ቅዱሳት መጻህፍት
፪ ኔፊ ፲፪


ምዕራፍ ፲፪

ኢሳይያስ የኋለኛውን ቀን ቤተመቅደስ፤ የእስራኤልን መሰብሰብና የአንድ ሺህ ዘመን ፍርድን እና ሰላምን ተመለከተ—በዳግም ምፅአቱ ኩራተኞችና ኃጢአተኞች ትሁት ይሆናሉ—ኢሳይያስ ፪ አነጻፅሩ። ከ፭፻፶፱–፭፻፵፭ ም.ዓ. ገደማ።

፩ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ቃል—

፪ እናም በኋለኛው ቀናት እንዲህ ይሆናል፣ የጌታ ቤት ተራራ በተራሮች ጫፍ ላይ ሲመሰረት፣ እናም ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ሲል፣ ህዝቦችም ሁሉ ወደ እርሱ ይሰበሰባሉ።

፫ ከእዚያም ብዙ ህዝብ ሄደው እንዲህ ይላል፣ ኑና ወደ ጌታ ተራራ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እናም እርሱ መንገዱን ያስተምረናልና፣ በጎዳናው እንራመዳለን፣ ህግ ከፅዮን፣ የጌታም ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና።

፬ እናም እርሱ በሃገሮች መካከል ይፈርዳል፣ ብዙ ህዝቦችንም ይገስፃል፣ እናም ሰይፋቸውን ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ—ሀገርም በሃገር ላይ ሰይፍ አያነሳም፣ ጦርነትም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።

፭ የያዕቆብ ቤት ሆይ፣ ኑ በጌታ ብርሃን እንራመድ፤ አዎን፣ ኑ ሁላችሁም ተቅበዝብዛችኋልና፣ እያንዳንዱም በኃጢያት ወደገዛ መንገዱ አዘነበለ።

፮ ስለዚህ፣ አቤቱ ጌታ፣ ሕዝብህን የያዕቆብን ቤት ትተሃል፣ ምክንያቱም እነርሱ የምስራቅን ሰዎች ልምድ ስለተሞሉና፣ እንደ ፍልስጤማውያን ምዋርተኞችን ስለሚያዳምጡ፣ እና በባዕድ ልጆች እራሳቸውን ስላስደሰቱ ነው።

፯ ምድራቸውም ደግሞ በብርና በወርቅ ተሞልታለች፣ ለመዛግብቶቻቸውም ፍጻሜ የለውም፤ ምድራቸውም ደግሞ በፈረሶች ተሞልታለች፣ ሰረገሎቻቸውም ፍፃሜ የላቸውም።

፰ ምድራቸውም ደግሞ በጣዖት ተሞልታለች፤ በጣቶቻቸውም ለሰሩት ለእጃቸው ስራ ይሰግዳሉ።

፱ እናም ተራው ሰው አልሰገደም፣ እናም ታላቁም ሰው እራሱን ትሁት አላደረገም፣ ስለዚህ፣ ይቅር አትበለው።

፲ እናንተ ክፉዎች ሆይ ወደ ድንጋዩ ዋሻ ግቡ፣ እናም በመሬት ውስጥም ተሸሸጉ፣ ምክንያቱም የጌታ ፍርሃትና የክብሩ ሞገስ ክብሩ ይመታችኋል።

፲፩ እናም እንዲህ ሆነ ኩራት የሆነው የሰው አመለካከት አልባሌ ይሆናል፣ የሰዎችም ትዕቢት ዝቅ ትላለች፣ እናም ጌታ ብቻውን በዚያ ቀን ከፍ ከፍ ይላል።

፲፪ የሰራዊት ጌታ ቀን በሁሉም ሀገር ላይ፣ አዎን፣ በማንኛውም ላይ፣ አዎን፣ በትዕቢተኛውና በኩራተኛው ላይና፣ ከፍ ባለውም ላይ ሁሉ በቅርቡ ይመጣልና፣ እናም እርሱም ይዋረዳል።

፲፫ አዎን፣ እናም የጌታ ቀን በሊባኖስ ዝግባዎች ላይ ሁሉ ይመጣል፣ ምክንያቱም እነርሱ ከፍና ኮራ ብለዋልና፤ እናም በበሳንም ዛፍ ሁሉ ላይ፤

፲፬ እናም ከፍ ባሉት ተራሮች ላይ ሁሉ፣ እናም በኮረብታዎች ላይ ሁሉ፣ እና በኮሩት ሀገሮች ሁሉ ላይ፣ እናም በማንኛውም ሀገር ላይ፤

፲፭ እናም በማንኛውም ረጅም ግንብና፣ በተመሸገውም ቅጥር ላይ ይመጣል፤

፲፮ እናም በባህሩ መርከቦች ላይ ሁሉና፣ በተርሴስ መርከብ ላይ ሁሉ፣ እናም አስደሳች ምስሎች ላይ ሁሉ።

፲፯ እናም የሰው የኩራት አመለካከት ይወድቃልና፣ የሰዎች ዕብሪትም ይዋረዳል፤ እናም በዚያም ቀን ጌታ ብቻውን ከፍ ከፍ ይላል።

፲፰ እናም ጣዖቶችን ፈፅሞ ያጠፋል።

፲፱ እናም እነርሱ ጌታ ምድርን በከፍተኛ ሁኔታ ያናውጥ ዘንድ በተነሣ ጊዜ ወደ ድንጋይ ጉድጓዶችና፣ ወደ ምድር ዋሻዎች ይገባሉ፣ የጌታ ፍርሃት ይመጣባቸዋልና፣ እናም የእርሱ ግርማ ሞገሱ ክብር ይመታቸዋልና።

፳ በዚያም ቀን ሰው ይሰግድላቸው ዘንድ ያበጃቸውን የብር ጣዖቶቹን፣ እና የወርቁን ጣዖቶቹን ለፍልፈልና ለሌሊት ወፍ ይጥላል፣

፳፩ ጌታ ምድርን በከፍተኛ ሁኔታ ያናውጥ ዘንድ በተነሳ ጊዜ፣ የጌታ ፍርሃት ስለሚመጣባቸው፣ እናም የእርሱ ግርማ ሞገሱ ክብር ስለሚመታቸው ወደ ተሰነጣጠቁ የድንጋይ ዋሻና ወደ ፍርስራሽ ዓለቶች ጫፍ ይገባሉ።

፳፪ እስትንፋሱ በአፍንጫው ያለበትን ሰው ተዉት፣ እርሱ ስለ ምን ይቈጠራል?