አጠቃላይ ጉባኤ
በጌታ መታመን
የሚያዝያ 2024 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


በጌታ መታመን

ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት ሊያድግ የሚችለው እኛ እርሱን ለማመን ባለን ፈቃደኝነት መጠን ብቻ ነው።

አንዳንድ ጊዜ በቤተሰባችን ውስጥ ‘’በማመን መውደቅ’’ ብለን የምንጠራውን ጨዋታ እንጫወታለን። እናንተም እንዲሁ ተጫውታችሁት ሊሆን ይችላል። ሁለት ሰዎች፣ አንደኛው ለሌላኛው ጀርባ በመስጠት በጥቂት ሜትር ርቀት ልዩነት ይቆማሉ። ከጀርባው ካለው ግለሰብ ምልክት ሲሰጠው፤ ከፊት ያለው ተዘርግቶ በሚጠባበቀው በጓደኛው እጅ ላይ ወደኋላ ይወድቃል።

እምነት የሁሉም ግንኙነቶች መሰረት ነው። ለማንኛውም ግንኙነት መሰረታዊው ጥያቄ “እኔ ሌላውን ሰው ማመን እችላለሁ?” የሚለው ነው። መቀራረብ ሊኖር የሚችለው፣ ሰዎች አንዳቸው በሌላኛው ላይ እምነት ለመጣል ፈቃደኞች ሲሆኑ ብቻ ነው። አንዱ ግለሰብ ሙሉ ለሙሉ እምነቱን ጥሎ ሌላኛው ግን እምነቱን ካልጣለ ግንኙነት አይደለም።

እያንዳንዳችን የተወደድን የሰማይ አባት የመንፈስ ወንድ እና ሴት ልጆች ነን።1 ነገር ግን ያ መንፈሳዊ የዘር ሀረግ መሰረት ቢጥልም፣ በራሱ ከእግዚአብሔር ጋር የጎለበተ ግንኙነት አይፈጥርም። ግንኙነት ሊገነባ የሚችለው በእርሱ ለማመን ስንመርጥ ብቻ ነው።

የሰማይ አባት ከእያንዳንዱ የመንፈስ ልጆቹ ጋር የቀረበ እና የግል ግንኙነትን መፍጠር ይሻል።2 ኢየሱስ፣ “በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፣ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ።”3 ብሎ በፀለየ ጊዜ ያንን መሻት ገልጿል። እግዚአብሄር ከእያንዳንዱ የመንፈስ ልጅ ጋር እንዲኖረውየሚሻው ግንኙነት ቅርብ እና ግላዊ ከመሆኑ የተነሳ እርሱ ያለውን ሁሉ እና እርሱ የሆነውን ሁሉ ያካፍላል።4 የዚያ ዓይነቱ ጥልቅ፤ የሚዘልቅ ግንኙነት ሊጎለብት የሚችለው ፍፁም፤ አጠቃላይ በሆነ እምነት ላይ ብቻ ነው።

በእርሱ በኩል የሰማይ አባት ከመጀመሪያው ጀምሮ እያንዳንዱ ልጆቹ ባላቸው መለኮታዊ ብቃት ላይ ፍፁም እምነት እንዳለው ለማስተላለፍ ሲሰራ ቆይቷል። እምነት ወደ ምድር ከመምጣታችን አስቀድሞ እንድናድግ እና እንድንሻሻል ላቀረበልንን እቅድ መሠረት ይጥላል። እርሱ ዘላለማዊ ህጎቹን በማስተማር፣ ምድርን በመፍጠር፣ ሥጋዊ አካልን በመስጠት፤ በራሳችን የምንመርጥበትን የመምረጥ ስጦታ በመስጠት እንዲሁም የራሳችንን ምርጫ በማድረግ እንማር እና እናድግ ዘንድ ይፈቅድልናል። የእርሱን ህጎች መከተልን እንድንመርጥ እና ከእርሱ እና ከልጁ ጋር በዘለዓለም ህይወት ለመደሰት እንመለስ ዘንድ ይሻል።

ዘወትር መልካም ምርጫን ልናደርግ እንደማንችል በማወቁ፤ ከመጥፎ ምርጫዎች ውጤት የምናመልጥበትን መንገድም እንዲሁ አዘጋጅቶልናል። በንሰሀ አማካይነት ዳግም እንድንነጻ የሃጢያት ክፍያን ይፈጽም ዘንድ አዳኙን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን አዘጋጀልን።5 የንሰሃ ስጦታን አዘወትረን እንድንጠቀም ጋብዞናል።6

እያንዳንዱ ወላጅ፣ ልጆቻቸው ስህተትን እንደሚሰሩ እና በተለይ ያንን ተከትሎ በሚመጣው ውጤት ተጎጂ እንደሚሆኑ በሚያውቅበት ጊዜ ልጆቻቸውን በራሳቸው እንዲወስኑ መፍቀድ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ያውቃል። ሆኖም፣ የሰማይ አባት መለኮታዊ አቅማችን ላይ እንድንደርስ የሚረዱንን ምርጫዎች እንድናደርግ ይፈቅዳል። ሽማግሌ ዴል ጂ. ረንለንድ እንዳስተማሩት፣ “[የእርሱ] የወላጅነት ዓላማ ልጆቹ ትክክለኛውን እንዲያደርጉ ማስገደድ ሳይሆን ልጆቹ ትክክለኛውን ነገር ማድረግን እንዲመርጡ፣ በመጨረሻም እንደ እርሱ እንዲሆኑ ነው።”7

ይሁን እንጂ እግዚአብሔር በእኛ ላይ እምነት ቢኖረውም፣ ከእርሱ ጋር ያለን ግንኙነት ሊያድግ የሚችለው እኛ እርሱን ለማመን ባለን ፈቃደኝነት መጠን ብቻ ነው። ችግሩ፣ በወደቀ ዓለም ውስጥ መኖራችን እና ታማኝ ባለመሆን፣ በማጭበርበር ወይም በሌሎች ሰዎች ማስገደድ ምክንያት ሁላችንም በሌሎች ላይ እምነት እንድናጣ ያደረጉን ገጠመኞች ስላሉን ነው። አንዴ ክህደት ከተፈፀመብን በኋላ፣ ዳግም ማመንን ከባድ ሆኖ እናገኘዋለን። ፍፁም ባልሆኑ ምድራውያን ምክንያት የሚከሠቱ አሉታዊ የእምነት ተሞክሮዎች፣ ፍጹም የሆነውን የሰማይ አባት የማመን ፈቃደኝነታችን ላይ ተፅዕኖ ያሳድሩብናል።

ከረዥም ዓመታት በፊት፣ ሁለት ጓደኞቼ ሌዎኒድ እና ቫለንቲና የቤተክርስቲያኗ አባል የመሆን ፍላጎታቸውን ገለጹልኝ። ሊዎኒድ ወንጌልን መማር እንደጀመረ፣ መፀለይ ከባድ ሆኖበት ነበር። ሊዎኒድ በቀድሞ ህይወቱ ማጭበርበር እና በአለቆች መቆጣጠር ስለደረሰበት ስልጣን ባላቸው ላይ እምነትን አጥቶ ነበር። የቀድሞ ገጠመኞቹ ልቡን መክፈትን እና ለሰማይ አባት ያለውን ስሜት መግለፅን ከባድ አድርገውበት ነበር። ከጊዜ በኋላ እና በጥናት፣ ሊዎኒድ ስለ እግዚአብሔር ባህርይ የተሻለ ግንዛቤን አገኘ እንዲሁም እግዚአብሔር ለእሱ ያለውን ፍቅር አወቀ። በመጨረሻም ፀሎት ምስጋናን የሚገልፅበት እና በምላሹም ለእግዚአብሔር ያለውን የፍቅር ስሜት የሚያሳይበት ተፈጥሮአዊ መንገድ ሆነለት። በእግዚአብሔር ላይ ያለው የጨመረ እምነት፣ እሱ እና ቫለንቲና ከእግዚአብሔር ጋር እና እርስ በእርሳቸው ያላቸውን ግንኙነት እንዲያጠነክሩ ቅዱስ ቃልኪዳኖችን ወደ መግባት መራቸው።

የቀድሞ እምነት የማጣት ገጠመኞቻችሁ እግዚአብሔርን እንዳታምኑት አድርገዋችሁ ከሆነ አባካችሁ የሌዎኒድን ምሣሌ ተከተሉ። ስለ እግዚአብሔር፣ ስለ ባህሪው፣ ስለ ማንነቱ እና ስለ ዓላማው ይበልጥ ለመማር በትዕግስት ቀጥሉ። በህይወታችሁ ውስጥ የእርሱን ፍቅር እና ሃይል ልምዶች ተመልከቱ እናም ዘግቡ። በሕይወት ያሉት ነቢያችን ፕሬዚዳንት ራስል ኤም ኔልሰን ስለ እግዚአብሔር በተማርን ቁጥር እርሱን ማመን ቀላል እንደሚሆንልን አስተምረዋል።8

አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔርን ለማመን ቀላሉ መንገድ እንዲሁ እርሱን ማመን ነው። ልክ “እንደሚሰቀጥጠው በማመን የመውደቅ ጨዋታ” አንዳንድ ጊዜ እርሱ እንዲይዘን ወደ ኋላ ለመውደቅ ፍቃደኞች መሆን ይኖርብናል። ምድራዊ ህይወታችን የፈተና ህይወት ነው። ከአቅማችን በላይ የሚወጥሩን ተግዳሮቶች ደጋግመው ይመጣሉ። የገዛ እውቀታችን እና መረዳታችን በቂ ሳይሆን ሲቀር፣ ሳንፈልግ እርዳታ ለማግኘት ወደ ግብአቶች እንመለከታለን። መረጃ እጅግ በበዛበት አለም ውስጥ፣ ለተግዳሮታችን የራሳቸውን መፍትሄ የሚያስተዋውቁ ምንጮች እጥረት የለብንም። ይሁን እንጂ መጽሐፈ ምሳሌ ቀላል የሆነ፣ በጊዜ የተፈተሸ ከሁሉም የተሻለውን ምክርን እንዲህ አቅርቦልናል፦ “በፍፁም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን።”9 የህይወት ፈተና ሲገጥመን አስቀድመን ወደ እግዚአብሔርን በመዞር ለእርሱ ያለንን እምነት እናሳያለን።

የህግ ትምህርቴን በዩታ ውስጥ እንደጨረስኩኝ፣ ሥራ የት እንደምንሰራ እና መኖሪያችንን የት ማድረግ እንዳለብን ቤተሰባችን ከባድ ውሳኔ ገጠመው። እርስ በርሳችን እንዲሁም ከጌታ ጋር ከተማከርን በኋላ፣ ከወላጆች እና ከእህት ወንድሞች እርቀን ቤተሰባችንን ወደ ምስራቃዊ ዩናይትድ ስቴትስ ለመውሰድ ምሪትን አገኘን። በመጀመሪያ ነገሮች እንዳሰብነው ሄዱልን እናም በውሳኔያችን ተማመንን። ነገር ግን ከዚያ በኋላ ነገሮች ተቀየሩ። ሴት ልጃችን ዶራ ከከባድ የጤና ችግር እና ከረዥም ጊዜ ልዩ ፍላጎቶች ጋር በተወለደችበት በዚያ ወቅት፣ የሕግ ተቋሙ የሥራ መደብ ቅነሳ አደረገ እናም ስራዬን እና ኢንሹራንሴን አጣሁ። እነዚህን ችግሮች በመጋፈጥ ላይ ሳለን፣ ብዙ ጊዜን እና ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ የቤተክርስቲያን ጥሪ ቀረበልኝ።

እንደዚህ አይነት ችግር አጋጥሞኝ አያውቅም ነበር ስለዚህ ተጨናነቅኩኝ። ያደረግነውን ውሳኔ እና ያስከተለውን ነገር መጠየቅ ጀመርኩኝ። በጌታ እምነት ነበረን እና ነገሮች መሳካት ነበረባቸው። ወደ ኋላ ወድቄ ነበር፣ ነገር ግን የሚይዘኝ ማንም እንዳልነበረ አሁን ግልፅ ሆነልኝ።

እንድ ቀን፣ “ለምን በማለት አትጠይቅ፣ ምን እንድትማር እንደምፈልግ ጠይቅ፣” የሚሉት ቃላቶች ጠንከር ባለ ሁኔታ ወደ አዕምሮዬ እና ወደ ልቤ መጡ። በዚህ ሰዓት የበለጠ ግራ ተጋባሁ። በቀድሞ ውሳኔዬ ላይ እየታገልኩኝ በነበረበት ወቅት፣ እግዚአብሔር እርሱን ይበልጥ እንዳምነው እየጋበዘኝ ነበር። ወደኋላ ስመለከት፣ በህይወቴ ውስጥ ይህ ወሳኝ ጊዜ ነበር፣ እግዚአብሔርን ለማመን ለመማር የተሻለው መንገድ እርሱን ዝም ብሎ ማመን እንደሆነ የተገነዘብኩበት ወቅት ነበር። በተከታዮቹ ሳምንታት ውስጥ፣ ጌታ ቤተሰባችንን ለመባረክ ያለውን እቅድ ተዓምራዊ በሆነ ሁኔታ ሲገልፅ በመገረም ተመለከትኩኝ።

