆ፣ እነርሱ እየተጣደፉ በፍጥነት ይመጣሉ፤ በመካከላቸውም ደካማና ስንኩል አይኖርም።

፳፯ የሚያንቀላፋም ሆነ የሚተኛ የለም፤ የወገባቸውም መቀነት አይፈታም፣ የጫማቸውም ማሰሪያ አይበጠስም፤

፳፰ ፍላፃዎቻቸው ስለታም ይሆናሉ፣ ቀስቶቻቸውም ሁሉ ተወጥረዋል፣ የፈረሶቻቸው ኮቴ እንደ ባልጩት እና ተሽከርካሪዎቻቸውም እንደአውሎ ነፋስ ይቆጠራሉ፣ ጩኸታቸውም እንደአንበሳ ነው።

፳፱ እንደ አንበሳ ደቦሎች ይጮሃሉ፤ አዎን፣ ይገሳሉም፣ ያዳኑአቸውንም አጥብቀው ይይዛሉ፣ እና በጥንቃቄም ይዘዋቸው ይሄዳሉ፣ ማንም አያድናቸውም።

እናም በዚያ ቀን እንደ ባሕር ጩኸት ይጮሁባቸዋል፤ ወደ ምድር ቢመለከቱ፣ እነሆ ጨለማና መከራን ይመለከታሉ፣ እናም ብርሃንም በዚያም ሰማያት ውስጥ ጨልሟል።