እንደራሱ መዝገብ መሰረት፣ በጌዴዎን ከተማ አልማ ለህዝቡ የተናገረው ቃላት።
ምዕራፍ ፯ አጠቃሎ የያዘ።
ምዕራፍ ፯
ክርስቶስ ከማርያም ይወለዳል—የሞትን እስራት ይፈታል፣ እናም የሕዝቡን ኃጢያት ይሸከማል—ንስሐ የሚገቡ፣ የሚጠመቁ፣ እናም ትዕዛዛቱን የሚጠብቁ ዘለአለማዊ ህይወት ይኖራቸዋል—ርኩሰት የእግዚአብሔርን መንግስት ለመውረስ አይቻለውም—ትህትና፣ እምነት፣ ተስፋና ልግስና አስፈላጊ ናቸው። በ፹፫ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እነሆ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ ወደ እናንተ እንድመጣ እስከተፈቀደልኝ ድረስ፣ ስለሆነም በራሴ አባባል ለመናገር እሞክራለሁ፤ አዎን፣ በራሴ አንደበት፣ በራሴ ቃል ለእናንተ ለመናገር የመጀመሪያዬ በመሆኑ፣ በፍርድ ወንበር ብቻ እንድሆን በመደረጌ፣ ብዙ ስራ ስላለብኝ ወደ እናንተ ለመምጣት አልቻልኩም ነበር።
፪ እናም አሁን የፍርድ ወንበር በእኔ ቦታ ሌላው እንዲገዛ ባይሰጥ ኖሮ፣ አሁን በዚህ ጊዜ ለመምጣት አይቻለኝም ነበር፤ እናም ጌታ በታላቅ ምህረቱ ወደ እናንተ እንድመጣ ፈቅዷል።
፫ እናም እነሆ፣ እናንተ በእግዚአብሔር ፊት ራሳችሁን ዝቅ አድርጋችሁ እንዳገኛችሁ፣ ፀጋውን ያለማቋረጥ ለምናችኋል፣ እናም በፊቱ እንከን የሌላችሁ ሆናችሁ እንዳገኛችሁ፣ ወንድሞቻችን በዛራሔምላ እንደነበሩበት በመጥፎ ሁኔታ ሳትሆኑ እንዳገኛችሁ በታላቅ ተስፋና ፍላጎት መጥቻለሁ።
፬ ነገር ግን እንድረዳ ያደረገኝ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን፤ አዎን፣ እነርሱ በድጋሚ በፅድቁ ሲቋቋሙ የማወቅ እጅግ ታላቅ ደስታን ሰጥቶኛል።
፭ እናም ውስጤ ባለው የእግዚአብሔር መንፈስ መሰረት፣ በእናንተም ላይ ደግሞ ደስታ ይኖረኛል ብዬ አምናለሁ፤ ይሁን እንጂ እኔ በእናንተ ላይ ያለኝ ደስታ በዛራሔምላ በነበሩ ወንድሞች በነበረኝ ስቃይና ሀዘን ምክንያት እንዲመጣ አልፈልግም፤ እነሆ፣ በእነርሱ ላይ የነበረኝ ደስታዬ የመጣው በብዙ መከራና ስቃይ ከተገፋሁ በኋላ ነበር።
፮ ነገር ግን እነሆ፣ እናንተ ግን እንደ ወንድሞቻችሁ ባለማመን ሁኔታ ውስጥ እንዳልሆናችሁ አምናለሁ፤ በልባችሁ ኩራት እንደማትወጠሩም አምናለሁ፤ አዎን፣ ልባችሁን በሀብት ላይ እናም በዓለም ከንቱ ነገሮች ላይ እንደማታደርጉት አምናለሁ፤ አዎን፣ ጣዖትን እንደማታመልኩ፣ ነገር ግን እውነተኛውንና ሕያው እግዚአብሔርን እንደምታመልኩ፣ እናም የሚመጣውን የኃጢአታችሁ ስርየትን ዘለአለማዊ በሆነው እምነት እንደምትጠብቁ አምናለሁ።
፯ እነሆም፣ ብዙ ነገር ይመጣል እላችኋለሁ፤ እናም እነሆ፣ ከሁሉም የበለጠ አንድ ነገር አለ—እነሆም አዳኙ የሚመጣበትና ከህዝቡ ጋር የሚኖርበት ጊዜ ሩቅ አይደለም።
፰ እነሆ በስጋ ሰውነቱ በሚኖርበት ጊዜ በመካከላችን ይገኛል አልልም፤ እነሆም መንፈስም ሁኔታው ይህ ነው አላለኝም። አሁን ይህንን በተመለከተ አላውቅም፤ ነገር ግን እስከዚህ ድረስ አውቃለሁ፣ ጌታ እግዚአብሔር ቃሉ መሰረት ሁሉንም ነገሮች ለማድረግ ሀይል እንዳለው አውቃለሁ።
