ቅዱሳት መጻህፍት
፫ ኔፊ ፳፭


ምዕራፍ ፳፭

በዳግም ምፅዓት ጊዜ ትዕቢተኞች፣ እናም ኃጢአተኞች እንደገለባ ይቃጠላሉ—ኤልያስ ከታላቁና ከአስፈሪው ቀን በፊት ይመለሳል—ሚልክያስ ፬ን አነጻፅሩ። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

እነሆም፣ እንደ ምድጃ እሳት የሚነድ ቀን ይመጣል፤ እናም ትዕቢተኞች ሁሉ አዎን፣ እናም ኃጢያትን የሚሰሩ ሁሉ ገለባ ይሆናሉ፤ የሚመጣውም ቀን ያቃጥላቸዋል፤ ሥርንና ቅርንጫፍንም አይተውላቸውም ይላል የሠራዊት ጌታ።

ነገር ግን ስሜን ለምትፈሩ፣ ለእናንተ የፅድቅም ልጅ ፈውስን በክንፎቹ ይዞ ይነሳል፤ እናንተም ትወጣላችሁ እናም እንደጥጃም በበረት ታድጋላችሁ

እናም ክፉዎችን ትረግጡአችዋላችሁ፤ እናም ይህንን በምሰራበት ቀን በደለኞች ከእግራችሁ ሥር አመድ ይሆናሉ፣ ይላል የሠራዊት ጌታ።

ለእስራኤል ሁሉ ስርዓትንና ፍርድን አድርጌ በኮሬብ ያዘዝሁትን የባሪያዬን የሙሴን ህግ አስቡ።

እነሆ፣ ታላቁና የሚያስፈራው የጌታ ቀን ሳይመጣ ነቢዩ ኤልያስን እልክላችኋለሁ፤

እናም ምድርን በእርግማን እንዳልመታ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፣ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል