አጠቃላይ ጉባኤ
በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በቃል ኪዳን መታመን
የሚያዝያ 2024 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በቃል ኪዳን መታመን

ወደ ጌታ ቤት ስንገባ፣ የተሻልን እና ቅዱስ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለመሆን የተቀደሰ የመማሪያ ጉዞ እንጀምራለን።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ በዚህ ቅዳሜና እሁድ፣ በመሪዎቻችን የተነሳሱ መልዕክቶች በመንፈስ እንድንታደስ እና “በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በቃል ኪዳን መታመን” ብዬ መጥራት በምወደው እንድንደሰት እጸልያለሁ። ይህ መተማመን ቃል ኪዳናቸውን ለሚጠብቁ ሰዎች እግዚአብሔር ቃል የገባቸውን በረከቶች የመቀበል ጸጥ ያለና እርግጠኛ የሆነ ማረጋገጫ ሲሆን በዘመናችን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በጣም የሚያስፈልግ ነው።

በፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን መሪነት በአለም ዙሪያ ያሉ የጌታ አዲስ ቤቶች ግንባታ በቤተክርስቲያኗ አባላት መካከል ታላቅ ደስታን አስገኝቷል ይህም የጌታን መንግስት መስፋፋት አስፈላጊ መሆኑ የሚያሳይ ምልክት ሆኖ ያገለግላል።

ባለፈው ጥቅምት በፌዘር ሪቨር ካሊፎርኒያ ቤተመቅደሰ ምረቃ ላይ ያጋጠመኝን አስገራሚ ልምድ ሳሰላስል፣ አንዳንድ ጊዜ በከተማችን እና በማህበረሰባችን ውስጥ አዲስ ቤተመቅደስ በመኖሩ ደስታ ውስጥ ተዘናግተን በቤተመቅደሶች ውስጥ የምንገባቸው ቅዱስ ቃል ኪዳኖችን አላማ ችላ እንል ይሆን ብዬ አስባለሁ።

በእያንዳንዱ ቤተመቅደስ ፊት ለፊት ላይ “ቅድስና ለጌታ” የሚል ፅሁፍ ተቀርጿል።1 እነዚህ በመንፈስ የተነሳሱ ቃላት ወደ ጌታ ቤት ስንገባ፣ የተሻልን እና ቅዱስ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ለመሆን የተቀደሰ የመማሪያ ጉዞ እንደምንጀምር ግልጽ ግብዣ ናቸው። በእግዚአብሔር ፊት በቅድስና ቃል ኪዳኖችን ስንገባ እና አዳኙን ለመከተል ቁርጠኛ ስንሆን፣ ልባችንን ለመቀየር ሃይልን እንቀበላለን፣ መንፈሳችንን እናድሳለን እንዲሁም ከእርሱ ጋር ያለንን ግንኙነት እናጠነክራለን። እንደዚህ አይነት ጥረት ለነፍሳችን ቅድስናን ያመጣል እንዲሁም የዘላለም ህይወት ስጦታን መውረስ እንደምንችል ቃል ከገቡት ከእግዚአብሔር እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ቅዱስ ትስስርን ይፈጥራል።2 የዚህ የተቀደሰ ጉዞ ውጤት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በገባነው ቃል ኪዳናችን ውስጥ ለዕለት ተዕለት ህይወታችን የበለጠ የተቀደሰ እና ከፍ ያለ መተማመንን ማግኘታችን ነው።

