ቅዱሳት መጻህፍት
አልማ ፴


ምዕራፍ ፴

ፀረ ክርስቶስ የሆነው ቆሪሆር፣ በክርስቶስ፣ በኃጢያት ክፍያው እና በትንቢት መንፈስ ተሳለቀ—እግዚአብሔር እንደሌለ፣ የሰው ልጅ መውደቅ እንደሌለ፣ ለኃጢያትም ቅጣት እንደሌለና፣ ክርስቶስ እንደሌለ አስተማረ—አልማ ክርስቶስ እንደሚመጣና ሁሉም ነገር እግዚአብሔር መኖሩን እንደሚያመለክት መሰከረ—ቆሪሆር ምልክትን ፈለገና ዲዳ ሆነ—ዲያብሎስ ለቆሪሆር እንደመልአክ ታይቶት እናም ምን ማለት እንዳለበት አስተምሮት ነበር—ቆሪሆር ተረገጠ፣ እናም ሞተ። ከ፸፮–፸፬ ም.ዓ. ገደማ።

እነሆ አሁን እንዲህ ሆነ የአሞን ህዝብ በኢየርሾን ምድር ከተቋቋሙ በኋላ፣ አዎን እናም ደግሞ ላማናውያን ከምድሪቱ ከተባረሩ እናም የሞቱባቸው በነዋሪው ከተቀበሩ በኋላ—

አሁን የሞቱባቸው ቁጥራቸው እጅግ ብዙ ስለነበር አልተቆጠሩም፤ ከኔፋውያን የሞቱትንም ለመቁጠር አይቻሉም ነበር—ነገር ግን እንዲህ ሆነ ሙታኖቻቸውን ከቀበሩ በኋላ፣ እናም ደግሞ ከፆማቸውና፣ ከሀዘናቸው፣ እንዲሁም ከፀለዩበት ቀናት በኋላ (እናም ይህም በኔፊ ህዝብ ላይ በአስራ ስድስተኛው የመሣፍንት አገዛዝ ዘመን ነበር) በምድሪቱ ላይ ሁሉ የማያቋርጥ ሰላም መሆን ጀመረ።

አዎን፣ እናም ህዝቡ የጌታን ትዕዛዛት ለመጠበቅ ጥረት አደረጉ፤ እናም በሙሴ ህግ መሰረትም የእግዚአብሔርን ስርዓቶች ለመፈፀም የሚተጉ ነበሩ፤ የሙሴን ህግም እስኪፈፀም ለመጠበቅ ተምረው ነበርና።

እናም ህዝቡ በኔፊ ህዝብ ላይ በኔፊ ህዝቦች ላይ በነገሱበት በአስራ ስድስተኛው የመሳፍንት ዘመን ውስጥ ሁሉ ምንም ሁከት አልነበረባቸውም።

እናም እንዲህ ሆነ በአስራ ሰባተኛው የመሣፍንት የንግስ ዘመንም መጀመሪያም ላይ የማያቋርጥ ሰላም ነበር።

ነገር ግን እንዲህ ሆነ በአስራ ሰባተኛው ዓመት በስተመጨረሻ አንድ ሰው ወደ ዛራሔምላ ምድር መጣ፣ እርሱም ፀረ ክርስቶስ ነበር፤ እናም ስለክርስቶስ መምጣት በነቢያቱ የተነገሩትን ትንቢቶች በመቃረን መስበክ ጀመረ።

እንግዲህ የሰዎችን እምነት የሚፃረር ህግ አልነበረም፤ ምክንያቱም ሰዎችን እኩል የማያደርግ ህግ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ፈፅሞ የተቃረነ ነውና።

ስለዚህ ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ ይላልና፥ የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ

እንግዲህ ሰው እግዚአብሔርን ለማገልገል ከፈለገ ይህ ልዩ መብቱ ነው፤ ወይም፣ በእግዚአብሔር ካመነ እርሱን ማገልገል መብቱ ነው፤ ነገር ግን በእርሱ ካላመነ እርሱን ለመቅጣት ምንም ዓይነት ህግ የለም።

ነገር ግን የሚገድል ከሆነ በሞት ይቀጣል፤ እናም ዘራፊ ከሆነም ደግሞ ይቀጣል፤ የሚሰርቅ ከሆነም ደግሞ ይቀጣል፤ እናም ዝሙትን ከፈፀመ ይቀጣል፤ አዎን ለዚህ ሁሉ ኃጢአቶች ተቀጥተዋል።

፲፩ ሰው እንደወንጀሉ የሚዳኝበት ህግ ነበርና። ይሁን እንጂ የሰውን እምነት የሚፃረር ህግ አልነበረም፤ ስለዚህ ሰው ባጠፋበት ብቻ የሚቀጣበትም ህግ ነበር፣ ስለዚህ ሰዎች ሁሉ እኩል አቋም ነበራቸው።

፲፪ እናም ይህ ቆሪሆር የሚባለው ፀረ ክርስቶስ፣ (እናም ህጉ በእርሱ ላይ መስራት የማይችለው) ክርስቶስ እንደሌለ ለህዝቡ ማስተማር ጀመረ። እናም እንዲህም በማለት ሰበከ፥

፲፫ አቤቱ በሞኝና በከንቱ ተስፋ የታሰራችሁ፣ ለምን ራሳችሁን በከንቱ ነገሮች ትገድባላችሁ? ክርስቶስንስ ለምንስ ትጠብቃላችሁ? ምክንያቱም ማንም ሰው የሚመጣውን ማንኛውንም ነገር ማወቅ አይችልም።

፲፬ እነሆ እነዚህ ትንቢት ብላችሁ የምትጠሩአቸው፣ በቅዱሳን ነቢያት ሲወርዱ መጥተዋል የምትሏቸው ነገሮች፣ እነሆ እነርሱ የአባቶቻችሁ ከንቱ ወግ ናቸው።

፲፭ እርግጠኝነታቸውን እንዴት ታውቃላችሁ? እነሆ ያላያችኋቸውን ነገሮች ለማወቅ አትችሉም፤ ስለዚህ ክርስቶስ እንደሚኖርም ለማወቅ አትችሉም።

፲፮ ወደፊትም ትመልከታላችሁ፣ እናም የኃጢአታችሁን ስርየት አየን ትላላችሁ። ነገር ግን እነሆ፣ ይህ የአዕምሮ እብደት ውጤት ነው፤ እናም ይህ የአዕምሮአችሁ እብደት የመጣው እናንተ ወዳልሆኑ እምነት በሚመራችሁ በአባቶቻችሁ ወግ ምክንያት ነው።

፲፯ እናም ለሰው ልጆች የኃጢያት ክፍያም መሆን እንደማይችል፤ ነገር ግን ማንኛውም ሰው በዚህ ህይወት እድሉን የሚወስነው እራሱ በሚያደርገው ነው እያለ እንደነዚህ ያሉ ብዙ ነገሮችን ተናገራቸው፤ ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው በተሰጥኦው ይበለፅጋል፣ እያንዳንዱም ሰው በጉልበቱ ያሸንፋል፤ እናም ማንም ሰው ያደርገው የነበረው ሁሉ ወንጀል አልነበረም።

፲፰ እናም እርሱ ህዝቡን ሰበከ፣ የብዙዎችንም ልብ አሳተ፣ በኃጢአታቸው እራሳቸውን ቀና እንዲያደርጉ አደረገ፤ አዎን ብዙ ሴቶችንና ደግሞ ወንዶችን ዝሙት እንዲፈፅሙ አደረገ—ሰው ሲሞት፣ በእዚያም ሁሉም ነገር እንደተፈጸመ ነግሯቸዋል።

፲፱ እንግዲህ ይህ ሰው በአንድ ወቅት የላማናውያን ህዝብ በነበሩት በአሞን ህዝቦች መካከል እነዚህን ነገሮች ለመስበክ ወደ ኢየርሾን ምድር ሄደ።

ነገር ግን እነሆ እነርሱ ከአብዛኞቹ ኔፋውያን የበለጠ ብልህ ነበሩ፤ ምክንያቱም እርሱን ወሰዱትና፣ አሰሩት፣ እናም ህዝብ ላይ ሊቀ ካህን ወደሆነው ወደ አሞን ዘንድ ወሰዱት።

