ቅዱሳት መጻህፍት
፪ ኔፊ ፰


ምዕራፍ ፰

ያዕቆብ ከኢሳይያስ ማንበብ ቀጠለ፥ በመጨረሻዎቹ ቀናት፣ ጌታ ፅዮንን ያፅናናል እንዲሁም እስራኤልን ይሰበስባል—የዳኑትም ወደ ፅዮን በታላቅ ደስታ ተከበው ይመጣሉ—ኢሳይያስ ፶፩ እና ፶፪፥፩–፪ን አነጻፅሩ። ከ፭፻፶፱–፭፻፵፭ ም.ዓ. ገደማ።

፩ እናንተ ፅድቅን የምትከተሉ ስሙኝ። የተቆረጣችሁበትን ድንጋይ፣ እንዲሁም የተቆፈራችሁበትን ጉድጓድ ተመልከቱ።

፪ ወደ አባታችሁ አብርሃምና ወደ ወለደቻችሁ ሣራ ተመልከቱ፤ ብቻውን ጠራሁት፣ እናም ባረክሁትም።

፫ ጌታ ፅዮንን ያፅናናል፣ በእርሷ ባድማ የሆነውን ቦታ ሁሉ ያፅናናል፤ እናም ምድረበዳዋንም እንደ ዔድን፣ እናም በረሃዋን እንደ ጌታ የአትክልት ስፍራ ያደርገዋል። ደስታና ተድላ፣ ምስጋና እና የዝማሬ ድምፅ ይገኝባታል።

፬ ሕዝቤ ሆይ፥ አድምጡኝ፤ ወገኔ ሆይ፣ ስሙኝ፤ ህግ ከእኔ ይወጣልና፣ እና ፍርዴን ለህዝብ እንደ ብርሃን እንዲያርፍ አደርጋለሁ።

፭ ፅድቄ ቀርቧል፤ ማዳኔም ወጥቷል፣ እናም ክንዴ በህዝቡ ይፈርዳል። ደሴቶች እኔን ይጠባበቃሉ፣ እናም በክንዴ ይታመናሉ።

፮ ዐይኖቻችሁን ወደ ሰማያት አንሱ፣ እናም ወደታች ወደ ምድር ተመልከቱ፤ ሰማያት እንደጢስ በንነው ይጠፋሉ፣ ምድርም እንደልብስ ታረጃለች፤ እናም የሚኖሩባት እንዲሁ ይሞታሉ። ነገር ግን ማዳኔ ለዘለዓለም ይሆናል፣ ፅድቄም አይፈርስም።

፯ ፅድቅን የምታውቁ፣ ህጌንም በልባችሁ የፃፍኩባችሁ እኔን አድምጡኝ፣ የሰዎችን ዘለፋ አትፍሩ፣ ወይም ስድባቸውንም አትፍሩ።

፰ እንደልብስም ብል ይበላቸዋልና፣ እናም ትል እንደሱፍ ይበላቸዋል። ነገር ግን ፅድቄ ለዘለዓለም፣ እናም ማዳኔ ከትውልድ ወደ ትውልድ ይሆናል።

፱ የእግዚአብሔር ክንድ ሆይ ተነስ! ተነስ! ኃይልንም ልበስ፣ እንደጥንቱ ቀናት ተነሳ። ረዓብን የቆራረጥክ፣ ዘንዶውንም የወጋህ አንተ አይደለህምን?

፲ ባህሩን፣ የታላቁን ጥልቅ ውሃ ያደረቅህ፣ የዳኑትም ይሻገሩ ዘንድ ጥልቁን ባህር መንገድ ያደረግህ አንተ አይደለህምን?

፲፩ ስለዚህ፣ ጌታ ያዳናቸው ይመለሳሉ፣ በዝማሬም ወደ ፅዮን ይመጣሉ፤ እናም የዘለዓለም ደስታና ቅዱስነት በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ እናም ደስታና ተድላን ያገኛሉ፤ ሀዘንና ልቅሶም ይሸሻሉ።

፲፪ እኔ እርሱ ነኝ፤ የማፅናናችሁ እኔ ነኝ። እነሆ፣ የሚሞተውን ሰውና እንደሳርም የሚሆነውን የሰው ልጅ ትፈራ ዘንድ አንተ ማን ነህ?

፲፫ እናም ሰማያትን የዘረጋውንና፣ የምድርን መሰረት የሰራውን፣ ጌታ ፈጣሪህን ረሳህ፣ እናም ሊያጠፉህ የተዘጋጁ ይመስል በአስጨናቂዎችህ ቁጣ ምክንያት ሁልጊዜ ቀኑን ሁሉ ፈራህ? እናም የአስጨናቂዎችህ ቁጣ የት አለ?

፲፬ ምርኮኛ እንዲፈታ፣ እና እርሱ በጉድጓድ እንዳይሞት፣ ወይም እንጀራም አይጐድልበት ይፈጥናል።

፲፭ ነገር ግን ሞገዱም እንዲተምም ባሕርን የማናውጥ ጌታ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤ ስሜም የሰራዊት ጌታ ነው።

፲፮ እናም ሰማያትን እዘረጋና ምድርንም እመሰርት ዘንድ፣ እናም ለፅዮን፣ እነሆ፣ አንቺ ህዝቤ ነሽ እንድላት ቃሌን በአፍህ አድርጌአለሁ፣ እንዲሁም በእጄ ጥላ ጋርጄሃለሁ።

፲፯ ከጌታ እጅ የቁጣውን አተላ በፅዋ የጠጣሽ ኢየሩሳሌም ሆይ ንቂ፣ ንቂ፣ ቁሚ፣ ከሚያንገደግድ ዋንጫ መራራን ጠጥተሻል—

፲፰ እናም ከወለደቻቸው ወንዶች ልጆች ሁሉ መካከል የሚመራትም የለም፤ ካሳደገቻቸውም ልጆች ሁሉ እጅዋን የሚይዝ የለም።

፲፱ እነዚህ ሁለቱ ወንዶች ልጆች ወደ አንቺ ይመጣሉ፣ ላንቺ ማን ያዝንልሻል—መደምሰስሽና መውደምሽ፣ ረሃብና ሰይፍም—እንዲሁም በማን አፅናናሻለሁ?

፳ ከእነዚህ ከሁለቱ በስተቀር ወንዶች ልጆችሽ ዝለዋል፤ በአደባባይ ላይ ተኝተዋል፤ በወጥመድ እንዳለ የሜዳ ኮርማ በጌታ ቁጣ፣ በአምላክሽ ተግሳፅ ተሞልተዋል።

፳፩ ስለዚህ አሁን ይህን ስሚ፣ አንቺ ተሰቃዪና ያለ ወይን ጠጅ የሰከርሽ፥

፳፪ ጌታሽ ይላል፣ ጌታ እና አምላክሽ የወገኑ ጉዳይ ይማፀናል፤ እነሆ፣ የሚያንገደግድን ፅዋ፣ የቁጣዬንም ዋንጫ አተላውን ከእጅሽ ወስጃለሁ፣ ደግመሽም ከእንግዲህ አትጠጪውም።

፳፫ ነገር ግን ነፍስሽን እንሻገር ዘንድ ዝቅ በይ በሚሉት በአስጨናቂዎችሽ እጅ አኖረዋለሁ፥ እናም ሰውነትሽንም ለሚሻገሩበት እንደ መሬት መንገድ አድርገሽ ዘርግተሽዋል።

፳፬ ፅዮን ሆይ ንቂ፣ ንቂ ሀይልሽን ልበሺ፤ ቅድስት ከተማ ኢየሩሳሌም ሆይ፣ ቆንጆ ልብስሽን ልበሺ፤ ያልተገረዘና እርኩስ ከእንግዲህ አይገባብሽምና።

፳፭ ትቢያን አራግፊ፤ ኢየሩሳሌም ሆይ፣ ተነሺ፣ ተቀመጪ፤ ምርኮኛይቱ የፅዮን ሴት ልጅ ሆይ የአንገትሽን እስራት እራስሽ ፍቺ።