ይህ አይነት መተማመን ከእግዚአብሔር ጋር ያለን መለኮታዊ ግንኙነት ጫፍ ነው እናም ለእርሱ ያለንን ፍቅር እና ለኢየሱስ ክርስቶስ እና ለሃጢያት ክፍያው ያለንን ምስጋና ይጨምራል። ሌሎችን ለመውደድ እና ለማገልገል ያለንን አቅም እንዲሁም እየጨለመ እና ተስፋ ማስቆረጡን እየቀጠለ ባለው ርኩስ አለም ውስጥ መኖር እንድንችል ነፍሳችንን ያጠነክራል። ህይወት ከባድ ስትሆን፣ ፈተናዎች ሲረዝሙ ወይም ሁኔታዎች አስቸጋሪ ሲሆኑ፣ ጠላት የጥርጣሬን እና የተስፋ መቁረጥን፣ የፍርሃትን እና የብስጭትን እንዲሁም የልብ ህመምን ፍሬዎች ወደ ልባችን በጥልቀት ሊያስገባ ሲሞክር ለማሸነፍ ሃይልን ይሰጠናል። በዛሬው አለማዊ ፈተናዎች ላይ ስናዘነብል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ለእያንዳንዳችን ምክርን ይሰጣል፦ “እንግዲህ ታላቅ ብድራት ያለውን ድፍረታችሁን አትጣሉ።”3

ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በጌታ ቤት ውስጥ በተገቡ ቃል ኪዳኖች እውነተኛ ድፍረት የሚያገኙ ሰዎች፣ በዚህ ህይወት ውስጥ ልናገኝ ከምንችላቸው እጅግ ጠንካራ ሃይሎች መካከል አንዱን ያገኛሉ።

መጽሐፈ ሞርሞንን በዚህ አመት በ ኑ፣ ተከተሉኝ ውስጥ ስናጠና፣ ኔፊ በጌታ በታዘዘው መሰረት ሰሌዳዎቹን ለማግኘት እንቅፋቶች እና ፈተናዎች በገጠሙት ጊዜ፣ በታማኝነቱ የዚህን አይነት የቃል ኪዳን መተማመን ሀይል እንዴት በሚያምር ሁኔታ እንዳሳየ አይተናል። ኔፊ በላማን እና በልሙኤል ፍርሃት እና እምነት ማጣት እጅጉን ቢያዝንም፣ ጌታ ሰሌዳዎቹን ለእነሱ ስለሚሰጥ ቆራጥ መሆኑን እና መተማመኑን ቀጠለ። ለወንድሞቹ እንዲህ አላቸው፣ “ጌታ ህያው እንደሆነ፣ እኛም እስካለን ድረስ ጌታ ያዘዘንን ሳናከናውን ወደአባታችን ወደ ምድረበዳ አንመለስም።”4 ኔፊ በጌታ በረከቶች ላይ ባለው እምነት ምክንያት እንዲያደርግ የታዘዘውን ለማከናወን ቻለ።5 ከዚያም በኋላ ኔፊ በህልሙ የዚህን አይነት እምነት ተጽዕኖ ተመለከተ፣ “እኔ ኔፊ በበጉ ቤተክርስቲያን ቅዱሳን እና የጌታ የቃልኪዳን ህዝቦች ላይ የእግዚአብሔር በግ ኃይል ሲወርድ ተመለከትኩ፣ … እነርሱም ፅድቅንና የእግዚአብሔርን ኃይል በታላቅ ክብር የታጠቁ ነበሩ”7በማለት ጻፈ።

የጌታ የፍቅር ተስፋዎች እና ሃይል ወደ እግዚአብሄር ልጆች ህይወት ሲፈስ እና የህይወት አጋጣሚዎችን እንዲጋፈጡ ሲያበረታታ አይቻለሁ። ባላቤቴ ባለፈው ቀን ከቤተመቅደስ አምልኮዋ ስትመለስ፣ እዚያ ባጋጠማት ነገር እንዴት በጥልቀት እንደተነካች ነገረችኝ። ወደ ጌታ ቤት ስትገባ፣ አንድ ሰው በተሽከርካሪ ወንበር ላይ ቀስ ብሎ ሲሄድ እንዲሁም አንዲት ሴት በከዘራ ለመራመድ እየተቸገረች ስትሄድ፣ ሁሉቱም በድፍረት ጌታን ለማምለክ ሲመጡ ተመለከተች። ባለቤቴ ወደ መግቢያው አካባቢ ስትራመድ፣ አንደኛውን እጇን መሉ በሙሉ፣ ሌላኛውን ደግሞ በከፊሉ ያጣች አንድ ደስ የምትል እህት፣ የተሰጣትን ማንኛውንም ተግባራት ደስ በሚል እና በሰለስቲያላዊ ሁኔታ ስትተገብር አየች።

