ቅዱሳት መጻህፍት
የጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ ፩


የጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ

ከነብዩ ጆሴፍ ስሚዝ ታሪክ የተወሰደ

ምእራፍ ፩

ጆሴፍ ስለትውልዱ፣ ስለቤተሰብ አባላቱ፣ እና ከጊዜው ቅድሚያ መኖሪያቸው ተናገረ—በምዕራብ ኒው ዮርክ ውስጥ ልዩ በሀይማኖት መነሳሳት ተሰራጨ—በያዕቆብ እንደተመራው ጥበብን ለመፈለግ ወሰነ—አብና ወልድ ታዩት፣ እና ጆሴፍ ወደነብያዊ አገልግሎቱ ተጠራ። (አንቀፅ ፩–፳።)

የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አነሳስ እና እድገትን በሚመለከት በክፋት በተጠመዱ እና መሰሪ ሰዎች የተሰራጩትን የዚህችን ጸባይ ላይ በጸሀፊዎቹ ስሟን እንደ ቤተክርስቲያን እና በአለም እያደገች እያለች ለማጥፋት ያቀዱባቸውን ብዙ ሀተታዎችን ለማስተዋወቅ—ይህን ታሪክ ለመጻፍ፣ የህዝብን አዕምሮ ለማረጋጋት፣ እና እውነት ለሚፈልጉት ሁሉ፣ እነዚህ ተጨባጭ ነገሮች እንዳሉኝ፣ በእኔ እና በቤተክርስቲያኗ በሚመለከት ያለፉትን ተጨባጭ ነገሮችን ለመስጠት ተገፋፍቼ ነበር።

በዚህ ታሪክ ውስጥ፣ በእውነት እና በፅድቅ፣ አስቀድመው እንደነበሩ፣ ወይም አሁንም እንዳሉት፣ ከአሁን [፲፰፻፴፰ (እ.አ.አ.)] ይህች ቤተክርስቲያን ከተደራጀችበት ስምንት አመት ጀምሮ ቤተክርስቲያኗን በሚመለከት የነበሩትን የተለያዩ ሁኔታዎች አቀርባለሁ።

የተወለድኩት በጌታችን አመት አንድ ሺህ ስምንት መቶ አምስት፣ በታህሳስ ሀያ ሶስት ቀን (እ.አ.አ.)፣ በሼረን ከተማ፣ በውንድሰር የግዛት ክፍል፣ በቨርሞንት ስቴት ውስጥ ነበር። … በአስር አመቴ ወይም በዚያ አካባቢ፣ አባቴ ጆሴፍ ስሚዝ፣ ቀዳማዊ የቨርሞንት ስቴትን ተወ፣ እና ወደፓልማይራ፣ በኦንታሪዮ (አሁንም ዌይን በሚባለው) የግዛት ክፍል፣ ወደ ኒው ዮርክ ስቴት ውስጥ ሄደ። አባቴ ፓልማይራ ውስጥ ከደረሰ አራት አመታት በኋላ፣ ከቤተሰቡ ጋር ወደ ማንቸስተር በአንድ አይነት ኦንታሪዮ የግዛት ክፍል ሄደ።

ቤተሰቡ አስራ አንድ ነፍሳት ያሉበት፣ ስማቸውም አባቴ ጆሴፍ ስሚዝእናቴ ሉሲ ስሚዝ (ስሟ ከመጋባቷ በፊት ማክ፣ የሰለሞን ማክ ሴት ልጅ፣ ነበረች)፣ ወንድሜ አልቭን (በህዳር ፲፱ ቀን ፲፰፻፳፫ [እ.አ.አ.] በ፳፮ አመቱ የሞተው)፣ ሀይረም፣ ራሴ፣ ሳሙኤል ሀሪሰን፣ ውልያም፣ ዶን ካርሎስ፣ እና እህቶቼ ሰፍሮንያ፣ ካትሪን፣ እና ሉሲ. ነበሩ።

ወደ ማንቸስተር ከሄድን በሁለተኛው አመት አካባቢ፣ በምንኖርበት ስፍራ ውስጥ ሀይማኖትን በተመለከተ ያልተለመደ የመነሳሳት ስሜት ነበረ። በመተዲስት ተጀመረ፣ ነገር ግን ወዲያውም በሀገሪቱ ባሉ ክልሎች ውስጥ በሁሉም ሀይማኖቶች መካከል የተሰራጨ ሆነ። በእርግጥ የሀገሩ ዲስትሪክት በሙሉ በዚህ የተነኩ ይመስል ነበር፣ እና ታላቅ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በተለያዩ የሀይማኖት ቡድኖች ራሳቸውን አባል አድርገው ነበር፣ ይህም በሰዎች መካከል አንዳንዶች “እንኳን በዚህ!” እና ሌሎች “እንኳን በዚያ!” በማለት በመጮህ፣ ትንሽ ያልሆነ ሁከትን እና መከፋፈልን ፈጥሮ ነበር። አንዳንዶች የሜተድስት፣ አንዳንዶች የፕረስብተሪያን፣ እና ሌሎች የባፕቲስት ሀይማኖትን የሚደግፉ ነበሩ።

በሚቀየሩበት ጊዜ እነዚህ የተለያዩ ሀይማኖቶች ተቀያሪዎች ታላቅ ፍቅርን የሚገልጹ ቢሆኑም፣ እና በመነሳት እና ይህን አስደናቂ የሀይማኖት ስሜት ትእይንትን የሚያበረታቱ እነዚያ ቀሳውስትም፣ ሁሉንም በፈለጉት የሀይማኖት ወገን አባል እንዲሆኑ ለመቀየር ታላቅ ጉጉትን ቢያሳዩም፤ ነገር ግን የተቀየሩት አንዳንዶቹ ወደ አንድ ቡድን እና አንዳንዶችም ወደ ሌሎች፣ ተለይተው ሲሄዱ፣ የቀሳውስቱም ይሁን የተቀየሩት ሰዎች መልካም ስሜት ከእውነተኛነት ይልቅ የማስመሰል በመሆኑ ታላቅ ግራ መጋባት እና መጥፎ ስሜት አይሏል—ቄስ ከቄስ፣ እና የተለወጡትም ከጠለወጡት ጋር ክርክር ውስጥ ነበሩ፤ ስለዚህ አንድ ለሌላ የነበራቸው ጥሩ ስሜት ሁሉ፣ ይህም ቢኖር፣ በቃላት ጠብ እና በአስተሳሰብ ፉክክር በሙሉ ጠፍተው ነበር።

በዚህ ጊዜ በአስራ አምስት አመቴ ላይ ነበርኩኝ። የአባቴ ቤተሰብ በፕረስብተርያን ሀይማኖት ለአባልነት ተመልምለው ነበር፣ እና አራቱ የዚያ ቤተክርስቲያን አባል ሆኑ፣ እነርሱም እናቴ ሉሲ፣ ወንድሞቼ ሀይረምና ሳሙኤል ሀርሰን፣ እና እህቴ ሰፍሮንያ ነበሩ።

በዚህ ታላቅ መነሳሳት ጊዜ አዕምሮዬ በጥብቅ ሀሳብና ታላቅ ችግር ላይ ተነሳስቶ ነበር፤ ነገር ግን ምንም እንኳን ስሜቴ ጥልቅ እና በአብዛኛውም ጊዜ ሀያል ቢሆንም፣ የሆነ ሆኖም ከእነዚህ ቡድኖች ሁሉ ራሴን ገለልተኛ አደረግሁኝ፣ ይህም ቢሆን በተቻለ መጠን ዘወትር በተለያዩ ስብሰባዎቻቸው እገኝ ነበር። ከጊዜም በኋላ አዕምሮዬ የሜተድስት ሀይማኖት ደጋፊ እየሆነ መጣ፣ እና ከእነርሱም ጋር አንድ ለመሆን ፍላጎት ተሰማኝ፤ ነገር ግን በተለያዩ ሀይማኖቶች መካከል ክርክሩ እና ጠቡ ታላቅ ስለነበረ፣ እንደ እኔ ወጣት እና በሰዎች እና ነገሮች ልምድ የሌለው ሰው የትኛው ትክክለኛ እና የትኛው ስህተተኛ እንደሆነ በምንም በእርግጠኝነት የምወስንበት መንገድ አልነበረም።

ጩኸት እና ሁከታው ታላቅ እና የማያቆም ስለነበረ፣ በየጊዜው አዕምሮዬ በጣም የተነሳሳ ነበር። የፕረስብተሪያኖች ባፕቲስት እና ሜተዲስቶቹን በጣም የተቃወሙ ነበሩ፣ እና የመረዳት ችሎታና ጥበብ ሀይሎችን በሙሉ ስህተቶቻቸውን ለማረጋገጥ ወይም ሰዎች እነርሱ የተሳሳቱ እንደሆኑ እንዲያስቡ ለማድረግ ይጥሩ ነበር። በሌላም በኩል፣ ባፕቲስቶች እና ሜተዲስቶች የራሳቸውን እምነት ለመመስረት እና ሌሎች እንደተሳሳቱ ለማረጋገጥ በእኩል በቅንአት ይጥሩም ነበር።

በዚህ የቃላት ጦርነት እና በአስተያየት ሁካታ መካከል፣ ለራሴ ሁልጊዜም፥ ምን ይደረግ? እላለሁ። ከእነዚህ ቡድኖች ሁሉ የትኛዎቹ ትክክል ናቸው፤ ወይም ሁሉም አብረው የተሳሳቱ ናቸውን? ከእነርሱ አንዱ ትክክል ከሆነ፣ የትኛው ነው፣ እና እንዴትስ አውቀዋለሁ?

