አጠቃላይ ጉባኤ
በቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖች ምክንያት ሁሉም ደህና ይሆናል
የሚያዝያ 2024 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


በቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖች ምክንያት ሁሉም ደህና ይሆናል

በቤተመቅደስ ውስጥ የገባችሁትን ወይም የምትገቡትን ቃል ኪዳኖች ከማክበር የበለጠ አስፈላጊ ነገር የለም።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ይህ የአጠቃላይ ጉባኤ ክፍለ-ጊዜ ለእኔ የተቀደሰ ጊዜ ነበር። በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩት የኋለኛው ቀን ቅዱሳን እንዲሁም በአለም ዙሪያ ላሉ ጓደኞቻችንን እንድናገር ለተሰጠኝ ስራ አመስጋኝ ነኝ። እወዳችኋለሁ፣ ጌታም እንደሚወዳችሁ አውቃለሁ።

ከ50 ዓመታት በፊት፣ በሬክስበርግ፣ አይዳሆ፣ የሪክስ ኮሌጅ፣ ፕሬዚዳንት በመሆን የማገልገል ዕድል ነበረኝ። ሰኔ 5፣ 1976 (እ.አ.አ) ጠዋት ላይ፣ እኔና ባለቤቴ ካቲ፣ የቅርብ ጓደኛዬ መታተም ላይ ለመገኘት፣ ከሬክስበርግ ወደ አይዳሆ ፎልስ፣ አይደሆ ቤተመቅደስ በመኪና ሄድን። እርግጥ ነው፣ በዚያን ጊዜ በቤታችን አራት ታዳጊ ወንዶች በመኖራቸው፣ የቤተመቅደስ ጉዟችን ሊሳካ የሚችለው በአንዲት ደፋር ሞግዚት እርዳታ ብቻ ነበር! ውድ ልጆቻችንን እንድትጠብቅልን ትተንላት አጭሩን የ30 ደቂቃ የመኪና ጉዞ ጀመርን።

የዚያን ቀን የቤተመቅደስ ውስጥ ቆይታችን እንደተለመደው አስደናቂ ነበር። ነገር ግን፣ የቤተ መቅደሱ መታተም ካለቀ በኋላ—እንዲሁም ወደ ቤት ለመመለስ በዝግጅት ላይ ሳለን—ብዙ የቤተመቅደስ ሰራተኞች እና አገልጋዮች በቤተመቅደሱ አዳራሽ ውስጥ በፍርሃት ሲነጋገሩ አስተዋልን። ወዲያውኑ፣ አንዲት የቤተመቅደስ ሰራተኛ በምስራቅ አይዳሆ አዲስ የተሰራው የቴቶን ግድብ መፍረሱን ነገረችን! ከ80 ቢሊዮን ጋሎን (300 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር) በላይ ውሃ በግድቡ በኩል እንዲሁም ወደ 300 ስኩዌር ማይል (775 ካሬ ኪሎ ሜትር) ወደ አጎራባች ሸለቆዎች ውስጥ ይፈስ ነበር። ቤቶች እና ተሽከርካሪዎች በጎርፍ ተወሰዱ እንዲሁም አብዛኛው የሬክስበርግ ከተማ በውሃ ተጥለቀለቀ። ከ9,000 ነዋሪዎች ውስጥ 2/3ኛው በድንገት ቤት አልባ ሆኑ።1

ልታስቡ እንደምትችሉት፣ ሀሳባችን እና ስጋታችን ወደ ውድ ልጆቻችን፣ በመቶዎች ለሚቆጠሩ የኮሌጅ ተማሪዎች እና መምህራን እንዲሁም ለምንወደው ማህበረሰብ ደህንነት ዞረ። ከቤታችን ከ30 ማይል (50 ኪሎ ሜትር) ባነሰ ርቀት ላይ የነበርን ቢሆንም፣ የሞባይል ስልኮች እና የጽሑፍ መልእክት መላላክ ከመቻሉ በፊት ስለነበረ፣ በዚህ ቀን፣ ከልጆቻችን ጋር ወዲያውኑ የምንገናኝበት ምንም አይነት መንገድ አልነበረንም፤ እንዲሁም ከአይዳሆ ፎልስ ወደ ሬክስበርግ የሚወስዱ ሁሉም መንገዶች ስለተዘጉ መመለስ አልቻልንም።