፱ ነገር ግን እነሆ፣ መንፈስ እንዲህ በማለት ይህን ያህል ተናግሮኛል፤ ወደ ህዝቡ እንዲህ ስትል ጩህ—ንስሐ ግቡ፣ እናም የጌታን መንገድ አዘጋጁና፣ ቀጭን በሆኑት ጎዳናዎች ተራመዱ፤ እነሆም፣ መንግስተ ሰማያት ቀርባለችና እናም የእግዚአብሔር ልጅ በምድር ፊት ይመጣል።
፲ እናም እነሆ፣ እርሱም ከማርያም በቅድመ አባቶቻችን ምድር በሆነችው በኢየሩሳሌም ይወለዳል፣ እርሷም ድንግል፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በመሸፈን፣ የተከበረች እንዲሁም የተመረጠች ዕቃ ሆና በመፀነስ ወንድ ልጅ፣ አዎን እንዲሁም የእግዚአብሔር ልጅ፣ ትወልዳለች።
፲፩ እናም በመከራና በሁሉም ዓይነት ህመምና ፈተናዎች በመሰቃየት ይሄዳል፤ የህዝቡን ህመምና በሽታ በራሱ ላይ ይወስዳል የሚለውን ቃል ይፈፀም ዘንድ ይህ ይሆናል።
፲፪ እናም ህዝቡን ያሰረውን የሞት እስር ይፈታ ዘንድ ሞትን በራሱ ላይ ይወስዳል፣ እናም በስጋ አንጀቱ በምህረት ይሞላ ዘንድ፣ በስጋ ህዝቡን ከድካሙ እንዴት እንደሚረዳ ያውቅ ዘንድ ድካማቸውን በራሱ ላይ ያደርጋል።
፲፫ እንግዲህ መንፈስ ሁሉን ነገር ያውቃል፤ ይሁን እንጂ የእግዚአብሔር ልጅ ሰዎችን በማዳን ኃይሉ መተላለፋቸውን ይሰርይላቸው ዘንድ የህዝቡንም ኃጢያት በራሱ ላይ ያደርግ ዘንድ በስጋው ይሰቃያል፤ እናም አሁን እነሆ በእኔ ያለው ምስክርነት ይህ ነው።
፲፬ እንግዲህ እናንተ ንስሐ መግባትና፣ በድጋሚ መወለድ አለባችሁ እላለሁ፤ መንፈስም በድጋሚ ካልተወለዳችሁ መንግስተ ሰማያትን መውረስ አትችሉም ይላልና፤ ስለዚህ ከኃጢአታችሁ ትነፁ ዘንድ የዓለምን ኃጢያት በወሰደው፣ ለማዳንና መጥፎ ከሆኑት ሁሉ ለማፅዳት ኃያል በሆነው በእግዚአብሔር በግ እምነት ይኖራችሁ ዘንድ ኑ እናም ለንስሀ ተጠመቁ።
፲፭ አዎን ኑና አትፍሩ፣ እናም በቀላሉ የሚጎዳችሁን ማንኛውንም ኃጢያት ወደ ጥፋት እንድታመሩ የሚያደርጋችሁን አስወግዱ እላችኋለሁ፤ አዎን፣ ኑና ወደ ፊት ቀጥሉ እናም ለኃጢአታችሁ ንሰሃ ለመግባትና፣ ትእዛዛቱን ለመጠበቅ ፈቃደኛ እንደሆናችሁ፣ እናም በዚህ ቀንም ይህን ወደ ጥምቀት ውኃ በመሄድ ለእግዚአብሔር በምስክር አሳዩት።
፲፮ እናም ማንም ይህንን ቢያደርግና፣ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ቢጠብቅ ይህንኑ እንዳልኩት ያስታውሳል፤ አዎን፣ በውስጤ ያለው ቅዱስ መንፈስ በመሰከረልኝ መሰረት ዘለአለማዊ ህይወት እንደሚኖረው የተናገርኩትን ያስታውሳል።
፲፯ እናም አሁን የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ እነዚህን ነገሮች ታምናላችሁን? እነሆ፣ እላችኋለሁ፣ አዎን እነርሱን ማመናችሁን አውቃለሁ፤ እናም እነርሱን ማመናችሁን የማውቀው በውስጤ ባለው መንፈስ መገለጥ ነው። እናም አሁን ይህን በተመለከተ፣ አዎን፣ እኔ የተናገርኳቸውንም በተመለከተ እምነታችሁ ጠንካራ በመሆኑ ደስታዬ ታላቅ ነው።
፲፰ ከመጀመሪያ ጀምሮ እንደተናገርኳችሁ፣ እንደ ወንድሞቻችሁ በተደናበረ ሁኔታ እንዳትሆኑ በጣም ፈልጌ ነበር፣ እንዲሁም የእኔም ፍላጎት አጥጋቢ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
፲፱ እናንተ በፅድቅ ጎዳና እንደሆናችሁ ተገንዝቤአለሁና፤ ወደ እግዚአብሔርም መንግስት በሆነው ጎዳና ላይ እንደሆናችሁ እገነዘባለሁ፤ አዎን፣ የእርሱንም ጎዳና የቀና እንደምታደርጉት እገነዘባለሁ።
፳ በጠማማው መንገድ እንደማይራመድ፣ ከተናገረው ፈቀቅ እንደማይል፣ ከቀኝ ወደ ግራም፣ ወይም ከትክክለኛው ወደተሳሳተው በመዞር ጥላ አንደማይኖረውም፣ ስለዚህ ጎዳናውም አንድ ዘለአለማዊ ዙሪያ እንደሆነ በቃሉ ምስክርነት ለእናንተ የታወቀ እንደሆነ ተገንዝቤአለሁ።
፳፩ እናም እርሱ ቅዱስ ባልሆነ መቅደስ ውስጥ አይኖርም፤ የረከሰም ይሁን ንፁህ ያልሆነ ማንኛውም በእግዚአብሔር መንግስት ተቀባይነት የለውም፤ ስለዚህ ጊዜው ይመጣል፣ አዎን፣ እና ይህም በመጨረሻ ቀን ይሆናል፣ የረከሰው ረክሶ ይቀራል እላችኋለሁ።
፳፪ እናም አሁን የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ ወደ እግዚአብሔር ላላችሁ ሀላፊነት ስሜታችሁን እቀሰቅሰው ዘንድ፣ በእርሱ ፊት እንከን የሌላችሁ በመሆን ትራመዱ ዘንድ፣ ተቀባይነትንም ባገኛችሁበት በእግዚአብሔር ቅዱሱ ስርዓት ትራመዱ ዘንድ፣ እነዚህን ነግሬአችኋለሁ።
፳፫ እናም አሁን ትሁትና፣ ጨዋና ታዛዥ፣ ሁሉን የምትቀበሉ፣ ታላቅ ፅናት የበዛባችሁና ታጋሽ የሆናችሁ፤ በሁሉም ነገር ራሳችሁን የምትገዙ፣ በሁሉም ጊዜ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ለመጠበቅ ትጉህ፤ የፈለጋችሁትን ነገር በመንፈስም ሆነ በስጋ የምትጠይቁ፣ ለተቀበላችሁትም ማንኛውም ነገር ሁልጊዜ ለእግዚአብሔር ምስጋና የምትስጡ እንድትሆኑ እፈልጋለሁ።
፳፬ እናም እምነት፣ ተስፋና ልግስና እንደሚኖራችሁ እርግጠኛ ሁኑ፣ እና ከዚያም ሁልጊዜ መልካም ስራን የምትሰሩ ትሆናላችሁ።
፳፭ እናም ጌታ ይባርካችሁ፣ ለዘለዓለም በመንግስተ ሰማያት እንድትቀመጡም የእነርሱ ልብስ እንከን እንደሌለው የእናንተም እንከን ሳይኖርበት፣ በመጨረሻ ከአብርሃም፣ ከይስሀቅና፣ ከያዕቆብ፣ እናም ዓለም ስትፈጠር ጀምሮ ከነበሩት ቅዱሳን ነቢያት ጋር ለመቀመጥ እንድትመጡ ዘንድ፣ ልብሳችሁን እንከን የለሽ አድርጉት።
፳፮ እናም አሁን የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ እነዚህን ቃላት የተናገርኳችሁ በውስጤ በሚመሰክረው መንፈስ መሰረት ነው፤ እናም ለቃሌ ታላቅ ትጋት በመስጠታችሁና በማዳመጣችሁ ነፍሴም እጅግ ሀሴት ታደርጋለች።
፳፯ እናም አሁን፣ የእግዚአብሔር ሰላም እንደ እምነታችሁና መልካም ስራችሁ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እስከዘለዓለም በቤታችሁና በምድራችሁና፣ በከብቶቻችሁና በመንጋዎቻችሁ ላይ እንዲሁም ባላችሁ ንብረቶች፣ በሴቶቻችሁ፣ በልጆቻችሁና በራሳችሁ ላይ ይሁን። እናም ይህንን ተናግሬአለሁ። አሜን።