ምዕራፍ ፴፪
አልማ ስቃያቸው ትሁት ያደረጋቸውን ድሆች አስተማረ—እምነት በዚያ በማይታየው እውነት በሆነው የሚደረግ ተስፋ ነው—አልማ መላዕክት ለወንዶች፣ ለሴቶች፣ እና ለልጆች እንደሚያገለግሉ መሰከረ—አልማ ቃሉን ከዘር ጋር አነፃፀረ—ይህም መተከልና እንክብካቤ ሊደረግለት ይገባዋል—ከእዚያም የዘለዓለም ህይወት የሆነው ፍሬ ወደሚሰበሰብበት ያድጋል። በ፸፬ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም እንዲህ ሆነ እነርሱ ሄዱና፣ በሰዎቹ ምኩራብና፣ በቤታቸው በመግባት የእግዚአብሔርን ቃል መስበክ ጀመሩ፤ አዎን እናም ቃሉን በእነርሱ መንገድም እንኳን ሰበኩ።
፪ እናም እንዲህ ሆነ በመካከላቸው ብዙ ከሰሩ በኋላ፣ በደሃው ህዝብ መካከል መልካም ውጤት ማግኘት ጀመሩ፤ ምክንያቱም፣ እነሆ፣ በልብሳቸው ቆሻሻነት የተነሳ ከምኩራቡ ተባርረው ነበርና—
፫ የረከሱ ናቸው ተብሎ ስለተቆጠሩ እግዚአብሔርን ለማምለክ ወደ ምኩራብ ለመግባት አልተፈቀደላቸውም ነበር፤ ስለዚህ እነርሱ ድሆች ነበሩ፤ አዎን፣ በወንድሞቻቸው እንደ አተላ ተቆጥረው ነበር፤ ስለዚህ በዓለም ነገሮች ድሆች ነበሩ፤ እናም ደግሞ በልባቸውም ድሆች ነበሩ።
፬ አሁን፣ አልማ በኦኒዳ ኮራብታ ላይ ለህዝቡ ሲያስተምር፣ እና ሲናገር ስለእነርሱም እኛ የተናገርነው፣ በዓለም ነገሮች ድሆች የሆኑት፣ እና በልባቸው ድሃ የሆኑ ብዙ ህዝብ ወደ እርሱ መጡ።
፭ እናም እነርሱ ወደአልማ መጡ፤ እናም ከመካከላቸው ዋና የሆነው እንዲህ አለው፥ እነሆ እነኚህ ወንድሞቼ ምን ያድርጉ፤ ምክንያቱም እነርሱ በድህነታቸው በሰዎች ሁሉ፣ አዎን በተለይ በካህናቶቻችን፣ ተጠልተዋል፤ ምክንያቱም በእራሳችን እጆች በእጅግ ጥረን ከሰራናቸው ከምኩራቦቻችን አስወጥተውናል፤ እጅግ ድሆች በመሆናችንም እኛን አባረውናል፤ አምላካችንንም ለማምለክ ምንም ስፍራ የለንም፤ እናም እነሆ ምን ማድረግ አለብን?
፮ እናም አሁን አልማ ይህንን በሰማ ጊዜ፣ አልማ ፊቱን በፍጥነት ወደ እርሱ አዞረ፣ እናም በታላቅ ደስታ ተመለከተ፤ ምክንያቱም ስቃያቸው በእውነት እራሳቸውን ዝቅ እንዳደረገና፣ እነርሱ ቃሉን ለመስማት በዝግጅት ላይ እንደነበሩ ተመለከተ።
፯ ስለዚህ ለሌሎቹ ሰዎች ምንም አልተናገረም ነበር፣ ነገር ግን ለሚመለከታቸው፣ በእውነት ለተፀፀቱት እጁን ዘረጋና፣ ጮኸ፣ እናም እንዲህ አላቸው፥
፰ እነሆ በልባችሁ ትሁት እንደሆናችሁ እመለከታለሁ፤ እናም እንደዚያ ከሆናችሁ የተባረካችሁ ናችሁ።
፱ እነሆ ወንድማችሁ ምን ማድረግ አለብን? ይላል—ከምኩራባችን ስለተባረርን፣ አምላካችንን ማምለክ አንችልም።
፲ እነሆ እንዲህ እላችኋለሁ፣ በምኩራባችሁ ብቻ ካልሆነ እግዚአብሔርን ለማምለክ አንችልም ብላችሁ ታስባላችሁን?
፲፩ እናም ከዚህ በተጨማሪ እጠይቃችኋለሁ፣ በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ እግዚአብሔርን ማምለክ እንዳለባችሁ ትገምታላችሁን?
፲፪ እንዲህ እላችኋለሁ፣ ትሁት ትሆኑ፣ እናም ጥበብን ዘንድ ከምኩራባችሁ መባረራችሁ መልካም ነው፤ ምክንያቱም ጥበብን መማራችሁ አስፈላጊ ነው፤ በመባረራችሁ፣ በእጅግ ድሀነታችሁ በወንድሞቻችሁ ስለተጠላችሁ ምክንያት ነው ልባችሁን ትሁት የሆነው፤ ትሁትም የሆናችሁትም ተገድዳችሁ ነው።
፲፫ እናም እንግዲህ፣ ትሁት እንድትሆኑ በመገደዳችሁ እናንተ የተባረካችሁ ናችሁ፤ አንዳንዴ ሰው ትሁት እንዲሆን ከተገደደ ንስሃን ይሻልና፤ እናም አሁን በእርግጥ ንስሃ የገባ ሁሉ ምህረትን ያገኛል፤ እናም ምህረትን ያገኘና፣ እስከመጨረሻው የፀና እርሱ ይድናል።
፲፬ እናም አሁን፣ እኔ እንደተናገርኳችሁ፣ ትሁት እንድትሆኑ በመገደዳችሁ የተባረካችሁ ናችሁ፤ በቃሉም የተነሳ በእውነት ዝቅ ያሉ ከዚህ የበለጠ የተባረኩ ናቸው ብላችሁ አትገምቱምን?
፲፭ አዎን፣ በእውነት እራሱን ዝቅ ያደረገና፣ ለኃጢአቱ ንስሃ የገባ፣ እናም እስከመጨረሻው የፀና፣ እርሱ ይባረካል—አዎን፣ በከፋው ድህነታቸው ዝቅ እንዲሉ ከተገደዱት የበለጠ በብዙ ይባረካል።
፲፮ ስለዚህ እራሳቸውን ዝቅ እንዲያደርጉ ሳይገደዱ እራሳቸውን ዝቅ ያደረጉት የተባረኩ ናቸው፤ ወይንም በሌላ አነጋገር፣ በእግዚአብሔር ቃል ያመነ፣ አዎን፣ ቃሉን እንዲያውቅ ሳይገደድ በልቡም ሳያመነታ የተጠመቀ፣ እርሱ የተባረከ ነው።
፲፯ አዎን፣ እንዲህ የሚሉ ብዙዎች አሉ፥ ከሰማይ ምልክትን ካሳየኸን፣ እርግጠኝነቱን እናውቃለን፣ ከዚያም እናምናለን።
፲፰ እንግዲህ እንዲህ ብዬ እጠይቃለሁ፥ ይህ እምነት ነውን? እነሆ፣ እንዲህ እላችኋለሁ፤ አይደለም፣ ሰው ነገርን የሚያውቅ ከሆነ ለማመን ምንም መንስኤ የለውም፣ ያውቀዋልና።
፲፱ እናም እንግዲህ፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እያወቀ የማያደርገው ከሚያምነው፣ ወይም የማመን ምክንያት ያለው እና በመተላለፍ ከሚወድቀው እንዴት ይበልጥ የተረገመ ነው?
፳ እንግዲህ ይህን ነገር በተመለከተ መፍረድ አለባችሁ። እነሆ፣ እንዲህ እላችኋለሁ በአንድ በኩል የሆነው በሌላ በኩልም ይሆናል፤ እናም ለእያንዳንዱ ሰው እንደስራው ይሆንለታል።
፳፩ እናም አሁን እምነትን በተመለከተ እንደተናገርኩት፣ እምነት ስለ ነገሮች ፍፁም የሆነ እውቀት አለ ማለት አይደለም፤ ስለዚህ እምነት ካላችሁ እውነት ስለሆኑትና ስለማይታዩት ነገሮች ተስፋ ይኖራችኋል።
፳፪ እናም አሁን፣ እነሆ፣ እንዲህ እላችኋለሁ፣ እግዚአብሔር በስሙ ለሚያምኑት ሁሉ መሃሪ መሆኑን እንድታስታውሱም እፈልጋለሁ፤ ስለዚህ በመጀመሪያ ደረጃ በእርሱ እንድታምኑ፤ አዎን በቃሉም እንኳን እንድታምኑ ይፈልጋል።
፳፫ እናም አሁን፣ ቃሉን በመላዕክት አማካኝነት ለወንዶች፣ አዎን፣ ለወንዶች ብቻ ሳይሆን ለሴቶችም እንዲሁ ይሰጣል። እንግዲህ ይህ ብቻም አይደለም፣ ጥበበኞችን እና የተማሩትን የሚያምታቱ ቃላት ህፃናት ልጆች ብዙ ጊዜም ይሰጣቸዋል።
፳፬ እናም አሁን፣ የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እናንተ የተሰቃያችሁና የተጣላችሁ በመሆናችሁ ምክንያት ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ከእኔ ለማወቅ በመፈለጋችሁ—አሁን እናንተን በዚያ እውነት በሆነው ብቻ ልፈርድባቸሁ እንደሆነ እንድትገምቱ አልፈልግም—