፳፩ እናም እንዲህ ሆነ እርሱም ከምድሪቱ ተወስዶ እንዲወጣ አደረገ። እናም ወደ ጌዴዎን ምድር መጣና፣ ደግሞ ለህዝቡ መስበክ ጀመረ፣ እናም በዚያ ብዙ ድል አላገኘም ነበር፣ ምክንያቱም እርሱ ተወሰደና ታሰረ፣ እናም ወደ ምድሪቱ ሊቀ ካህንና ደግሞ በዋናው ዳኛ ፊት ቀርቧልና።

፳፪ እናም እንዲህ ሆነ ሊቀ ካህኑም እንዲህ አለው፥ የጌታን መንገድ ለማሳት ለምን ትሄዳለህ? ይህንን ህዝብ ደስታውን ለማቋረጥ ለምን ክርስቶስ የለም ብለህ ታስተምራለህ? ከቅዱሳን ነቢያት ትንቢት ሁሉ ተቃራኒ የሆነውንስ ለምንስ ትናገራለህ?

፳፫ እንግዲህ የሊቀ ካህኑም ስም ጊዶና ነበር። እናም ቆሪሆር እንዲህ አለው፥ ከንቱ የሆነውን የአባቶችህን ወግ አላስተምርም፣ እናም ያለአግባብ ኃይላቸውንና ሥልጣናቸውን በእነርሱ ላይ ለማድረግ፣ እራሳቸውንም ቀና እንዳያደርጉ ነገር ግን በቃላቶችህ መጥፎ እንዲሰማቸው፣ ደንቆሮ ለማድረግ፣ ይህንን ህዝብ ከንቱ በሆነው ስርዓትና በጥንት ካህናት የተመሰረተውን አሰራር ለማሰር ይህንን ህዝብ አላስተምርም።

፳፬ አንተም ይህ ህዝብ ነፃ ነው ብለሃል። እነሆ፣ እነርሱ በባርነት ናቸው እላለሁ። የጥንት ትንቢቶች እውነት ናቸው ብለሃል። እነሆ፣ እነርሱ እውነት መሆናቸውን አታውቅም እላለሁ።

፳፭ በወላጆቻቸው መሳሳት ምክንያት ይህ ህዝብ ጥፋተኛና የወደቀ ነው ትላላችሁ። እነሆ፣ ልጅ በወላጆቹ ምክንያት ጥፋተኛ አይሆንም እላለሁ።

፳፮ እናም ደግሞ ክርስቶስ ይመጣል ብለሃል። ነገር ግን እነሆ፣ ክርስቶስ እንደሚኖር አታውቅም እላለሁ። እናም ደግሞ አንተ ለዓለም ኃጢያት ይሞታል ብለሃል—

፳፯ እናም ይህን ህዝብ ከንቱ በሆነው በአባቶች ወግና እንደ ፍላጎትህ መሰረት እንደዚህ ትመራለህ፤ እናም በባርነት እንዳሉም፣ በእጆቻቸው በሰሩትም ራስህን ታንደላቅቅበት ዘንድ፣ በድፍረትም ለመመልከት እንዳይደፍሩና፣ በልዩ መብቶቻቸውና በዕድላቸውም ለመደሰት እንዳይደፍሩ ተገዢ ታደርጋቸዋለህ።

፳፰ አዎን፣ እንደራሳቸው ፍላጎት ያሰራቸውን፣ እና በወጎቻቸውና ህልሞቻቸው፣ ቅዠታቸውና፣ ራዕዮቻቸው፣ እናም የማስመሰል ሚስጥሮቻቸው እንዲያምኑ ያደረጓቸውን ካህናቶቻቸውን እናሳዝናቸዋለን ብለው ይፈራሉ፣ እናም ያንኑ ማድረግ ነበረባቸውና፣ እንደቃሎቻቸው የማያደርጉም ከሆነ እነርሱ አምላክ ብለው ያሉትን—አንድ ያልታወቀን፣ እስከዛሬ ያልታየን፣ ወይንም እስከዛሬ ያልታወቀን አምላክ እናሳዝናለን ይላሉ።

፳፱ እንግዲህ ሊቀ ካህኑና ዋናው ዳኛ የልቡን ጠጣርነት በተመለከቱ ጊዜ፤ አዎን በእግዚአብሔር ላይ መሳደቡን በተመለከቱ ጊዜ፣ ለቃሉ ምንም መልስ አልሰጡም፤ ነገር ግን እንዲታሰር አደረጉ፤ እናም ለሹማምንቶቹ አስረከቡት፣ እናም ከዋናው ዳኛ፣ በምድሪቱ ላይ ሁሉ ገዢ ከነበረው ከአልማ ፊት ይቀርብ ዘንድ ወደ ዛራሔምላ ምድር ላኩት።

እናም እንዲህ ሆነ ከዋናው ዳኛና ከአልማ ፊት በቀረበ ጊዜ፣ በጌዴዎን ምድርም ያደርግ እንደነበረው ማድረጉን ቀጠለ፣ አዎን፣ የእግዚአብሔርንም ስም በከንቱ ማንሳቱን ቀጠለ።

፴፩ እናም በአልማ ፊት ጮክ ብሎ ለመናገር ተነሳ፣ እናም በህዝቡም ድካም ለመንደላቀቅ፣ በከንቱው የአባቶቻቸው ወግ ይመሯቸዋል በማለት ካህናቶቹንና መምህራንን በመሳደብ ይከሳቸው ጀመር።

፴፪ እንግዲህ አልማ እንዲህ አለው፥ በዚህ ህዝብ ስራ አለመንደላቀቃችንን ታውቃለህ፤ እነሆም ከመሣፍንት አገዛዝ ጀምሮ ምንም እንኳን በምድሪቱ ዙሪያ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ለህዝቡ ለማወጅ የተጓዝኩ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ራሴን ለመርዳት ሰርቼአለሁ።

፴፫ እናም በቤተክርስቲያን ውስጥ ብዙ ስራዎችን የሰራሁ ቢሆንም ለስራዬ አንድ ሰኒን እንኳን አልተቀበልኩም፤ ከፍርድ ወንበሩ በስተቀር ወንድሞቼም አልተቀበሉም፤ እናም በዚያም የተቀበልነው በህጉ መሰረት ለጊዜአችን ነበር።

፴፬ እናም አሁን በቤተክርስቲያኗ ለሰራንበት ምንም የማናገኝ ከሆነ በወንድሞቻችን ደስታ ሐሴት እናደርግ ዘንድ በቤተክርስቲያኗ እውነትን ለማወጅ ማገልገላችን እኛን ምን ይጠቅመናል?

፴፭ አንተ ራስህ እኛ ምንም ጥቅም እንዳላገኘን ባወቅህ ጊዜ ከህዝቡ ጥቅም እንድናገኝ ነው የምንሰብከው ለምን አልህ? እናም አሁን በህዝቡ ልብ ውስጥ ደስታን እንደሚፈጥር አድርገን ይህንን ህዝብ እንዳታለልን ታምናለህን?

፴፮ እናም ቆሪሆር አዎን በማለት መለሰ።

፴፯ እናም አልማ እንዲህ አለ፥ እግዚአብሔር እንዳለ ታምናለህን?

፴፰ እናም አላምንም ሲል መለሰ።

፴፱ እንግዲህ አልማ እንዲህ አለው፥ በድጋሚ እግዚአብሔር እንዳለ ትክዳለህን፣ እናም ደግሞ ክርስቶስን ትክዳለህን? እነሆም እንዲህ እልሃለሁ፣ እግዚአብሔር እንዳለና ደግሞ ክርስቶስ እንደሚመጣ አውቃለሁ።

እናም አሁን እግዚአብሔር እንደሌለ፣ ክርስቶስም እንደማይመጣ ምን ማረጋገጫ አለህ? ከቃላትህ በስተቀር ምንም ማረጋገጫ የለህም እላለሁ።

፵፩ ነገር ግን፣ እነሆ፣ እነዚህ ነገሮች እውነት ለመሆናቸው ለምስክርነት ሁሉም ነገር አሉኝ፤ እናም አንተ ደግሞ እውነት ለመሆናቸው ሁሉም ነገሮች ለምስክርነት አሉህ፤ እናም አንተ እነዚህን ትክዳለህን? እነዚህ ነገሮች እውነት መሆናቸውን ታምናለህን?