ጎበዝ መምህራን እና አሰልጣኞች፣ የአዕምሮ እድገት እና የሰውነት ጥንካሬ ሊመጣ የሚችለው በአዕምሮ እና በጡንቻ ላይ ጫና በመፍጠር እንደሆነ ያውቃሉ። በተመሳሳይ መልኩ፣ እግዚአብሔር ነፍስን በሚመረምር ጫና በሚያደርጉ ልምዶች አማካኝነት የእርሱን መንፈሳዊ አሰልጣኝነት በማመን እንድናድግ ይጋብዘናል። በመሆኑም ባለፉት ጊዜያት በእግዚአብሔር የቱንም አይነት እምነት አሳይተን ቢሆን፣ ሌላ እምነትን የሚጠይቅ ልምድ ከፊታችን እንዳለ እርግጠኛ መሆን እንችላለን። እግዚአብሔር በእድገታችን እና በመሻሻላችን ላይ ያተኩራል። እርሱ ታላቁ መምህር ነው፣ መለኮታዊ ብቃታችንን ይበልጥ እንድንገነዘብ ሁሌም የሚረዳን ፍጹም የሆነ አሰልጣኝ ነው። ያም ዘወትር እርሱን በጥቂቱ ይበልጥ እንድናምነው የሚቀርብን የወደፊት ግብዣን የካትታል።

መፅሐፈ ሞርሞን፣ እግዚአብሔር ጠንካራ ግንኙነትን ለመገንባት የሚጠቀምበትን መንገድ ያስተምራል። ኑ፤ ተከተሉኝ በሚለው መጽሐፍ ውስጥ ኔፊና ወንድሞቹ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው የነሀስ ሰሌዳውን ማግኘት እንደነበረባቸው ሲነገራቸው ኔፊ በእግዚአብሔር ላይ የነበረው እምነት እንዴት እንደተፈተነ በቅርቡ አጥንተናል። የመጀመሪያው ሙከራቸው ከከሸፈ በኋላ ወንድሞቹ ተስፋ ቆርጠው ሰሌዳዎቹን ሳይዙ ለመመለስ ተዘጋጁ። ነገር ግን ኔፊ ሙሉ እምነቱን በጌታ ለማድረግ መረጠ ስለዚህ ሰሌዳዎቹን ለማግኘት ቻለ።10 ያ ተሞክሮ፣ ኔፊ ቀስቱ በተሠበረበት እና ቤተሰቡ በምድረ በዳ ለረሃብ ተጋልጦ በነበረ ጊዜ በእግዚአብሔር ላይ የነበረውን እምነት እንዲጠነክር ሳያደርገው አልቀረም። ኔፊ እንደገና በእግዚአብሔር ማመንን መረጠ በዚህም ምክንያት ቤተሰቡ ዳነ።11 እነዚህ ተከታታይ ተሞክሮዎች፣ ኔፊ ለትልቁ፣ እምነትን ለሚፈትነው የመርከብ ግንባታ ሃላፊነት በእግዚአብሄር ላይ ጠንካራ እምነት እንዲኖረው አስችለዋል።12

በእነዚህ ተሞክሮዎች አማካኝነት፣ ኔፊ በጽናት እና በቀጣይነት እግዚአብሔርን በማመን፣ ከእርሱ ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክሯል። እግዚአብሔር በእኛ ላይም ተመሳሳይ መንገድን ይጠቀማል። በእርሱ ላይ ያለንን እምነት ጠንካራ እና ጥልቀት ያለው እናደርግ ዘንድ በግል ይጋብዘናል።13 ግብዣውን በምንቀበልበት እና ተግባራዊ በምናደርግበት በእያንዳንዱ ጊዜ፣ በእግዚአብሔር ላይ ያለን እምነት ያድጋል። አንድን ግብዣ ቸል ካልን ወይም ካልተቀበልን፣ ለአዲስ ግብዣ ምላሽ እስክንሠጥ ድረስ የምናደርገው መሻሻል ይቆማል።

መልካሙ ዜና፣ ባለፉት ጊዜያት እምነታችንን በእግዚአብሔር ላይ ለማድረግ የመረጥን ብንሆንም ወይም ባንሆን፣ ዛሬ እንዲሁም ወደፊት እግዚአብሔርን ለማመን መምረጥ እንችላለን። ይህን በምናደርግበት በእያንዳንዱ ሰዓት፣ እግዚአብሔር ሊይዘን ከኋላችን ይቆማል እንዲሁም ከእርሱ እና ከልጁ ጋር አንድ የምንሆንበት ቀን እስከሚደርስ የእምነት ግንኙነታችን የበለጠ በመጠንከር እንደሚያድግ ቃል እገባለሁ። ከዚያም ልክ እንደ ኔፊ እንዲህ እናውጃለን፣ “አቤቱ ጌታ፣ በአንተ ታምኛለሁ፣ እንዲሁም ለዘለዓለም በአንተ እታመናለሁ።”14 በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።