ቅዱሳት መጻህፍት
፫ ኔፊ ፳፪


ምዕራፍ ፳፪

በመጨረሻው ቀን ፅዮንና ካስሚያዎችዋ ይቋቋማሉ፣ እናም እስራኤል በምህረትና በደግነት ይሰበሰባሉ—እነርሱም አሸናፊ ይሆናሉ—ኢሳይያስ ፶፬ን አነጻፅሩ። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

፩ እናም የተፃፈውም እንዲህ ይፈፀማል፥ አንቺ ያልወለድሽ መካን ሆይ ዘምሪ፤ አንቺ ያላማጥሽ እልል በይ፤ እናም በዝማሬ ጩኺ፣ ባል ካላት ይልቅ ፈት የሆነችው ልጆች በዝተዋልና ይላል ጌታ።

፪ የድንኳንሽን ስፍራ አስፊ፤ መጋረጃዎችሽንም ይዘርጉ፤ አትቆጥቢ፣ ገመድሽን አስረዝሚና ካስሞችሽንም አፅኚ፤

፫ በቀኝና በግራም ትስፋፊያለሽ፣ እናም ዘሮችሽም አህዛብን ይወርሳሉና የፈረሱትን ከተሞች መኖሪያ ያደርጋሉ።

፬ አታፍሪምና አትፍሪ፤ እንድታፍሪ ስለማይደረግ ዝም አትበይ፤ የልጅነትሽን እፍረት ትረሺዋለሽ፣ የልጅነትሽን ብሉሽነትሽን ውቅት ከእንግዲህ አታስታውሺም፣ የመበለትነትሽንም ወቅት ከእንግዲህ ወዲህ አታስቢውም።

፭ ፈጣሪሽ ባልሽ ነው፤ ስሙም የሰራዊት ጌታ ነው፤ እናም የእስራኤል ቅዱስ የሆነውም አዳኝሽ ነው—የምድር ሁሉ አምላክ ተብሎም ይጠራል።

፮ ጌታ እንደተተወችና እንደተበሳጨች መንፈስ፣ እናም በልጅነት እንደጣሉአት ሚስት ጠርቶሻል ይላል አምላክሽ።

፯ ለጥቂት ጊዜ ጣልኩሽ፣ ነገር ግን በታላቅ ምህረት እሰበስብሻለሁ።

፰ በጥቂት ቁጣ ለቅፅበት ፊቴን ከአንቺ ሰወርኩ፣ ነገር ግን በዘለዓለም ቸርነት እምርሻለሁ ይላል ጌታ አዳኝሽ።

፱ ይህ ለእኔ እንደ ኖህ ውኃ ነው፤ የኖህ ውሃ ደግሞ በምድር ላይ እንዳያልፍ እንደማልሁ እንዲሁ አንቺን እንዳልቆጣ እንዳልዘልፍሽም ምያለሁ።

፲ ተራሮች ይፈርሳሉ፤ ኮረብቶችም ይወገዳሉ፣ ቸርነቴ ግን ከአንቺ ዘንድ አያልፍም፣ የሰላሜም ቃል ኪዳን አይወገድም ይላል መሃሪሽ የሆነ ጌታ።

፲፩ አንቺ የተቸገርሽ ሆይ፣ በአውሎ ነፋስም የተናወጥሽ፣ ያልተፅናናሽም! እነሆ፣ ድንጋዮችሽን ሸላልሜ እገነባለሁ፤ በሰንፔርም ጌጥ እመሰርትሻለሁ።

፲፪ የግንብሽንም ጉልላት በቀይ ዕንቁ፤ በሮችሽንም በሚያብረቀርቅ ዕንቁ፤ ዳርቻሽንም ሁሉ በከበሩ ድንጋዮች እሰራለሁ።

፲፫ እናም ልጆችሽ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፤ እናም የልጆችሽም ሰላም ታላቅ ይሆናል።

፲፬ በፅድቅ ትታነፂያለሽ፤ ከግፍ አድራጊ አትፈሪምና ድንጋጤም ወደ አንቺ አይቀርብም።

፲፭ እነሆ፣ በእርግጥም ባንቺ ላይ ይሰበሰባሉ ነገር ግን ከእኔ ዘንድ አይሆንም፤ በአንቺም ላይ የሚሰበሰቡ ሁሉ ከአንቺ የተነሳ ይወድቃሉ።

፲፮ እነሆ፣ ፍሙን በወናፍ የሚያናፋ ለስራውም መሳሪያ የሚያወጣ ብር ሰሪን እኔ ፈጥሬአለሁ።

፲፯ በአንቺ ላይ የተሰራ መሳሪያ ሁሉ አይከናወንም፣ በፍርድም በሚነሳብሽ ምላስ ሁሉ ትፈርጂበታለሽ። የጌታ ባሪያዎች ቅርስ ይህ ነው፤ ጽድቃቸውም ከእኔ ዘንድ ነው ይላል ጌታ።