፲፩ በእነዚህ ሀይማኖተኛ ሰዎች ቡድኖች ፉክክር ምክንያት በጣም አስቸጋሪ በሆነው ሁኔታ እየታገልኩኝ እያለሁ፣ አንድ ቀን በያዕቆብ መልእክት ምዕራፍ አንድ አንቀፅ አምስት ውስጥ እያነበብኩ ነበር፣ እንዲህም ይል ነበር፥ ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፣ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፣ ለእርሱም ይሰጠዋል።

፲፪ ምንም የቅዱስ መጸሐፍ ጥቅስ በዚህ ጊዜ በዚህ ጊዜ በልቤ ውስጥ ያመጣውን ሃይል ያህል በማንም ሰው ልብ ውስጥ ፈጽሞ መጥቶ አያውቅም። ይህም ወደልቤ ስሜት በሙሉ በታላቅ ሀይል የገባ ይመስል ነበር። ማንም ሰው የእግዚአብሔርን ጥበብ የሚሻ ቢኖር እኔው እንደሆንኩኝ በማወቅ፣ ይህን ደጋግሜ አሰብኩበት፤ ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላወቅሁምና፣ እና ካለኝ ተጨማሪ ጥበብ ካላገኘሁ በስተቀር፣ በምንም ማወቅ አልችልም ነበር፤ የተለያዩ ቡድኖች የሀይማኖት አስተማሪዎች አንድ አይነት የቅዱሳት መጻህፍት ምንባብን በጣም በተለያየ ሁኔታ ስለሚገነዘቡት፣ ጥያቄ ለመመለስ ወደ መፅሐፍ ቅዱስ የመመካትን እምነትን አጥፍተውታልና።

፲፫ ከጊዜም በኋላ በጭለማ እና በግራ በመጋባት ለመቅረት ወይም ያዕቆብ እንዳመለከተው፣ ያም እግዚአብሔርን መጠየቅ፣ እንዳለብኝ ወሰንኩኝ። ከጊዜም በኋላ፣ ጥበብ ለሚጎድለው ጥበብ የሚሰጥ እና በልግስና ሳይነቅፍ የሚሰጥ ከሆነ “እግዚአብሔርን ለመጠየቅ” በመሞከር ውሳኔ ውስጥ ገባሁ።

፲፬ ስለዚህ፣ በዚህም እግዚአብሔርን ለመጠየቅ በወሰንኩበት መሰረት፣ ሙከራ ለማድረግ ወደ ቁጥቋጦው ውስጥ ሄድኩኝ። ጊዜውም ግሩም እና ግልፅ በሆነው በጸደይ ማለዳ በዓስራ ስመንት መቶ እና ሀያ አመተ ምህረት ነበር። በከፍተኛ ጭንቀቴ መካከል ሁሉ ድምጼን በማሰማት መጸለይን ገና ሞክሬው ስላልነበር፣ ይህን አይነቱን በህይወቴ የሞከርኩት ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር።

፲፭ ቀደም ብዬ ለመሄድ ወደመረጥኩት ስፍራ ከሄድኩ በኋላ፣ ዙሪያዬን ከተመለከትኩ በኋላና ብቻዬን እንደሆንኩም አየሁ፣ ተንበረከኩ እና የልቤን ፍላጎቶች ለእግዚአብሔር መግለፅ ጀመርኩ። ይህን ማድረግ እንደጀመርኩም፣ ወዲያው በሙሉ በሚቋቋመኝ ሀይል ተያዝሁ፣ እና በእኔም ላይ የሚያስገርም ተፅዕኖ ኖሮት እንዳልናገርም አንደበቴን አሰረው። ጥቅጥቅ ያለ ጭለማም ዙሪያዬን ከበበኝ፣ እና ለጊዜውም በድንገት ጥፋት የተፈረደብኝ መስሎኝ ነበር።

፲፮ ነገር ግን በላዬ ላይ ከሰለጠነው የጠላት ሃይል እንዲያድነኝ ሃይሌን ሁሉ አሰባስቤ እግዚአብሔርን ለመጥራት እና ተስፋ ወደመቁረጥ እና ራሴንም ለጥፋት፣ ይህም ምናባዊ ጥፋት ሳይሆን ከዚህ ቀደም በየትኛውም አካል በጭራሽ ተሰምቶኝ በማላውቀው አስደናቂ ሃይል ባለው ከማይታየው አለም በሆነው አንድ ሃይል፣ አሳልፌ ለመስጠት በተዘጋጀሁበት በዚያች ቅጽበት፣ ልክ በዚህ ታላቅ የድንጋጤ ሰአት፣ ከፀሀይ ይልቅ የደመቀ የብርሀን አምድ ከራሴ በላይ ተመለከትኩ፣ በላዬም ላይ እስኪያርፍ ድረስ ይህም በዝግታ ወደ እኔ ወረደ።

፲፯ ወዲያው እንደታየም ይዞኝ ከነበረው የጠላት ሀይል በመዳን ነጻ ሆንኩ። ብርሀኑም በእኔ ላይ ባረፈ ጊዜ ብርህነታቸውና ክብራቸው ቃላት ከሚገልጸው በላይ የሆኑ ሁለት ሰዎች በአየር ከበላዬ ቆመው ተመለከትኩ። አንዱም ስሜን በመጥራት እና ወደሌላውም በማመልከት ተናገረኝ—የምወደው ልጄ ይህ ነው። እርሱን ስማው!

፲፰ ጌታን የመጠየቄ ዋና አላማዬም፣ የየትኛው የሀይማኖት ቡድን አባል ለመሆን ለማወቅ ከቡድኖቹ ሁሉ የትኛው ትክክል እንደሆነም ለማወቅ ነበር። ስለዚህ፣ ለመናገር ለመቻል ራሴን ለመቆጣጠር ወዲያው እንደቻልኩም፣ ከበላዬ በብርሀን ለቆሙት ሰዎች (በዚህ ጊዜ ሁሉም የተሳሳቱ እንደሆኑ ምንም በልቤ ስላልገባ) የትኛው ድርጅቶች ትክክል እንደሆነ እና የየትኛውም አባል መሆን እንደሚገባኝ ጠየቅሁኝ።

፲፱ ሁሉም ስህተተኞች ስለሆኑ፣ የማንኛዎቹም አባል እንዳልሆን ተመለሰልኝ፤ እና የሚያነጋግረኝም ሰው ሁሉም ሀይማኖቶች በፊቱ አስጸያፊ እንደሆኑ፣ በእነዚህ የሚያምኑትም ሁሉ የተበከሉ እንደሆኑ፣ “በከንፈራቸው ወደ እኔ ይቀርባሉልባቸው ግን ከእኔ የራቀ ነው፣ የሰው ትእዛዛት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ፣ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል” ብሎ ነገረኝ።

የማንኛቸውም አባል እንዳልሆን እንደገናም ከለከለኝ፤ እና በዚህ ጊዜ ልፅፋቸው የማልችለውን ሌሎች ብዙ ነገሮችንም ነገረኝ። እንደገና ራሴን ለማወቅ ስጀምር፣ በጀርባዬ ተኝቼ ወደ ሰማይ እየተመለከትኩ ነበር። ብርሀኑ ከሄደ በኋላ፣ ምንም ጥንካሬ አልነበረኝም፤ ነገር ግን ጥቂት ብርታት ካገኘሁ በኋላ፣ ወደ ቤት ሄድኩኝ። በቤት ማሞቂያ ምድጃ አጠገብ ተደግፌ እያለሁ፣ እናቴ ምን እንደሆንኩኝ ጠየቀችኝ። እንዲህም መለስኩኝ፣ “ምንም አታስቢ፣ ሁሉም መልካም ነው—እኔም ደህና ነኝ።” ከዚያም ለእናቴ እንዲህ አልኳት፣ “ለራሴ ፕረስብተሪያን እውነት እንዳልሆነ አውቄአለሁ።” ጠላትም በለጋነት የእድሜዬ ዘመን የእርሱ የመንግስት በጥባጭ እና ረባሽ ለመሆን የተመረጥኩኝ መሆኔን ያወቀ ይመስል ነበር፤ ይህ ባይሆን ኖሮ የጭለማ ሀይላት ለምንስ በእኔ ላይ ይተባበሩብኝ ነበር? በህጻንነቴም፣ ለምን ተቃራኒዎች እና ስቃዮች በእኔ ላይ ይነሱብኝ ነበር?