ባለቤቴ እና እኔ ስለዚያ ተሞክሮ ስንነጋገር፣ እግዚአብሔር በቤቱ ውስጥ ከእርሱ ጋር በተደረገ ቅዱስ ቃል ኪዳኖች አማካኝነት በሚሰጠው ዘለዓለማዊ ተስፋ ንጹህ እና ከልብ የሆነ እምነት፣ እነዚያን ድንቅ የክርስቶስ ደቀመዛሙርት የግል ህይወታቸው ሁኔታ ሳይገድባቸው በዚያ በጣም በሚበርድ ቀን ከቤታቸው እንዲወጡ እንዳደረጋቸው ደመደምን።

ውድ ጓደኞቼ፣ ልንይዘው የሚገባ አንድ ነገር—እናም ለልጆቻችን እና ለልጅ ልጆቻችን እያንዳንዳቸውን ወደ ፊት በሚገጥማቸው ፈተናዎች እና ችግሮች የሚረዳቸው የምናወርሳቸው አንድ ነገር ቢኖር፣ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በተደረጉት ቃል ኪዳኖች እምነት እንዲያገኙ ማድረግ ነው። እንደዚህ አይነቱን መለኮታዊ ንብረት ማግኘት ጌታ ታማኝ ተከታዮቹ ቃል በገባላቸው መሰረት እንዲኖሩ ይረዳቸዋል፦ “ነገር ግን ደቀ መዛሙርቴ በተቀደሰ ስፍራዎች ላይ ይቆማሉ፣ እናም አይነቃነቁም።”7

በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት እንደዚህ አይነት እምነት የምናገኘው እንዴት ነው? በትህትና፣ ህይወታቸንን በአዳኙ ላይ በማተኮር፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መርሆዎች በመኖር፣ የመዳን እና ከፍ የመደረግ ስርአቶችን በመቀበል እንዲሁም በቅዱስ ቤቱ ውስጥ የገባናቸውን ቃል ኪዳኖች በማክበር አማካኝነት ሊመጣ ይችላል።

ውድ ነቢያችን በጥር 2019 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ የመዝጊያ ንግግራቸው ላይ፣ በቃል ኪዳን መተማመንን ለማግኘት ስለሚያስፈልግ አንድ እርምጃ እንዲህ በማለት አስታውሰውናል፣ “ወደ ጌታ ቤት ለመግባት ግላዊ ብቁነት ብዙ ግላዊ መንፈሳዊ ዝግጅትን ይጠይቃል። ግላዊ ብቁነት፣ የበለጠ ጌታን ለመምስል፣ ሐቀኛ ዜጋ ለመሆን፣ የተሻለ ምሳሌ ለመሆን፣ እና ይበልጥ የተቀደሰ ሰው ለመሆን ሙሉ በሙሉ የአእምሮ እና የልብ ለውጥ ማድረግን ይጠይቃል።”8 ስለዚህም፣ ወደ ቤተመቅደስ ለመግባት የምናደርገውን ዝግጅት ከቀየርን፣ በቤተመቅደስ ውስጥ የሚኖረንን ተሞክሮ እንለውጣለን፣ ይህም ከቤተመቅደስ ውጭ ህይወታችንን ይለውጣል። “ከዚያም ልበ ሙሉነትህ በእግዚአብሔር ፊት እየጠነከረ ይሄዳል፤ እና የክህነት ትምህርትም በነፍስህ ላይ እንደ ሰማይ ጠል ትንጠባጠብልሀለች።”9

አንድ የማውቀው ኤጲስ ቆጶስ፣ በመጀመሪያ ክፍል ውስጥ ከፍ ከፍ ያሉ ልጆች ያሉበትን ክፍል “የመጀመሪያ” ክፍል ብሎ አይጠራውም፣ ነገር ግን “የቤተመቅደስ መዘጋጃ” ብሎ ይጠራዋል። በጥር ወር፣ ኤጲስ ቆጶሱ የክፍሉ አባላት እና መምህራኖቻቸው ወደ ቢሮው በመምጣት፣ አመቱን ሙሉ ወደ ቤተመቅደስ ለመግባት በመዘጋጀት እንዴት እንደሚያሳልፉ ይነጋገራሉ። ኤጲስ ቆጶሱ ተግባራዊ የቤተመቅደስ መግቢያ ቃለ መጠይቅ ጥያቄዎችን በመከለስ ጊዜ ይወስዳል፣ ከዚያም በመጀመሪያ ክፍል ትምህርታቸው ውስጥ ይካተታሉ። ልጆች እንዲዘጋጁ ይጋብዛል፣ በመሆኑም ከአንድ አመት በኋላ ወደ ኤጲስ ቆጶሱ ቢሮ ሲመጡ፣ ደፋሮች፣ በቃል ኪዳን የሚተማመኑ፣ የቤተመቅደስ መግቢያ መታወቂያን ለመቀበል እና ወደ ጌታ ቤት ውስጥ ለመግባት የተዘጋጁ ይሆናሉ። በዚህ አመት ቤተመቅደስ ለመሄድ በጣም የጓጉ፣ ዝግጁ እና በራስ የመተማመን ስሜት ያደረባቸው ወጣት ሴት ልጆች ኤጲስ ቆጶሱ የቤተመቅደስ መግቢያ መታውቂያቸውን በዘመን መለወጫ በዓል ቀን ከለሊቱ 6፡01 ሰዓት ላይ አትሞ እንዲሰጣቸው ጠይቀውት ነበር።

ዝግጅት የሚያስፈልገው ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቤተመቅደስ ለሚሄዱ ሰዎች ብቻ አይደለም። ወደ ጌታ ቤት ለመሄድ ሁላችንም ሳናቋርጥ መዘጋጀት ይኖርብናል። አንድ የማውቀው ካስማ፣ ይህን መሪ ቃል ተጠቀመ፣ “ቤት ተኮር፣ በቤተክርስቲያን የተደገፈ እና በቤተመቅደስ የተገደበ።” የተገደበ 10የሚገርም ቃል ነው፣ በአቅጣጫ ላይ ያተኮረ ማላት ነው፣ ነገር ግን የታሰረ ወይም የጠበቀ፣ መፍትሄ ያለው፣ የተወሰነ እና እርግጠኛ የሆነ ማለትም ነው። ስለሆነም፣ በቤተመቅደስ የተገደብን መሆን፣ ከአዳኙ ጋር ያጣምረናል፣ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት የቃል ኪዳን መታመን እንዳለን እያረጋገጠ ተገቢ አቅጣጫን እና መረጋጋትን ይሰጠናል። ስለሆነም፣ ቤተመቅደስ ቅርብም ይሁን እሩቅ ቀጣዩን ቀጠሮአችንን ከጌታ ጋር በቤቱ በማድረግ ሁላችንም ሆን ብለን እንደዚህ አይነትን ትስስርን ማዳበር ይኖርብናል።11

ውዱ ነቢያችን፣ ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን፣ ስለእነዚህ አስፈላጊ መርሆዎች እንዲህ በማለት እንድናስታውስ አድርገውናል፦ “ቤተመቅደስ እምነታችንን እና መንፈሳዊ ምሽጋችንን ለማጠንከር ማዕከላዊ ቦታ ላይ ይገኛል ምክንያቱም አዳኙ እና የእርሱ ትምህርት የቤተመቅደስ ማዕከለኛ ክፍል ነውና። በመመሪያ እና በመንፈስ አማካኝነት፣ በቤተመቅደስ ውስጥ የሚስተላለፈው ሁሉም ትምህርት ስለኢየሱስ ክርስቶስ የሚኖረንን መረዳት ይጨምራል። በቅዱስ የክህነት ቃል ኪዳኖች አማካኝነት አስፈላጊዎቹ የእርሱ ስርዓቶች ከእርሱ ጋር ያጣምሩናል። ከዚያም በኋላ፣ ቃል ኪዳኖቻችንን ስንጠብቅ፣ በእርሱ ፈዋሽ፣ የሚያበረታ ኃይል ይባርከናል። እና አቤቱ፣ የእርሱ ኃይል በመጪዎቹ ቀናት እንዴት እንደሚያስፈልገን።”12

ከሰማይ አባታችን ጋር በእርሱ ስም ቃል ኪዳኖችን ስንገባ እንዴት መተግበር እንዳለብን በታላቅ ግልጽነት ለመረዳት ዝግጁ እንድንሆን አዳኙ ይሻል። በዚህ ህይወት የሚያስፈልገንን መንፈሳዊ መነሳሳቶች እና መንቃቶች እንዲኖረን ለመዘጋጀት የእኛን መብቶች፣ ቃል ኪዳኖች እና ሃላፊነቶች ለመለማመድ ዝግጁ እንድንሆን ይፈልጋል። ጌታ በእርሱ እና በቤቱ ባደረግነው ስርአቶች እና ቃል ኪዳኖች በማተኮር በህይወታችን ውስጥ የፍላጎትን ብልጭታ ወይም የጽድቅን ጥረት ፍንጣቂ ሲመለከት፣ ፍጹም በሆነው መንገዱ፣ በሚያስፈልገን ተአምራቶች እና ግላዊ በረከቶች እንደሚባርከን አውቃለው።

የጌታ ቤት በክፍተኛ እና በቅዱስ መንግዶች የምንለወጥበት ቦታ ነው። ስለሆነም፣ በቃል ኪዳኖቹ በረከቶች ተስፋ ተቀይረን፣ ከላይ በሚመጣ ሃይል ታጥቀን ከቤተመቅደስ ስንወጣ፣ ቤተመቅደስን ወደ ቤታችን እና ወደ ህይወታችን እንወስዳለን። የጌታ ቤት መንፈስ በውስጣችን መኖሩ ሙሉ በሙሉ እንደሚቀይረን አረጋግጥላችኋለው።

በህይወቶቻችን ውስጥ የጌታ መንፈስ ያልተገደበ እንዲሆን ከፈለግን፣ በጎ ያልሆኑ ስሜቶች ለማንም ሊኖሩን እንደማይችል እና እንደማይገባ ከቤተመቅደስ እናውቃለን። በልባችን ወይም በአእምሮአችን ውስጥ በጎ ላልሆኑ ስሜቶች እና ሃሳቦች ቦታ መስጠት፣ የጌታ መንፈስ ከልባችን እንዲሄድ በማድረግ በማህበራዊ ድህረ ሚዲያ ላይም ይሁን በቤታችን ውስጥ በጎ ያልሆኑ ቃላትን እና ተግባራትን እንድናደርግ ያደርገናል። ስለሆነም፣ እባካችሁን መተማመናችሁን አትጣሉት፣ ነገር ግን አጠንክሩት።

እየቀጠለ እና እየተፋጠነ ያለው የቤተመቅደሶች ግንባታ ማስደሰቱን፣ ማነሳሳቱን እና መባረኩን ይቀጥላል። ይበልጥ አስፈላጊ በሆነ ሁኔታ፣ ቤተመቅደስ ለመግባት በጽድቅ መዘጋጀት ላይ የምናተኩር ስንሆን፣ በቤተመቅደስ ውስጥ የሚኖረንን ተሞክሮ እንለውጣለን፣ ይህም ከቤተመቅደስ ውጭ ህይወታችንን ይለውጣል። ይህ ለውጥ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በተደረጉት ቅዱስ ቃል ኪዳኖች መተማመንን ይሙላ። እግዚአብሔር ህያው ነው፣ ኢየሱስ አዳኛችን ነው እናም ይህ በምድር የተመለሰው ቤተክርስቲያኑ ነው። እነዚህን እውነቶች በቅዱስ አዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በትህትና አውጃለው፣ አሜን።