፵፪ እነሆ፣ ማመንህን አውቃለሁ፣ ነገር ግን አንተ ለውሸት መንፈስ ተገዢ ሆነሃል፣ እናም በውስጥህ ሥፍራ እንዳይኖረው የእግዚአብሔርን መንፈስ ክደሃል፤ ነገር ግን ዲያብሎስ በአንተ ላይ ስልጣን አለው፣ እናም የእግዚአብሔርን ልጆች ያጠፋበት ዘንድ በዕቅዱ በአንተ ላይ ገዢ ሆኗል።

፵፫ እናም አሁን ቆሪሆር ለአልማ እንዲህ አለው፥ እግዚአብሔር መኖሩን ለማመን እችል ዘንድ ለእኔ ምልክትን የምታሳየኝ ከሆነ፥ አዎን፣ ኃይል እንዳለው አሳየኝ፣ እናም በቃልህ እውነተኛነት አምናለሁ።

፵፬ ነገር ግን አልማ እንዲህ አለው፥ በቂ ምልክት አግኝተሃል፣ አምላክህን ትፈትናለህን? የወንድሞችህ ሁሉና፣ ደግሞ የቅዱሳን ነቢያት ምስክርነትን ባገኘህ ጊዜ ምልክት አሳዩኝ ትላለህን? ቅዱሳት መጻሕፍት በፊትህ ቀርበውልሃል፣ አዎን፣ እናም ሁሉም ነገር እግዚአብሔር መኖሩን ያመለክታሉ፣ አዎን፣ ምድርም እንኳን፣ እናም ሁሉም በምድር ገፅ ላይ ያሉት ነገሮች በሙሉ፤ አዎን እናም የምድር እንቅስቃሴ፣ አዎን፣ እናም ደግሞ በተለመደው ሁኔታ የሚንቀሳቀሱት ፕላኔቶች ታላቅ ፈጣሪ እንዳለ ያመለክታሉ።

፵፭ እናም የዚህን ህዝብ ልብ በማሳሳት እግዚአብሔር የለም ብለህ ለመመስከር ትሄዳለህን? እናም የእነዚህን ሁሉ ምስክርነት ትክዳለህን? እንዲህም አለ፥ አዎን፣ ምልክትን ካላሳየኸኝ እክዳለሁ።

፵፮ እናም እንግዲህ እንዲህ ሆነ አልማ እንዲህ አለው፥ እነሆ፣ በልብህ ጠጣርነት፣ አዎን፣ ነፍስህም እንድትጠፋ ዘንድ የእውነትን መንፈስ ስለምትቃወም አዝኜአለሁ።

፵፯ ነገር ግን እነሆ፣ በውሸታሙና በሚሸነግለው ቃልህ ብዙ ነፍሳትን ወደጥፋት ከማምጣት ይልቅ ነፍስህ ብትጠፋ ይሻላል፤ ስለዚህ በድጋሚ ከካድህ እነሆ እግዚአብሔር ይመታሃል፣ ደንቆሮም ትሆናለህ፤ ከእንግዲህም አፍህን ለመክፈት አትችልም፣ ከእንግዲህም ይህንን ህዝብ አታታልልም።

፵፰ እንግዲህ ቆሪሆር እንዲህ አለው፥ የእግዚአብሔርን መኖር አልክድም፣ ነገር ግን እግዚአብሔር እንዳለ አላምንም፤ እናም ደግሞ እንዲህ እላለሁ፥ እግዚአብሔር እንዳለም አንተ አታውቅም፤ እናም ምልክትን ካላሳየኸኝ አላምንም።

፵፱ እንግዲህ አልማ እንዲህ አለው፥ ይህን ለአንተ በቃሌ መሰረት ዲዳ እንድትሆን ለምልክት እሰጥሃለሁ፤ እናም በእግዚአብሔር ስም፣ ከእንግዲህ እንዳትናገር ዲዳ እንድትሆን ይህን እላለሁ።

እንግዲህ አልማ እነዚህን ቃላት በተናገረ ጊዜ፣ በአልማ ቃል መሰረትም ለመናገር እንዳይችል ቆሪሆር ዲዳ ሆነ።

፶፩ እናም ዋናው ዳኛ ይህን በተመለከተ ጊዜ፣ ለቆሪሆር እንዲህ በማለት ፃፈለት፥ በእግዚአብሔር ኃይል አምነሀልን? አልማ በማን ላይ ምልክቱን እንዲያሳይ ፈልገህ ነበር? ለአንተ ምልክቱን ለማሳየት ሌሎችን እንዲያሰቃይ ትፈልጋለህን? እነሆ፣ ምልክትን አሳይቶሀል፤ እናም አሁን ከዚህ በላይ ትከራከራለህን?

፶፪ እናም ቆሪሆር እጁን አነሳ፣ እንዲህም በማለት ፃፈ፥ ዲዳ መሆኔን አውቃለሁ፣ ምክንያቱም ለመናገር አልቻልኩም፤ እናም ከእግዚአብሔር ኃይል በቀር ማንም በእኔ ላይ ይህን ማምጣት እንደማይችል አውቃለሁ፤ አዎን፣ ሁል ጊዜም እግዚአብሔር እንዳለም አውቅ ነበር።

፶፫ ነገር ግን እነሆ፣ ዲያብሎስ አሳተኝ፤ ምክንያቱም እርሱ በመልአክ አምሳል ታየኝ፣ እናም እንዲህ አለኝ፥ ሂድና ህዝቡ ሁሉ ወደ ማይታወቀው አምላክ በተሳሳተው መንገድ ሄደዋልና መልሳቸው። እናም እንዲህ አለኝ፥ እግዚአብሔር የለም፤ አዎን፣ ማለት ያለብኝንም አስተማረኝ። ቃሉንም አስተማርኩኝ፤ እናም ለስጋዊ አዕምሮ የሚያስደስቱ በመሆናቸው አስተማርኳቸው፤ እናም አጥጋቢ ውጤት እስከማገኝ ድረስ አስተማርኳቸው፣ እንዲህም ሆኖ በእርግጥም እውነት መሆናቸውንም አመንኩኝ፤ ይህንንም ታላቅ እርግማን በራሴ ላይ እስከማመጣው ድረስ እውነትን የተቃወምኩት ለዚህም ነው።

፶፬ እንግዲህ እርሱ ይህንን በተናገረ ጊዜ፣ እርግማኑ ከእርሱ እንዲወሰድ አልማ ወደ እግዚአብሔር እንዲፀልይ ለመነው።

፶፭ ነገር ግን አልማ እንዲህ አለው፥ ይህ እርግማን ከአንተ ከተወሰደ በድጋሚ የህዝቡን ልብ ወደ ስህተት ትመራለህ፤ ስለዚህ፣ ጌታ እስከፈቀደ ድረስ ይህ በአንተ ላይ ይሆናል።

፶፮ እናም እንዲህ ሆነ እርግማኑ ከቆሪሆር አልተወሰደም፤ ነገር ግን እርሱ ወደውጪ ተጣለና፣ ከቤት ወደ ቤት ምግብ በመለመን ተዘዋወረ።

፶፯ እንግዲህ በቆሪሆር ላይ የሆነው ወዲያውኑ በምድሪቱ ሁሉ ተወራ፤ አዎን፣ አዋጁ በቆሪሆር ቃል ለሚያምኑት በፍጥነት ንስሃ እንዲገቡ አለበለዚያ ተመሳሳዩ ፍርድ በእነርሱ ላይ እንደሚመጣ በማወጅ አዋጁ ለምድሪቱ ነዋሪዎች ሁሉ በዋናው ዳኛ ተላከ።

፶፰ እናም እንዲህ ሆነ ሁሉም ስለቆሪሆርን ኃጢያት አመኑ፤ ስለዚህ ሁሉም በድጋሚ ወደ ጌታ ተለወጡ፣ እናም ይህም በቆሪሆር መተላለፍ ስለነበረው ማብቂያ ሆነ። ቆሪሆርም እራሱን ለመርዳት ከቤት ቤት በምግብ ልመና ዞረ።

፶፱ እናም እንዲህ ሆነ በህዝቡ፣ አዎን ከኔፋዉያን መካከል እራሳቸውን የለዩትና ዞራማውያን ብለው የጠሩት፣ ዞራም ተብሎ በሚጠራው ሰው በተመሩት መካከል በሄደ ጊዜ—እናም በእነርሱ መካከል በሄደ ጊዜ፣ እነሆ እስከሚሞት ድረስ ተረማመዱበትም ተረጋገጡበት።

እናም እኛ የጌታን መንገድ የሚያሰተውን የእርሱን መጨረሻ እንመለከታለን፣ እንደዚህም ዲያብሎስ በመጨረሻው ቀን ልጆቹን እንደማይደግፍ ነገር ግን በፍጥነት ወደሲኦል እንደሚጎትታቸው እንመለከታለን።