የነበረን ብቸኛ አማራጭ በአይዳሆ ፎልስ ውስጥ በሚገኝ ሆቴል ውስጥ ማደር ብቻ ነበር። እኔ እና ካቲ በትንሽ የሆቴል ክፍላችን ተንበርክከን፣ ለውድ ልጆቻችን እና በአሳዛኙ ክስተት ለተጎዱ በሺዎች ለሚቆጠሩት ሰዎች ደህንነት በትህትና የሰማይ አባትን ተማጸንን። ካቲ በጭንቀት እንቅልፍ አጥታ እስከ ጠዋት ድረስ ስትንጎራደድ የነበረውን አስታውሳለሁ። እኔም ስጋት ቢኖረኝም አእምሮዬን አረጋግቼ እንቅልፍ መተኛት ቻልኩ።

ብዙም ሳይቆይ፣ ውዷ የዘለዓለም አጋሬ ቀሰቀሰችኝና፣ “ሃል፣ በዚህ ጊዜ እንዴት ትተኛለህ?” አለችኝ።

እነዚህ ቃላት ወደ ልቤ እና ወደ አእምሮዬ በግልፅ መጡ። ለሚስቴም፣ “ካቲ፣ ውጤቱ ምንም ቢሆን፣ በቤተመቅደሱ ምክንያት ሁሉም ነገር ደህና ይሆናል። ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ገብተናል እንዲሁም እንደ ዘላለማዊ ቤተሰብ ታትመናል” አልኳት።

በዚያን ጊዜ፣ የጌታ መንፈስ ሁለታችንም የምናውቀውን እውነት በልባችን እና በአእምሮአችን ያረጋገጠልን ያይል ነበር፣ በጌታ ቤት ውስጥ ብቻ የሚገኙ እና በትክክለኛው የክህነት ስልጣን የሚሰጡ የዕትመት ሥርዓቶች፣ እንደ ባልና ሚስት አንድ ላይ አስረውናል እንዲሁም ልጆቻችን ከእኛ ጋር ታትመዋል። በእውነት መፍራት አያስፈልግም ነበር፣ በኋላም ላይ ወንዶች ልጆቻችን ደህና መሆናቸውን ስላወቅኩኝ አመስጋኞች ሆንን።

ምናልባት ይህ የፕሬዘደንት ቶማስ ኤስ ሞንሰን ንግግር፣ እኔ እና ካቲ በማይረሳው ምሽት የተሰማንን ስሜት በተሻለ ሁኔታ ይገልፃል። “በቤተመቅደስ ስንሣተፍ፣የመንፈሳዊነት እና የሰላም ስሜት በስፋት ወደ እኛ ሊመጣ ይችላል። … አዳኙ የተናገረውን እነዚህን ቃላት እውነተኛ ትርጉም እናገኛለን፤ “ሰላምን እተውላችኋለሁ፣ ‘ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፣ ልባችሁ አይታወክ አይፍራም [ዮሀንስ 14፥27]።’”2

ወደ ቅዱስ ቤተመቅደስ በገባሁ ቁጥር ያ ሰላም ስለሚሰማኝ ተባርኬአለሁ። ወደ ሶልት ሌክ ቤተመቅደስ የገባሁበትን የመጀመሪያ ቀን አስታውሳለሁ። ወጣት ነበርኩ።

ክፍሉን በብረሃን በመሙላት ሰማይ የተከፈተ እንዲመስል ያደረገውን ከፍ ያለ ነጭ ጣሪያን ተመለከትኩ። በዚያች ቅጽበት፣ በግልፅ ቃላት “ከዚህ በፊት በዚህ ብርሃን በተሞላ ቦታ ነበርኩ” የሚል ሃሳብ ወደ አእምሮዬ መጣ። ነገር ግን ወዲያው በራሴ ድምጽ ሳይሆን ወደ አእምሮዬ እነዚህ ቃላት መጡ፣ “አይ፣ ከዚህ በፊት እዚህ መጥተህ አታውቅም። ከመወለድህ በፊት የነበረህን ጊዜ እያስታወስክ ነው፡፡ ጌታ ሊመጣ በሚችልበት ይህን በመሰለ ቅዱስ ስፍራ ነበርህ።”

ወንድሞች እና እህቶች፣ ወደ ቤተመቅደስ ስንሄድ፣ የመንፈሳችንን ዘላለማዊ ተፈጥሮ፣ ከአብ እና ከመለኮታዊ ልጁ ጋር ያለን ግንኙነት እንዲሁም ወደ ሰማያዊ ቤታችን ለመመለስ ያለንን የመጨረሻ ፍላጎት እንድናስታውስ እንደምንደረግ በትህትና እመሰክራለሁ።

በቅርቡ በተደረገው የጉባኤ ንግግር ፕሬዘደንት ራስል ኤም. ኔልሰን፥

“በመንፈስ በደህንነት ቦታ ለመሆን የምትችሉበት ቢኖር በቤተመቅደስ ቃል ኪዳናችሁ ውስጥ መኖር ነው።”