አንዳንድ ሰባኪዎች እና ሌሎች የሀይማኖት አባሎች የመጀመሪያ ራዕይን ታሪክን አልተቀበሉም—ስቃይ በጆሴፍ ስሚዝ ላይ ተቆለለበት—ስለራዕዩ እውነተኛነት መሰከረ። (አንቀፅ ፳፩–፳፮።)

፳፩ ይህን ራዕይ ካየሁ ከጥቂት ቀናት በኋላ፣ ቀደም ብሎ በተጠቀሰው የሀይማኖት መነሳሳት ተሳታፊ ከነበረ ከአንድ ሜተድስት ሰባኪ ጋር በአጋጣሚ ተገናኘሁ፤ እና ስለሀይማኖት ርዕስ ከእርሱ ጋር ስነጋገር፣ ያየሁትን ራዕይ ታሪክ ነገርኩት። በጸባዩ በጣም ተደነቅሁኝ፤ የነገርኩትን ክብደት ሳይሰጠው፣ በንቀትም ሁሉም ከዲያብሎስ ነው፣ በእነዚህ ቀናት ራዕይ ወይም መገለጥ የሚባል ነገር የለም፣ እንደዚህ አይነት ነገሮች ሁሉ ከሐዋሪያት ጋር ስለተፈጸሙ፣ እና ደግመውም አይኖሩም አለ።

፳፪ ነገር ግን ታሪኬን ስለነገርኩኝ በሀይማኖት አማኞች መካከል በእኔ ላይ የተዛባ አስተሳሰብ አነሳሳ፣ እና ሁልጊዜም የቀጠለ የታላቅ ስቃይ ምክንያት ሆነ፤ እና ታዋቂ ያልሆንኩኝ ከአስራ አራት እና አስራ አምስት አመት መካከል የሆንኩኝ፣ እና የህይወት ጉዳዬ እንዲህ ሆኖ በአለም ላይ ምንም አስፈላጊ ያልሆንኩኝ ልጅ ነበርኩኝ፣ ነገር ግን ታዋቂ ሰዎች በእኔ ላይ የ ህዝቦችን አዕምሮ ለማነሳሳት፣ የሚመር ስቃይም ለመፍጠር በእኔ ላይ አተኩረው ነበር፤ እና ይህም በሁሉም ቡድኖች መካከል አንድ አይነት ነበር—ሁሉም እኔን በማስቃየት አንድ ሆነው ነበር።

፳፫ በዚያም ጊዜ በትኩረት እንዳሰላስል እና ከዚህም ጀምሮ ለብዙ ጊዜ እንዳደርገው አድርጎኛል፣ በትንሽ ከአስራ አራት አመት በላይ የሆንኩኝ ታዋቂ ያልሆንኩ ልጅ፣ እና የእለት ጉርሴን ለማግኘት በየቀኑ ስራ ለማግኘት የተመደብኩ፣ ለእኔ ብቁ አስፈላጊነት በመስጠት በጣም ታዋቂ የሆኑ ቡድኖች በክፉ ስቃይ እና ስድብ መንፈስ በውስጣቸው በሚፈጥር ሁኔታ በእኔ ላይ ትኩረት መስጠታቸው እንዴት የሚያስገርም ነበር። ያልተለመደም ቢሆንም ባይሆንም፣ እንደዚህም ነበረ፣ እና ለእኔም ታላቅ ሀዘን ሁልጊዜም የፈጠረብኝ ነበር።

፳፬ ነገር ግን ራዕይ እንዳየሁ በምንም ቢሆን እውነት ነው። አሁንም ሳስብበት፣ በንጉስ አግሪጳ ፊት እንደተከራከረው፣ እና ብርሀንን ሲያይ ስለነበረው ራዕይ ታሪክ እንደነገረው ጳውሎስ አይነት ይሰማኝ ነበር፤ ነገር ግን ያመኑት ብዙ አልነበሩም፤ አንዳንዶችም እርሱ ሀሰተኛ ነው፣ ሌሎችም እርሱ ያበደ ነው ብለውም ነበር፤ እና ያፌዙበትም ይሰድቡትም ነበር። ይህ ሁሉ ግን ራዕይ እንደነበረው እውነትን አላጠፋውም። ራዕይ አይቷል፣ ማየቱንም አውቋል፣ እና ከሰማይ በታች ያሉት ስቃዮች ሁሉ ሊለውጡት አይችሉም፤ እና እስከሚሞት ድረስ ቢያሰቃዩትም፣ ማየቱን ያውቀው ነበር፣ እና ብርሀንን እንዳየ እና ያናገረውን ድምፅ እንደሰማ እስከመጨረሻው እስትንፋሱ ድረስ ያውቀዋል፣ እና አለም ሁሉ ከዚህ ሌላ እንዲያስብ ወይም እንዲያምን ሊያደርጉት አይችሉም።

፳፭ ለእኔም እንዲሁ ነበር። ብርሀንን በእውነትም አይቼ ነበር፣ እና በብርሀኑ መካከልም ሁለት ሰዎችን አየሁ፣ እና እነርሱም በእውነት አነጋገሩኝ፤ እና ምንም እንኳን ራዕይ አይቻለሁ በማለቴ ብጠላና ብሰቃይም፣ ይህ ግን እውነት ነበር፤ እና ይህን በማለቴ እነርሱ ሲያሰቃዩኝ፣ ሲሰድቡኝና፣ ሁሉንም አይነት ክፉ ነገሮች በእኔ ላይ ሲያደርጉብኝ፣ በልቤም ይህን እንድል ተመርቼ ነበር፥ እውነትን በመናገሬ ለምን ታሰቃዩኛላችሁ? በእውነትም ራዕይን አይቻለሁ፤ እና እግዚአብሔርን እቋቋም ዘንድ ማን ነኝ፣ ወይም ለምን አለም በእርግጥ ያየሁትን እንድክደው ለማድረግ ያስባል? ራዕይን አይቻለሁ፣ አውቀዋለሁ፣ እና እግዚአብሔር እንደሚያውቀውም አውቃለሁ፣ እና ልክደውም አልችልም፣ እና ይህን ላደርግም አልሞክርም፣ ይህን በማድረግ እግዚአብሔርን እንደሚያስቀይምና ፍርድ በላዬ እንደሚመጣብኝ አውቃለሁና።

፳፮ የሀይማኖት አለምን በሚመለከት—ከማንኛቸው ጋር አባል መሆኑ የእኔ ሀላፊነት አልነበረም፣ ነገር ግን ተጨማሪ መመሪያ እስካገኝ ድረስ እንደነበርኩትም መቀጠል እንዳለብኝ በማወቅ አዕምሮዬ ረክቶ ነበር። የያዕቆብ ምስክር እውነት እንደሆነም አወቅሁኝ—ጥበብ የሌለው ሰው እግዚአብሔርን መጠየቅ ይችላል፣ እና አይነቀፍም።

ሞሮኒ ጆሴፍ ስሚዝን ጎበኘው—የጆሴፍ ስም ለበጎም ሆነ ለክፉም በህዝቦች መካከል ይታወቃል—ሞሮኒ ስለመፅሐፈ ሞርሞንና ስለሚመጣው የጌታ ፍርድ ነገረው እና ቅዱስ መጻህፍትንም ጠቀሰ—የወርቅ ሰሌዳው ስውር ስፍራ ተገለጸ—ሞሮኒ የነቢዩን ትምህርት ቀጠለ። (አንቀፅ ፳፯–፶፬።)

፳፯ የእለት ህይወቴ ስራዬን እስከ መስከረም ሀያ አንደኛው ቀን፣ አንድ ሺህ ስምንት መቶ ሀያ ሶስት (እ.አ.አ.) ድረስ ቀጠልኩ፣ በዚህም ጊዜ ሁሉ፣ ራዕይ እንዳየሁ ማረጋግጥን ስለቀጠልኩኝ፣ በሁሉም አይነት ሰዎች፣ ሀይማኖታዊም ይሁን ሀይማኖት በሌላቸው፣ ብዙ ተሰቃየሁኝ።

፳፰ ራዕይ ካየሁበት እና በአስራ ስምንት መቶ ሀያ ሶስት አመተ ምህረት መካከል በነበረው ጊዜ—በዚያ ጊዜ ከነበሩት ከማናቸውም የሀይማኖት ድርጅቶች አባል እንዳልሆንም ስለተከለከልኩኝ፣ እና በጨቅላዎቹ እድሜዬ ላይ ስለነበርኩኝ እና ግራ የተጋባሁ እንደሆንኩ የሚያስቡም ቢሆን በትክክለኛውና በመልካም የፍቅር ስሜት እንደገና ከስህተቴ ሊመልሱኝ በሚገባቸው ባልንጀሮቼ ሊሆኑና በርህራሄም ሊመለከቱኝ በሚገባቸው ስደት የደረሰብኝ—በሁሉም አይነት ፈተናዎች ተፈተንኩኝ፤ እና ከሁሉም አይነት ህብረተሰብ ጋር በመቀላቀልም፣ በብዙ ጊዜም የሞኝ ስህተቶችን ሰራሁ፣ እና የወጣትነትን ደካማነትንና የሰው ፍጥረት ፍጹም ያለመሆንን አሳየሁ፣ ይህም በእግዚአብሔር አስተያየት በሚያስቀይሙ ወደተለያዩ ፈተናዎች ስለተመራሁ ጸጸት ይሰማኛል። ይህን በመናዘዜ፣ ማንም በምንም ታላቅ እና ክፉ ኃጢአቶችን የሰራሁ አይምሰለው። እንደዚህ አይነት ነገር የመፈጸም ዝንባሌም አልነበረኝም። ነገር ግን እኔ እንደነበርኩት ከእግዚአብሔር የተጠራ ሰው እንዲኖረው በማይገባ አይነት ጸባዮች፣ በቅብጠት፣ እና አንዳንዴም ከሚደሰቱ ሰዎች ጋር መገናኘት፣ እና በሌሎችም ጥፋተኛ ነበርኩኝ። ነገር ግን ወጣትነቴን በሚያስታውሱት እና በሀገራዊ ደስተኛ ጸባዬን በሚያውቁት ዘንድ ይህ አስገራሚ ላይሆን ይችላል።

፳፱ በእነዚህ ነገሮች ምክንያት፣ በደካማነቴ እና ፍጹም ባለመሆኔ እንደተኮነንኩኝ ይሰማኝ ነበር፤ ከላይ እንደተጠቀሰውም በመስከረም ሀያ አንድ ቀን፣ በምሽት ወደመኝታዬ ከገባሁ በኋላ፣ ወደ ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር ለኃጢአቶቼ እና ለጥፋቶቼ ይቅርታ በመጠየቅ፣ እና በፊቱ የት እንዳለሁ እና ምን ላይ እንደቆምኩኝ አውቅ ዘንድ እንዲገለጥልኝ እጸልይ እና አመልክ ነበር፤ ከዚህ በፊት እንደነበረኝ መለኮታዊ መገለጥን ለማግኘት ሙሉ እምነት ነበረኝ።

እግዚአብሔርን በመጥራት ላይ ባለሁበት ጊዜ፣ ብርሃን በክፍሌ ውስጥ ሲመጣ ተመለከትኩ፤ ብርሃኑም ከቀትር ፀሐይ እስኪበልጥ ድረስ መጨመሩን ቀጠለ፤ ወዲያውኑም አንድ ሰው በአልጋዬ አጠገብ እግሩ መሬት ሳይነካ በአየር ላይ ቆሞ ተገለጠልኝ።

፴፩ በጣም ያሸበረቀ ነጭ ካባ ለብሶ ነበር። ንጣቱም ምድራዊ ከሆኑ ካየኋቸው ነገሮች በሙሉ የበለጠ ነበር፤ ማንኛውም ምድራዊ ነገር እንደዚህ እጅግ ነጭና ደማቅ መሆን ይችላል ብዬ አላምንም። እጆቹ፣ እናም ደግሞ ክንዶቹ ከአንጓው ትንሽ ከፍ ብሎ በልብስ አልተሸፈኑም ነበር፤ እግሮቹም ደግሞ እንዲሁ ከቁርጭምጭሚቱ በላይ በልብስ አልተሸፈኑም ነበር። ራሱና አንገቱም የተገለጡ ነበሩ። ካባው በተገለጠ ጊዜ ደረቱን ማየት እችል ስለነበር፣ ከካባው በቀር ሌላ ልብስ እንዳልነበረው ለማወቅ ችዬ ነበር።

፴፪ እጅግም የነጣው ካባው ብቻ አልነበረም፣ ነገር ግን መላ ሰውነቱ መግለፅ ከሚቻለው በላይ ብሩህ ነበር፣ እንዲሁም ፊቱ በእውነት ልክ እንደ መብረቅ ነበር። ክፍሉ እጅግ ብርሃን ነበር፣ ነገር ግን ልክ በእርሱ ዙሪያ እንደነበረው በጣም የደመቀ አልነበረም። በመጀመሪያም ወደ እርሱ በተመለከትኩ ጊዜ ፈርቼ ነበር፣ ነገር ግን ፍርሃቱ ወዲያው ለቀቀኝ።

፴፫ በስሜ ጠራኝ፣ እናም እርሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እኔ የተላከ መልዕክተኛ እንደሆነና ስሙም ሞሮኒ እንደሆነ፣ እግዚአብሔርም ለእኔ የምሰራው ስራ እንደነበረው፣ እናም ስሜም በሁሉም ሀገሮች፣ ነገዶች፣ ቋንቋዎችና ህዝብ መካከል በመልካምና በጥፋት እንደሚነሳ፣ ወይም በሁሉም ህዝብ መካከል መልካምና መጥፎ እንደሚባልልኝ ነገረኝ።

፴፬ እርሱ ቀደም ያሉትን የዚህ አህጉር ነዋሪዎች ታሪክ እና እነርሱ የመጡበትን ምንጭ ከየት እንደሆነ የሚናገር በወርቅ ሰሌዳዎች ላይ ተፅፎ የተቀበረ መጽሐፍ እንዳለም ተናገረ። ለጥንት ነዋሪዎች በአዳኙ የተሰጠውን የዘለዓለማዊውን ወንጌል ሙሉነትም በውስጡ እንደያዘም ደግሞ ተናገረ፤

፴፭ ደግሞ ከሰሌዳዎቹ ጋር የተቀበሩ ሁለት ድንጋዮች በብር ቅስት ውስጥ ነበሩ—እናም እነዚህ ድንጋዮች ከደረት ኪስ ታስረው፣ ኡሪምና ቱሚም ከሚባለው የተሰሩ ናቸው፤ እናም የእነዚህ ድንጋዮች ባለቤትና ተጠቃሚ በጥንት ወይም በድሮ ጊዜ ባለራዕይ የሚባሉት ናቸው፤ እናም እግዚአብሔር መጽሐፉን ለመተርጎም ዓላማ እነሱን አዘጋጅቷቸዋል።

፴፮ እነዚህን ነገሮች ከነገረኝ በኋላ ከብሉይ ኪዳን ትንቢቶችን መጥቀስ ጀመረ። መጀመሪያ የጠቀሰው የሚልክያስ መፅሐፍ ምዕራፍ ሶስትን ክፍል ነበር፤ ደግሞም የዚያን ትንቢት አራተኛ ወይም የመጨረሻ ምዕራፍ፣ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚነበብበት በትንሽ ቀይሮ ጠቀሰ። የመጀመሪያውን አንቀጽ በመፅሐፎቹ እንደሚነበበው ከመጥቀስ ፈንታ፣ እንዲህ ጠቀሰው፥

፴፯ እነሆም፣ እንደ ምድጃ እሳት የሚነድ ቀን ይመጣል፤ እናም ትዕቢተኞች ሁሉ፣ አዎን፣ እናም ኃጢአትን የሚሰሩ ሁሉ እንደ ገለባ ይቃጠላሉ፤ የሚመጡትም ያቃጥሏቸዋል፣ አለ የሰራዊት ጌታ፣ ሥርንና ቅርንጫፍንም አይተውላቸውም።

፴፰ ደግሞም አምስተኛውን አንቀፅ እንዲህ ጠቀሰ፥ እነሆ ታላቁና የሚያስፈራው የጌታ ቀን ከመምጣቱ በፊት በነቢዩ ኤሊያስ እጅ ክህነትን እገልጥላችኋለው።

፴፱ የሚቀጥለውንም አንቀጽ በልዪነት ጠቀሰው፥ እናም ለአባቶች የተገባውን የተስፋ ቃል በልጆች ልብ ይተክላል፣ እናም የልጆቹንም ልብ ወደ አባቶቻቸው ይመልሳል። እንዲህ ባይሆን ኖሮ፣ መላው ምድር በምጽአቱ ይጠፋ ነበር።

በእነዚህም ተጨማሪ፣ የኢሳይያስ ምዕራፍ አስራ አንድ በዚህ ያሉት ሊፈጸሙ ተቃርበዋል በማለት ጠቀሰ። የሐዋርያት ስራ ምዕራፍ ሶስት፣ ሀያ ሁለት እና ሀያ ሶስት አንቀፅን በአዲስ ኪዳን ውስጥ በትክክል እንደሚገኙት ጠቀሰ። ነቢዩም ክርስቶስ ነበር፤ ነገር ግን “ድምጹን የማይሰሙ ከሕዝብ ተለይተው ይጠፋሉ” የተባለበት ቀን ገና አልመጣም፣ ግን ወዲያው ይመጣል አለ።

፵፩ የኢዩኤልን ሁለተኛ ምዕራፍ ከአንቀፅ ሀያ ስምንት እስከ መጨረሻውም ጠቀሰ። ደግሞም ይህ ገና እንዳልተፈጸመ፣ ግን ወዲያውም እንደሚሆን ተናገረ። በተጨማሪም የአህዛብ ሙላት ወዲያው እንደሚመጣም ተናገረ። ከቅዱሳት መጻህፍት ብዙ ምንባብን ጠቀሰ፣ እና በዚህ ሊጠቀሱ የማይችሉ ብዙ ማብራሪያዎችንም ሰጠ።

፵፪ ደግሞም፣ እርሱ የተናገረኝን ሰሌዳዎች ሳገኝ—እነርሱን የምወስድበት ትክክለኛው ጊዜ ገና አልተፈጸመምና—እኔ ማሳየት እንዳለብኝ ከምታዘዘው በቀር የደረት ኪሱን ከኡሪምና ቱሚም ጋር ለማንም ሰው ማሳየት እንደሌለብኝና ካደረግሁ ግን መጥፋት እንዳለብኝ ተናገረኝ። እርሱ ከእኔ ጋር ስለሰሌዳዎቹ በሚነጋገርበት ጊዜ፣ ሰሌዳዎቹ የተቀበሩበትን ስፍራ ማየት እንድችል ራዕይ ለአዕምሮዬ ተገለፀ፣ እናም ስፍራውንም እንደገና ስጎበኘው በግልፅና በጉልህ አወቅሁት።

፵፫ ከዚህ ንግግርም በኋላ፣ ብርሃን በክፍሉ ውስጥ ባናገረኝ ሰው ዙሪያ በፍጥነት መሰብሰብ ሲጀምር አየሁ፣ እናም ከእርሱ ዙሪያ በቀር ክፍሉ እንደገና እስኪጨልም ድረስ እንዲህም ማድረግ ቀጠለ፤ ወዲያውም ስመለከት መተላለፊያ ቀጥታ ወደ ሰማይ የተከፈተ መሰለኝ፣ እና እርሱ እስኪጠፋ ድረስ ወደላይ አረገ፣ እናም ክፍሉ ይህ ሰማያዊ ብርሃን ከመታየቱ በፊት እንደነበረው ሆነ።

፵፬ እኔም ተኝቼ በዚህ እንግዳ ዕይታ በጥንቃቄ እያሰብኩ፣ እናም ይህ እንግዳው መልዕክተኛ በነገረኝ በጣም እየተደነቅሁ ነበር፤ በሃሳቤ ሳወጣና ሳወርድ፣ ክፍሌ እንደገና እየደመቀ መምጣቱን በድንገት ተመለከትኩ፣ እናም በቅፅበት ያው የሰማይ መልዕክተኛ በድጋሚ አልጋዬ አጠገብ መሆኑን ተመለከትኩ።

፵፭ እርሱም መናገር ጀመረ፣ እናም እንደገና በመጀመሪያ ጉብኝቱ ያደረጋቸውን አንድ አይነት ነገሮች ምንም ሳይለውጥ ተናገረ፤ ይህንን ካደረገ በኋላ ታላቅ ፍርድ በምድር ላይ ከታላቁ ጥፋት ጋር በረሃብ፣ በሰይፍ እና በቸነፈር እንደሚመጣ፤ እናም እነዚህ አሳዛኝ ፍርዶች በምድር ላይ በዚህ ትውልድ እንደሚመጡ ገለፀልኝ። እነዚህን ነገሮች ከነገረኝ በኋላ ልክ እንደ በፊቱ በድጋሚ አረገ።

፵፮ በዚህ ጊዜ በአዕምሮዬ የተቀረፁት በጣም ጥልቅ ነገሮች ስለነበሩ፣ እንቅልፍ ከዐይኖቼ ጠፋ፣ እናም ባየሁትና በሰማሁት በመደነቅ ተሞላሁ። ነገር ግን ይገርመኝ የነበረው ነገር በድጋሚ ያንን መልዕክተኛ በአልጋዬ በኩል ሳየው፣ እናም ያንኑ የበፊቱን ነገሮች እንደገና ሲደግመው ስሰማ ነበር፤ እናም ማስጠንቀቂያ ሲጨምርልኝ ነበር፣ (የአባቴ ቤተሰቦች ድሃ በመሆናቸው ምክንያት) ሰይጣን ሀብታም ለመሆን ዓላማ ሰሌዳዎቹን ለማግኘት እንዳገኝ ሊፈትነኝ እንደሚሞክር በመንገር ተጨማሪ ማስጠንቀቂያን ሰጠኝ። እርሱም ይኸውም ጌታን ለማሞገስ ካልሆነ በስተቀር ሰሌዳዎቹን በማግኘቴ ሌላ አእምሮዬን የማያነሳሳ ነገር እንዳይኖረኝ፣ እናም የእርሱን መንግስት ከመገንባት ሌላ በማንኛውም ነገር ተፅዕኖ እንዳይኖርብኝ በማለት ከለከለኝ፤ አለበለዚያ እነዚህን ለማግኘት አልችልም።

፵፯ ከዚህ ከሦስተኛው ጉብኝት በኋላ፣ ልክ እንደበፊቱ በድጋሚ ወደ ሰማይ አረገ፣ እናም አሁን ስለአጋጠመኝ እንግዳ ነገር በድጋሚ እንዳሰላስል ተተውኩ፤ ልክ የሰማዩ መልዕክተኛ ለሦስተኛ ጊዜ እኔ ከነበርኩበት ወደ ሰማይ ሲያርግ፣ ዶሮ ጮኸ፣ እናም እየነጋ መሆኑን ተገነዘብኩ፣ ስለዚህ ንግግራችንም ያን ምሽት በሙሉ የያዘ እንደነበር ተረዳሁ።

፵፰ ከጥቂት ጊዜም በኋላ ከመኝታዬ ተነሳሁ፤ እናም እንደተለመደው፣ ለቀኑ አስፈላጊ ወደ ሆነው ስራ ሄድኩ፤ ነገር ግን በሌላ ጊዜ እንደምሰራው ስሞክር፣ ኃይልን በማጣቴ ያንንም ለመስራት ፍፁም አላስቻለኝም። ከእኔ ጋር ሲሰራ የነበረው አባቴ በእኔ በኩል አንድ ችግር እንዳለ ተገነዘበ፣ እናም ወደ ቤት እንድሄድ ተናገረኝ። በፍላጎት ወደ ቤት ለመሄድ ጀመርኩ፤ ነገር ግን እኛ የነበርንበትን የሜዳ አጥር ለማቋረጥ ስሞክር ብርታቴን በሙሉ አጣሁ፣ እናም አቅቶኝ በመሬት ላይ ወደቅሁ፣ እናም ለተወሰነ ጊዜ አዕምሮዬን ስቼ ነበር።

፵፱ የመጀመሪያው የማስታውሰው ነገር አንድ ድምፅ ወደ እኔ ተናግሮ፣ በስሜም ሲጠራኝ ነበር። ተመለከትኩ፣ እናም የፊተኛው መልዕክተኛ ልክ እንደበፊቱ በብርሃን ተከቦ በአናቴ በኩል ቆሞ አየሁ። እናም እርሱ ባለፈው ምሽት ለእኔ የተናገረውን ሁሉ እንደገና ተናገረ፣ እናም ወደ አባቴ በመሄድ ስለራዕዩና ስለተቀበልኩት ትዕዛዛት እንድነግረው አዘዘኝ።

እኔም ተቀበልኩ፤ በሜዳው ወደአለው አባቴም ተመለስኩ እናም ሁሉንም ነገር ለእርሱ ነገርኩት። እርሱም ከእግዚአብሔር ነው ብሎ መለሰልኝ፣ እናም በመልዕክተኛው የታዘዝኩትን እንድሄድና እንዳደርግ ነገረኝ። ከሜዳው ሄድኩኝ፣ እናም መልዕክተኛው ሰሌዳዎቹ ተቀምጠዋል ብሎ ወደነገረኝ ስፍራ ሄድኩኝ፤ እና ያንን በተመለከተ ግልፅ ራዕይ ስለነበረኝ፣ ወደስፍራው እንደደረስኩ ወዲያው አወቅሁት።

፶፩ በኒውዮርክ በማንቸስተር ኦንታሪዮ መንደር አጠገብ አንድ ትልቅ ኮረብታ ቆሟል፣ እናም በአቅራቢያው ካሉት ከሌሎች ሁሉ ይበልጣል። በኮረብታው በስተምዕራብ በኩል ከጫፉ ራቅ ሳይል፣ በትልቁ ድንጋይ ስር ሰሌዳዎቹ በድንጋይ ሳጥን ተቀብረዋል። ይህም ድንጋይ በላይ በኩልና ከመሀሉ ወፍራምና ክብ ነበር፣ እና ወደጠርዙም በኩል ቀጭን ነበር፣ ስለዚህ የመካከለኛው ክፍሉ ከመሬት በላይ ከፍ ብሎ ይታይ ነበር፤ ነገር ግን ጠርዞቹ በሙሉ በመሬቱ ተሸፍነው ነበር።

፶፪ ከመሬት ከቆፈርኩም በኋላ፣ ከድንጋዩ ጠርዝ ላይ የተጣበቀ ለማንሻነት የሚጠቅም ዱላ አገኘሁ፣ እናም በትንሽ ጉልበት አነሳሁት። ወደ ውስጥም ተመለከትኩ፣ እናም መልዕክተኛው እንደገለፀው በእርግጥ ሰሌዳዎቹንኡሪምና ቱሚም እናም የደረት ኪሱን ተመለከትኩ። በውስጡ የተቀመጡበት ሳጥንም የተሰራው ሲሚንቶ በሚመስል በተጣበቁ በተነባበሩ ድንጋዮች ነበር። ከሳጥኑ በታች በኩል ሁለት ድንጋዮች ጎን ለጎን ተቀምጠው ነበር፣ እናም በእነዚህ ድንጋዮች ላይም ሰሌዳዎችና ሌሎች ነገሮች ተቀምጠውባቸው ነበር።

፶፫ እኔ እነርሱን ለማውጣት ሞከርኩ፣ ነገር ግን በመልዕክተኛው ተከለከልኩ፣ እናም እንደገና የነሱ ማውጫ ጊዜ ገና እንዳልደረሰ፣ ከዚያም ጊዜም እስከ አራት አመት ድረስም ጊዜው እንደማይመጣም ነገረኝ፤ ነገር ግን እርሱ ልክ በአንድ አመት ጊዜ ወደዚያ ስፍራ መምጣት እንዳለብኝ ነገረኝ፣ እናም እርሱ እዚያ ከእኔ ጋር ለመገናኘት እንደሚመጣ፣ እና ሰሌዳዎቹ የሚወሰዱበት ጊዜ እስከሚመጣ ይህን ማድረግ መቀጠል እንዳለብኝ ተናገረኝ።

፶፬ በመሰረቱም እንደታዘዝኩት፣ በየአመቱ መጨረሻ ሄድኩኝ፣ እናም በእያንዳንዱ ጊዜም ያንኑ መልዕክተኛ እዚያ አገኘሁት፣ እናም በእያንዳንዱ ንግግራችን ጌታ ምን እንደሚያደርግ በተመለከተ፣ እና እንዴትና በምን አይነት ሁኔታ የእርሱ መንግስት በመጨረሻው ቀን እንደሚመራ መመሪያና እውቀት ከእርሱ እቀበል ነበር።

ጆሴፍ ስሚዝ ኤማ ሔልስን አገባ—የወርቅ ሰሌዳዎችን ከሞሮኒ ተቀበለ እና አንዳንድ ፊደሎችን ተረጎመ—ማርቲን ሀሪስ የፊደሎችን ትርጉም፣ “የታተመ መፅሐፍ ለማንበብ አልችልም” ላለው ፕሮፌሰር አንቶን አሳየ። (አንቀፅ ፶፭–፷፭።)

፶፭ የአባቴ አለማዊ ሁኔታ የተወሰነ ስለነበረ፣ እድሎች ባጋጠሙን ቁጥር በእጆቻችን በመስራት እንደ ቀን ሰራተኞች በመቀጠር መስራት ነበረብን። አንዳንዴ እቤት ነን፣ እና አንዳንዴም በውጪ ነን፣ እና በየጊዜው በመስራትም የሚመች መጠነኛ ኑሮ እንዲኖረን ችለናል።

፶፮ በ፲፰፻፳፫ ዓመተ ምህረት (እ.አ.አ.) የአባቴ ቤተሰብ የታላቅ ወንድሜ፣ አልቭን፣ የሞተበት ስቃይ አጋጠማቸው። በጥቅምት ወር፣ ፲፰፻፳፭ (እ.አ.አ.)፣ በኒው ዮርክ ስቴት፣ ቻነንጎ ወረዳ በሚኖረው ስሙ ጆዛያ ስቶል በተባለ ሽማግሌ ሰው ተቀጠርኩ። በስፓኒያን በሀርመኒ፣ ሰስኮሀና ወረዳ ፔንስልቬንያ ውስጥ የብር የማእድን ጉድጓድ እንደተከፈተ ሰምቶ ነበር፤ እና ይህን የማዕድን ጉድጓድ ለማግኘት የሚቻል ከሆነ እኔን ከመቅጠሩ በፊት ይቆፍር ነበር። ከእርሱ ጋር ለመኖር ከሄድኩኝ በኋላ፣ ከሌሎቹ ሰራተኞቹ ጋር በብር የማዕደን ጉድጓድ ውስጥ እንድቆፍር ወሰደኝ፣ በምናደርገው ውጤታማ ሳንሆን፣ ለአንድ ወር በሚሆንም በዚህም እሰራ ነበር፣ እና በመጨረሻም ይህን ለመቆፈር እንዲያቆም ሽማግሌውን አንዲስማማ አደረግሁኝ። በዚህም እኔን የገንዘብ ቆፋሪ ነው የሚለው የተሰራጨ ታሪክ ተነሳ።

፶፯ እንደዚህ በተቀጠርኩበት ጊዜም፣ ከዚያው ስፍራ አቶ አይዛክ ሔልስ ጋር አብረን እንድኖር ተደርጌ ነበር፣ እዚያም ነበር ባለቤቴን (ሴት ልጁን) ኤማ ሔልስን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየኋት። በጥር ፲፰፣ ፲፰፻፳፯ (እ.አ.አ.)፣ አቶ ስቶልን ለማገልገል እንደተቀጠርኩ ተጋባን።

፶፰ ራዕይን አይቼ ነበር በማለት በማረጋገጥ መናገሬን በመቀጠሌ፣ ስቃይ ተከተለኝ፣ እና የባለቤቴ አባት ቤተሰብም ጋብቻችንን በጣም ተቃውመውት ነበር። ስለዚህ፣ እርሷን ወደ ሌላ ስፍራ መውሰድ ያስፈልገኝ ነበረ፤ ስለዚህ፣ ሄድን እና በሳውዝ ቤይንብርጅ፣ በቸናንጎ ወረዳ ኒው ዮርክ፣ በዳኛ ታርቢል ቤት ውስጥ ተጋባን። ከጋብቻችን በኋላ ወዲያውም፣ አቶ ስቶልን ትቼ ወደ አባቴ ተመለስኩኝ፣ እና ለጊዜውም አብሬው አረስኩኝ።

፶፱ ከጊዜ በኋላ ሰሌዳውን፣ ኡሪምና ቱሚምን፣ እና የደረት ኪስን የምቀበልበት ጊዜ ደረሰ። በመስከረም ሀያ ሁለተኛው ቀን፣ አንድ ሺህ ስምንት መቶ ሀያ ሰባት ዓመተ ምህረት፣ እንደለመድኩት በአመቱ መጨረሻ ላይ ሰሌዳዎቹ ወደተቀበሩበት ስፍራ ሄጄ፣ ያው መላዕክተኛ ሰሌዳዎችን እንዲህ ከሚል ከትእዛዝ ጋር ሰጠኝ፥ ለእነርሱም ሀላፊነት አለኝ፤ በቸልተኝነት ወይም በዝንጉነት ምክንያት ቢጠፉብኝ፣ ከህይወት ተለይቼ እንደምቆረጥ፣ ነገር ግን መዕክተኛው መልሶ እስከሚጠይቅባቸው ድረስ ተግቼ ብጠብቃቸው፣ ይጠበቃሉ

እነዚህን በደንብ እንድጠብቃቸው ለምን እንደዚህ አይነት ጥብቅ ትእዛዝ እንደተቀበልኩኝ፣ እና ለምን መልእክተኛው በእጆቼ አስፈላጊ የሆኑትን ከፈጸምኩኝ በኋላ መልሶ እንደሚወስዳቸው እንደነገረኝ ወዲያው አወቅሁኝ። እነዚህ እንዳሉኝ ወዲያው ሲታወቅ፣ ወዲያኑ እነዚህን ከእኔ ለመውሰድ ብርቱ ተፅዕኖ ተፈጥሮ ነበር። ሊፈጠር የሚቻለው እያንዳንዱ እቅድ ሁሉ ለዚህ አላማ ተሞክሮ ነበር። ስቃዩም ከቀድሞው በላይ የከፋ እና ሀይለኛም ሆነ፣ እና ብዙዎችም የሚቻል ከሆነ እነዚህን ከእኔ ለመውሰድ በንቃት ይጠብቁ ነበር ነገር ግን በእግዚአብሔር ጥበብ፣ በእጆቼ የተጠበቁብኝን በእነርሱ እስክፈፅም ድረስ፣ በእጆቼ በደህንነት ቆዩ። በታቀደው መሰረት መልእክተኛው ሊወስዳቸው ሲመጣ፣ እነሱንም መልሼ ሰጠሁት፤ እና እስካሁን እስከ ግንቦት ሁለት ቀን፣ አንድ ሺህ ስምንት መቶ ሰላሳ ስምንት አመተ ምህረት ደረስ በእርሱ ጥበቃ ስር ናቸው።

፷፩ ትርምሱ ግን አሁንም ቀጥሏል፣ እና አሉባልታም በአንድ ሺህ ምላሶቿ ስለአባቴ ቤተሰቦችና ስለእኔ ሀሰቶችን ለማሰራጨት ጊዜዋን ሁሉ ታሳልፋለች። አንድ ሺህ ክፍሉን እንኳን ብናገር፣ ብዙ መጻሀፍትን ይሞላሉ። ስደቱ ግን በጣም አስቸጋሪ በመሆኑ ማንቸስተርን ትቼ መሄዴ፣ እና ከባለቤቴ ጋር ወደ ፔንስልቬንያ ስቴት በሰስኮሀና ወረዳ መሄዴ አስፈላጊ ሆነ። ለመጀመር እየተዘጋጀን እያለን—በጣም ድሆችም ስለነበርን፣ እና ስደቱም በጣም ከባድ ስለነበረብን ከዚህም የተለየ የምንሆንበት ምንም እድል አልነበረንም—በስቃዮቻችን መካከል ማርቲን ሀሪስ በሚባል የተከበረ ሰው ባልንጀራ አገኘን፣ እርሱም ወደእኛ መጣ እና ለጉዞአችን እንዲረዳን ሀምሳ ዶላሮችን ሰጠን። አቶ ሀሪስ በኒው ዮርክ ስቴት የፓልማይራ ከተማ፣ የዌይን ወረዳ ነዋሪ፣ እና የተከበረ ገበሬም ነበር።

፷፪ በዚህ በጊዜአዊው እርዳታ ወደምሄድበት ስፍራ ወደ ፔንስልቬንያ እንድደርስ አስቻለኝ፤ እና እዚያም እንደደረስኩ ወዲያውም የሰሌዳውን ፊደሎች መጻፍ ጀመርኩኝ። ብዙዎችንም ጻፍኩ፣ እና ኡሪምና ቱሚምን በመጠቀም አንዳንዶቹን ተረጎምኩ፣ ይህንም ያደረኩት በሚስቴ አባት ቤት ከደረስኩበት፣ ከታህሳስ ወር፣ እና በሚቀጥለው የካቲት መካከል ነበር።

፷፫ በዚህ የካቲት ወር ውስጥ አንዴ ከዚህ በፊት የተጠቀሰው አቶ ማርቲን ሀሪስ ወደ ስፍራችን መጣ፣ ከሰሌዳዎቹ የጻፍኳቸውን ፊደሎች ወሰደ፣ እና ወደ ኒው ዮርክ ከተማ ይዞአቸው ሄደ። በእርሱ እና በፊደሎቹ ስለደረሰባቸው በሚመለከት፣ ሲመለስ ለእኔ እንደነገረኝ፣ ስለጉዳዮቹ ታሪክ ወደተናገራቸው አመለክታለሁ፣ ይህም እንዲህ ነበር፥

፷፬ “ወደ ኒው ዮርክ ከተማ ሄጄ የተተረጎሙትን ፊደላት፣ እና ትርጉማቸውን በድርሰት ችሎታቸው ታዋቂ ወደ ነበሩት ክብር ሰው ፕሮፌሰር ቻርልስ አንቶን ወሰድኩኝ። ፕሮፌሰር አንቶን ትርጉሙ ከዚህ በፊት ከግብጻውያን ትርጉሞች ካያቸው ሁሉ በላይ ትክክል እንደሆነ ነገረኝ። ከዚያም ያልተተረጎሙትን አሳየሁት፣ እና እነርሱ ግብጻውያን፣ ችሃልዴይክ፣ አሲርኛ፣ እና አረባዊ ናቸው አለ፤ እና እነዚህ እውነተኛ ፊደላት ናቸው አለ። ለፓልማይራ ህዝቦች እነዚህ እውነተኛ ፊደላት እንደሆኑ፣ እና ትርጉሞቹ እንደተተረጎሙት ትክክል እንደሆኑ የሚያሳይ የምስክር ወረቀትንም ሰጠኝ። የምስክር ወረቀቱን ወሰድኩኝ እና በኪሴ ውስጥ አስቀመጥኩት፣ እና ቤቱን ትቼ ለመሄድ ስወጣ፣ አቶ አንቶን ጠራኝ፣ እና ወጣቱም ሰው እንዴት ባገኛቸው ስፍራ የወርቅ ሰሌዳዎች እንደነበሩ እንዳወቀ ጠየቀኝ። የእግዚአብሔር መልአክ ገለጠለት ብዬ መለስኩኝ።

፷፭ “ከዚያም እንዲህ አለኝ፣ ‘የምስክር ወረቀቱን ልየው።’ ከኪሴም አውጥቼ ሰጠሁት፣ ሲወስደውም አሁን የመላእክት አገልግሎት የሚባል ነገር እንደሌለ፣ እና ሰሌዳዎቹን ወደእርሱ ባመጣቸው እንደሚተረጉማቸው በመናገር ቀደደው። የሰሌዳዎቹ ክፍሎች የተዘጉ እንደሆኑ፣ እና እኔም እንዳላመጣቸው የተከለከልኩኝ እንደሆነም ነገርኩት። እንዲህም መለሰልኝ፣ ‘የታሸገ መፅሀፍ ማንበብ አልችልም።’ ከእርሱ ተለይቼ ወደ ዶክተር ሚችል ሄድኩኝ፣ እርሱም ፕሮፌሰር አንቶን ስለፊደላቱ እና ስለትርጉማቸው በሚመለከት የተናገረውን ደገፈ።”

· · · · · · ·

ኦሊቨር ካውደሪ መፅሐፈ ሞርሞንን በሚተረጎምበት ጸሀፊ በመሆን አገለገለ—ጆሴፍ እና ኦሊቨር ካውደሪ የአሮናዊ ክህነት ከመጥመቁ ዮሐንስ ተቀበሉ—እነርሱም ተጠመቁ፣ ተሾሙ፣ እናም የትንቢት መንፈስን ተቀበሉ። (አንቀፅ ፷፮–፸፭።)

፷፮ በሚያዝያ ፭ ቀን፣ ፲፰፻፳፱ (እ.አ.አ.) ኦሊቨር ካውደሪ ወደቤቴ መጣ፣ እስከዚህ ጊዜ ድረስ አይቼው አላውቅም ነበር። አባቴ በሚኖርበት መንደር ትምህርት ያስተምር እንደነበር፣ እና አባቴ ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት ከሚልኩት አንዱ በመሆኑ፣ በእርሱ ቤት ለጊዜው ለመኖር እንደሄደ፣ እዚያም እያለ ቤተሰብ ሰሌዳዎችን የተቀበልኩባቸውን ጉዳይ እንደነገሩት፣ እና በዚህም መሰረት እኔን ለመጠየቅ እንደመጣ ነገረኝ።

፷፯ አቶ ካውደሪ ከመጣ ሁለት ቀናት ካለፉ በኋላ (ሚያዝያ ፯ ሆኖ)፣ መፅሐፈ ሞርሞንን መተርጎም ቀጠልኩኝ፣ እና እርሱም ለእኔ መጻፍ ጀመረ።

· · · · · · ·

፷፰ የትርጉም ስራውን ቀጠልን፣ በሚቀጥለውም ወር [ግንቦት፣ ፲፰፻፳፱ (እ.አ.አ.)]፣ አንድ ቀን ወደ ቁጥቋጣዎቹ በመሄድች ለመጸለይ እና በሰሌዳዎች ትርጉም ውስጥ ስለተጠቀሱት ለኃጢአት ስርየት መጠመቅን በሚመለከት ጌታን ለመጠየቅ ሄድን። እየጸለይን እና ጌታን እየጠራን ሳለን፣ የሰማይ መልእክተኛ በብርሀን ዳመና ወረደ፣ እና እጆቹን በራሳችን ላይ በመጫን እንዲህ በማለት ሾመን

፷፱ በእናንተ አገልጋይ ባልንጀሮቼ ላይ፣ የመላእክትን፣ እና የንስሃ ወንጌልን፣ እና ለኃጢአት ስርየት በማጥለቅ የመጠመቅን አገልግሎት ቁልፎች የያዘውን የአሮንን ክህነት በመሲሁ ስም ለእናንተ እሰጣችኋለሁ፤ እናም የሌዊ ልጆች እንደገና መስዋዕት ለጌታ በጽድቅ እስከሚሰዉ ድረስ ይህ ከምድር ላይ ዳግመኛ በፍጹም አይወሰድም።

ይህ የአሮናዊ ክህነት እጆችን በመጫን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን የመስጠት ሀይል እንደሌለው፣ ነገር ግን ይህም ከዚህ በኋላ እንደምንሾምበት ነገረን፣ እና እንድንሄድ እና እንድንጠመቅ አዘዘን፣ እና እኔ ኦሊቨር ካውደሪን እንዳጠምቅ፣ እና ከዚያም በኋላ፣ እርሱ እንዲያጠምቀኝ መመሪያዎችን ሰጠን።

፸፩ በዚህም መሰረት ሄድን እና ተጠመቅን። እርሱን መጀመሪያ አጠመቅሁት፣ እና በኋላም እርሱ እኔን አጠመቀኝ—ከዚያም በኋላ እጆቼን በራሱ ላይ በመጫን ለአሮናዊ ክህነት ሾምኩት፣ በኋላም እርሱ እጆቹን ጭኖብኝ ለዚህ አይነት ክህነት ሾመኝ—እኛ እንደዚህም ታዘን ነበርና።*

፸፪ በዚህ ጊዜ የጎበኘን እና ይህን ክህነት ለእኛ የሰጠን መልእክተኛ ስሙ በአዲስ ኪዳን ውስጥ መጥምቁ ዮሐንስ ተብሎ የተጠራው፣ ዮሐንስ እንደነበር፣ እና ይህን ያደረገውም የመልከ ጼዴቅ ክህነት ቁልፎችን በያዙት በጴጥሮስያዕቆብ፣ እና ዮሐንስ አመራር እንደሆነ ነገረን፣ ይህም ክህነት በጊዜው ለእኛ እንደሚሰጠን፣ እና እኔም የቤተክርስቲያኗ የመጀመሪያ ሽማግሌ፣ እና እርሱም (ኦሊቨር ካውደሪ) ሁለተኛ ተብለን እንደምንጠራም ነገረን። በዚህ መልእክተኛ እጆች የተሾምንበት እና የተጠመቅንበት ቀን ግንቦት አስራ አምስት፣ ፲፰፻፳፱ (እ.አ.አ.) ነበር።

፸፫ ከተጠመቅን በኋላ ከውሀው ወዲያው ስንወጣ፣ ታላቅ እና የከበሩ በረከቶችን ከሰማይ አባታችን አገኘን። ኦሊቨር ካውደሪን ወዲያው እንዳጠመቅሁት፣ መንፈስ ቅዱስ አረፈበት፣ እና ተነሳ እና በቅርቡ የሚፈጸሙ ብዙ ነገሮችን ተነበየ። ደግሞም፣ ወዲያው እኔ እንደተጠመቅሁ፣ ተነስቼ ስለዚህ ቤተክርስቲያን መነሳት፣ እና ቤተክርስቲያኗን እና የዚህ ትውልድ የሰው ልጆችን በሚመለከት በብዙ ሌሎች ነገሮች ስተነብይም፣ የትንቢት መንፈስ እኔ ደግሞ ነበረኝ። በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተን ነበር፣ እና በደህንነታችን አምላክ ተደሰትን።

፸፬ አዕምሮአችን አሁን ተብራርተው ቅዱስ መጻህፍት ይገቡን ዘንድ ተከፈቱልን፣ እና የእነዚህ ብዙ ሚስጥራዊ ምንባቦች እውነተኛ ትርጉምና እቅድ ከዚህ በፊት ልናገኛቸው በማንችለው፣ ወይም ከዚህ በፊት አስበንባቸው በማንውቀው መንገድ ተገለጡልን። በሰፈራችን ራሱን እያሳየ በነበረው የስደት መንፈስ ምክንያት፣ በዚህም ጊዜ ክህነትን የመቀበላችንን እና የመጠመቃችንን ጉዳይ በሚስጥር ለመጠበቅ ተገድደን ነበር።

፸፭ ከጊዜ ወደ ጊዜም፣ በአመጽ የተነሳሱ ሰዎች አስፈራርተውናል፣ እና ይህም በሀይማኖት በሚያምኑት ነበር። የሚያስፈራሩን አመጸኞች ፍላጎትም የተቆጣጠረው ለእኔ ባልንጀራ እየሆኑ በመጡት፣ እና አመጸኛዎችን በሚቃወሙት፣ እና ያለማቋረጥ የትርጉም ስራን ለመቀጠል እንዲፈቀድልኝ ፍላጎት በነበራቸው በባለቤቴ አባት ቤተሰብ ተፅዕኖ (በመለኮታዊ ጥበቃ) ብቻ ነበር፤ ስለዚህም ህጋዊ ካልሆኑ እርምጃዎች፣ እስከችሎታቸው ድረስ፣ እኛን ለመጠበቅ ፈቃደኛነታቸውን ገለጹ እና ቃል ኪዳንም ገቡልን።

  • ኦሊቨር ካውደሪ እነዚህን ሁኔታዎች እንደዚህ ገለጠ፥ “እነዚህ በምንም የማይረሱ ቀናት ነበሩ—በሰማይ መነሳሳት በታገዘ ድምጽ በታች መቀመጥ፣ የዚህን ልብ ታላቅ ምስጋናን ያስነሳል! ከቀን ወደ ቀን፣ ሳይቋረጥ፣ በኡሪምና ቱሚም ወይም ኔፋውያን እንደሚሉትም ‘መተርጓሚያዎችን’ በመጠቀም፣ ‘መፅሐፈ ሞርሞን’ የሚባለውን ታሪክ ወይም መዝገብ ከአፉ ለመጻፍ ቀጠልኩኝ።

    “በሞርሞን እና በታማኝ ልጁ ሞሮኒ የተሰጡትን የሚያስደንቁ በሰማይ ተወደው እና ተደግፈው የነበሩ ህዝቦችን ታሪክ በጥቂት ቃላት መጥቀስ አሁን ካለኝ እቅዴ በላይ ነው፤ ስለዚህ ይህን ለመጪው ጊዜ እተወዋለሁ፣ እና በመግቢያው እንዳልኩት በዚህ ቤተክርስቲያን መነሻ ጊዜ ስለነበሩት፣ በአክራሪዎች መናደድ እና በግብዞች አሉባልታ መካከል ወደፊት ለሄዱት እና የክርስቶስን ወንጌል ለተቀበሉት የሚያስደስታቸው አንዳንድ ጥቂት ጉዳዮች ጋር ስለተያያዙት እፅፋለሁ።

    “ንጹህ አለመሆን በሰዎች መካከል የሚጠቀሙበት ሁሉም አይነት ድርጅቶች እና ዘዴዎች ላይ አለመረጋገጥ በሚያስፋፋበት ጊዜ፣ ማንም ሰው በረጋ ስሜታቸው፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ የበጎ ህሊናን ለመመለስ የልብ ፈቃድን በማሳየት በውሀ መቃብር ውስጥ የመቀበር መብትን ፍላጎት ያለማሳየት ለኔፋውያን ከአዳኝ አፍ ቤተክርስቲያኑን ሰዎች የሚገነቡበትን ትክክለኛ መንገድ የተሰጣቸውን መመሪያዎች ለመተርጎም እና ለመጻፍ ማናቸውም ሰዎች አይችሉም።

    “በዚህ ክፍለ አህጉር ላይ ለያዕቆብ ዘር ቅሪቶች ስለአዳኝ አገልግሎት የተሰጠውን ታሪክ ከተጻፈ በኋላ፣ ነቢዩ ይሆናል እንዳለው ጭለማ ምድርን እና ያልታረመ ጭለማ የህዝቦችን አዕምሮዎች እንደሸፈነ ለማየት ቀላል ነበር። በተጨማሪ በማሰብም ሀይማኖትን በሚመለከት በነበረው ታላቅ ሁካታ እና ጩኸት መካከል፣ የወንጌልን ስነስርዓቶች ለማከናወን ማንም ከእግዚአብሔር ስልጣን እንደሌለው ለማየት ቀላል ነበር። ይህንንም ጥያቄ ሊጠየቅም ይቻላል፣ ምስክሩ ከትንቢት መንፈስ ያነሰ ሳይሆን፣ እና ሀይማኖቱ በሰዎች በምድር በነበረበት በአለም እድሜዎች ሁሉ በራዕይ ላይ በተመሰረቱ፣ በተገነቡ፣ እና በተደገፉ በክርስቶስ ስም፣ ራዕይን የሚክዱ ሰዎች ለማስተዳደር ስልጣን አላቸውን? እነዚህ ነገሮች በሰዎች ፊት ከተገለጹ ስራዎቻቸው አደጋ ላይ በሚሆኑባቸው የተቀበሩትና በጥንቃቄ የተደበቁት እነዚህ እውነቶች ለእኛ ከዚህ በኋላ አልተደበቁም፤ እና ‘ተነሳና ተጠመቅ’ የሚለውን ትእዛዝ እንዲሰጠን ብቻ እንጠብቃለን።

    “ይህም እውነት ከመሆኑ በፊት ለብዙ ጊዜ በፍላጎት አልጠበቅንም። በምህረቱ ባለጠጋ የሆነው፣ እና የትሁቱን ዘላቂ ጸሎት ለመመለስ ፍላጎት ያለው ጌታ፣ ሰዎች ከሚኖሩበት ተለይተን፣ ልብ በሚነካ አኳኋን ከጠራነው በኋላ፣ ፈቃዱን ለእኛ ለማሳየት ወረደ። በድንገት፣ ከዘለአለም መካከል እንደሆነ አይነት፣ መጋረጃው ተከፈተ እና የእግዚአብሔር መልአክ በክብር ልብስ ተሸፍኖ፣ እና በጉጉት ይጠበቅ የነበረውን መልእክት፣ እና የንስሀን ወንጌል ቁልፎችን ለመስጠት ሲወርድ፣ የአዳኝ ድምፅ ሰላምን ተናገረን። ምን አይነት ደስታ! ምን አይነት ድንቅ! እንዴት ያስገርማል! አለም በጣም እየተቸገረ እና እየተምታታ እያለ—ሚልዮኖችም እንደ አይነ ስውር ግድግዳን ለመንካት በዳበሳ ሲፈልጉ፣ እና ሁሉም ሰዎች በማይረጋገጥ ነገር ላይ እየተመኩ እያሉ፣ እንደ ‘ቀትር ብርሀን’ አይነት አይኖቻችን አዩ፣ ጆሮዎቻችንም ሰሙ፤ አዎ፣ ተጨማሪም—በፍጥረት ፊት ላይ ብሩህነቱን እንደሚጥለው ከግንቦት የጸሀይ ብርሀን መንጸባረቅ በላይ! ከዚያም ድምጹ፣ ረጋ ያለ ቢሆንም፣ ውስጥን ሰንጥቆ የሚገባ ነበር፣ እና ‘እኔ ከእናንተ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ’ ያለው ቃላቶቹ እያንዳንዱን ፍርሀት በተናቸው። አዳመጥን፣ አተኮርን፣ ተገረምን! ይህም ከክብር የመጣ የመልአክ ድምፅ ነበር፣ ይህም ከልዑል የመጣ መልአክ ነበር! ፍቅሩም በነፍሶቻችን ላይ እየተቀጣጠለ እያለ፣ ስናደምጥም ተደሰትን፣ እና ሁሉን በሚገዛ ራዕይ ተጠቅልለን ነበር! ለመጠራጠር ምን ስፍራ ነበረ? የትም አልነበረም፤ እርግጠኛ አለመሆን ሸሸ፣ ልብ ወለድ እና ሐሰት ለዘለአለም ሲሸሽም፣ መጠራጠርም እንደገና ላለመነሳት ሰመጠ!

    “ነገር ግን፣ ውድ ወንድም፣ አስብ፣ በተጨማሪም ለጥቂት ጊዜ አስብ፣ ልባችንን ምን አይነት ደስታ ሞላው፣ እና በምን አይነት ድንቅ ሰገድን፣ (ለዚህ አይነት በረከት የማን ጉልበቶች ታጥፈው አይሰግዱም?) ከእጆቹ ቅዱስ ክህነትን ስንቀበል እንዲህ አለ፣ ‘አገልጋይ ባልንጀሮቼ፣ የሌዊ ልጆች እንደገና መሰዋዕትን ለጌታ በጽድቅ እስኪያቀርቡ ድረስ ይህ ከምድር ላይ ዳግመኛ በፍጹም የማይወሰደውን ይህን ክህነት እና ሀላፊነት በመሲሁ ስም ለእናንተ እሰጣችዋኋለሁ!’

    “የዚህን ልብ ስሜት፣ ወይም በዚህ ጊዜ የከበበንን ውበት እና ክብር ልገልፅላችሁ አልሞክርም፤ ነገር ግን ምድር ወይም ሰው በጊዜ ልሳን ቅንነት እንደዚህ ቅዱስ ሰው አይነት የሚያስደንቅ ወይም ልብ የሚማርክ ቋንቋ ለማልበስ ለመጀመር አይቻልም ስላችሁ ታምኑኛላችሁ። አይደለም፤ ይህች ምድርም ደስታን የመስጠት፣ ሰላም የመስጠት፣ ወይም በመንፈስ ቅዱስ ሀይል እያንዳንዱ አረፍተ-ነገር ሲሰጡ በውስጣቸው የነበራቸውን ጥበብ ለመረዳት ሀይል የላትም! ሰው ጓደኛውን ለማታለል ይችላል፣ ማታለልም ማታለልን ይከተላል፣ እና የክፉው ልጆችም ሞኞችንና ያልተማሩትን ከልብ ወለድ በስተቀር ምንም ብዙዎችን ለመመገብ እስከማይችል ድረስ ለማዳራት፣ እና የሀሰተኛነት ፍሬም ወረተኛውን ወደመቃብሩ በፍሰቱ ይዞት የሚሄድበት ሀይል ይኖራቸው ይችላሉ፣ ነገር ግን በፍቅሩ አንድ ጣት መነካት፣ አዎ፣ ከከፍተኛው አለም አንድ የክብር ጨረር፣ ወይም አንድ ቃል፣ ከዘለአለም እቅፍ፣ ከአዳኝ አንደበት፣ ሁሉንም ዋጋ የሌላቸው ያደርጋቸዋል፣ እና ከአዕምሮምለዘለአለም ይሰርዛቸዋል። በመልአክ ፊት እንደነበርን ማረጋገጫ፣ የኢየሱስን ድምፅ እንደሰማን ማረጋገጫ፣ እና እውነቱ ሳይበላሽ ከንጹህ ሰውየው በእግዚአብሔር ፈቃድ የቃል ፅህፈት ሳይቋረጥ መምጣቱ ለእኔ መግለጫ የማይቻልበት ነው፣ እና በህይወትም እያለሁ በዚህ የአዳኝ መልካምነት መግለጫ ላይም በድንቅ እና በምስጋና ነው የምመለከተው፤ እና ፍጹምነት በሚኖርበት እና ኃጢአት በምንም በማይገባበት ቤቶች ውስጥ፣ እርሱን ማለቂያ በሌለው ቀን ውስጥ ላፈቅረው ተስፋ አለኝ።”—Messenger and Advocate ቅፅ ፩ [ጥቅምት ፲፰፻፴፬ (እ.አ.አ.)]፣ ገፅ ፲፬–፲፮።