፳፭ ሁላችሁም ራሳችሁን ዝቅ እንድታደርጉ ተገድዳችኋል ማለቴም አይደለምና፤ ጉዳያቸው ምንም ቢሆንም ከእናንተ መካከል እራሳቸውን ዝቅ የሚያደርጉ ጥቂቶች እንዳሉ በእርግጥ አምናለሁ።
፳፮ እንግዲህ፣ እምነትን በተመለከተ እንደተናገርኩት—ፍፁም እውቀት አይደለም—የእኔም ቃል እንዲህ ነው። እምነትም ፍፁም ዕውቀት እንዳልሆነ፣ በቅድሚያ የእርሱን እርግጠኛነት በፍፁም ልታውቁ አይቻላችሁም።
፳፯ ነገር ግን እነሆ፣ አዕምሮአችሁን ካነቃችሁት፣ እናም ካነሳሳችሁት፣ በቃሌም እስከምትለማመዱ እንኳን፣ እናም ቅንጣት ያህል እምነትን ከተለማመዳችሁ፣ አዎን ከማመን በላይ የበለጠ ለመፈለግ ባትችሉም፣ ለቃላቴ በውስጣችሁ ትንሽ ቦታ ለመስጠት እስከምትችሉ ድረስ ይህ ፍላጎት በእናንተ እንዲሰራ አድርጉ።
፳፰ እንግዲህ፣ ቃሉን ከዘር ጋር እናነፃፅራለን። እንግዲህ፣ ዘሩ በልባችሁ ውስጥ እንዲተከል ሥፍራን ከሰጣችሁት፣ እነሆ፣ እውነተኛ ዘር ከሆነ ወይም መልካም ዘር ከሆነ፣ ባለማመናችሁ የጌታን መንፈስ በመቃወም የማትጥሉት ከሆነ፣ እነሆ፣ እርሱም በደረታችሁ ውስጥ ማደግ ይጀምራል፤ እናም ይህ ዕድገት በልባችሁ ውስጥ ሲሰማችሁ፣ በውስጣችሁ እንዲህ ማለት ትጀምራላችሁ—ይህ መልካም ዘር መሆን አለበት፣ ወይንም ቃሉ መልካም ነው፣ ምክንያቱም በነፍሴ ውስጥ ማደግ ጀመሯልና፤ አዎን ግንዛቤዬን ያበራልኝ ጀምሯል፤ አዎን፣ ለእኔም አስደሳች መሆን ጀምሯል።
፳፱ እናም እነሆ፣ ይህ እምነታችሁን አያሳድግላችሁምን? እኔ እንዲህ እላችኋለሁ፣ አዎን፣ ይሁን እንጂ እምነታችሁ ወደፍፁም እውቀት ከፍ ባይልም እንኳን ይህ እምነታችሁን አያሳድገውምን?
፴ ነገር ግን እነሆ፣ ዘሩ በፋፋና በበቀለ፣ እናም ማደግ በጀመረ ጊዜ፣ ከዚያም ዘሩ መልካም ነው ማለት አለባችሁ፤ ምክንያቱም እርሱ ይፋፋልም፣ ይበቅላልም፣ ማደግ ይጀምራልም። እናም አሁን እነሆ፣ ይህ እምነታችሁን አያጠነክርምን? አዎን፣ እምነታችሁን ያጠነክራል፤ ምክንያቱም ይህ መልካም ዘር እንደሆነ አውቃለሁ ትላላችሁና፤ ምክንያቱም እነሆ በቅሏል እናም ማደግ ጀምሯል።
፴፩ እናም አሁን፣ እነሆ፣ ይህ መልካም ዘር ለመሆኑ እርግጠኞች ናችሁን? እኔ እንዲህ እላችኋለሁ፤ አዎን፣ ማንኛውም ዘር እራሱን መሰል ዘር ይሰጣል።
፴፪ ስለዚህ፣ ዘሩ የሚያድግ ከሆነ መልካም ነው፤ ነገር ግን የማያድግ ከሆነ፣ እነሆ መልካም አይደለም ስለዚህ ይጣላል።
፴፫ እናም አሁን እነሆ ልምምዱን በመሞከራችሁና፣ ዘሩን በመትከላችሁ፣ እርሱም በመፋፋቱና፣ በመብቀሉ፣ እናም ማደግ በመጀመሩ ዘሩ መልካም መሆኑን ማወቅ ይገባችኋል።
፴፬ እናም እንግዲህ፣ እነሆ፣ እውቀታችሁ ፍፁም ነውን? አዎን፣ እውቀታችሁ በእዚያ ነገር ፍፁም ነው፣ እምነታችሁም ዘገምተኛ ነው፤ እናም ይህንን በማወቃችሁ፣ ቃልም ነፍሶቻችሁን እንደሚያፋፋ ታውቃላችሁ፣ ደግሞም መብቀሉን ስላወቃችሁ፣ ግንዛቤአችሁ ብርሃን ማግኘት ይጀምራል፣ እናም አዕምሮአችሁ መስፋፋት ጀምሯል።
፴፭ አቤቱ ይህ እውነት አይደለምን? እኔ እንዲህ እላችኋለሁ፤ አዎን፣ ምክንያቱም ይህ ብርሃን ነው፣ እናም ብርሃን የሆነው ማንኛውም መልካም ነው፣ ምክንያቱም እርሱ የሚለይ ነውና፣ ስለሆነም መልካም መሆኑን ማወቅ ይገባችኋል፤ እናም አሁን እነሆ፣ ይህንን ብርሃን ከሞከራችሁት በኋላ እውቀታችሁ ፍፁም ይሆናልን?
፴፮ እነሆ አይደለም እላችኋለሁ፣ ወይም እምነታችሁን መተው የለባችሁም፣ ምክንያቱም ዘሩ መልካም መሆኑን ለማወቅ ልምምዱን ትሞክሩ ዘንድ፣ ዘሩን ለመትከል ብቻ እምነታችሁን ተለማምዳችኋልና።
፴፯ እናም እነሆ፣ ዛፍ ማደግ ሲጀምር፣ እንዲህ ትላላችሁ፥ ስርን እንዲያገኝ፣ እርሱም እንዲያድግ፣ እናም ፍሬን እንዲያስገኝልን፣ በታላቅ ጥንቃቄ እንንከባከበው። እናም አሁን እነሆ፣ በተገቢው ጥንቃቄ ከተንከባከባችሁት ስር ያገኛልም፣ ያድጋልም፣ እናም ፍሬን ያስገኛል።
፴፰ ነገር ግን ዛፉን ከተዋችሁትና፣ ለእንክብካቤው ማሰብ ካቆማችሁ፤ እነሆ ስር አያገኝም፤ እናም የፀሐይ ሙቀት መጥቶ ባቃጠለው ጊዜ፣ ስር ስለሌለው ይደርቃል፤ እናም ትቆርጡትና ትጥሉታላችሁ።
፴፱ እንግዲህ፣ ይህም የሆነው ዘሩ መልካም ስላልነበረ አይደለም፤ ወይም ፍሬውም ቢሆን ተፈላጊ ባለመሆኑ አልነበረም፣ ነገር ግን መሬታችሁ መካን በመሆኑ፣ እናም ዛፉን አትንከባከቡትም፤ ስለዚህ የዚህን ፍሬ አታገኙም።
፵ እናም ለእዚያ ፍሬ በእምነት ዓይን በመጠበቅ እንደዚህ ቃሉን የማትንከባከቡት ከሆነ፣ ከህይወት ዛፍ ፍሬ በጭራሽ መቅጠፍ አትችሉም።
፵፩ ነገር ግን ቃሉን የምትንከባከቡ ከሆነ፣ አዎን በእምነታችሁ በታላቅ ትጋት፣ ትዕግስት፣ እና ለዚያ ፍሬ በጉጉት በመጠበቅ የምትንከባከቡት ከሆነ፣ ይህም ስር ያወጣል፤ እናም እነሆ ይህም ወደ ዘለዓለማዊው ህይወት የሚያድግ ዛፍ ይሆናል።
፵፪ እናም ስር እንዲያወጣ ዘንድ ቃሉን ለመንከባከብ ትጉ በመሆናችሁና፣ በታማኝነታችሁ እንዲሁም በትዕግስተኛነታችሁ፣ እነሆ፣ የተከበረውን፣ ከጣፋጮች ሁሉ ጣፋጭ የሆነውንና ከነጡት ሁሉ በላይ ነጭ፣ አዎን ከንፁህ ሁሉ በላይ ንፁህ የሆነውን ፍሬ ከጊዜ በኋላ ትቀጥፋላችሁ፤ እናም እርሃባችሁ እስከሚጠፋና፣ ጥማታቸሁ እስኪቆረጥ ድረስ እንኳን ቢሆን ይህንን ፍሬ ትመገባላችሁ።
፵፫ ከዚያም ወንድሞቼ፣ ዛፉ ፍሬ እንዲያስገኝላችሁ በመጠበቃችሁ ለእምነታችሁ፣ ለትጋታችሁና፣ ለፅናታችሁ፣ እናም ለታጋሽነታችሁ ደመወዝን ታገኛላችሁ።