እያንዳንዱ የምናምነው እና እግዚአብሔር ለቃል ኪዳን ህዝቦቹ የገባው እያንዳንዱ የተስፋ ቃል በቤተመቅደስ ውስጥ ይገኛል” በማለት አስተምረዋል።3

“በቤተመቅደስ ውስጥ ቃል ኪዳን የሚገባ—እና ቃል ኪዳኑን የሚያከብር—እያንዳንዱ ሰው የኢየሱስ ክርስቶስን ሀይል የማግኘት ተጨማሪ ችሎታ አለው።”4

በተጨማሪም እንዲህ በማለት አስተምረዋል፣ “ከእግዚአብሔር ጋር አንዴ ቃል ኪዳን ከገባን ገለልተኛ ሃሳቦችን ለዘላለም እንተዋለን። እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንዲህ ያለውን ግንኙነት የፈጠሩትን አይተውም። በእርግጥ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን የገቡ ልዩ የሆነ ፍቅር እና ምህረትን ማግኘት ይችላሉ።”5

በፕሬዚዳንት ኔልሰን በመንፈስ የተነሳሳ አመራር ስር፣ ጌታ በአለም ዙሪያ ያሉ ቤተመቅደሶችን ግንባታ አፍጥኗል እንዲሁም ማፋጠኑን ይቀጥላል። ይህ፣ ሁሉም የእግዚአብሔር ልጆች የመዳን እና ከፍ ከፍ የመደረግ ስርአቶችን የመቀበል እንዲሁም ቅዱስ ቃል ኪዳኖችን የመግባት እና የመጠበቅ እድል ይሰጣቸዋል። ቅዱስ ቃል ኪዳኖችን ለማድረግ ብቁ መሆን የአንድ ጊዜ ሳይሆን የህይወት ዘመን ጥረት ነው። ጌታ ሙሉ ልባችንን፣ ኃይላችንን፣ አእምሮአችንን እና ጥንካሬያችንን እንደሚጠይቅ ተናግሯል።6

በቤተመቅደስ ስርአቶች ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜ መሳተፍ ለጌታ የመሰጠትን ንድፍ ሊፈጥር ይችላል። የቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖቻችሁን ስትጠብቁ እና ስታስታውሷቸው፣ እናንተን እንዲያጠነክር እና እንዲያነጻ የመንፈስ ቅዱስን አጋርነት ትጋብዛላችሁ።

ከዚያም ተስፋዎቹ እውነት መሆናቸውን የሚመሰክር የብርሃን እና የተስፋ ስሜት ሊሰማችሁ ይችላል። ከእግዚአብሔር ጋር የተደረገ እያንዳንዱ ቃል ኪዳን፣ ወደ እርሱ ለመቅረብ እድል እንደሆነ ታውቃላችሁ፣ ይህም የቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖችን ለመጠበቅ በልባችሁ ውስጥ ፍላጎት ያሳድራል።

“ከእግዚአብሔር ጋር በገባነው ቃል ኪዳን ምክንያት፣ እኛን ለመርዳት በሚያደርገው ጥረት አይታክትም እንዲሁም ለእኛ ያለውን የምሕረት ትዕግሥትም አንጨርሰውም”7 ተብሎ ቃል ተገብቶልናል።

ከሞት በኋላ የሚቀጥሉትን እና ለዘለአለም የሚቆዩትን የምንወዳቸውን የቤተሰብ ትስስሮች ማረጋገጫ የምንቀበለው፣ በቤተመቅደስ ውስጥ ባለው የማተሚያ ቃል ኪዳኖች ነው። በእግዚአብሔር ቤተመቅደሶች ውስጥ የተደረገን ጋብቻ እና የቤተሰብ ቃል ኪዳኖችን ማክበር፣ ከራስ ወዳድነት እና ከትዕቢት ክፋት ይጠብቃል።

በወንድምና እህት መካከል መተሳሰብ የሚመጣው ቤተሰባችሁን በጌታ መንገድ ለመምራት የማያቋርጥ ጥረት ሲደረግ ብቻ ነው። ልጆች አንዳቸው ለሌላቸው እንዲጸልዩ እድል ስጡ። አለመስማማት ገና ከመጀመሪያው ሲፈጠር በፍጥነት ለዩ እንዲሁም ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ አገልግሎትን፣ በተለይም አንዳችን ለሌላችን ስናደርግ በአዎንታዊ መልኩ ተገንዘቡ። ልጆች አንዳቸው ለሌላው ሲጸልዩ እና ሲያገለግሉ፣ ልባቸው ወደሌላው እና ወደ ወላጆቻቸው ይመለሳል እንዲሁም ይራራል።

