ቅዱሳት መጻህፍት
አልማ ፷፫


ምዕራፍ ፷፫

ሺብሎን እናም በኋላ ሔለማን ቅዱሳን መፃሕፍቶቹን ወሰዱ—በርካታ ኔፋውያን ወደ ሰሜኑ ምድር ተጓዙ—ሐጋዝ በባህሩም በስተምዕራብ በኩል የሔዱትን መርከቦች ሰራ—ሞሮኒሀ ላማናውያንን በውጊያ አሸነፋቸው። ከ፶፮–፶፪ ም.ዓ. ገደማ።

፩ እናም እንዲህ ሆነ በኔፊ ህዝብ ላይ በመሣፍንቱ ሰላሳ ስድስተኛ ዓመት የንግስና ዘመን በአልማ ለሔለማን የተሰጡትን ቅዱሳን ነገሮችን ሺብሎን ተረከባቸው።

፪ ሺብሎንም ፃድቅ ሰው ነበር፣ እናም በእግዚአብሔር ፊትም በቅንነት ይራመድ ነበር፤ እናም ያለማቋረጥ እርሱም፣ ደግሞ ወንድሙም፣ መልካም ለመስራት የጌታ አምላካቸውን ትዕዛዛት ለመጠበቅ ጥረት ያደርጉ ነበር።

፫ እናም እንዲህ ሆነ ሞሮኒም ሞተ። የመሣፍንቱ ሰላሳ ስድስተኛ የንግስና ዘመንም እንደዚህ ተፈፀመ።

፬ እናም እንዲህ ሆነ በመሣፍንቱ ሰላሳ ሰባተኛ የንግስና ዘመን ብዙ ሰዎች፣ እንዲሁም በአንድነት ወደ አምስት ሺህ አራት መቶ የሚጠጉ፣ ከሚስቶቻቸው እናም ከልጆቻቸው ጋር ከዛራሔምላ ምድር ወጥተው በምድሪቱ በስተሰሜን በኩል ሄዱ።

፭ እናም እንዲህ ሆነ ሀጋዝ፣ እጅግ ትጉህ ሰው ስለነበር፣ ስለዚህ ሄደና በወደመው ስፍራ በለጋስ ምድር ዳርቻ እጅግ ታላቅ የሆነ መርከብ ሰራ፤ እናም በቀጭኑ በምድሪቱ በስተሰሜን በሚያመራው መንገድ ወደ ምዕራብ ባህር ላከው።

፮ እናም እነሆ፣ በውስጡ የገቡና ብዙ ስንቅ ይዘውም የተጓዙ ብዙ ኔፋውያን፣ እናም ሴቶችና ልጆች ነበሩ፣ ጉዞአቸውንም ወደ ሰሜን አቅጣጫ አደረጉ። እናም ሰላሳ ሰባተኛው ዓመት ተፈፀመ።

፯ እናም በሰላሳ ስምንተኛው ዓመት ይህም ሰው ሌላ መርከቦችን ሰራ። እናም ደግሞ የመጀመሪያዋ መርከብ ተመለሰችና፣ ከዚህ የበለጡ ብዙ ሰዎችም ገቡባት፤ እናም እነርሱ ደግሞ ብዙ ስንቅ ያዙና፣ በምድሪቱ በስተሰሜን በኩል በድጋሚ ተላኩ።

፰ እናም እንዲህ ሆነ ከዚህ በኋላ ስለእነርሱ ምንም አልተሰማም ነበር። በጥልቅ ባህሩ ውስጥ ሰጥመዋል ብለን ገምተንም ነበር። እናም እንዲህ ሆነ ሌላኛዋ መርከብም ሄደች፤ እርሷም የት እንደደረሰችም አላወቅንም ነበር።

፱ እናም እንዲህ ሆነ በዚህ ዓመት በምድሪቱ በስተሰሜን በኩል የሄዱ ብዙ ሰዎች ነበሩ። እናም ሰላሳ ስምንተኛው ዓመት እንደዚህ ተፈፀመ።

፲ እናም እንዲህ ሆነ በመሣፍንቱ ሰላሳ ዘጠነኛ የንግስና ዘመን፣ ሺብሎንም ሞተ፣ እናም ወደዚያች ምድር ለሄዱት ሰዎች ስንቅ ለመውሰድ ቆሪያንቶን በምድሪቱ በስተሰሜን በኩል በመርከብ ሄደ።

፲፩ ስለዚህ ሺብሎን ከመሞቱ በፊት ለሔለማን ልጅ፣ በአባቱ ስም ሔለማን ተብሎ ለሚጠራው፣ ቅዱስ የሆኑትን ነገሮች መስጠቱ አስፈላጊ ነበር።

፲፪ እናም እነሆ፣ በሔለማን እጅ የነበሩት የተቀረጹ ጽሑፎች ሁሉ ተፅፈው፣ እናም በአልማ እንዳይሄዱ ከታዘዙት በስተቀር፣ በምድሪቱ ሁሉ በሰው ልጆች መካከል ተልከዋል።

፲፫ ይሁን እንጂ፣ እነዚህ ነገሮች ቅዱስ ሆነው መቀመጥ ይኖርባቸዋል፣ እናም ከትውልድ እስከ ትውልድ መተላለፍ ይኖርባቸዋል፤ ስለዚህ በዚህ ዓመት ሺብሎን ከመሞቱ በፊት እነዚህ ነገሮች ለሔለማን ተሰጡት።

፲፬ እናም እንዲህ ሆነ ደግሞም በዚህ ዓመት ጥቂት ወደ ላማናውያን የሄዱ ተገንጣዮች ነበሩ፤ እናም በኔፋውያን ላይ በድጋሚ ለቁጣ ተነሳስተው ነበር።

፲፭ እናም ደግሞ በዚሁ ዓመት ከሞሮኒሀ ሰዎች ጋር፣ እንዲሁም ከሞሮኒሀ ወታደሮች ጋር ለመዋጋት ከብዙ ወታደሮች ጋር በመሆን መጡ፤ ሆኖም ላማናውያን ተሸነፉና ወደራሳቸው ምድር በድጋሚ ተመልሰው ተባረሩና በብዙ ጥፋትም ተሰቃዩ።

፲፮ እናም በኔፊ ህዝብ ላይ የመሣፍንቱ ሰላሳ ዘጠነኛ የንግስና ዘመን እንደዚህ ተፈፀመ።

፲፯ እናም የአልማ ታሪክና፣ የልጁ የሔለማን፣ እንዲሁም ደግሞ የልጁ የሺብሎን ታሪክ በዚሁ ተፈፀመ።