በከፊል፣ ሚልክያስ ስለ ነቢዩ ኤልያስ መምጣት አስቀድሞ በተነበየው ትንቢት ላይ፦ “ለአባቶች የተገባውን የተስፋ ቃል በልጆች ልብ ይተክላል፣ እናም የልጆቹም ልብ ወደ አባቶቻቸው ይመለሳል። እንዲህ ባይሆን ኖሮ፣ መላው ምድር በምጽአቱ በጠፋ ነበር”8 በማለት የገለጸው ይህን ነው።

ፈተናዎች፣ ተግዳሮቶች እንዲሁም ከባድ ሃዘን ወደ ሁላችንም መምጣቱ አይንደማይቀርም። ማናችንም ብንሆን “ከሥጋ መውጊያ”9 አናመልጥም። ሆኖም ግን፣ በቤተመቅደስ ስንገኝና ቃል ኪዳኖቻችንን ስናስታውስ ከጌታ የግል መመሪያ ለመቀበል መዘጋጀት እንችላለን።

እኔ እና ካቲ በሎጋን ዩታ ቤተመቅደስ ውስጥ ተጋብተን ስንታተም፣ የያኔው ሽማግሌ ስፔንሰር ደብሊው ኪምቦል ነበር የማተም ስርዓቱን ያከናወኑት። ከተናገራቸው ጥቂት ቃላት ውስጥ፣ “ሃል እና ካቲ፣ ጥሪው ሲመጣ በቀላሉ መሄድ እንድትችሉ ሆናችሁ ኑሩ” የሚል ምክር ነበረ።

በመጀመሪያ፣ ያ ምክር ለእኛ ምን ማለት እንደነበረ አልገባንም ነበር፣ ነገር ግን ጥሪው ሲመጣ፣ ጌታን ለማገልገል ለመሄድ በተቻለን አቅም ህይወታችንን በማዘጋጀት ኖረናል። ወደ 10 ዓመታት ያህል በጋብቻ ከቆየን በኋላ፣ ያልጠበቅነው ጥሪ ከቤተ ክርስቲያኗ ትምህርት ኮሚሽነር ኒል ኤ. ማክስዌል ቀረበ።

በቤተመቅደስ ውስጥ ፕሬዘዳንት ኪምቦል “በቀላሉ መሄድ” እንድትችሉ በማለት በፍቅር የሰጡት ምክር እውን ሆነ። እኔ እና ካቲ በካሊፎርኒያ ውስጥ አስደሳች ይመስል የነበረውን የቤተሰብ ሁኔታ ትተን ምንም ወደማላውቅበት ቦታ እንድናገለግል ጥሪ ቀረበልን። ነገር ግን፣ ቤተሰባችን ለመሄድ ዝግጁ ነበር ምክንያቱም አንድ ነቢይ፣ በመገለጥ ቦታ፣ በቅዱስ ቤተ መቅደስ ውስጥ፣ የወደፊቱን ክስተት ስላየና እኛም ዝግጁ ስለነበርን ነው።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ በቤተመቅደስ ውስጥ የገባችሁትን ወይም የምትገቡትን ቃል ኪዳኖች ከማክበር የበለጠ አስፈላጊ ነገር እንደሌለ እመሰክራለሁ። በቃል ኪዳኑ መንገድ ላይ የትም ብትሆኑ፣ ቤተመቅደስ ለመሄድ ብቁ እና የሚገባችሁ እንድትሆኑ አጥብቄ እለምናችኋለሁ። ሁኔታዎች በሚፈቅዱላችሁ መጠን በተደጋጋሚ ጎብኙ። ከእግዚአብሔር ጋር የተቀደሱ ቃል ኪዳኖችን ግቡ እንዲሁም ጠብቁ። ከአምስት አስርት ዓመታት በፊት፣ በአንዲት ትንሽዬ የአይዳሆ ፎልስ ሆቴል ክፍል ውስጥ “ውጤቱ ምንም ቢሆን ምን፣ በቤተ መቅደስ ምክንያት ሁሉም ነገር ደህና ይሆናል” በማለት በእኩለ ሌሊት ለካቲ የተናገርኩትን ተመሳሳይ እውነት ላረጋግጥላችሁ እችላለሁ።

ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ እርግጠኛ ምስክርነቴን እሰጣችኋለሁ። እርሱ ህያው ነው፣ ቤተክርስቲያኑንም ይመራል። ቤተመቅደሶች የጌታ ቤቶች ናቸው። ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልስን በምድር ያሉ የጌታ ነቢይ ናቸው። እወዳቸዋለሁ፣ እያንዳንዳችሁንም እወዳችኋለሁ። በተቀደሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሜን።